የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ለጻፉት የጉዞ ማስታወሻ የተሰጠ ምላሽ – በተለይ የአማራን የመደራጀት ጥያቄ ከአእምሮ በሽታ ጋር ስለማያያዝዎ

Print Friendly, PDF & Email

(ከሰለሞን ዳኛቸው)

የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አቶ ኤፍሬም ባዴቦ የኔ የግሌ የብቻዬ አተያይ እንጂ የማንም የሌላ አይደለም ባሉት የጉዞ ማስታወሻቸውን አስታከው የአማራን መደራጀት የነቀፉበትንና የአማራን በማንነት መደራጀት አቀንቃኞችን በአዕምሮ በሽተኝነት የፈረጁበትን ጽሑፍ ላይ እኔ በግል የተሰማኝን አስተያየት የምጀምረው “…አማራው በዘር ተደራጅቶ ከሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን በተለየ መንገድ የኢትዮጵያ ጠባቂ ይሆናል የሚለው አባባል እራሱን አግዝፎ ወይም ሌሎቹን አሳንሶ ከማየት የመጣ የአዕምሮ በሽታ ነው።” ከሚለው የአቶ ኤፍሬም እይታ ነው።

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስና ጓደኞቻቸው አማራውን በማንነቱ ዙሪያ ለማደራጀት የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) ሲያቋቁሙ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርጅቱ አባል መሆን ይችላል ያሉት አማራነት ከኢትዮጵያዊነት የተዋሃደ የተጋመደ የማይተረተር ለመሆኑ አማራው የሚኖረው እውነት በመሆኑ እንጂ በተለየ መንገድ የኢትዮጵያ ጠባቂ ይሆናል በማለት ራሱን አግዝፎ ሌላውን አሳንሶ ከማየት የመጣ የአዕምሮ በሽታ አልነበረም። አይደለሞም።

ሐምሌ 5 ቀን በጎንደር ከ10ቀናት በኋላም በባህር ዳር ከዚያም በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም በሰሜንና በደቡብ ጎንደር የተቀጣጠለውና ህወሓትን ከስር ከመሰረቱ የናጠው የአማራው ተጋድሎ በዋናነት መነሻው አማራነት ወልቃይት አማራ ነው የሚል ቢሆንም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገ የወደቀችውን ባንድራ አንስቶ ከፍ አድርጎ የሰቀለ ነበር። አማራው በአማራነቱ ሲነሳ ራሱን አግዝፎ ሌላውን አሳንሶ ሳይሆን “የኦሮሞው መሪ የኔም መሪ ነው።” “የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው።” ብሎ ነው። አማራው የሚፈፀምበትን የዘር ማጥፋት ተደራጅቶ እንዲመክት መአህድን ከጓደኞቻቸው ጋር ያቋቋሙትና በመሪነት የተመረጡት ፕሮፌሰር አስራት አማራው ራሱን መከላከል ወደሚችልበት ደረጃ ያደርሰዋል ብለው የሰጉትና አማራን በጠላትነት ፈርጀው ከግብርአበሮቻቸው ጋር የዘር ማጥፋት የሚፈፅሙበት ህወሓቶች ፕሮፌሰሩን ገድለው መአህድን አሽመደመዱት።

ዛሬ የህወሓት ግብረአበሮቹ እነ ሌንጮ ለታ ከቀድሞው ድርጅታቸው ተገንጥለው በጎሳ ያደራጁት አቶ ኤፍሬም ባዴቦ በከፍተኛ አመራርነት ከሚመሩት የአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንባር ሲፈጥር አቶ ኤፍሬም እነ ሌንጮ ለታን አሞገሱ እንጂ ” የአዕምሮ በሽተኞች” ማለታቸውን አልሰማሁም። ተፅፎም ከሆነ አላነበብኩም። አቶ ኤፍሬም ”የአማራው በዘር መደራጀት ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት አደጋዎች ሁሉ ትልቁ ነው።” ይላሉ እንጂ ከኤርትራ ተንቀሳቅሶ በሰሜን ጎንደር በኩል ገብቶ የትጥቅ ትግል ማቀጣጠል ተስኖት ለነበረው ድርጅታቸው በሩን አስፍቶ የከፈተለት ሐምሌ 5 የተቀጣጠለው የአማራ ተጋድሎ በነጎቤ መልኬ የጎበዝ አለቃነት የተደራጀው የአማራ ገበሬና ወጣት በህወሓት ላይ ጠመንጃ አንስቶ ዱር ቤቴ ካለ በኋላ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ልባቸው ያውቀዋል።

ያልገባኝ አቶ ኤፍሬም እንዲመልሱልኝ የምፈልገው ግን በኢትዮጵያ በህዝብ ቁጥር አብላጫነቱን የያዘው ኦሮሞ በጎሳ መደራጀት ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት አደጋዎች ሁሉ ቀዳሚው ሳይሆን ቀርቶ በህዝብ ብዛቱ ሁለተኛ የሆነው አማራ በማንነቱ መደራጀቱ እንዴት ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት አደጋዎች ግንባር ቀደምት ሊሆን ይችላል? የሚለው እንቆቅልሽ ነው። በህብረ ብሔር የተደራጁት አንድነት መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ በአማራው ላይ የተፈፀመውን ግፍ አጋልጠው በአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ ቢያወግዙም በህወሓት ሰርጎ ገቦችና ሆድ አደሮች መንኮታኮታቸው ያየነው ከፍተኛ አመሬሮቹ የነበሩት እነ ማሙሸት እነ ሀብታሙ አያሌው የመሰከሩት ነው።

አማራው በአማራነቱ እንዳይደራጅና ራሱን እንዳይከላከል መሪው ተገድለው ድርጅቱ መላው አማራ ከተሽመደመደ በኋላ አማራው ራሱን ከመጥፋት ለመከላከል በሀገር ውስጥ ማደራጀት ባለመቻሉ ከአብራኩ የወጡት ልጆቹ የአማራውን ጉዳይ ከፊት አድርጎ የሚሸከምለት ድርጅት ቢያጡ በማንነታቸው ዙሪያ መደራጀታቸውና አማራው ህልውናውን ለማቆየት በማንነቱ ዙሪያ ተደራጅቶ ራሱን መከላከል አለበት ብሎ መቀስቀስ እንዴት በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠ ትልቅ አደጋ የአዕምሮ በሽታ ይሆናል? አልገባኝም!