ህወሃት ከየመን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን እንጂ የታገሉለትን አላማ መጥለፍ አልቻለም

Print Friendly, PDF & Email

(ቢንያም ሙሉጌታ ከኖርዌ)

ዘረኞቹ ህወሃት ወያኔዎች የምንወዳትን ኢትዮጵያ ሀገራችንን ደግመው ደጋግመው እንዳያደሙት የህዝባችን መከራና ስቃይ እንዲያቆም ገዳዮቻችንን አጥፊዎቻችንን ሊፋረዳቸው በህይወቱና በቤተሰቦቹ የጨከነ የስርዓቱን የውድቀት ምዕራፍ ወደፊት ያፋጠነ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኃላ የምንመለስባት ሌላ ኢትዮጵያ እንደሌለን እውነታውን አስረግጦ ያስገነዘበን አንዳርጋቸው ፅጌ ዛሬ በወያኔ ህወሃት ውድቀት ዋዜማ ልናስታውሰው ይገባል። ዳኛውም ዝንጀሮ ፍርድ ቤቱም ገደል እምን ላይ ተሁኖ ይነገራል በደል እንዲሉ በሀገራችን ውስጥ ምንም ዓይነት ፍትህ እኩልነትና ዲሞክራሲ እንደሌለና ዜጎች በመናገራቸው የሚታሰሩበት የሚገደሉበት በዘራቸው ምክንያት እንደ ጠላት የሚፈረጁበት ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎች ብቻ ሀገሪቱን ኢኮኖሚዋን ስልጣኑን ተቆጣጥረው ሌላውን ኢትዮጵያዊ የበይ ተመልካች አድርገው ወያኔዎች ሲጨርሱት ሲያስፈልጋቸው በጥይት ሲደፉት ይህንን እውነት ቀድሞ የተረዳው ያስቆጣው ያንገበገበው አንድአርጋቸው ፅጌ ፍትህ በዛች ሀገር ላይ እንዲሰፍን በማለት የኔ የሚለውን ነገ ሁሉ ላይ ጨክኖ ህወሀት (ወያኔን) ሊፋለም እስከ ህይወት መስዋአትነት ሊከፍል እርሱ ሞቶ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ነፃ ሊያወጣ ሁሉን ጥሎ ሜዳ ገብቶ አምባገኑን የወያኔ ስርዐትን ሊታገል የወሰነና የታገለ ሁሌም በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ያለ ታላቅ ታጋይ ነው አንድአርጋቸው ፅጌ፡፡

እርሱ ነዶ ብርሀን ሆነ የድርሻውን ያለውን ሁሉ ለአንዲት ኢትዮጵያ ከፈለ። አምባገነኑ ስርዐት የአንዳርጋቸው ፅጌን አቅምና ችሎታ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ እንቅልፍ ነስቶትና ስጋቱንም ከጫፍ አድርሶት እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ታጋይ ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት የህወሀት (ወያኔ) የስለላ ተቋም በሚልዮን የሚቆጠርን ዶላር ከማውጣት ጀምሮ ብዙ ድካምና ዋጋ እንዳሰከፈለው ግልፅ ነው ለዚህም ነው በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሀገራትን አቋርጦ በመሄድ ጠለፋን ያካሄደው የታጋይ አንድአርጋቸው ፅጌን ተፅእኖ ፈጣሪነትና ለሕወሀት ወያኔ ራስ ምታት እንደነበር የሚያሳይ ግልፅ ትእይንት ነው።

አንድአርጋቸው ፅጌ ዛሬም ቢሆን በልባችን ውስጥ ያለ ጀግና ነው ባለው ፅኑ አቋምና ቆራጥነት አልበገሬነት የወያኔን አምባገነንና አፋኝ ስርዐትን እንቅልፍ የነሳ የቁርጥ ቀን ልጅ እንዲሁም የኢትዮጵያዊያን ባለውለታ ነው፡፡ ለሁሉም ነፃነት ናፋቂና ታጋይ ኢትዮጵያዊ ለትግል ጉዞ አርአያ በመሆን የቆራጥነትን ጥግ ያሳየ መሪ ነው፡፡

አቶ አንድአርጋቸው ፅጌ ከማንም በተሻለ ሁኔታ የወያኔ (ሕወሀት) መሰሪ አሰራርን ጠንቅቆ የሚያውቅ እና ኢትዮጵያ ሀገራችንን ወደ ድቅድቅ ጨለማ እየከተትዋት እንደሆነ የተረዳ ሰው ነው ዛሬ ላይም ለነፃነት፣ ለአንድነት ፣ ለዲሞክራሲ መከበር የምንታገል ኢትዮጵያዊያን ትግል ማለት ምን እንደሆነ በደንብ የተረዳነው ከአንድአርጋቸው ፅጌ የህይወት ቆራጥነት ነው ለነፃነት የሚከፍሉ መስዋዕትነት ግራ ቀኝን ማየት መመልከት አይጠይቅም፡፡ በጠቅላላ ትኩረት እና ሀሳብን ግብ ላይ ማድረግን ብቻ ነው የሚፈልገው።

ይህ አጥፊ ስርዐት ላለፉት 26 አመታት ኢትዮጵያዊያን ላይ የቀበራቸው ፈንጂዎች ኢትዮጵያዊያን ላይ ሳይሆን ራሱ ላይ እያፈነዳ እየፈጀው ይገኛል። ጀግናው ታጋይ አንድአርጋቸው ፅጌን ቢያስሩም እርሱን የቆመለትን አላማ ማሰር አልቻሉም ለዚህም ነው ከሃገር ውስጥ ሆነ ከውጭ ሀገራት ወያኔን ገዝግዞ ሊጥለው የደረሰው አዲሱ ነፃነት ፈላጊው ትውልድ ያነገበው የፍትህ የዲሞክራሲ ጥያቄና ስርዐቱንም ከስልጣን የማስወገድ ትግል አቶ አንድአርገቸው ፅጌ ዋጋ የከፈለለትና ማየት የሚናፍቀው የነበር ነው ዛሬ ላይ ግን የእርሱ ህልም እውን ሊሆን የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ዘመን ሊያበቃ ዘረኝነቱም ሊቋጭ ቀብሩ ሊፈፀም 11ኛ ሰዐት ላይ እንገኛለን፡፡

የነፃነት አባት የሆነውን አንድአርጋቸው ፅጌና ሌሎች ብዙ ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያዊያንን የታሰሩ የተገደሉ አሁንም ድረስ በየ እስር ቤቱ የሚገኙትን ጨምሮ ሁሉንም ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሃገራችንን ኢትዮጵያን ሕወሀት ወያኔ አጥፍቶ ሳይጨርሳት ታጋይ አንድአርጋቸው ፅጌ እና ከፍተኛ የተቀዋሚ አመራሮችን ጨምሮ ህዝብን በማደራጀት እንዲሁም በማስተማርና ግንዛቤው እንዲጨምር በማድረግ የእያንዳንዳቸውን ድርሻ ቀድመው ተወተዋል ዛሬ የምናየው ህዝባዊ እንቢተኛነትና የነፃነት ትግል በእነ አቶ አንድአርጋቸው ፅጌ የመመካከርና የመተባበር አጀንዳ የመጣ ውጤት ነው፡፡

አሁን በምናየው የሃገራችን ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲያሸንፍ አንድነት ሀይል እንደሆነ ዘረኛውንና አሸባሪውን የወያኔ ስርዐት በዘረጋው የመከፋፈል እና የመበታተን ሃሳብ ውጤታማ እንዳይሆን ይህንን የሕወሀት (ወያኔ) ሴራ ቀድሞ በማጋለጥ አቶ አንድአርጋቸው ፅጌ ዋነኛና ቀዳሚ ነው፡፡

አንድአርጋቸው ፅጌ ለሃሩና ለወገኑ ቆመ እንጂ ወገኑንና ሀገሩን ለገንዘብና ለንዋይ አልሸጠም ለግል ክብሩ አልተጨነቀም የኢትዮጵያ ህዝብን እንደ መዥገር ከተጣበቀበት ስርዐት ለመገላል የከፈለውን ዋጋ እንዲሁም ለዜጎች መብትና ነፃነት መከበር የነበረውን አስተዋፅኦ የትግል አጋሮቹና ኢትዮጵያዊያን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

የወያኔ (ሕወሀት) ግፍና በደል የህዝባችን ሮሮ ማብቂያ ዋዜማ ላይ የደረስነው ቆራጥና ለአላማው ብርቱ የነበረው አንድአርጋቸው ፅጌ ያነገበውን አላማ ይዘን በፍጥነት በመጔዝ ስለቻልን ነው ከዚ ቡሃላ ያረጀው ስርዐት ምንም እድል ፋንታ የለውም በኢትዮጵያ ህዝብ እምቢተኛነት የተሸነፈ ነው፡፡ አርቆ መቅበር ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!