አማራነት የተናቀዉ ብሄራዊ አደረጃጀቱን በማፍረሱ ነዉ!

Print Friendly, PDF & Email

(TemesgenTessema)

ከአድዋ ጦርነት በፊት አማራ ጠንካራ ብሄራዊ አደረጃጀት የነበረዉ ብሄረሰብ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ነገር ግን አድዋ ላይ የተመዘገበዉ አለም አቀፋዊ ድል የመላዉ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ድል ሆኖ በታሪክ ከመመዝገብ አልፎ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር የነበሩ ሌሎች የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የኤዥያ አገሮችም ጭምር በአዉሮፓ ቅኝ ገዥዎች ላይ ያስመዘገቡት የጋራ ድል ተደርጎ መቆጠር በመጀመሩና የዚህ ታላቅ ድል ስሜት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሄራዊ ማንነታቸዉን ትተዉ በአንድት ኢትዮጵያ ፍቅር እንድወድቁና በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መንፈስ እንድዋሃዱ በማድረጉ ቀደም ሲል የነበረዉ የአማራ ብሄራዊ አደረጃጀት ወደ ኢትዮጵያዊነት አገራዊ አደረጃጀት ሊሸጋገርና ኢትዮጵያዊነት አማራነትን ሊተካ ችሏል።

ከዚህ ጊዜ በጟላ አማራነት እየከሰመ ኢትዮጵያዊነት እየጎለበተ መጥቶ በመጨረሻም አማራ የሚባል ብሄረሰብ የለም እስከመባል ደርሷል። በዚያ ዘመን የነበረዉ የአማራ ብሄራዊ አደረጃጀት ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ዉህደት በመፍጠር ወደ አገርነት በመሸጋገሩ ሳቢያ አማራነት መክሰሙ ነባራዊ ነዉ።

የ1983ቱን የመንግስት ለዉጥ ተከትሎ የአገራችን የመንግስት አወቃቀር ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም አወቃቀርን በመከተሉና ቀደም ሲል የነበረዉ ክፍለ ሃገራዊ አወቃቀር ፈርሶ ዝርያን መሰረት ያደረገ የራስ ገዝ ወሰን ሲበጅ ቀድሞ የነበረዉን ጠንካራ ብሄራዊ ቁርኝት በኢትዮጵያዊነት የቀየረዉ ትልቁ ዘዉግ አማራ ዉህድ ማንነቱን የሚያፈርሰዉን አዲስ አወቃቀር የተቃዎመ ከመሆኑም በላይ ወደየ አገርህ ሲባል አማራዊ መብትና ጥቅሙን የሚሞግት ወኪል አልነበረዉም።

በዚህ ማህበረሰባዊ ቀዉስ ሳቢያ ለኢትዮጵያ ህዝቦች መብት መከበር ከዘዉግ ነፃ አዉጭዎቹ ጎን ተሰልፎ የታገለዉ ኢህዴን የዚህ ማንነት አልቦ ብዝሃ ማህበረሰብ አሰፋሪ ሆነ ።

በዚህም ምክንያት በሽግግር መንግስቱም ሆነ ከዚያም በጟላ በነበረዉ መንግስታዊ አወቃቀር የብሄር አልባዉ አማራ እጣ ፈንታ በብሄር በተደራጁ አነስተኛ ዘዉጎች ጭምር ያለርህራሄ መጨፍጨፍ፣ በላቡና በጉልበቱ ያፈራዉን ሃብትና ንብረት እየተቀማ ከሰላማዊ ህይወቱ መፈናቀልና ብሄራዊ ዉርደት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

በወቅቱ አማራና የአማራ እርስት በግዛትነት የተመረቀላቸዉ የኢህዴን አባላት ይህ የተበተነ ብሄረሰብ ከያቅጣጫዉ ይደርስበት ከነበረዉ ጥቃት ከመጠበቅና ስለመብቱ ከመሞገት ይልቅ ያለፈ ገድሉን በመኮነን አድስ ኩልስ ማንነት ተላብሶ ተሸማቆና አንገቱን ደግቶ እንድኖር ከአሸናፊዉ ብሄር ገዥዎች የሚሰጣቸዉን ተልዕኮ ያለማመንታት ሲፈፅሙና ሲያስፈፅሙ ቆይተዋል።

ለኢትዮጵያዊነት የታገለዉ ኢህዴን ስያሜዉን ቀይሮ ብአዴን ከተባለና ለአማራ ብሄር መብትና ጥቅም መከበር መቆሙን ካወጀ በጟላም ቢሆን የአማራን መብትና ጥቅም በተጨባጭ በማስከበር አኳያ ለዘብተኛ ሆኖ ቆይቷል። ጭፍጨፋዎቹ፣ ማፈናቀሎቹ፣ የማጥላላትና የማዋረድ ዘመቻዎቹም ይበልጥ ተጠናክረዉ ተስተዉለዋል።

ብአዴን ለአማራ መብትና ጥቅም መከበር የቆመ መሆኑን ለመጀመሪያ ግዜ በመድረክ ላይ የተነፈሰዉ የድርጅቱ 35ኛ የምስረታ በአል በባህር ዳር ከተማ በተከበረበት ግዜ ሲሆን ይህን ተከትሎ በተደረጉት የአመራር መተካካት ሂደቶች አማራ ጠሎቹ የአማራ ገዥዎች ከሞላ ጎደልም ቢሆን በወጣት አማራ አመራሮች በመተካታቸዉ የአማራ ህዝብ መጠነኛ የሆነ ብሄራዊ መነቃቃት ፈጥሯ ተስተዉሏል።

የአማራን መበተንና የአማራነትን መርከስ ተገንዝበዉ የነሱ ያልሆነ ማንነት ተሰጥቷቸዉ በሌላ ብሄር የተዋጡ አማራዎች ወደ ተፈጥሯዊ ማንነታችን መልሱን በማለት አደረጃጀት ፈጥረዉ ህግን መሰረት ያደረገ አቤቱታ አቅርበዋል ፣ ወጣቶቹ የብአዴን አመራሮች ማንም ሊያምነዉ በማይችል ሁኔታ የሚመሩትን ህዝብ ስነ ልቦና በማጥናት በተለይም ደግሞ አማራ ከጦር መሳሪያ ጋር ያለዉን ልማዳዊ ቁርኝት በማጤንና ህገ ወጥነትን በህጋዊነት ለመከላከል በማሰብ የራሱ የሆነዉን የአስተዳደር ስልጣን በመመርኮዝ የጦር መሳሪያ ፈቃድ የሰጠ በመሆኑ ብዛት ያለዉ የክልሉ ማህበረሰብ ሸሽጎ ይዞት የነበረዉን ህገ ወጥ ትጥቅ ህጋዊ እንዲሆን አድርገዋል።

እነዚህ የንቅናቄዉ እርምጃዎች ፈታኝ የነበሩ ቢሆንም አማራነትን በአማራ ልብ ዉስጥ ዳግም እንድቀጣጠል አድርገዋል፣ ይህ ብቻ አይደለም ወጣቶቹ የብአዴን አመራሮች ቀደም ሲል ትዕዛዝ ብቻ ሲቀበሉበት በነበረዉ የጋራ መድረክ / ኢህአዴግ/ ዉስጥ ሌሎችንም ሊያስተምር የሚችል ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል።

አማራነት አሁን የሁሉም አማራ አጀንዳ የሆነ ይመስላል። አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት ማስቀደም ኢትዮጵያዊነትን በአማራነቱ ለዋጀዉ ብሄረ አማራ ፈታኝ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊነት ሊከፋፈል የማይችል በመሆኑ በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስም የተቀመጠ የማንም መሆን የማይችል፣ ለማንም የማይጠቅም ፣ ማንንም ከጭቆና የማያድን የጋራ ዉርስ እንጅ ዉህድ ማንነት አለመሆኑን በተጨባጭ እየተረዳ በመምጣቱም ወደጥንተ እርስቱ ምልሰት በማድረግ በአማራዊ አደረጃጀቱ ላይ ተግቶ ይስተዋላል።

አማራነት ቀደም ሲል የነበረዉን ክብር የተገፈፈዉ ኢትዮጵያን ሲያደራጅ ኢትዮጵያዊነትን ሲዋጅ አማራነቱን በመርሳቱ ሳቢያ መሆኑ እሙን ነዉ። ያልተደራጀዉን የተደራጀዉ ማፈኑ ፣ መጨቆኑ ፣ ማስገበሩና የራሱን ቀዳሚ ታሪክ ተፀይፎ የአድሶቹን ገዥዎች ታሪክ አወዳሽ መሆን መቻሉ የማንኛዉም ህብረተሰብ ነባራዊ ባህሪ በመሆኑ ባለፉት የምፅዐት ዓመታት ያልተደራጀዉ አማራ ለተደራጁት አነስተኛ ቡድኖች ጭምር ነፃ ታዳኝ እንስሳ ሆኖ ቆይቷል።

አሁን ላይ በተጨባጭ የሚስተዋለዉ ማንነትን የመሻት ሂደትም እነዚህ የምጽዐት ዘመናት የዋጁት ነባራዊ ለዉጥ እንጅ የአሁኑ አብዮት የዋጀዉ ስኬት አይደለም።

አማራነት ከማበብ አልፎ ጎምርቷል፣ የቀረዉ ነገር ቢኖር ይህን ዳግም ዉልደት በዘመነና የአገሪቱን ህግጋት መሰረት ባደረገ ሁኔታ መቅረፅ መቻል ነዉ። ይህ ደግሞ ይበልጥ በመቀራረብና በመወያየትና መብትን በፅናት በመሞገት ሊተገበር የሚችል የቤት ስራ ነዉ። ይህ የማንነት ጉዞ ለማንም ስጋት ሊሆን በማይችልና አገሪቱ የምትከተለዉን የፌደራሊዝም አወቃቀር መርህ መሰረት አድርጎ መከናወን ያለበት እንደሆነ አምናለሁ።

እርግጥ ነዉ ጉዞዉ ምሉዕ የአማራዊ ማንነት ጉዞ እንጅ አማራን አማራ ካሰኙት ነባራዊ ባህሪያቶቹ ነጥሎ ክልሱን አማራነት አንጠልጥሎ መንከላወስ ሊሆንም አይገባም።

ብሄራዊ ማንነት በግምገማ ሊታረም የሚችል ባለመሆኑ እኛ ለሌላዉ ብሄረሰብ ባለብን የዚህን ብሄረሰብ ልዩነት የመቀበልና ችሎ የመኖር ግዴታ ልክ ሌላዉ ብሄርም የኛን ልዩነት እንዲያከብርና በበኩሉ ያለበትን ችሎ የመኖር ተነፃፃሪ ግዴታ እንድከፍል ተግተን መሞገት ይኖርብናል ።

ይህ የተናጠል ጉዞ ኢትዮጵያን የሚበትን ከሆነም ሳንጎዳ፣ እራሳችንን እንደቻልን ከሌላዉ ብሄረሰብ ሳናንስም ሳንበዛም አማራ ሆነን መኖር እንችላለን። በተጨማሪም እንደቃልኪዳኑ ተስፋና እንደተሰነቀልን ራዕይ ኢትዮጵያ በዚህ የተናጠል ጉዞ ሃያልነትን የምትዋጅ ቢሆን አሁንም ከማንም ሳናንስና ሳንበዛ የድርሻችንን እያዋጣን ብሄራዊ ታሪካችንን ከነ ክብራችን ማስቀጠል እንችላለን።

የጀመርነዉ አማራዊ የተናጠል ጉዞ ስነልቦናችንን የሚፈትን ቢሆንም ዝርያችንን ጠብቆ የሚያቆይ አማራጭ የሌለዉ የዘመን ምርጫ ነዉና ተጨማሪ የማሰላሰያ ግዜ የለንም።