የአስቴር ስዩም ልብን የሚሰብር መልእክት ከቃሊቲ እስር ቤት – የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ የጎንደር አመራር አባል

Print Friendly, PDF & Email

አስቴር ስዩም ደብዳቤ ከቃሊቲ እስር ቤት ለህጻን ልጇ የተጻፈ

ይድረስ ለውድ ልጄ—–እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ፥
እናትህ አስቴር ስዩም ከቂሊንጦ እስር ቤት ኢትዮጵያ፥

ልጄ ላይቻል፣ እባባዬ በመጀመሪያ አንተ በምትፈልገኝ ቦታ ሳልገኝ ቀርቼ የእናትነት ድርሻየን ባለመወጣቴ ይቅር በለኝ የእኔ ልጅ፥ ከአቅሜ በላይ ሆኖ ቼግሮኝ ነው እንጂ ጨክኘብህ ዓይደለም እኔ እጅግ እወድሃለሁ ልጄ፥ ተኝቼም ተነስቼም አንተን የማላስብበት ጊዜ የለም፥ ሁሌም ትናፍቀኛለህ ፀጋዬ፥ እጆቼ በሰንሰለት ታስረው፣ ስጋየ በትልቅ ግድግዳ ተከልሎ እሩቅ አገር ባለሁበት የስቃይ ቦታም ድንገት ጣፋጭ ድምጽህ ይሰማኛል፥ ባሰብኩህ ቁጥር ዓይኖቼ በእንባ ይርሳሉ።

ከየት እንደምጀምር ዓላውቅም እንጂ እሄውልህ፥ ስማኝማ ብላቴናየ፥ ልንገርህ፥

ያለ እናት ያደከው ትልቁ ሰውዬ፥
ውድ ልጄ የልጅነት በረከት ስጦታዬ፥
ጎንደር ተወልጄ፥ አርማጭሆ አድጌ ከእውነተኛው መንደር
አልችልበት ብዬ ውሸትን መናገር፥
ታስሬልሃለሁ ሽዋ አዲስ አበባ ከቃሊቲው ሰፈር።

ፍትህና ነፃነትን ፈልጌ በወጣሁ ግፍና በደል ተፈራረቁብኝ
ከምወድህ ልጄ እርቄ ዘመናትን ቆጠርኩኝ
የስጋየ ክፋይ ልጄ የእናትነት ወጉን ጡቴንም ሳትጠባኝ
ድንገት እንደ ወጣሁ በዚሁ ቀረሁኝ
ቀኑን ቀን ሸኝቶት እስከምንገናኝ
እናቴ ጨካኝ ናት ብለህ እንዳትጠላኝ።

ልጄ ነፃነቴ፥ ከአያት ከቅድም-ዓያቴ የተቀበልኩትን እውነትን ላወርስህ፥ ደም አጥንታቸውን የከሰከሱባትን እምዬ ኢትየጵያን እንደ እነሱ ሁኜ ላሳይህ ፈልጌ ለእውነትና ለፍትህ ብቆም፥ ሆድ አደሩ በዛ ውሸት አሸነፈና መኖሪያየ ቃሊቲ ሆነ።

ወንጀል አልሰራሁም ግን አሸባሪ ነሽ ተባልኩኝ፥ አምላክ የሰጠኝን ማንነቴን ሊያሳጡኝ፥ አያት ቅድም-አያቴ ያቆዩልኝን ነፃነትና አገሬን ሊዘርፉኝ፣ ሲያደቡኝና በማንነቴ ሲዘባበቱብኝ አልዋጥሽ ቢለኝ፥ በአገሬ ድንበር ሲደራደሩ አይቼ አይሆንም ብላችው፥ አቋሜን ለማስቀየር አስበው በስቃይና በመከራ እሄው ማረሚያ ቤት በሚሉት በቃሊቲ የግዞት ቦታቸው አኖሩኝ አሸባሪ ብለው።

አባባዬ የኔ ውድ ልጅ አንተን የወለድኩህ በዘመን መለወጫ፣ ሰው ሁሉ ደስ በሚሰኝበት በመባቻው ጊዜ ነውና፥ አለመታደል ሆኖ አጥብቼ ባላሳድግህም፣ ለእንቁጣጣሽ አብሬህ ባልውልም፥ ምኞቴን ቢገልፅልኝ ብየ እንቁጣጣሽ አልኩህ ለእኔ አዲስ ዘመኔ ትልቅ ተሰፋዬ ነህ፥ አባባየ እሄን አትርሳው ልጄ።

አየህ ልጄ፥ እኔ አባባዬ አልኩህ አባቴን መስዬ፣ ነፃነትም አልኩህ በአገሬ በእምዬ፣ መስከረምም አልኩህ ቀን ይወጣል ብዬ፣ ላይቻል ተባለ ጎንደር አርማጭሆ፥ መንጋቱስ አይቀርም እንዲህ ጮሆ ጮሆ።

ፊትህን ፈቅጀ በባርነት ቀንበር ላልኖር ተቀፍድጀ ከሁሉም እርቄ
ምየ ተገዝቸ ለራሴው ነግሬው በተስፋይቱ ሀገር ተስፋየን ሰንቄ፥
በእስር እየገፋሁ ብኖርም በሀዘን ብኖርም ናፍቄ
ቀን ይመጣል ብየ ነገን ተስፋ አድርጌ፥
ያንተም የእኔም አምላክ አያንቀላፋም፥ ይህን እንደ ተረት እንደ እንቆቅልሽ የምናወራበት ጊዜ ቅርብ ነው አቡሽየ፥ እወድሃለሁ እባባየ።

መልካም አዲስ ዓመት! አምላኬ አደራህን ልጄን ላይቻል በለጠን አሳድግልኝ!