ተክለሚካኤል አበበ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መካድ ጥጋብ ወይስ ንቀት?

Print Friendly, PDF & Email

ተክለሚካኤል አበበ የሚባል ግለሰብ በተለያዩ ጊዜዎች በዜና ማሰጣጫዎች ላይ እየቀረበ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የተወላገዱና የተውለሸለሹ ሃሳቦችን በማቅረብ ይታወቃል። ግለሰቡ የሚያቀርባቸው ሃሳቦች በባዶ ቃላት የታጀሉ፣ አሉባልታ የሞላባቸው መናኛና ከንቱ ናቸው። ምሁራዊና የበሰለ እንዲሁም በማስረጃ የተረጋገጠ ነገር አንድም ቀን ሲናገር ተደምጦ አያውቅም። ያልሆነውን መስሎ ለመገኘት ምንም ዓይነት ምርምርና ጥናት ሳያካሂድ በዘፈቀደ የሚተፋቸው ሃሳቦች ጉዳዮችን እግር በእግር ለማይከታተሉ ሰዎች አደናጋሪ እንደሚሆኑባቸው ለመገመት ይቻላል። አዘውትሮ በአገራዊ አንኳር ጉዳዮች ላይ ጸጉር ከመሰንጠቅና ባዶ ፍልስፍና ከማቅረብ በስተቀር ጉዳዮችን ብትንትን አድርጎ መተንተንና መገምገም ሞክሮትም አያውቅም።በገሃድ የሚታወቁና የተረጋገጠ መሠረት ያላቸውን ሃቆች ሽምጥጥ አድርጎ ይክዳል። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። የተለየ ሃሳብና የግል አስተያየት ማቅረብ የማንም ሰው መብት መሆኑ አይታበልም። ሆኖም ተክሌ ግን የአእምሮ ምጥቀትና ክህሎት ሳይኖረው በጭፍን ከሰው የተለየ ሆኖ ለመታየት ብቻ ሲዘላብድና መያዣና መጨበጫ የሌላቸውን ቅዠቶች ሲነዛ ይታያል። ለአብነት ያህል አንዳዶቹን ልጥቀስ

• በዘመናችን ከተነሱትና አገር ጥለው ሳይሸሹ የኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል ሆነው ለአገር አንድነት፣ ለህዝብ መከባበር፣ እኩልነትና ሰላም የሚቻላቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙትን እንደ ድምጻዊ ቲዎድሮስ ካሳሁን ያሉትን ያጣጥላል፣ ያንቋሽሻል

• ወያኔ የሚያራግባቸው በብሔሮች መካከል ያለውን ግንኙነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይደግፋል

• አማራው እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔረሰብ የሚደርስበትን ጥቃት ተከራጅቶ መከላከል አያምርበትም፣ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ አለበት ይላል

• በወያኔ ላይ ሰልፍ የሚወጣ በሙሉ አማራ ነውና የመሳሰሉትን ቅጥፈቶች ይነዛል

ይህችን አጭር ማስታወሻ ለመጻፍ ያስገደደኝ ተክሌ አዲሱን የኢትዮጵያን ዓመት አስመልክቶ የላከውንና በፌስቡክ ላይ የለቀቀውን መልዕክት ስላየሁ ነው። ተክሌ እንደሚታወቀው መተዳዳሪያው/ገቢው በኢትዮጵያውያን ማህበረስብ አባላት ላይ የተመሠረተ ነው። (አሁን እንደበፊቱ ከካናዳ መንግሥት ዳረጎት/ዌልፌር የሚበላ አይመስለኝም) ስለሆነም ለኢትዮጵያውያን ደንበኞቹ መልካም አዲስ ዓመት የሚል መልዕክት ማስተላለፉ አይከፋም። ሆኖም በላከው መልዕክት ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሳያወጣ በምትኩ የካናዳን ሰንደቅ ዓላማ አስፍሯል። (ከዚህ በታች ያለውን እራሱ አስረጅ የሆነውን በተክሌ ፌስቡክ ላይ የሚገኘውን ተመልከቱ)

አዲስ ዓመት የምታከብረው አገር ኢትዮጵያ ናት እንጅ ካናዳ አይደለችም። የካናዳ አዲስ ዓመት ከሶስት ወር በላይ ይቀረዋል። የኢትዮጵያ አዲስ አመት መልካም ምኞት መግለጫ ካርድ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሳያወጣ የካናዳን ማውጣት ግለሰቡ የአእምሮው ሚዛን የተቃወሰና ፉርሽካ ለመሆኑ አያጠራጥርም።ስለሆነም በፊስ ቡክ ላይ ለምን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላም አላወጣህም ተብሎ ለቀረበበት ተቃውሞ የሰጠው መልስ እጅግ አሳፋሪና ደደብነቱንና ባዶ ስልቻነቱን ያረጋጥጣል። አንዳዶች በፌስቡክ የተጻፈውን ተመልከተው እንደተናገሩት “አይጥ ዝሆን አክላለሁ ብላ ፈንድታ ሞተች” እንደሚባለው ተረት ተክሌም አለችሎታው የማያውቀውን ከሚያቦካ ቢቀርበት ይሻል ነበር ብለዋል።የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ የመታው በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለሞች ባሸበረቀው ሰንደቅ ዓላማችን መሆኑንና እንዲሁም ከዛም ወዲህ ባሉት ጊዜዎች የተለያዩ የአገር ሉዓላዊነት ማስከበሪያ ተጋድሎዎችና ህዝብ በቤተክርስቲያንና በመስጊድ አክብሮ የሚያውለበልባትን ሰንደቅ ዓላማን “የትኛው እንደሆነ ስላማላውቅ አላወጣም” ብሎ በድፍረት መልስ ሰጥቷል። በዚህም ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጠቀምበትን “የዲያብሎስ” አርማ ለተለጠፈበት ባንዲራ እውቅና ሰጥቷል። ተክሌ በካናዳ ተደላድሎ ከኢትዮጵያውያን በሚያገኘው ገቢ ተመችቶትና ወፍሮ ቂቤ እንደጠገበ ማሰሮ አወልውሎ እየኖረ ሁልቆ መስፍርት የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን የደም ዋጋ የገበሩባትን ሰንደቅ ዓላማ እያዋረደ ነው። ይህንን የሚመለከት ኢትዮጵያዊ በሙሉ ከዚህ ከሃዲና ወራዳ ግለሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ባስቸኳይ ማቋረጥ ይኖርበታል እላለሁ።አገርን እያዋረዱ ከአገር ሰው ገንዘብ ለመሞጭለፍ መሞከር የዘቀጠ ድርጊት ነው። ኢትዮጵያን ማዋረድ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑንንም እሱና መሰሎቹ አበክረው መረዳት ይገባቸዋል።

አሉላ መካሻ
ቦልትሞር፣ ሜሪላንድ