በጎንደር በቅማንት ስም ሕዝበ ውሳኔ ከሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች መካከል 2 ጎንደር ከተማ የሚገኙ ሲሆን ሕዝቡ ውሳኔውን እየተቃወመ ነው።

Print Friendly, PDF & Email

በሰሜን ጎንደር ዞን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቅማንት ሕዝብ አንስቶት የነበረውን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ሲባል በ12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጭልጋ ወረዳ ያሉ አራት ቀበሌዎች በሕዝበ ውሳኔው ላይ ቅሬታ ማንሳታቸውን አቶ ዳኘው ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ዳኘው ገለጻ፣ ጭልጋ ወረዳ ሕዝበ ውሳኔው ከሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች መካከል ስድስቱ የሚገኙበት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አራቱ ማለትም ገለድባ፣ አንከራደዛ፣ ሹምየና አውርደርዳ ቀበሌዎች ውስጥ ከነዋሪዎች ቅሬታ ቀርቧል፡፡

በእነዚህ ቀበሌዎች የሚኖረው ሕዝብ ዋነኛ ጥያቄም፣ ‹‹ቅማንቶች ከ20 በመቶ በታች ሆነውና በቁጥር ደረጃ እኛ አማራዎች በልጠን ሳለ ሕዝበ ውሳኔው ለምን አስፈለገ የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ለቅሬታው በሰጠው ምላሽ እንደተባለው የአማራዎች ቁጥር የሚበልጥ ከሆነ በድምፅ መስጠት ሒደት የሚረጋገጥ እንደሚሆን፣ መጭበርበር እንዳይኖር ተብሎም ታዛቢዎች የሚመጡት ከሌላ ክልል እንደሆነም እንደተገለጸ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አቶ ዳኘው ማብራርያ፣ ሕዝበ ውሳኔ ከሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች መካከል ሁለቱ ጎንደር ከተማ ውስጥ ሲገኙ፣ አራቱ ደግሞ መተማ ውስጥ የሚገኙ ቀበሌዎች ናቸው፡፡

የቅማንትና የአማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ከተነሳባቸው መካከል በ12 ቀበሌዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔውን መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማድረግ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡- ኢትዮጵያን ሪፖርተር