በውጭ ሀገራት የሚኖረው የአማራ ዲያስፖራ ነገር!

Print Friendly, PDF & Email

(YohannesAmhara)

በዚህ አለም ላይ እንደ አማራ ዲያስፖራ ራስ ወዳድ የለም..በአፋቸው ህዝባቸውን እንዋደለን ይላሉ እንጂ በተግባር ዜሮ የሆነ የማህበረሰብ ክፍል ነው። በመላው አለም ከ1 ሚሊዮን በላይ የአማራ ዲያስፖራዎች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከእኒህ ውስጥ ለአማራ ህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀትም ሆነ የአቅማቸውን ለማበርከት የሚሞክሩት 100 እንኳ አይሞሉም። በፖለቲካው ዘርፍም ቢሆን ለህዝቡ ነጻነት እና እኩልነት የሚታገሉ ሰዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አብዛኛው የአማራ ዲያስፖራ ‘ልጄን ላሳድግበት፤ አፓርትመንቴን ልጨርስበት፤ ሃገር ውስጥ ያለው ኢንቨስትመንቴ ይጎዳል፤ የልጆቼ ትምህርት ይስተጓጎላል፤ ሃገር ቤት እንዳልገባ እከለከላለሁ’ በሚሉ ተልካሻ ምክንያቶች የአማራን ህዝብ ህይወት ሊቀይሩ ከሚችሉ የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትግሎች ርቆ የራሱን ህይወት ብቻ የሚያጣጥም ከሞቀ ጎጆችውም መውጣት የማይፈልግ ህዝብ ነው።

ይህንን ጉዳይ እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ የህዝባችንን ብሶት እና እየተሸረበበት ያለውን ሴራ ለማሳወቅ እና ለማንቃት የሚያስችል ሚዲያ ባለማቋቋማችን የአማራ ህዝብ ህይወት ከትላንት እና ዛሬ ይልቅ ነገ አሳሳቢ ሆኖ ስለሚታየኝ ነው። ስለ ወልቃይት፤ ራያ፤ ቅማንት፤ አዲስ አበባ የማንነት እና የግዛት ጉዳዮች እንዲሁም ህዝቡ ስለተደቀነበት የድህነት እና ኋላቀርነት አረንቋ ለማሳወቅ የሚችል ሚዲያ ስለሌለን ችግሮች በችግሮች ላይ እየተደራረቡ ነገን በፍርሃት እንድንኖር ተገደናል። ሚዲያ ሃይል ነው፤ ሚዲያ መስታወት ነው፤ ጉድፍህን አጥርቶ የሚያሳይ..ከምንም በላይ ሚዲያ የህዝብ እስትንፋስ ነው።

ታዋቂው አፍሮ- አሜሪካዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር

“በምድር ላይ እጅጉ ጠንካራ ነገር ሚዲያ ነው። ሚዲያ ንጹሃንን ወንጀለኛ ማድረግ ይችላል፤ ወንጀለኛን ደግሞ ንጹህ የማድረግ ሃይል አለው። ምክንያቱም የብዙሃንን አእምሮ የመቆጣጠር ችሎታ አለውና“
The media’s the most powerful entity on earth. They have the power to make the innocent guilty and to make the guilty innocent, and that’s power. Because they control the minds of the masses”

ሚዲያ ይህንን ያህል አቅም ካለው በአማራ ጉዳይ ላይ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንስቶ እስከ ሲቪክ ማህበራት፤ ከኢንቨስተሮች እስከ አክቲቪስቶች፤ ከምሁራን እስከ ተማሪዎች በውጭም ይሁን በሃገር ውስጥ ያለን አማሮች በሙሉ በጋራ ተባብረን አንድ አማራዊ ሚዲያ ማቋቋም ግድ ይለናል። በተለይ ደግሞ በፋይናንስም ይሁን በእውቀት የተሻለ እድል ያለው የአማራ ዲያስፖራ ግንባር ቀደም ሃላፊነት አለበት። ገንዘብ በመርዳት፤ የቴክኖሎጂ እገዛ በማድረግ፤ የሚዲያ ስራ በመስራት እና መረጃዎችን በማሰባሰብ እንወደዋለን ለምንለው ህዝብ አንድ ቁምነገር መስራት ግድ ነው።

አማራዊ ሚዲያ ለማቋቋም የሃይማኖት ልዩነት ምክንያት አይሆንም፤ የነገድ ልዩነት ምክንያት አይሆንም፤ የፖለቲካ ርእዮተ አለም ልዩነት ምክንያት ሊሆን አይገባም። ፕሮጀክቱን ዳር ለማድረስ አማራ ወይንም የአማራ ወዳጅ መሆን ብቻ በቂ ነው። ጥቂት የአማራ ወጣቶች ከትምህርት እና ስራ የተረፈቻቸውን ጊዜ እንደምንም አብቃቅተው በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰሯት ስራ ብዙ ለውጦች መጥተዋል። ይህ የወጣቶች ልፋት ግን 40 ሚሊዮን የአማራ ህዝብን መድረስ አይችልም፤ የዚህን ሁሉ ህዝብ ችግርም መቅረፍ አይችልም። የወጣቶቹ ተነሳሽነት ሚዲያ ለማቋቋም እና ትግሉን ዳር ለማድረስ እርሾ ይሆናል እንጂ በራሱ በቂ አይደለም።

እናም ገንዘቡ እና አቅሙ ያላችሁ የአማራ ዲያስፖራዎች ሊቆጫችሁ ይገባል። አንድ የሃይማኖት መሪ፤ የኪነጥበብ ባለሙያ ወይንም ባለሃብት የግል ቴሌቪዥን በሚያቋቁምበት ሃገር ለ40 ሚሊዮን ህዝብ አንድ ሚዲያ ማጣትን የመሰለ ምን የሚያስቆጭ ነገር አለ። እንወደዋለን ብለን የምንምልለት እና ምንገዘትለት ህዝብ በወልቃይት፤ ራያ፤ ቅማንት እና አዲስ አበባ እንዲሁም በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል መከራውን እያየ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ኢሰብአዊነት፤ አረመኔነት እና ህሊና ቢስነት ነው።

የአማራ ሚዲያ አሁኑኑ ያስፈልገናል!
ዲያስፖራው ደግሞ ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት!