የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) የውህደት መግለጫ

Print Friendly, PDF & Email

የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) የውህደት መግለጫ  ( pdf )

የተከበራችሁ የዐማራ ልጆች፤ የዐማራ ወዳጆች እና ኢትዮጵያውያን፤

እንደሚታወቀው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የሰፊውን የዐማራ ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት መፈጸም ከጀመረ 42 ዓመታትን አስቆጥሯል። በተለይ የስልጣን ርካቡን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 26 ዓመታት ጥቃቱ ተጠናክሮ ቀጥሎ እስካሁን ከ6,000,000 (ስድስት ሚልዮን) በላይ የዐማራ ሕዝብ ለእልቂት እንደተዳረገ አሳማኝ መረጃዎች አሉ። የራሱ የትግሬ ወያኔው የአፓርታይድ አገዛዝ “ተወካዮች ምክር ቤት” ሳይቀር በተጠናቀቀው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት የዐማራው ሕዝብ ከሚጠበቀው በ2.4 ሚልዮን አንሶ መገኘቱን አምኗል። የህወሃት መራሹ አገዛዝ ዐማራውን በዘር ለይቶ ማጥቃቱን/ማስጠቃቱን አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል። ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በ”አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ሰበብ ወጣቶችን ያስራል፤ በየማጎሪያ ጣቢያዎች ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ይፈጽማል፤ አልፎ ተርፎም ይገድላል። የዓለማአቀፉን ማሕበረሰብ ተቀባይነት ላለማጣት ሲል “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን” አነሳሁ ብሎ ቢያስነግርም አሁንም የወገን ግድያ፣ እንግልት፣ የጅምላ እስራትና ግፉ እንደቀጠለ ነው።

ስለሆነም ዛሬ የዐማራው ሕዝብ ህልውና በመኖር እና ባለመኖር መካከል የሚገኝ ሲሆን ከዚህ እየተፈጸመበት ካለው የዘር ማጥፋት እልቂት እና መጠነ ሰፊ መፈናቀል ለመታደግ ይቻል ዘንድ በዐማራ ስም የተዋቀሩ የተለያዩ ድርጅቶች ወደ አንድ መጥተው በጋራ መስራት ከመቸውም ጊዜ የበለጠ አስፈላጊ ነው። ይህን የተረዱት የቤተ አማራ-መድሕን እና የዳግማዊ መላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (ዳግማዊ መዐሕድ) ድርጅቶች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የውህደት ሂደት ማካሄድ መጀመራቸውን በመጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም የሁለቱ ድርጅቶች ሊቀ መናብርት በጋራ ባወጡት መግለጫ ለሕዝብ ማሳወቃችን ይታወቃል። ከሁለቱ ድርጅቶች የተውጣጣው የውህደት ጉባዔም በዋሽንግተን እና ዙሪያው በተደጋጋሚ እየተሰበሰበ ድርድሮችን ሲያካሂድ፤ የየድርጅቶችን መተዳደሪያ ደንቦች ሲመረመርና ሲያቻችል ቆይቶ የተጣለበትን ኃላፊነት ስለተወጣ ውህደቱ ነሐሴ 14 2009 ዓ.ም. ፍጻሜውን አግኝቷል። የውህድቱ ድርጅት ስያሜም የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) እንዲሆን የወሰንን ሲሆን የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ፈለግ ተከትለን ዐማራው ለህልውናው ለሚያደርገው ትግል ድርጅታችን አጋር እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለን። ይህ ውህደት የመጀመሪያችን እንጂ የመጨረሻ አይሆንም። ሁሉንም ዐማራ በአንድ የትግል ጥላ ሥር የማሰባሰቡ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ድርጅቱን ወደተሻለ ደረጃ ያደርሳሉ የተባሉ ጊዜያዊ የአመራር አባላትን የመረጥን ሲሆን ከ6 ወራት በኋላ ጠቅላላ ጉባዔው በተገኘበት ይፋዊ ምርጫ የሚካሄድ መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

ድል ለዐማራ ሕዝብ!
ፈለገ አስራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!
የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት

http://www.aapo2nd.org/?p=1608