“አለባብሰዉ ቢያርሱ፣ በአረም ይመለሱ”!! – የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ደርጅት

Print Friendly, PDF & Email

“አለባብሰዉ ቢያርሱ፣በአረም ይመለሱ”!!

ቅጽ ፩ ቁጥር ፰ እሑድ ነሐሴ ፳፰ ቀን ፪ሺ፱ዓ.ም.    (አለባብሰዉ ቢያርሱ፣ በአረም ይመለሱ pdf)

ይህ ከላይ የተጠቀሰው አባባል የአገራችን “ትጉሁ ገበሬ” የጥራት ሥራ መርሑ ነው። እያንዳንዱ ትልም እንደ መሬቱ ዓይነት በሚገባው የጥልቀት መጠን ማረሻው ወደ ውስጥ ጠልቆ ፣ የውስጡን ወደ ውጭ የውጭውን ወደ ውስጥ ገለባብጦ ካላረሰ በአረም ወቅት አስቸጋሪ ሥራ የሚገጥመው እንደሚሆን ስለሚረዳ፣በአስተራረሱ ላይ አስፈላጊውን ማድረግ እንዳለበት የሚመራበት የግብርና ሥራ መርሑ ነው። ለዚህም ገበሬው አስቀድሞ ለዘር የሚያመቻቸዉን መሬት ባግባቡ ያርሳል፤ የአረም ዘር የሆኑትን ከሥራቸው በማፍለስ ዳግም ወደ አረምነት እንዳይለወጡና የአረም ሥራውን አስቸጋሪ እንዳያደርጉበት ለፀሐይ በማጋለጥ እንዲደርቅ ያደርጋል። ጎቶዎችን ይነቅላል። አፈሩን ያለሰልሳል። ይህንም በአግባቡ ሲያከናውን የአረም ወቅት ሥራው የቀለለ ከመሆኑም በላይ የዘራው አዝመራ ተፈላጊውም ምርት እንዲሰጥ ያስችለዋል። ሕዝብን አደራጅቶ የመብትና የነፃነቱ ባለቤት ለማድረግ የሚተጉ ወገኖችም ከዚህ የትጉ ገበሬዎች አባባል ቁምነገር ሊገበዩ እንደሚችሉ እናምናለን።

ዛሬ ዐማራው የተከፈተበትን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ለማስቆምና ዐማራው ኅልውናውን አስጠብቆ የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ዓላማን አንግቦ የተነሳው የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አባላት፣ አካላትና ደጋፊዎች ወደ ዓላማቸው ግብ ለመድረስ የዐማራውን ነገድ ከኢትዮጵያዊነት ማንነት ጋር ማዕከል ያደረገ የማንቃት፣ የማደራጀትና የማስታጠቅ ሥራ በትጋት ሊሠሪ ይገባል። ይህ በአግባቡ ሢሠራ፣ ውጤቱ ያማረ፣ የድል ጊዜው ያጠረ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ “የትግሬ ወያኔን ቡድን የሥልጣን አገዛዝ በቃህ” ብሎ አምርሮ ከመጮህ አልፎ ክቡር ሕይወቱን በአደባባይ ቤዛ እያደረገ እንዳለ በየዕለቱ እያየን ነው። ሕዝቡ የትግሬ ወያኔን አገዛዝ በቃህ ያለው፣የሥልጣን ባለቤቶቹ ትግሬዎች ስለሆኑ አይደለም። የሚያራምዱት ፖለቲካ ዘረኛ፣ ከፋፋይ ከመሆኑም በላይ፣የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፣ ሕዝቡን በቋንቋ ሸንሽኖ አንድነቱን ከማሳጣቱም በላይ፣ በኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የተጫወተውን የዐማራን ነገድ በጠላትነት ፈርጆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸምበት ያደረገ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ዐማራ በመሆኑም ጭምር ነው።

ይህን ወያኔ በአገርና በዜጎች ላይ የፈጠረውን አስከፊ ሁኔታ በማስወገድና በምትኩ በሁሉም ዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚቋቋም ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ፀረ-ወያኔ የሆነው የኅብረተሰባችን ክፍል ትግሉን በተቀነባበረና በተቀናጀ መንገድ ሊመራው ይገባል። ይህን ለማድረግም ከሁሉም ወገን የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም መከበር፣ የሕዝቡን ዕኩልነት፣ ነፃነት፣ የሕግ የበላይነትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ለሆኑት ተቋሞች ግንባታ ዙሪያ የማያወላውል አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ወሳኝ አቋም በግልጽ መያዝና ለተግባራዊነቱ ቆርጦ መሥራት ባልተቻለበት ሁኔታ ዉስጥ “የተናጠሉም ይሁን የጋራ ድርጅታዊ አቋም” ፣ ሕዝብ በአስቸኳይ ለሚሻው የሥራዓት ለውጥ አስተማማኝ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። በሌላ አባባል “በትግሬ ወያኔ ቡድን” የተዘረጋዉን “የፖለቲካ ሥርዓት” ንዶ፣ ሁሉን አሳታፊ በሆነ ዴሞከራሲያዊ “የፖለቲካ ሥርዓት” ለመተካት የፀረ-ወያኔው ቡድን ከኅብረት እስከ ግንባርና ውኅደት ባሉት የአንድነት ቅርፆች መደራጀት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይሆንም።

በዐማራ ኅልዉና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) እሳቤ መሠረትም ትልቁ የአገሪቷ የፖለቲካ ችግር፣የተቃዋሚው ጎራ ወጥ አመለካከትና አደረጃጀት ይዞ፣ ከወያኔ የተለየ ለኢትዮጵያ አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል አማራጭ ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ሕዝብ አለመቅረብ አንኳሩ ችግር እንደሆነ ያምናል:: ለዚህም ነው ወያኔ 26 ዓመት ሙሉ ሥልጣን ላይ ለመቆየት የቻለው። የሥልጣን ዕድሜው መራዘምም አገሪቱ እንደ አገር እንዳትቀጥል የሚያስችለውን የማፍረስ ሥራ እንዲሠራ ምቹ ሁኔታ እንዲያገኝ እንዳደረገው የምንገኝበት ሁኔታ ያሳያል። የተቃዋሚው ጎራ በዚህ መንገድ ከቀጠለ ወያኔ ኢትዮጵያን የማፍረሱን ሥራ እንዲያጠናቅቅ የፈቀደለት ያል መሆኑን ሊገነዘብው ይገባል።

ብዙዎቹ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶች፣ ወያኔ ለረጅም ጊዜ አገርና ሕዝብ እየገደለ በሥልጣን መቆየቱን ይቃወማሉ እንጂ፣ ወያኔ የዘረጋዉን አስከፊ የፖለቲካ ሥርዓት ከሥሩ ለመንቀል የሚያስችል የበሰለ የፖለቲካ ሥራ ሢሠሩ አይስተዋሉም። የዚህም ዋናው ምክንያት ሁሉም ተቃዋሚ ነን የሚሉት ድርጅቶች የአደረጃጀት መርሕ ወያኔ ከዘረጋው ዘር ተኮር ከሆነ አደረጃጀት መላቀቅ አለመቻላቸው ነው። የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱም ወያኔ የሚጠቅመውም ሆነ የሚጎዳው ዘርን መነሻና መድረሻ ማድረጉ ነው። ይህም እነዚህ ድርጅቶች በአንድ ወቅት የወያኔ አባሪና ተባባሪ ሆነው የተፈጠሩና በሂደት ከጨዋታው የተገፉ፣ሌሎች ደግሞ ወቅት በፈጠረውና ይህም ትክክል ነው ብለው ባሰቡ ቡድኖች የተመሠረቱ በመሆናቸው የፊተኞቹም ሆኑ የኋለኞቹ አቋማቸውን ፈትሸው ለለውጥ አለመዘጋጀታቸው ነው። ከሁሉም በላይ በዘመነ ወያኔ የተመሠረቱ ድርጅቶች ሁሉም ሊባል በሚቻልበት ደረጃ፣ የተደራጁት ዐማራን በጠላትነት ፈርጀው ነው። ይህም በዘር ተደራጅቶ የማያውቀው የዐማራ ነገድ ኅልውናውን ለማስጠበቅ ሲል በቋንቋ መሥፈርትነት እራሱን እንዲያደራጅ ግድ ብሎታል። ይህ የኅልውና ጉዳይ ተፈጥሮአዊ ራስን ከመከላከል ያለፈ ሌሎችን በጠላትነት የማይፈርጅ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ሥጋት ይሆናል የሚባል አይሆንም። ምክንያቱ በዘር የመደራጀቱ መሠረታዊ ምክንያት ኅልውናን የማስጠበቅ እንጂ፣ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅን አይደለም። ኢትዮጵያ ለዐማራው ምንነቱ ብቻ ሳትሆን እምነቱ ጭምር ናትና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ጠሪም ሆነ ነጋሪ የሚሻ አለመሆኑ ጠላትም ወዳጅም በሚገባ ያውቁታል።

የዐማራ ኅልዉና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)ም ሆነ ሌሎች በዚሁ ነገድ ዙሪያ የተደራጁ ድርጅቶች ሁሉም በሚያስብል መልኩ ወያኔን ለማስወገድና በምትኩ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው “የጋራ ጥረት” የየራሳቸውን ጉልህ ሚና ለመጫወት ቀዳሚዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፕሮግራሞቻቸው መረዳት ይቻላል::

እንዲያዉም የዐማራ ነገድ ትልቁ ችግሩ በወያኔና ተላላኪዎቹ እየደረሰበት ያለውን እጅግ የከፋ የኅልውና አደጋ ለመለወጥ “ቢያንስ ቢያንስ እንኳ አቅሙ በቻለ” መጠን ፊት ለፊት የተከፈተበትን ጥቃት ለመመከት ከመሞከር ይልቅ፣ የአንድነትንና የኢትዮጵያን ስም ለጠሩ ድርጅቶችና ቡድኖች ሁሉ ዛሬም ድረስ ገንዘቡን፣ ጊዜዉንና ሕይዎቱን ከመገበር ወደ ኋላ አለማለቱ፣ ወዳጅና ጠላቱን በአግባቡ ፈትሾ መለየት አለመቻሉ ነዉ::

በሌላ በኩል ደግሞ “በዐማራ ስም የተደራጁ የሉም፣ ወይም ደግሞ ለትብብር አይመጥኑም” ባሉበት አንደበታቸው እዚያው በዚያው፣”የዐማራ መደራጀት ለኢትዮጵያ አንድነት አደገኛ ነዉ፣ ወይም ወያኔ በከፈተው ቦይ መፍሰስ ነዉ” እያሉ ውኃ የማያነሳ ምክንያት የሚደረድሩ እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ዛሬም ድረስ እየሰማን ያለው አሳዛኝ ሁኔታ ቢሆንም ቅሉ፣ ሐቁ ግን የዐማራ ነገድ በወያኔና በተላላኪዎቹ አማካኝነት በአራቱም ማዕዘን ጥቃት እየተፈጸመበት ያለ በመሆኑ ዐማራው ራሱን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ ቅድሚያ የራሱን ኅልውና መታደግ መቻል ለኢትዮጵያ አንድነትም መድኅን መሆኑ ምስጢር አይደለም!!

እርግጥ ነው አንዳንዶቹ በዐማራው ነገድ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ ያልታያቸው ወይም ሆን ብለው እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ “ወላጅ እናቱ ገበያ የሄደችበትን ሕፃን ልጅና እናቱ የሞተችበት”ን በዕኩል መልክ የሚያዩ ሰዎች፣ በዐማራው ላይ የተፈጸመውን የዘር ዕልቂትና የዘር ማጽዳት ተግባር አቃለው የሚያዩ እንዳሉ ይታወቃል። የዚህም መሠረታዊ ምክንያቱ አንድም ዐማራውን በጠላትነት የመፈረጁ፣ ሌላም «በሰው ቁስል ስንጥር ስደድበት» የሆነባቸው እንደሆን መገንዘብ ይቻላል። ቁስሉ የሚሰማቸው የዐማራ ልጆች ደግሞ፣ የጥቃት ሰላባ የሆነው ወገናቸው ኅልውናው አደጋ ላይ ወድቆ እያዩ ዝምታን አልመረጡምና ፊት ለፊት ዕውነታውን በመጋፈጥ ዐማራው ራሱን አደራጅቶ ከጥቃት እንዲከላከል የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው። ይህን ድርጊት መደገፍ ዐማራ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ ይበቃል። ለዚህም የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዐማራዊ ብሔርተኝነትን ሳይሆን፣ የዐማራን ኅልውና ከማስጠበቅ ጎን፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።

በዐማራ ነገድ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና ግፍ ሌሎች አለን ከሚሉት ችግሮች ጋር ሊመዘን አይችልም። ሌሎች ችግር እንዳለባቸው ቢታወቅም፣ አገር ልቀቁ ግን አልተባሉም። በጠላትነትም አልተፈረጁም፤ በዚህም የተነሳ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል አልተፈጸመባቸውም። ይህም በመሆኑ በዘመነ ወያኔ ግፈኛ አገዛዝ ከሁሉም ነገዶች ተለይቶ እጅግ የከፋ በደል የተፈጸመበት ዐማራው ነው። በነገዱ ዙሪያ የመደራጀቱም ዋና ምክንያት ይህ በተለየ የተፈጸመበት ግፍ መብዛት የተነሳ ኅልውናውን አደጋ ላይ በመጣሉ ራሱን ከጥፋት ለመከላከል መሆኑን ማንም ሊረዳው ይገባል እንላለን። ይህም በመሆኑ ለኢትዮጵያ አንድነት በሚሉ ስብስቦች የሚቀርቡ ጥሪዎች ይህን የዐማራውን ልዩ ሁኔታ ያገናዘቡ መሆን አለባቸው እንላለን። ይህን ሁኔታ ሳያገናዝቡ ፣ መነሻውና መዳረሻው ከወያኔ ላልተለየ የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታ ትብብር ወይም ኅብረት ስለተባለ ብቻ በዐማራ ነገድ ዙሪያ የተደራጁ ድርጅቶች እየሄዱ የሚወዘፉበት ፋይዳው አይታየንም:: በዚህ ረገድ በአግ7 አስተባባሪነት ተመሠረተ የተባለው “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ ከመያዙ ባለፈ በዐማራው ነገድ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ትኩረት ካለመስጠቱም በላይ፣ በዐማራው ላይ የዘር ፍጅት የፈጸሙ ግለሰቦችን ያቀፈ መሆኑ በራሱ አገራዊ ንቅናቄው በአስተሳሰብ ከወያኔ የተለየነው ሊባል የሚችል ሆኖ አላገኘነውም።

እንዲያዉም እጅግ በጣም በሚገርም ሁኔታ የዚሁ “የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ” ማሰሪያ ሰነዶች የወያኔና ኦነግ ዐማራውን አግልለው ብቻ ሳይሆን፣ ሆን ብለው ብሔራዊ ጥቅሙንና ማንነቱ አዋርደው በጫካ የቋጠሯቸው ሰነዶች ዐብይ ሰነዶች ሆነው የቀረቡብትን ሁኔታ ስናጤን ይህ ንቅናቄ የስም እንጂ በተግባር ከወያኔ ያልተለየ ለመሆኑ ሰነዶቹ ነቃሾች ናቸው:: ይህ ድርጊት በአሮጌው ጠርሙስ ውስጥ ያለውን የወያኔን “መርዝ” ከ26 ዓመታት በኋላ፣ በአዲስ ጠርሙስ አጋብተው ዐማራውን ሊግቱት ዝግጅት እያደረጉ እንዳሉ ልንረዳ ይገባል።

ይህን እንድንቀበል ጫና ማድረግ ወይም ባለመቀበላችን ደግሞ ዞር ብሎ በአሉባልታ መጠመድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን ትግል አንድ እርምጃም እንኳ ፈቀቅ አያደርገውም:: በአንጻሩ ዐኅኢአድ ሕብረት/ትብብር ወይም ዉኅደት ሲል የትግሬ ወያኔና ኦነግ በ1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎ ውጭ (የዐማራ ነገድ በማግል ጭምሮ) የተወሰኑ አፍራሽ አገራዊ ዉሳኔዎች “በአዲስ: ኢትዮጵያዊነትንና የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ አንድነትና እኩልነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው ብሎ በጽኑ ያምናል”!!

ማንም ያለፉትን የ26 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት የተከታተለ ሰው ሊረዳው እንደሚችለው፤ የትግሬ ወያኔና ኦነግ ኢትዮጵያን ለመበታተን በሌንጮ ለታ የተዘጋጀውን «የሽግግር መንግሥት ቻርተር» የተባለውን የሻዕቢያ፣ የወያኔና የኦነግ የጋራ ስምምነት ውጤት የሆነውን ሰነድ የወያኔ አገዛዝ «ሕገ-መንግሥት» ሆኖ በሥራ ላይ የዋለ መሆኑ ይታወቃል። ዛሬ ከ26 ዓመታት በኋላም «የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የተባለው ድርጅት ዋና ተዋንያን ሌንጮ ለታ መሆን ግልጽ ነው። ይህ ሰውና የሚመራው ድርጅት ከተሰኔ የሦስቱ ድርጅቶች ስምምነት ውጭ ያመጣው ሀሳብ ካለ፣ ይህም እንደአዲስ ከተቀበልነው፣ «በኢትዮጵያ አንድነት ሥር የኦሮሞ የራስ ግዛት መከበር አለበት» ማለቱ ብቻ ነው። ይህ የወያኔን ሕገ-መንግሥት እንዳለ ከመቀበል የሚለየው ነገር የለም። ይህ በግልጽ እየታወቀ፣ ከትግሬ ወያኔ አገዛዝ የተለየ የፖለቲካ

ሥርዓት ለመዘርጋት ፍላጎቱም ሆነ የማድረግ አቅሙ ከሌላቸው ወገኖች ጋር በዐማራ ነገድ ዙሪያ የተደራጁ ድርጅቶች ተባባሪ እንዲሆኑ የሚታሰበው በምን ስሌት እንደሆነ በግልጽ ሊፈተሽ ይገባል እንላለን።

እርግጥ ነው የትግሬ ወያኔን የፖለቲካ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ አውርዶ ለመጣል በፊታችን ያለው ውጣ ውረድና ትግል እየጠየቀ ያለው መሥዋዕትነት እንዲህ ቀላል አለመሆኑን ከማንም በላይ ለኅልውናችን እየተዋደቀ ያለው የዐማራ ልጆች በሚገባ ያዉቁታል:: ከዚህም አኳያ ኅብረት/ትብብርና የጋራ የመፍትሔ ሀሳቦች እጅግ በጣም አስፈላጊና ለነገ የሚባሉ ጉዳዮች እንዳልሆኑም ዐኅኢአድ በሚገባ ይገነዘባል:: ዐኅኢአድ የማይቀበለው ኢትዮጵያንም ሆኖ የዐማራን ነገድ ለዳግም ጥቃት አጋልጦ የሚሰጥን አለባብሶ ማረስን ነው!!

የዐማራ ኅልውና መረጋገጥ፣ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!!