የዐማራው ጉዳይ?

Print Friendly, PDF & Email

የዐማራው ጉዳይ?

ቅጽ 1 ፣ ቁጥር 7 ቀን፦ ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2009 ዓ.ም.

ዐማራው በኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ የሚያምን ሕዝብ ነው። ለነፃነት ቀናዒ ነው። ፍትሕ አክባሪና ፈላጊ ነው። ጀግንነት ከርኅራኄ እና ከየዋሕነት ጋር ለንቅጦ የያዘ ነው። ይህ አቋሙና እምነቱም በተለያዩ ጊዜአቶች ተነስተው ለነበሩ ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዥዎች ፍላጎት የሚመች አልሆነም። በመሆኑም በተደጋጋሚ ሊወሩትና ቅኝ ተገዥ ሊያደርጉት የሞከሩትን ድባቅ በመምታት ነፃነቱን፣ ክብሩንና ማንነቱን አስጠብቆ የዘለቀ የብቸኛ ነፃ አፍሪካዊ አገር ባለቤት ለመሆን የበቃ ነው። ይህ የፀና እምነቱና አቋሙ በቅኝ ገዥዎች ጥርስ እንዲገባ አደረገው።

ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካ አቀማመጥ፣ የቀይ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ ባለቤት መሆን፣ አገሪቱ የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት መሆን የየዘመኑን ኃያላን ትኩረት እንድትስብ አድርጓታል። ይህም የቅርብም የሩቅም ጠላቶቿ እንዳይተኙላት የስበት ኃይል ሆኖ ማገልገሉ አልቀረም። ይህም ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያን በፈለጉት መልኩ እጃቸው ለማድረግ የቀጥታ ወረራ በተደጋጋሚ እንዲያደርጉ ግፊት ሰጣቸው። ወረራው ግን ጀግኖቹ አባቶቻችን በድኆኖ፣ በእንትጮ፣ በጉራ፣ በጉነደት፣ በሣርውኃ፣ በአምባላጌ፣ መቀሌ፣ ዐድዋ፣ ማይጨው፣ እንዳባጉና፣ ተንቤን፣ ኦጋዴን ወዘተ ባስመዘገቡት የነፃነትና የማንነት ድል ኢትዮጵያ «የነፃነት ምሽግ» የተሰኘ ስም ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል።

ጀግኖች አባቶቻችን በከፈሉት የሕይዎት ዋጋ ፣ኢትዮጵያ የጥቁሩ ዓለም ሕዝብ በነፃነት፣ በጀግንነት፣ በአይበገሬነት ምሳሌ እንድትሆን አስችሏታል። የማንነትና የነፃነት ድሎቹ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የኩራትና የአይበገሬነት ስሜትን ያጎናጸፈንን ያህል፤ ድል ሆነው የተመለሱትን ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዥ ኃይሎች ደግሞ፣ እንዴት ተሸነፍን? ለምን ተሸነፍን? እኛ ሥልጡንና የዘመናዊ አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች ባለሌት ሆነን እያለ፣ እንዴት በኋላቀርና በገበሬ የክተት ሠራዊት እንሸነፋለን? የሚል ቁጭት፣ ብስጭትና የመጠቃት ስሜት እንዲቋጥሩ አድርጓቸዋል። ይህን ቁጭታቸውንና ሽንፈታቸውን ለመበቀል ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንቅልፍ አጥተው ለዘመናት አስበዋል። ሀሳቦችን አውጥተው አውርደዋል። በዚህ ጥረታቸውም ለሽንፈታችንና ለእኛ ዓላማ ፀር-ሆኖ የቆመው የትኛው ነገድ ነው? እርሱንስ ለማጥፋት ምን ማድረግ አለብን? ብለው እንዲጠይቁና መልሱንም በጥናት ማረጋገጥ አለብን ከሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ባደረጉት ሠፊ ጥናትም፣ ሌሎች የአፍሪና የእስያ አገሮችን በመናኛ ሥጦታዎችና በወንጌል ሰባኪዎች ስም እጅ ስናደርግ፣ ኢትዮጵያን ከሥጦታና ከወንጌል ስብከት አልፎ፣ በተጠናከረ ወታደራዊ ኃይል የፍላጎታችን ተገዥ ማድረግ ያልቻልነው ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ ምን ስላላት ነው?ብለው ለጠየቁት ጥያቄና ላደረጉት የመልስ ፍለጋ ፣ሦስት ጠናካራና ዘመን ጠገብ ተቋሞች ስላሏት ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። እነዚህ ተቋሞችም የሥልጣን ምንጭ እና የአንድነት ምልክት የሆነ ዘውዳዊ ሥርዓት፣ የዘውዱ ርዕዮተ-ዓለማዊ መሠረትና የሕዝቡ ሃይማኖት የሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት፣ እንዲሁም፣ በዘውዳዊ ሥርዓቱ በጥብቅ የሚያምን፣ የአንድነት አፍቃሪ፣ ጀግናና ተዋጊ፣ ማንነቱን በኢትዮጵያዊነት የሚገልጽ ዐማራ የተሰኘ ነገድ መሆናቸውን አረጋገጡ።

የኢትዮጵያዊነት ልዩ መገለጫና የቀጣይነቱ መሠረትና ምሰሶ የሆኑትን ተቋሞች አበጥረው ከለዩ በኋላ፣ ተከታዩ ጥናታቸው እነዚህን ተቋሞች እንዴት ማጥፋት ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ለጥያቄው ሁነኛ መልስ ለማግኘት ጥናታቸውን ቀጠሉ። በጥናታቸውም ኢትዮጵያ አገር እንዳልሆነች፣ የብዙ ነገዶች ስብሰብ እንደሆነች፣ እነዚህን ነገዶች ባንድ ላይ አስተሳስሮ የያዘው ዐማራው መሆኑን፣ ዐማራው ከሥልጣን ቢነሳ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደማትኖር ግንዛቤ ወሰዱ። ለዚህም ለሥልጣን የቋመጡና የየነገዳቸው አውራ ለመሆን የሚፈልጉ ቀለም ቀመስ ጥራዝ ነጠቅ ማርክሲስት-ሌኒኒስ ነን ባዮችን ከተማሪው መሐል መልምለው አሰለጠኑ፤ አደራጁ፤ አስታጥቀውም ጃዝ አሏቸው። የነዚህ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት አስፈጻሚ ሆነው ከተሰለፉት ግለሰቦችና ድርጅቶች መካከል የሚከተሉት ግንባር ቀደምቶቹ ናቸው። በግለሰብ ዋለልኝ መኮንን፣ ጥላሁን ይግዛው፣ ብርሃነ-መስቀል ረዳ፣ ተስፋዬ ደበሣይ፣ እና በተማሪዎች እንቅስቃሴ «አዞ» የሚባለው ቡድን አባሎች የሆኑት ይገኙበታል። ዋለልኝ መኮንን ቅኝ ገዥ ኃይሎች ዐማራው ተነጥሎ እንዲመታ በሮማን ፕሮቻስካ አማካኝነት እኤአ 1935 «ኢትዮጵያ፥የባሩድ በርሚል» በሚል ርዕስ ያሳተመውን የመጽሐፉ አንኳር ጭብጥ «የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ » በሚል ርዕስ የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መመሪያ እንሆን በተነ። ይህም ዛሬ በአገሪቱ ላለው የነገድ ፖለቲካና ለሕዝቡ በቋንቋ መከፋፈል ዕንቅላሉን ጥሎ ያለፈ መሆኑ ግልጽ ነው።

በድርጅት ደረጃ ፣የቅኝ ገዥዎችን ፍላጎት አስፈጻሚ ሆነው ከቆሙት ጀብሓ፣ ሻዕቢያ፣ ኢሕአፓ፣ ደርግ (ኢሠፓአኮ/ኢሠፓ)፣ ሕወሓት እና ኦነግ የሚጠቀሱ ናቸው። የሁሉም ድርጅቶች ፕሮግራሞች እነዚህን የኢትዮጵያዊነት ዋና መገለጫ የሆኑ ተቋሞችን በማጥፋት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ዛሬ አገራችን የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ አፍ አውጥቶ ይናገራል። ዘውዳዊ ሥርዓቱን በተማሪ ጫጫታ ደርግ አፈረሰው። ከዘውዳዊ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የነባራትን «ሢሶ ያንጋሽ፣ ሢሶ የቀዳሽ» መብቷን ቀምቶ፣ በመንግሥት ውስጥ ትጫዎት የነበረውን ሚናዋን ከማሳጣት አልፎ፣ ሕዝቡ ፀረ-ሃይማኖት አቋም እንዲይዝ የሚችለውን ሁሉ አደረገ። በውጭ ኃይሎች በተገዙ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች ለሚገፋው «የመሬት ላራሹ» ጥያቄና ለፍትሕና ዕኩልነትን መነሻ አድርገው ለሚቀነቀኑ የብሔረሰብ መብት ጥያቄዎች፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ተገቢ መፍትሔ መስጠት አለመቻል፣ በወሎ የተከሰተው ድርቅ ያስከተለው ዕልቂት፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ያስነሳው ሕዝባዊ ቁጣ፣ የኑሮ መወደድ በወታደሩ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ያሳደረው ቁጣ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ያስከተለው ሕዝባ አመጽ፣ ሕዝቡ የኋላውን ሳያይ፣ ምን ሊመጣ እንደሚችል በቂ ግንዛቤ ሳይኖረው ፣በሥርዓቱ ላይ ያሳደረው ግፊት ለዘውዳዊ ሥርዓቱ መውደቅና ለደርግ ሥልጣን መቆጣጠር ምቹ መንገድ የፈጠረለት እንደሆነ ይታወቃል። ደርግም የሥልጣን መቆያ፣ የኃይል መደላድል ይሆነኛል ብሎ የተከተለውን ስልት፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ለረጅም ዘመን ትከተለው ከነበረውና፣ ለኅልውናዋ መጠበቅ ዋልታና ማገር የሆኑት ተቋሞች የትኞቹ እንደሆኑ ሳይለይ፣በግብታዊነት በወሰደው እርምጃ ሁለቱን ጥንታቂ ተቋሞች ማለትም ዘውዳዊ ሥርዓቱንና የኢትዮጵያን ኦርቶዶክሶ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአንድ አዋጅ አፈረሳቸው። ይህ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን ሲጥሩ ለነበሩ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ታላቅ የምሥራች ሆነላቸው። «እስበሱ ሥጋን በኩበት ጠበሱ» የሚሉት የአባቶቻችን ቃል ሕያው ሆኖ፣ በገንዘብ፣ በወንጌል ማስፋፋት እና በታጠቀ ጦር ሠራዊት እጅ ለማድረግ ያልቻሏትን ኢትዮጵያን፣ ዕርስ በርሳችን በማናከስ ወደ ግባቸው እያመሩ ይገኛሉ።

ደርግ በመደብ ትግል እና የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም በማስፋፋት ስም ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ እንዲገደል፣ እንዲሰደድ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅምና መብቱን እንዲነጠቅ ያደረገው የዐማራውን ነገድ እንደሆነ ይታወቃል። በሌላ በኩል ደርግን እንዋጋለን፣ የየነገዳችን መሪ እንሆናለን፣ ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ብለው ጫካ የገቡ ቡድኖችም በአውራ ጠላትነት ፈርጀው የጥፋት እጃቸውን ያነሱት በዐማራው ላይ ነው። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ዘውዳዊ ሥርዓቱ፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖቱና የዐማራው ነገድ ተያያዥና ተደጋጋፊዎች ነበሩ። ይህ ተደጋጋፊነትና ተባባሪነት እንዳይኖር ለያይቶ መምታት ያስፈልጋቸው ነበርና፣ ዘውዳዊ ሥርዓቱና ሃይማኖቱ ባንድቀን አዋጅ እንዲፈርሱ ሲደረግ፣ ዐማራው ብቻውን ቀረ። የሚገርመው ዐማራው ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ልጆቹ ምን ሊመጣና ሊከተል እንደሚችል ለማሰብና ከመጭ አደጋዎች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ዘዴ አልዘየዱም። ዐማራው በዘር ተልይቶ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመበት እያዩና እየሰሙም ለምን ያሉት እግጅ ጥቂቶች ናቸው። ይህም በመሆኑ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዐማራው የመኖርና ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱን ተነፍጎ፣ በተገኘበት እየታደነ በመገደል ላይ ነው። ባለፉት 26 ዓመታት የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዐማራ ከምድር ገጽ እንዲጠፋ ተደርጓል። ይህ አልበቃ ብሎ የመዋለድ መብቱን በሕዝብ ዕድገት መቆጣጠሪያ ስም መካንና ታማሚ እያደረጉት ነው።

ከሁሉም በላይ ዐማራው በብዛት የሚኖርባቸውን ጠቅላይ ግዛቶች ሕዝብ ፣ከዐማራው ውጭ ነኝ ወይም አገው ነን፣ ኦሮሞ ነን፤ እና ቅማንት ነን የሚሉትን ፣ከዐማራው በመነጠል የየራሳቸው አስተዳደር እንዲመሠርቱ አድርገዋል። ይህ ድርጊት ለነገዶችና ጎሳዎች ዕኩልነት ታስቦ ከሆነ፣ ሥራው መጀመር የነበረበት ትግራይ ውስጥ በትግሬዎች ለተጨቆኑት ኩናማዎች፣ ሣሆዎች፣ ኢሮጶች፣ አገዎች፣ አፋሮችና ኦሮሞች መሆን ነበረበት። ወያኔ የትግራይን ግዛት እስከ ቤንሻጉል ለማስፋት ባለው የቆየ የመሥፋፋት ዓላማ፣ ሰሜን ጎንደርን የግዛቱ አካል ለማድረግ ላቀደው ዕቅድ ተፈጻሚነት እንቅፋት ከጎንደር ሕዝብ እንዳይገጥመው በማሰብ ቀድሞ ቅማንቶቹን አደራጅቶ በፀረ-ዐማራው ግንባር ተሳታፊዎች እንዲሆኑ እያደረገ ነው። በጎንደር ዐማራና በቅማንት ሕዝብ መካከል ምንም ዓይነት ቅራኔና ልዩነት እንዳልነበር ማንም ያውቀዋል። ሆኖም የፀረ-ኢትዮጵያ ፍላጎት አስፈጻሚ በሆነው የትግሬ ወያኔ ጥቅም የተገዙ ጥቂት የቅማንት ተወላጆች ጽሕፈት ቤታቸውን መቀሌ እና አዲስ አበባ ላይ አድርገው ወያኔ በሚሰጣቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ የጎንደርን ዐማራ አርዶ ጨርሶ የመሬቱ ባለቤት ለመሆን እየጣሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። ይህ በቅማንትና በዐማራ ሕዝቦች መካከል ሆን ተብሎ የተፈጠረ ችግር የሚጠቅም ከሆነ የሚጠቅመው ወያኔንና ግብረ አበሮቹን እንጂ፣ የቅማንትን ሕዝብ ሊሆን ከቶ አይችልም። በመሆኑም በዚህ በወያኔ ጀሌነት ሁለቱን ነገዶች ዓይንና ናጫ ለማድረግ የተሰለፋችሁ የቅማንት ወንድም እህቶቻችን ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡና ወደ ጥንት ጧቱ የአንድነት ስሜት እንድትገቡ ጥሪያችን እናቀርብላችኋለን። ይህን ጥሪአችን በማይቀበሉና ወያኔ የጫናቸውን ተሸክመው የሚጓዙ ጌኛዎችን የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ትምህርት ሰጭና ማስጠንቀቂያ የሆነ ርምጃ ሊወስድ የሚገደድ መሆኑን ከወዲሁ ለማሳወቅ እንወዳለን።

የግፍ ዓይነት ተቀባይና ዘርህ እንዲጠፋ የተፈረደብህ የዐማራ ወጣት ነገ ሳትል ፣ዛሬ የሕዝባዊ እንቢተኝነቱን እንቅስቃሴ እንድትቀላቀል ጥሪያችን እናቀርብልሃለን። የወያኔ ጀሌ ሆኖ በወገኖቹ ላይ ጥፋት የፈጸመ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የትም ለማምለጥ እንደማይችል አውቆ፣ ከዐማራ ወገኑ ጎኑ እንዲቆም እንመክራለን። በብአዴን ውስጥ ያላችሁ የዐማራ ልጆች «ከዘላለም ባርነት፣ የአንድን ቀን ነፃነት» በመምረጥ ከወገናችሁ ጎን እንድትቆሙ ራሳችሁ ለራሳችሁ ቃል እንድትገቡ እናሳስባለን። «ሊነጋ ሲል ይጨልማል» እና፣ በዐማራው ላይ ጨልሞ የነበረው የወያኔ የ26 ዓመታት ጥቁር ጨለማ በዐማራው ልጆች ተጋድሎ ብርሃን ማሳየት ጀምሯል። ይህ በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥይት አብሪነት፣ በጎቤ መልኬ መስዋዕትነት የተጀመረው የዐማራ ተጋድሎ እንቅስቃሴ ወያኔን ወደ መቃብሩ ሳይከት አይጠፋም። ብርሃኑ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚዳረስና የዘላለም እንዲሆን፣ኢትዮጵያውያን በዐማራው ትግል ዙሪያ የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችን እናቀርባለን። ድል የመስዋዕትነት ፍሬ ነውና፣ ለድሉ በምንችለው መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ እንሁን!

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!