አጽማቸው የፈለሰው መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ማናቸው?

Print Friendly, PDF & Email

ቀሲስ አስተርአየ

(nigatuasteraye@gmail.com) ነሐሴ ሁለት ሽ ዘጠኝ ዓ.ም

የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውን እንመሰክራለን(ዮሐ 3፡11)

መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ

መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ

የመላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ስም ከሸበል በረንታ እስከ ብቸና ቅዱስ ጊርጊስ ደብር ባሉት መንደሮች የሚነሳው ከእነ በላይ ዘለቀና ሌሎችም አርበኞች ሥሞች ጋር ተሳስሮ ነው። ስለ መላከ ብርሃን የአምስቱ ዘመን የአርበኝነት ተጋድሎና ቤተክርስቲያናችንን ተወራሪዎችና ተመጤ ሃይማኖቶች ለመጠበቅ ዛሬ በህይወት ሳይኖሩ እንኳን የሚያደርጉትን የሰማእትነት ተጋድሎ ጨልፌ ተማቅረቤ በፊት ሥለ እኒህ ታላቅ ሊቅ ምንነት በትንሹ እንድናገር ፍቀዱልኝ።

በተለያዩ መጻሕፍት እንደተገለጠው መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ በጎጃም ክፍለ ሀገር በብቸና አውራጃ በዲማ ጊዮርጊስ ተወለዱ። ተወልደው ባደጉበት በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስና በሌሎችም በዘመናቸው አሉ ከሚባሉት የሊቃውንት ትምህርት ቤቶች ትምርታቸውን አጠናቀው ማስተማር ከጀመሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጡ። በወቅቱ በአዲስ አበባ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል ተመርጠው ለአጼ ምኒልክ መታሰቢያ በተመሰረተው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መጋቤ ምስጢር ተብለው እያገለገሉና በህዝባውያን ጉዳዮችም እየተሳተፉ ባዲስ አበባ ቆዩ። በዚህ ቆይታቸው ባሳዩት የሙያ ብቃታቸው ለጠቅላላው ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ጉባዔ አባል ሆነው ባባረከቱት እውቀታቸውና ችሎታቸው የብዙውን ሊቃውንት ቀልብ ሳቡ።

በዚያን ዘመን በጎጃም ክፍለ ሀገር በብቸና አውራጃ ለሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሊቀጠበብት የሚሰየመው ከመላ ሊቃውንቱ እየተመረጠ ስለነበር የሊቃውንት መፍለቂያ ለነበረው ለዚህ ደብር ሊቀጠበብት ተብለው ጣልያን ከመውረሩ በፊት በ 1927 ዓ.ም ተሰየሙ። ሊቀጠበብትነትም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሆነው እስከ ተሰየሙበት 1949 ዓመተ ምህረት ድረስ ለ 22 ዓመታት መታሰቢያ ሐውልት እንድንሰራላቸው የሚያስገድደን በዚህ ታላቅ ደብር ብዙ ሥራዎች ሰርተዋል።

በአምስቱ ዘመን ተጋድሏቸውም የእነ በላይ ዘለቀና ሌሎችም ያካባቢው ጀግና አርበኞች ስሞች በሚወሱበት ሁሉ የሳቸው ስም አይታለፍም። ተወልደው ካደጉበት ከዲማ ይልቅ በሰፊው የሚታወቁት ዓባይ አፋፍ ላይ ከሚገኘው ከጎይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ሸበል በረንታ ለምጨንና ሌሎች ጀግኖች በተዋደቁበት አካባቢ ነው።

አርበኛውና መምህሩ መላከ ብርሃን በእውቀታቸው ተወዳዳሪ አልነበራቸውም። በብሩህነታቸውና ሊቅነታቸው የሚያደንቋቸው ሊቃውንት የመላከ ብርሀን አድማሱ እውቀት፣ ችሎታና ማስተዋል “ወህሊናሁ ለጠቢብ ብዙህ ከመ ማየ ክረምት። ወምክሩኒ ይነቅእ ከመ ማየ ህይወት” ሲራ 21፡13)የሚለውን ይጠቅሱና “እውቀቱ እንደ ዓባይ ወንዝ ፈስሶ እማያልቅ ነው፤ ምክሩና ትምህርቱ የደረቀውን ስርዶ ነፍስ ዘርቶ እንደሚያንቀሳቅስ ደመና ነው” እያሉ ያደንቋቸው ነበር። በተመሳሳይ መንገድ “ማይ ዕሙቅ ውስተ ልበ ጠቢብ። ስፍሀ አእምሮው ጥልቅ ምጡቅ ረቂቅ ነው። “ወብእሲ ጠቢብ ይዘልሆ” (ምሳ 20፡5) የሚለውን ይጠቅሱና “ተቀድቶ የማያልቅ የመላከ ብርሃን አድማሱ እውቀትና ጥበብ የሚኖረው ሰው፤ መላከ ብርሃን አድማሱ በተፈጠሩበት ሌሊት የተፈጠረ ሰው ብቻ ነው እያሉ አቻ የሌላቸው ሊቅ መሆናቸውን ይገልጡ ነበር።

እውቀት አፍቃሪውና እውቀትም የወደደቻቸው መላከ ብርሃን ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ካብነት መምህራን በተለይም በሰምና ወርቅ ቅኔያቸው ከሚደነቁት ከመሪጌታ ውብሸት ጋር ነበር። እውቀትን ለማስፋፋት በሳምንት አንድ ቀን ከሊቃውንቱ ጋራ የሚወያዩበት በራሳቸው በሊቀ ጠበብትነት ስልጣናቸው የሚመራ ጉባዔ ነበራቸው።

ከተራ ካህናት ጋራ የሚገናኙት እሳቸው መገኘት የሚያስፈልጉባቸው ጉዳዮች ሲገጥማቸው ብቻ ነበር። በሊቀጠበብትነት ባገለገሉበት ዘመን የተሰጣቸውን ሀላፊነት፣ ጥልቅ እውቀታቸውንና ጥበባቸውን ተጠቅመው የደብሩን መምህራንንና ካህናቱን በእውቀት፣ በእምነት፣ በመንፈስና በሥነ-ምግብር ቀርጸው የነበረውን መዋቅር አሻሽለው በጥኑ መሰረት ገንብተውት ነበር።

መላከ ብርሃን ከምሳሌ 14፡6 “ፌዘኛ ጥበብን ይሻል ግን አያገኛትም። አስተዋይዎች በቀላሉ ያገኟታል” ሚለውን የሰሎሞንን ምክር እየጠቀሱ “ቀልደኛና ፌዘኛ የራሱን ጭንቅላት አሟልጎ ሌላውን ሞላጋ ያደርጋል። የሞላጋ ጭንቅላትም መያዝ መቋጠር የማይችል ከረጢት ይሆናል። ስለዚህ ደብራችን ከቀልደኛ ቄስና ሞላጋ ደብተራ መላቀቅ አለበት” ይሉ ነበር።

የሞላጋ ባህርይ በሚታይበት ሰው ላይ ዮታ እንዳለበት ነብዩ ኢሳያስ ኢስ 5፡19 እየጠቀሱ፤ ቀልድ ሰውን ለማሳቅ እውነትንና ውሽትን የተደረገውንና ያልተደረገውን እያዝጎረጎረ የሚያቀርብ አፍዛዥ፤ አደናዛዥና አቅነዝናዥ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። በዚህም ምክንያት ክህነት ከፌዝና ከቀልድ ተላቆ የቁም ነገር መፍለቂያ ሆኖ ለሁለነተናዊ የሕዝብ አገልግሎት መቆም እንዳለበት ያስተምሩ ነበር።

ቅዱስ ጴጥሮስ በ(2 ጴ 3፡3)”በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላልሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ” ሲል የተናገረውን መሰረት በማድረግም ክህነት ዘበት ከሆነ ህዝብ መዘባበቻ ቤተ ክርስቲያንም የዘበት ምንጭ ትሆናለች ብለው ያስተምሩና ካህን ለህዝብ ሁለንተናዊ አገልግሎት ለመቆም በቅድሚያ የራሱን ሥጋዊ ጥቅም መካድ አለበት። የራሱን ሥጋ ወይም ጥቅም ክዶ ለእግዚአብሔርና ለህዝብ ሁለንተናዊ አገልግሎት የማይቆም ክህነት ዘበት ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን የዘበት ምንጭ ስትሆን ህዝብም ተዘባባች ይሆናል።

ቤተክርስቲያን የዘበት ምንጪ ሕዝብም ተዘባባች ሲሆኑ አገር የቀልደኞች፣ የፌዘኞችና የዋዘኞ ከተማ ትሆንና ትፈርሳለች ይሉ ነበር።

መላከ ብርሃን በቅኔአቸውም ካህናትንና ሕዝብን ፍልስፍና ያስተምሩ ነበር። የመላክ ብርሃን አድማሱ ቅኔዎች በቅዱሳት መጻህፍት ላይ የተመሰረቱ ፈጣሪንና ተፈጥሮን እየመረመሩ በዘመናቸው ባካባቢያቸው ያለውን ሂደት የሚቃኙ ናቸው። የመላከ ብርሃን ቅኔዎች የሊቃውንቱን ጭንቅላት ከተደበተበት የሚቀሰቅሱ፤ ሊቃውንቱንና በስራቸው ያሉት ካህናት እንደዚሁም ህዝቡን በእምነት፣ በመንፈስ፣ በሥነ- ምግባር እንዲበረታ የሚኮተኩቱና የሚያበረታቱ ቅኔዎች ናቸው።

በዚህ እውቀታቸው፣ ጥበባቸውና ብርታታተቸው ደብሩንና በደብሩ ዙሪያ ያሉ ቅፈፎችንና ጎጦች ያሉትን ካህናት በመምራትና ሕዝቡን በማስተማር ላይ ሳሉ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ለመውረር በዝግጅት መሆኑ ብቸና ላይ ተሰማ። ተሰምቶም አልቀረ አገራችንን በእብሪት ወረረ፡

መሰሎኒ አገራችንን ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ መላከ ብርሃን አድማሱና ሌሎች የበቁ ካህናት እንደ በላይ ዘለቀ ላሉ ተናዳፊ አርበኛ ተዋጊዎች ምሰሶ፣ ወጋግራ፣ ግድግዳና ማገር በመሆን ያበረከቱትን የአርበኝነት ተጋድሎ በሚቀጠለው ክፍል ጨልፌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ይቆየን።