በጅማ ዞን ጦላይ አካባቢ የዐማራ ተወላጆች ቤት ለ4ኛ ቀን እየተቃጠለ ነው፤ የበርካታ ሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል

Print Friendly, PDF & Email

በጦላይ የዐማራ ተወላጆች ቤት ለአራተኛ ቀን እየተቃጠለ ነው፤ የበርካታ ሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል

ብራና ሬዲዮ፤ በጂማ ዞን ጦላይ አካባቢ ከአርብ ዕለት ጀምሮ የዐማራ ተወላጆች ቤት በጅምላ እየተቃጠለ እንደሆነ ተጎጂዎች ገለጹ። በግጭቱ በርካታ ንብረትና የሰው ሕይወትም እንደጠፋ ተገልጧል።

ንብረትነቱ የዐማራ ተወላጅ የሆነ መሬት ላይ ይገባኛል ያነሳ ግለሰብ በፍርድ ቤት ክርክር ከቆዩ በኋላ ለዐማራው ተወላጅ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የሚገልጹት ምንጮች ይህን ተከትሎ የአካባቢው ባለሥልጣናት የኦሮሞ ተወላጆችን በማነሳሳት ከነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የዐማራ ተወላጆች ቤት በጅምላ እየተቃጠለና ሰዎችም በገጀራና በጥይት እየተገደሉ እንደሆነ ተጎጂዎች ገልጸዋል።

ችግሩ እንደተፈጠረ የደረሱት የክልሉ ፖሊሶች ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በርካታ ሰዎችን በጥይት ገድለዋል። የጦላይ ጦር ማሰልጠኛ ተቋም እዚያው ቢሆንም የዐማሮችን ሕይወት መታደግ አልቻለም የሚሉት ተጎጂዎች አብረን የኖርነውን በባለሥልጣናት ግፊት ደም መቃባታችን አሳዛኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ከ2000 በላይ የሚሆኑ ቤትና ንብረታቸው የወደመባቸው የዐማራ ተወላጆች በጦላይ ጦር ካምፕ ሕይታቸውን ለማትረፍ ቢገቡም እስካሁን ባለው ሒደት ከ10 የማያነሱ ሰዎች በገጀራና በጥይት ተጨፍጭፈው የተገደሉ ሲሆን ቁጥራቸው የማይታወቅ ደግሞ አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የዐማራ ተወላጆችን ቤት አንድ በአንድ እየተለቀመ እየተቃጠለ ሲሆን ይህ ዜና እስከተሰራበት ጊዜ ድረስ ያስቆመው አካል የለም።