“የአንድ ፓርቲ ስብሰባ ወይስ የሽማግሌ መድረክ?”

Print Friendly, PDF & Email

መ/አለቃ ማስረሻ ሰጤ (ከቅሊንጦ ወኅኒ ቤት)

የኢሕአዴግ የፌዴራሊዝም ስርዓት እና አወቃቀር ራሱን የቻለ የግጭት መንስዔ መሆኑ ላለፉት 26 ዓመታት አይተናል። ለዚያም ነው በየክልሉ የሚነሱ የድንበር ግጭቶች መፍትሔ ያጡት። የአማራና የትግራይም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው። የአማራ እና የትግራይ ክልል ድንበር የት ነው?

በደርግም ይሁን ከዚያ በፊት በነበሩት አገዛዞች ድንበራችን ተከዜ ወንዝ መሆኑ ይታወቃል። ወልቃይትም በአማራ ክልል (ግዛት) ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው። ነገር ግን ሕዝባችን በማያውቅበት ሁኔታ በጉልበት ወልቃይትን ለመውሰድ ሞክሯል፤ ወስደውታልም። አሁንም በጉልበት መውሰዳቸውን ሊያበስሩን በሽምግልና ሥም አያገባችሁም፤ የሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ነው እያሉን ይገኛሉ። ይህ ሕልም እንጂ የአማራ ሕዝብ ሙቶ ሳያልቅ እውን ሊሆን አይችልም። ሠላምም አይታሰብም። ወልቃይት መሬቱ የኛ ነው። ይህ ማለት በወልቃይት የሠፈሩ የትግርኛ ተናጋሪዎች ይፈናቀሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን መሬታችንንና በወልቃይት የሚኖሩ ሕዝባችንን መልሳችሁ አብረው የሚኖሩ የትግርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ ማንነታቸው ተከብሮ በቋንቋቸው እየተማሩ እና እየተዳኙ መቀመጥ አለባቸው ነው ያልነው። አሁን ሕወሓት እያደረገ ያለው የጭፍንነት ተግባር እንደራሳቸው “ጠበው ሊያጠቡን” እየሞከሩ ነው። የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት ስሜት አለው ሲባል ማንነቱ ተገፎ አንገቱን ደፍቶ በቅኝ ግዛት ይኖራል ማለት አይደለም።

በሽማግሌዎች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ የተወሰነ ልበል፡- በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሽማግሌዎች በፍፁም ከአማራ ሕዝብ የተወከሉ አይደሉም። የአማራን ሕዝብ ጥያቄም ሊያነሱ እና የሕዝቡን ጥቅም ሊያስከብሩ አይችሉም። ሌላው በስብሰባው የተገኙ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዳችን ማየት ምን ያህል አሁንም በማስፈራራት /deterrence/ በመፍጠር ሕዝቡ አንገቱን እንዲደፋ እና በድርጅቶች መካከል የበላይነትን የማሳየት ዓላማ ያለው ነው። ከዚህ ላይ የኔ ጥያቄ የስብሰባው ዓላማ ምንድን ነበር? አጥፍተናል ይቅርታ እንድንል የተፈለገ ይመስለኛል።

በስብሰባው ላይ የተገኙ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ስብሓት ነጋ፣ አባይ ፀሐየ፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ አባይ ወልዱ እና ቴዎድሮስ ሐጎስ… ሌሎችም ሲሆኑ ከብአዴን የቀረቡ ደግሞ አቶ ካሳ ተክለብርሃን እና ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው። አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ማንነታቸውን በግልጽ አላውቅም። ከዚህ በተጨማሪ በስብሰባው ላይ የበላይ ሁኖ መታየትን ስለተፈለገ በሕወሓት በኩል የመከላከያ ሠራዊቱም ነበሩበት። ሌላው በተጋባዥ እንግድነት የተገኙት ደግሞ በሕወሓት በኩል የድሮ ታጋዮችና እሳት የላሱ ካድሬዎች ሲሆኑ ከአማራ (ብአዴን) በኩል የብአዴን አባሎች በተጨማሪም ምንም ዓይነት የፖለቲካ አካሔድ አይደለም። ከሠፈራቸው ውጪ ያለ ስለአማራ ሕዝብ ያለበት ሁኔታ እንኳን ማየት የማይችሉ ጥቂት ምስኪን አርሶ አደሮችን በመያዝ ነው። ሠላም በእንደዚህ ዓይነት ድብብቆሽ መጥቶ አያውቅም። በስብሰባው ላይ የአማራን ወይም የትግራይን ሕዝብ current ሁኔታ ተረድቶ ትክክለኛ አስተያየት የሰጡ ሰዎች ተገኝተዋል ለማለት አልችልም። በዚህ አጋጣሚ ግን ባልተጠበቀ መልኩ ከዚህ ሁሉ ተሰብሳቢ ውስጥ አንድ የትግራይ እናት አግኝቻለሁ። የትግራይ ሕዝብን ሕመም አውጥተው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ለሥልጣን ማራዘሚያ የተጠቀማችሁበት የብሔርተኝነት አካሔድ አሁን ለገባንበት ከፍተኛ ችግር ዳርጎናል። ይህ የአማራ ሕዝብ ችግር አይደለም። የፀረ አብዮተኞችም ችግር አይደለም። የስርዓቱ ችግር ነው። ተዉን እንኑርበት ብለዋል። ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸውም ሳግ ሲተናነቃቸውና በጀመሩበት የአማርኛ ቋንቋ መግለጽ ተቸግረው በትግርኛ ቋንቋ መግለጽ ተቸግረው በአማርኛ ቋንቋ የየዋሁ የትግራይን ሕዝብ ድምፅ ሲያሰሙ ሰምቻለሁ። በእውነት ክብር አለኝ – ለእኚህ እናት። ምክንያቱም የምወደውን የትግራይ ሕዝብ ግልጸኝነት እና ድፍረት በእኚህ እናት ስላገኘሁ። የወቅቱም የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ እንኑርበት የሚል ነው። በዚህ ስርዓት በትግሬነታቸው ያገኙት ጥቅም ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ዘንድ መገፋትን እና መጠላትን ነው። በባለፈው ዓመት የታየው ምልክትም ለሕዝቡ ትልቅ ትርጉም አለው።

ሌላው ምሁራንም ሆነ የሕወሓት ታጋዮች በአማራ ሕዝብ ላይ ስድብ እና ምንም አታመጡም የሚል እብሪትን አንፀባርቀዋል። ለዚህም ቢሆን ክብር አለን። ነገር ግን ባነሱት ሐሳብ ላይ እንኳን ሠላም የሚያመጣ መሐል ላይ በሐሳብ የነበረውን የአማርኛ ተናጋሪ እንደራሳቸው ሊያጠቡ የተሰጡ አስተያየቶች ናቸው እና ለማንም የማይጠቅም መሆኑን ማሳወቅ እፈልጋለሁ። ያኔ በርሃ እያሉ ለሕወሓት አባሎች ወይም ወታደሮቻቸው የሚሰጡ የፖለቲካ ትምህርት የአማራው መደብ ነው የጨቆነን እና እየጨቆነንም ያለው፣ ስለዚህ አማራን መግደል ላሰብነው ዓላማ መሳካት ትልቅ እርምጃ ነው የሚል እንደነበር የማይክዱት ሐቅ ነው። ታዲያ ዛሬም ይህ አስተሳሰብ አለመሞቱን እንዲያውም ወደፊት በስትራቴጂ ደረጃ የተያዘ ዕቅድ እንዳለ በአስተያየት ሰጪዎቹ የሕወሓት አባላትና አመራሮች ለመረዳት ችለናል።

“ድሮ ያሸነፍናቸው ጠላቶቻችን ናቸው ዛሬ ነፍስ ዘርተው የመጡብን፣ አሁንም እናሸንፋቸዋለን። ተሸንፈውም ይኖራሉ” ሲሉ የአማራ ሕዝብን ሲሳደቡ ሰምተናል። መድረኩ የሽማግሌ መድረክ ወይስ የአንድ ፓርቲ የስብሰባ መድረክ ነው? ይሄ ሁሉ ወጣት ሞቶብን እንኳን ጥላቻቸውን ለምን አያነሱልንም? በአስተያየታቸውም የአማራን ሕዝብ በተለይም ጎንደርን ነጥሎ ለመምታት የተያዘ አጀንዳ እንዳለ ለመረዳት ችለናል። በዚህ ስብሰባ ላይ ሌላው በትግራይ ሕዝብ እና በምሁራን መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት አይተናል።

አንዲት ፕሮፌሰር አጠቃላይ የንግግራቸው ይዘት “እንሥራበት” የሚል ነው። የትግራይ ሕዝብም ሆነ የአማራ ሕዝብ ስለመኖር ይጨነቃል። ምሁራን ስለመሥራት። ይህ የሕዝቡን ትክክለኛ ስሜት አለመረዳት የሚያሳይ ነው። የሕዝቡንም ሕመም sense አለማድረግ ነው። በስብሰባው ላይ የስርዓቱን አምባገነንነትና የአማራን ሕዝብ በንቀት በማየት በአብዛኛው በአብዛኛው ተሳታፊ የቀረበውና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በአቶ አባይ ወልዱ የቀረበው አስተያየት እና የአርፋችሁ ተቀመጡ መልዕክት ነው። ይኸውም የወልቃይት ጉዳይ ብአዴንም፣ የአማራ ክልል ሕዝብም አይመለከታችሁም የሚል ነው። እንደነዋሪም የሚመለከተው የወልቃይት ነዋሪ እንጂ ጎንደር የሚኖርና የአማራ ሕዝብ ምናገባው ተብሏል። ይህ አባባል በ2008 ዓ.ም. ወ/ሮ አዜብ መስፍን የቡራዩ መሬት ለቡራዩ ነዋሪዎች እንጂ ለወለጋ እና ለሐረር ኦሮሞዎች ምን አገባቸው ካሉት የእብሪት ንግግር ጋር ተመሳሳይ ነው።

ተከዜ ወንዝ ዳር የሚጮኸው የአንድ የአማራ ድምፅ፣ ወልቃይት ላይ የሚጮኸው የአንድ አማራ ጩኸት ለኔ ካልተሰማኝ አማራነቴ ምኑ ላይ ነው? ወለጋ፣ አርሲ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሐረሪ፣ ደቡብ፣ ድሬድዋና አዲስአበባ ላይ የሚጮኸው የኢትዮጵያዊ ድምፅ ለኔ ካልተሰማኝ ኢትዮጵያዊነቴ ምኑ ላይ ነው? ሕወሓት ወይም ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ይህንን የግትርነት አቋሙን ቀይሮ ለሕዝቡ መልስ ሊሰጠው ይገባል።

በወ/ሮ አዜብ ንግግር ስንት የኦሮሞ ወንድሞቻችን እንዳለቁ አይተናል። በሕወሓትም ንግግር በ2008 ብቻ በጣም ብዙ የአማራ ወገኖች በጅምላ ሲገደሉና ሲታሰሩ አይተናል። ሊበቃችሁ ይገባል። ወልቃይት ላይ ክልላዊ ሕመም የታመመ አማራን ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎና ሰሜን ሸዋ ላይ የሚኖርን አማራ እንደሚያመው ማወቅ ይገባችኋል። የወልቃይት ጉዳይ የአማራ ሕዝብ ጉዳይ እንጂ የሕወሓትም ሆነ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ አይደለም፤ አይመለከታቸውም።

እኛ እንደብአዴን የሰጡን እና የሚሉንን አሜን ብለን መቀበል አንችልም። ለትግራይ ሕዝብም ቢሆን ወንድማማችነታችንን የምንገልጽባቸው “የሚመለከታቸውን የእናንተ፣ የማይመለከታቸውን ደግሞ አይ የናንተ አይደለም” ለማለት እንጂ ግዚያዊ ፈገግታ ለማሳየት አይደለም። ምክንያቱም ወዳጅነታችን የድሮ፣ የአምናና የሚቀጥል ቋሚ መሆኑን ነው የምናውቀው እንጂ እንደስርዓቱ ግዚያዊ እና የሚለዋወጥ አይደለም። የትግራይ ሕዝብም ቢሆን እንደአማራ ሕዝብ ገፍቶ ስርዓቱን ተጠያቂ የማድረግ ድፍረት አይኑረው እንጂ የአማራው ሕዝብ ንብረት ለኛ ይገባናል ሊሉ እንደማይችሉ እገነዘባለሁ። አጠቃላይ በ2008 ዓ.ም. ከጎንደርና አካባቢዎቹ ብዙ የትግርኛ ተናጋሪዎች ተፈናቅለዋል። ነገር ግን ጥያቄው ያኔም አሁንም የሕወሓትን መንግሥት እንዲወርድ እንጂ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻ ኑሮት አይደለም። ራሳቸው የሕወሓት አመራሮችና አባላት በቀሰቀሱት ጎንደርን ለቆ የመውጣት እና የትግራይ ሕዝብን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሲሉ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው።

ሕወሓትም ይህንን ክፍተት ይፈልገው ስለነበር፣ ወደጫፍ ወይም ፅንፍ ወስዶ በብሔሩ ላይ የተቃጣ አደጋ አስመስሎታል። አሁንም ልለው የምፈልገው ሕወሓት በመጨረሻ ሊጠቀመው የፈለገው የፖለቲካ ካርድ ነው እንጂ አንድም ከስርዓቱ ጋር ንክኪ የሌለውን ሠርቶ በላ የትግርኛ ተናጋሪ የአማራ ሕዝብ ቀና ብሎ አላየውም። ወደፊትም አያደርገውም። ነገር ግን በስርዓቱ ላይ እና በስርዓቱ ደጋፊዎች ላይ የሚቀጥል ይሆናል።

ጎንደርና ባሕርዳር ላይ ኮንዶሚኒየም ፎቅ ላይ ሆነው ሠላማዊ ሰልፍ የወጡትን ወንድሞቻችንን ተኩሰው ሲገድሉ የነበረው የሕወሓት አባላት መኖራቸው የሚታወቅ፣ ታሪክም የማይረሳው ጠባሳ ነው። ሌላው እኛ የድንበር ጉዳይን አልፈን ሰው ሞተብን እያልን ባለንበት ሰዐት በሕወሓት የንብረት ኪሳራ ገጠመን መባሉ ሁለት የማይነፃፀሩ ጉዳዮችን ማነፃፀረቸው አልበቃቸው ብሎ ይቅርታ እንድንጠይቅ ይሄ ስብሰባ መዘጋጀቱ የሚያስገርም ነገር ነው። አዳራሹን በሞሉት የሕወሓት አመራሮች ባሉበት ስብሰባ ውስጥ አቶ ገዱ ብቻቸውን ተገኝተው ለአድርባዮችም ጭምር ቆመው ውርጅብኝ ሲያስተናግዱ አይተናል። (በቲቪ) ይቅርታ እንዲሉም ቢጎተጎቱም ቃሉን ሳያወጡ መመለሳቸውን አድንቄያለሁ። እነ አቶ አለምነው መኮንን አማራን ተሳድበው በሕወሓት ታማኝ አገልጋይ ተብለው ሲሞገሱ ስላየን ብአዴን እንደድርጅት ሕወሓትን ለማስደሰት ተግቶ የሚሠራ በመሆኑ ከአቶ ገዱ ያልተጠበቀ መልስ ሲሰጡ ሰምተናል። ጥሩ ጅምር ነው። መደገፍ እና መበረታታት ይኖርበታል።

የሞትን እኛ፣ የታሰርን እኛ፣ እርዳታው ደግሞ ወደትግራይ ሲሔድ ኢትዮጵያዊነታችን ላይ አላነሳንም። አሁንም በግልጽም ይሁን በድብቅ የሚደረገው ድጋፍ ለሕወሓት ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብ… ቢሰጥ ደስ ይለኛል። በአጠቃላይ አሁን የትግራይ ሕዝብ ትግል የሌሎችንም ብሔር ብሔረሰቦች ትግል ደግፎ ስርዓቱ ይውረድልን ወደሚለው አጀንዳ ተሸጋግሯል። ስርዓቱ በለመደውና በታጠቀው መሣሪያ መጨፍጨፉን ይቀጥላል እንጂ ትግላችንን እንቀጥላለን። በመሆኑም የአማራ ሕዝብም ይሁን ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች የሕወሓት ወይም ኢሕአዴግ ግፍና ጭቆና በማየት በመተባበርና የአንዱን ሕመም ሌላው በመረዳት ለትግል እንዲነሳና በመካከላችን የተቀበረውን የልዩነት ፈንጅ አውጥተን እንድንጥል ስል ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ
ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት