የዶክተር በያን አሶባ ነገር (ክፍል ፩)

Print Friendly, PDF & Email

(አቻምየለህ ታምሩ)

ዶክተር በያን አሶባ

ዶክተር በያን አሶባ ከሰሞኑ አውስትራሊያ በሚገኘው SBS Amharicሬዲዮ ላይ ቀርቦ ከዶክተር አብርሃም ዓለሙና ከአቶ ገለታው ዘለቀ ጋር ያደረጉትን «ውይይት» አዳመጥሁት። ዶክተር በያን አሶባ በፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሚመራው አርበኞች ግንቦት ሰባት አባል የሆነበት «የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ» አባል የሆነው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ከፍተኛ አመራር አባል መሆናቸውን ስለማውቅ በጋራ ውይይቱ ወቅት ያነሱትን የድርጅታቸው አቋም ምንነት ገለጥ አድርጌ አስተያየት እንድሰጥ ጋብዞኛል።

የዶክተር በያንን ንግግር ላዳመጠ አስመራ ባለው በዳዎድ ኢብሳ በሚመራው ኦነግና ሚኒሶታ ባለው የኖርወዩ ዮሐንስ ለታ [ማተቡን ከበጠሰ በኋላ ሌንጮ ለታ ሆኗል] በሚመራው ኦዴግ መካከል ስላለው ልዩነት ወደ ስልጣን ለመውጣት ከመረጡት መንገድ በስተቀር በመርህ ደረጃ ሲዳክር ቢውል ልዩነት አያገኝም። ዶክተር በያን በውይይታቸው ኦነግ እነ ዶክተር በያን አሶባን ገፍትሮ አባረራቸው እንጂ ኦነግ ከውስጣቸው እንዳልወጣ በአንደበታቸው አረጋግጠውልናል።

ዶክተር በያን አሶባ ውይታቸውን ሲጀምሩ አዲስ አበባ እሳቸው «ኦሮምያ» ለሚሉት ክልል መገበር ወይንም ግብር መክፈል አለበት ይላሉ። ይህ ማለት ዶክተር በያን አሶባና ድርጅታቸው ኦዴግ እያሉን ያለው አዲስ አበባ «ኦሮምያ» ለሚባለው ክልል ኪራይ መክፈል አለበት ማለት ነው። እነዶክተር በያን አዲስ አበባ ኦሮምያ ለሚባለው ክልል ግብር መክፈል አለበት ማለታቸው አዲስ አበባ ኦሮምያ ለሚባለው ኪራይ መክፈል አለበት ማለታቸው መሆኑን ለመገንዘብ ግብር ማለት ምን ማለት መሆኑን ማወቅ ብቻ በቂ ነው።

ግብር የመዝገበ ቃላት ፍቺው ሲታይ መንግስት በሕግና ደንብ ላይ ተመስርቶ ከሕዝብና ከድርጅቶች ገንዘብ የሚያገኝበት መሳሪያ ነው። ዜጎች በመነገድ፣ ቤትና ንብረት በማከራየት፣እውቀታቸውን በመሸጥ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በሕግ በተቀመጠው መሰረት ግብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ ግብር ሕብረተሰቡ ወይም ግብር ከፋዮች ለመንግሥት በግዴታ ክፍያ የሚፈጽሙበት መንገድ/ሥርዓት ነው። ዜጎች በግብር መልኩ የሚከፍሉት ገንዘብ መንግሥት በለውጡ ወይም በምትኩ በቀጥታ ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም ልዩነት ሳይፈጥር ለራሳቸው ለሚያቀርበው አገልግሎትና መሰረተ ልማቶች ግንባታ እንዲውል ነው።

ባጭሩ ዜጎች ግብር የሚከፍሉት መንግሥት ለከፋዩ አገልግሎቶችው እንዲያቀርብ ወይንም በአካባቢያቸው ለሚያካሂደው የግብር ልማት፣ለማህበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት፣ ለባህል እድገት፣ለጸጥታና ደህንነት፣ ለፍትህና መልካም አስተዳደር መስፈን፣ ለአከባቢ ጥበቃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣የሀይል አቅርቦቶችን ለመስፋፋት፣የግብር ከፋዩን ሕብረተሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት፣ በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ እና የመሳሰሉ ገበያ ሊያቀርባቸው የማይችሉ ስራዎችን መንግሥት ለማከናወን እንዲችል ነው።

እንግዲህ! የአዲስ አበባ ሕዝብ ግብር የሚከፍለው አገዛዙ ለአዲስ አበባ ኗሪ ለሚያካሂደው የግብር ልማት፣ለማህበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት፣ ለባህል እድገት፣ለጸጥታና ደህንነት፣ ለፍትህና መልካም አስተዳደር መስፈን፣ ለአከባቢ ጥበቃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣የሀይል አቅርቦቶችን ለመስፋፋት፣የግብር ከፋዩን ሕብረተሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት፣በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ እና የመሳሰሉ ገበያ ሊያቀርባቸው የማይችሉ ስራዎችን ለማከናወን እንዲችል ነው። በሌላ አነጋገር ግብር የሚከፈለው ለከፋዩ የሕብረተሰብ ክፍል መገልገያ ነው።

የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚከፍለው ግብር ከአዲስ አበባ አስተዳደር ውጭ ለሆነ ሕዝብ እንዲገበር ከተደረገ ይህ ግብር አይደለም። ከአዲስ አበባ ሕዝብ የሚሰበሰብ ግብር ከራሱ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ውጭ ላለ ሌላ ሕዝብ ገቢ እንዲደረግ ከሆነ ይህ አንድም በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የተጣለ መቀጮ ነው አሊያም ኪራይ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው ዶክተር በያን አሶባ የአዲስ አበባ ሕዝብ ኦሮምያ ለሚሉት ክልል ግብር ይክፈል የሚሉት ክፍያ ኪራይ ወይንም መቀጫ እንጂ ግብር የማይሆነው። ይህ ደግሞ አንድም የባርነት አስተዳደር ነው አሊያም አፓርታይድ ነው። ይህ ማለት ዶክተር በያን አሶባና ድርጅታቸው «እየታገሉ» ያሉት «የብሔራችን አካል አይደለም» በሚሉት ሕዝብ ላይ የባርያ አስተዳደር ሊያቆሙ አሊያም የአፓርታይድ አገዛዝ ለመትከል ነው ማለት ነው። እኔ ከሁሉም በላይ የሚገርመኝ «No Taxation without Representation» የሚል መርህ የዋና ከተማዋ መፈክር በሆነባት አገር እየኖሩ ለአዲስ አበባ ግን «taxation without representation»ን ፍትሕ አድርገው ማቅረባቸው ነው። መማርም ሆነ ለአስርት አመታት ውጪ አገር መኖር ምንም አለመቀየሩ ሳይገርመኝ አልቀረም።