የኢትዮጵያ ባለውለታ እምዬ ምኒልክ ከውጭ አገር አዘው ወደ ኢትዮጵያ ባስገቡት የመጀመሪያው ፎቶ ካሜራ እና የተነሱት ፎቶ ግራፍ

Print Friendly, PDF & Email

የኢትዮጵያ ባለውለታ እምዬ ምኒልክ!

ፎቶግራፍ እና አጼ ምኒልክ

ከውጪ ሀገር የመጡ ሰዎች ለአፄ ምኒልክ ስለ ፎቶግራፍ እንዲህ ብለው አስረዷቸው “በአውሮፖ አንድ ትንሽ ሳጥን አለች ሰውን፣ በቆሎን፣ ፈረሱን፣ ቤተመንግስቱን ሁሉ ወደ ሳጥኗ ታስገባና ሁሉን ትንሽ አርጋ ታሳያለች”

ግንቦት 13 ቀን 1875 ዓ.ም አጼ ምኒልክ ከውጭ አዘው ባስመጡትና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ በሆነው የፎቶ ካሜራ የመጀመሪያውን ፎቶ ሲነሱ

ምኒልክም በሰሙት ነገር ተገርመው እንዴት ይሆናል ይሄን ነገር ማየት አለብኝ ብለው የፎቶ ማንሻ እንዲመጣ አዘዙ ።

የፎቶ ማንሻውም(ካሜራ) ከእነ አንሺው በ1875 ዓ/ም ወደ ሀገራችን ገባ ። ሆኖም ግን አጼ ምኒልክ ፎቶውን ሊነሱ ሲሉ ቀሳውስቱ መኳንንቱ ከለከሏቸው ርኩስ ነገር ነውና አጥፉልን አሏቸው።

ምኒልክም “እግዚአብሔር የፈጠረውን ነገር አታርጉ፣ አትንኩ፣ ነውር ነው ማለት አምላክን መቃውም ነው እንዲህ ያለ ሀሳብ አታስቡ ዞር በሉ ከፊቴ” ብለው ግንቦት 13 ቀን 1875 ዓ/ም አጼ ምኒልክ የምትመለከቱትን የመጀመሪያ ፎቶ ተነሱ።

መልካቸውንም በማየታቸው ወደዱት ከዚህም በኋላ ራሳቸው አጼ ምኒልክ ፎቶግራፍ ማንሳትን ፊልሙን አጥቦ እስከማሳተሙ ተማሩ፡፡

ምንጭ-፡ የኢትዮጲያ ስልጣኔ መጽሐፍ

ነሐሴ 12 የእምዬ ልደት
መልካም ልደት!
ክብር ለቀደሙት አባቶቻችን

ምንጭ-፡ የኢትዮጵያ ስልጣኔ መጽሐፍ (ሔለን ምኒልክ ቴዎድሮስ)

 

****
አቶ ዘመድኩን በቀለ የካቲት 22/6/2008 ዓ.ም “ክብር ለእምዬ ምኒልክና ለአድዋ ጀግኖቻችን” በሚል እርስ ጽፎት ከነበረው በከፊል የተወሰደውን ከዚህ በታች እንድታነቡ አቅርበነዋል።

አጼ ምኒልክ ለኢትዮጵያ እናት ሀገራችን ካበረከቷቸው መልካምና በጎ ሥራዎች መካከል ከተለያዩ ዶክመንቶች የተገኙ መረጃዎችን በጥቂቱ እንመልከት።

ሁሉንም ማለት ይቻላል የዘመኑን ቴክኖሎጂ እንዲሁ በፈለጉት ሰዓት በፈለጉት መጠን ለማስገባት ግን ትልቅ ችግርና ተቃውሞ በየጊዜው ከቤተክህነቱም ከቤተመንግስቱም ሹማምንት ያለማቋረጥ ይገጥማቸው እንደነበር ብዙ ያታሪክ ጸሐፊዎች በየመጻሕፍቶቻቸው ከትበውት እናገኛለን።

ከቧንባ ሥራ እንጀምር ። የቧንቧ ሥራ በመኳንንቱ ተቃውሞ ቢኖርበትም እምዬ ምኒልክ ግን ተቃውሞውን በመቋቋም ለቧንቧው መግዣ የሚውል ሰባት ሺህ ማርትሬዛ ብር ሰጥተዋል። ይህ ሰባት ሺህ ብር የጨረሰው ቧንቧ የመዘርጋት ሥራ በ1886 ዓ/ ም በጥር ወር አለቀ። ከላይ ከኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ካለ ምንጭ የተጠለፈው ውሃ ከቤተ መንግስቱ ካለው የመጨረሻ ቧንቧ አልደርስ አለ።ቧንቧው ሲከፈትም ጠብ የምትል ውሃ ታጣች። ውሃው የቀረበት ምክንያት ይፈለግ ጀመር። በፍተሻ እንደተገኘው ውሃው ሊመጣ ያልቻለው ቧንቧው በጥጥ ፍሬ በመደፈኑ ሆኖ ተገኘ። ጥጥ ፍሬው ተጠርጎ ከወጣ በኋላ ውሃው ከቤተ መንግስቱ ደረሰ።

በዚህም መሰረት እንግዲህ የቧንቧ ውሃ በ1886 ዓ/ ም ማለትም አዲስ አበባ ከተማ በተመሰረተች በሰባተኛ አመት አገልግሎት ጀመረ። በቤተ መንግስቱ የገባው የቧንቧ ውሃ ሁሉን አስደስቶ ዘዴው ከታወቀና ከተጠና በኋላ ይህ የቧንቧ ውሃ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዲዳረስ ምኒልክ የውሃ ቧንቧ አስገዙ። የተገዛውም የውሃ ቧንቧ ከጅቡቲ፣ ድሬደዋ ድረስ በባቡር ከመጣ በኋላ በዘመኑ የባቡሩ መስመር አዲስ አበባ ስላልደረሰ ከድሬደዋ አዲስ አበባ ድረስ በሰው ሸክም እንዲመጣ ምኒልክ አዘዙ ይለናል ጳውሎስ ኞኞ ።

※ እጅግ ዘመናዊና እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀን የጣሊያንን ጦር አደዋ ላይ በእምነትና በጥበብ በአሮጌ ጋሻና ጦር ድባቅ የመቱ ። በዚሁ ምክንያት በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ነጭን ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ።

※ በሀገራችን ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን አውቶሞቢል የነዱና ፐርፌክት ድራይቨር የሚለውን የመጀመሪያውን የመንጃ ፈቃድ የተቀበሉ ።

※ የመጀመሪያውን የእህል ወፍጮ መኪና ያስመጡና በወቅቱ ወፍጮው ሰይጣን ነው ተብሎ ሰው በመሸሹ ሰይጣን ያለመሆንኑን ለማሳየት ቆመው እህል ያስፈጩ ።

※ የመጀመሪያውን ስልክ አስገብተው ጋኔኑ ከዙፋኑ ይውጣ ብለው የዘመኑ
ጳጳስ ጭምር ከባድ ተቃውሞ ቢያነሱባቸውም ታግለው ስልክን የመሠረቱ ።

※ የመጀመሪያውን ብስክሌት መንዳት ተምረው ባለቤታቸውንም በማስተማር ሴቶች ከመሸፋፈንና ከማፈር እንዲወጡ የታገሉ ።

※የመጀመሪያውን ሆቴል ከፍተው ሚስታቸውን ወጥ ቤት አድርገው በገንዘባቸው መኩዋንንቱን እየጋበዙ ሆቴል መብላትን ያስተማሩ ።

※የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በ 1881ዓ/ም በአዋጅ አረንጏዴ ቢጫ ቀይ እንዲሆን ያደረጉ ።

※ለመጀመሪያ ጊዜ ፎቶግራፍ ማንሳትና፣ ፊልም አጥቦ ማተም የተማሩ ።

※የተለያዩ አበቦችንና ጽጌረዳዎችን ከአውሮፓ እያስመጡ እስካሁን የምንጠቀምባቸውን ልዮ ልዩ አበቦችን ያራቡ ።

※የኮክ፣ የእንጆሪ፣ የወይን እና የመሳሰሉትን የአትክልት ልዩ ዘሮችን እያስመጡ ያራቡ ።

※ እስከ ዛሬ ለኢትዮዽያ ትልቅ ጥቅም እየሰጠ ያለውን ባህር ዛፍን ከውጭ ሀገር አስመጥተው የተከሉና ያባዙ ።

※በአዲስ አበባ የመጀመሪያውን የውጭ አገር ትምህርት ቤት የከፈቱ ።

※ የመጀመሪያውን የሙዚቃ ትምህረት ቤት የከፈቱ ።

※ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስገቡ ።

※ ከጂቡቲ አዲስ አበባ ድረስ የባቡር ሀዲድ አዘርግተው የመጀመሪያውን የባቡር አገልግሎትን ያስጀመሩ ።

※የመጀመሪያውን ዘመናዊ የመንገድ ሥራ ያስጀመሩ ።

※የመጀመሪያውን የፖስታ ድርጅትን የከፈቱ ።

※ ሰው ሲባል እኩል ነውና ማንም ሰው ሰውን ባርያ እንዳይል ብለው የባርያን ነፃነት ያወጁና ሰው እንደከብት እንዳይሸጥ የታገሉ ።

※ ሴት ልጅ በወላጆችዋ ምርጫ ሳይሆን በፈቃድዋ የመረጠችውን ባል እንድታገባ ያወጁና ለሴት ልጆች ነፃነት የታገሉ።

※ ሠራተኛ በሥራው እንዳይበደል አዋጅ ያስነገሩ።

※ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ አስገዳጅ ሕግ ያወጡ።

※ የተሠራ ጨርቅ ከማስመጣት ይልቅ ድር እያስመጡ ማሠራት እንደሚረክስ አውቀው የመጀመሪያውን ድር ማስመጣትን የጀመሩ ።

※ የመጀመሪያውን የጥይት ፋብሪካን ያቁዋቁዋሙ ።

※ የሕክምና ሙያ በዘመናዊ መንገድ እንዲተገበር ፣ ሆስፒታልና የመድኃኒት መሸጫ ፋርማሲ እንዲከፈት ያደረጉ ።

※ የባንክና የገንዘብ አገልግሎት እንዲጀምር ያደረጉ

※ የአረቄ በዘመናዊ መንገድ እንዲጠመቅ የሙዚቃ በሸክላ መምጣትን ፈር የቀደዱ።

※ የማተሚያ ማሽን በማስመጣት ኅትመትን ያስጀመሩ ።

※ አዕምሮ የተሰኘች ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትታተም ያደረጉ ።

※ በወቅቱ ዘበኛ ይባል የነበረውንና የዘመናዊው ፖሊስ ሠራዊት መሥራች።

※ የጽሕፈት መኪና
※ ሲኒማ
※ ጫማ
※ የፍልውኃ አገልግሎት እና ሌሎችንም ለሀገር የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን ያስመጡ ታላቅ መሪ ናቸው ።

“አንዲት አነስተኛና የህክምና መሣሪያ እንኳ በቅጡ ያልተሟላላትን የጤና ጣቢያ አሠርቶ ስሜ በጊነስ ቡክ ላይ ካልተጻፈልኝ ሞቼ እገኛለሁ በሚባልበት በዚህ ዘመን የእምዬ ምኒልክን ግዙፍና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ያለማወደስ ግፍም ፣ ነውርም ፣ ኃጢአትም ነው ።

“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ።

ለዛሬ ማንነታችን መሰረት ናቸውና ክብር ለእምዬ ምኒሊክ ይገባል እያልኩ ከመሰነባበታችን በፊት በአርቲስት ቴዲ አፍሮ አንዲት መስመር ቃል ነገር ግን በውስጧ ብዙ ሺ ገጽ የሚወጣው ድልብ ኃሳብ በያዘች ዓረፍተ ነገር እንሰነባበት ።

“የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ”

ዘመድኩን በቀለ ነኝ
የካቲት 22/6/2008 ዓም
አዲስአበባ – ኢትዮጵያ