ሃይሌ ገብረስላሴ የተላመጠ ሸንኮራ መሆኑ መሰለኝ!

Print Friendly, PDF & Email

(መስቀሉ አየለ)

አንድ አሁን ስሙን የማልገልጠው የሚንስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ይሰራ የነበረ ሰው እንደነገረኝ ባንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ስልሳ ያህል ነጋዴዎችን ይዞ ጉዞውን ወደ ሩቅ ምስራቅ አገሮች ያደርጋል። ሴንጋፖር፣ ሆንግኮንግ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን ወዘተ ማካለልን አላማ ያደረገ ነበር። ሃይሌ ገብረስላሴም በንግዱ ዘርፍ ውስጥ በነበረው ተሳትፎ ባለሃብት ተብሎ ተካቷል። ነገር ግን በግዜው በደረሱበት ከተማ ሁሉ ህዝቡም ሆነ ፖሊሱ ለማየት የሚሻማው ወይንም ፈርምልን፣ ፎቶም አብረንህ እንነሳ የሚባለው ሃይሌ ገብረስላሴ እንጅ መለስ ዜናዊ አልነበረም። ይልቁንም መለስን ያወቀውም ሆነ ከቁብ የቆጠረው አንድም ሰው ነበር ማለት አይቻልም። በሁኔታውም መለስ ዜናዊ ደም ፍላቱ ለማንም በሚያስታውቅበት ደረጃ ራዲያተሯ እንደጋለባት አሮጌ ቮልስዋገን መንተፍተፍ ጀመረ።ሃይሌ ገብረስላሴንም በግልምጫ ያጨሰው ጀመረ። ሃይሌ ሁኔታው ይሻሻላል ብሎ በያስብም ሰውየው እያደር እየብሳበት ሄደ። በዚህ መሃል ሃይሌ ግልምጫው ሲበዛበት አቋርጦ ለመመለስ ቢወስንም በወቅቱ አብረውት ከተሳፈሩት ሰው ምክር የተነሳ አቋርጦ መመለሱ የሚያስከፍለውን ዋጋ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ቀጭን ምክር ቢጤ ሺክ ተባለ። በመጨረሻም የቶኪዮው ጉብኝት እንዳለቀ ሃይሌ “ጀርመን ላይ የሃኪም ቀጠሮ አለኝ” በሚል ሂሳብ በፍራንክፈርት በኩል ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።

ሃይሌ ገብረስላሴ

ቀጥሎም ሃይሌ ሪል እስቴት እመሰርትበታለሁ ብሎ የተቀበለው ጠፍ መሬት አዜብ ጎላ “ነብር አየኝ በል” አለችበት። በዚህ ድንጋጤ ውስጥ የወደቀው አትሌት የዱባይ ማራቶን ያሸነፈበትን ማሊያ ናዝሬት ላይ በተካሄደ የወያኔ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመለስ ዜናዊ ሸለምኩ አለና ለመጀመሪያ ግዜ ከወያኔ ጋር መቁረቡን በአደባባይ አሳወቀ።

ከዚያን ግዜ ጀምሮ ወያኔ አቅመ ቢስ ሆኖ ቅርቃር ውስጥ የገባ በመሰለ ግዜ ሁሉ የተሻለ ታማኝ ሎሌ ሆኖ ራሱን በማቅረብ ባርነትን እንደ ኒሻን አጎንብሶ ተቀብሏል። ወያኔዎች አንደበታቸው ሲጎለድፍ እርሱ ይሳደብላቸዋል። ባጭሩ መለስ ዜናዊ ባነጠሰ ቁጥር መሃርብ ይዘው ከሚሮጡት አንዱ ሆኖ አረፈው። መለስ ዜናዊ ሲበክት ደግሞ ጣምራ ጣምራውን የእንብ ጎርፍ ሲቀዳለት ላየ ሰው አብሬ ልቀበር አለማቱን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ዛሬ ደግሞ አከርካሪው ላይ ለሁለት የተጎመደውን ዘንዶ መልሶ ለማጣባቅ ላይ ታች ከሚባክኑት ግንባር ቀደሙ ሃይሌ ቢሆንም ነቀርፉኝቶቹ (ነቀርሳና እፉኝት) ውለታ የሚያውቁ አይደሉምና አሁን ደግሞ ከጀርባ ሊወጉት(stabbing behind) ሲዳዳቸው ይታያል ።እርሱኑ አጀንዳ አድርገውታል፤።መጭ ሁኔታዎች ጥላቸውን ያጠላሉ እንዲባል የዘፈን ዳርዳሩ ሳይሆን አልቀረም። ብቻ የባርነት ደመዎዝ ከዚህ አልፎ አያውቅም።