በሰሜን ሸዋ የቅርስና ጽላት ዘረፋው ከሀ/ስብከቱ አቅም በላይ ኾነ፤ “በሀ/ስብከቱ ውስብስብ ኔትወርክ ዘርግቶ በከፍተኛ ምዝበራ የተሰማራ አደገኛ ቡድን አለ”/ዞኑ/

Print Friendly, PDF & Email
 •  “አዲስ ጽላት እንደርባለን” በሚል ሰበብ፣ ነባር ታቦታትና ቅርሶች ይሰረቃሉ፤ ይለወጣሉ
 •  “ተወላጆች ነን” የሚሉ ከተሜ ካህናትና ምእመናን በበጎ አድራጊነት ሽፋን ይፈጽሙታል
 • ዝርፊያው፥ የወታደር ልብስ በለበሱ እና የጦር መሣርያ በታጠቁም ይፈጸማል፤ ተብሏል
 • የቅጣት ጊዜን ሳይጨርሱ የሚለቀቁ የቅርስ ዘራፊዎች ጉዳይ፣ አጽንዖት ሊሰጠው ያሻል
 • ዞኑን ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ ሀገረ ስብከቱ እንዲያግዝ አስተዳደሩ ጠይቋል
 • ከደብረ ሲና ተራራ እስከ እመ ምሕረት አንኮበር ተራራ የአየር ኬብል ማጓጓዣ ይዘረጋል
 • “ስለ ቅርስ ጥበቃ፣ ለ29ኙም የወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች በየዓመቱ መመሪያ እየሰጠን ነው፤ ምዝገባም እናካሒዳለን፤ ነገር ግን የቅርስ ዘረፋው ስልቱና ዝግጅቱ ከእኛ አቅም በላይ ነው፤ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ነው የሚመጡት፤ ይህ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፤ ከሞላ ጎደል መንግሥትም መሣሪያ እየሰጠ ጥበቃው እየተካሔደ እንደኾነ መረጃው አለን፤ ግን በቂ ሥራ ተሠርቷል ለማለት አያስደፍርም።” /የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ/
 • “እንደ መንግሥት አረዳድ፣ በሀገረ ስብከቱ ያለው አሰላለፍ በሦስት መደብ እንደሚመደብና አንደኛው ቡድን፥ ውስብስብ ኔትወርክ ዘርግቶ በከፍተኛ ምዝበራ ላይ የተሰማራና ሌሎችን የሚያጠፋ አደገኛ አካሔድ ያለው ነው።… የአብያተ ክርስቲያናት መፍረስና የቅርስ ዘረፋው አያጣላቸውም፤ አላግባብ የግል ተጠቃሚ ለመኾን የሚደረግ እሽቅድምድምና የሥልጣን ሽሚያ ነው የሚያጣላቸው፤ ይህንንም ዞናችን በሚገባ ያውቀዋል።” /የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ/
 • “በሀገረ ስብከቱ የቅርስ ምዝገባና መለየት በአስቸኳይ ተሠርቶ ወደ ዳታ ቤዝ እንዲገባ፤ ለችግረኛ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የቅርስ ጥበቃ ድጎማ እንዲደረግ፤ ተአማኒነት ያላቸው የጥበቃ ሠራተኞች በኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲቀጠሩ፤ ከዞን አስተዳደር ጋራ የቅርስ ጥበቃ ጥምር ኮሚቴ እንዲቋቋምና ሥልጠና እንዲሰጥ፤ ለቅርስ ለውጥ ምክንያት ይኾናል ተብሎ የተገመተው ዐዲስ ጽላት የማስገባት ሒደት በሀገረ ስብከቱ በማዕከል እንዲሠራ፤ ‘ጽላት’   እያሉ ከመንደር እያመጡ በሚለወጡት ላይ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድ፤” /ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ/

በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ጥንታውያንና ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናት ከበርካታ ታሪካውያን ቅርሶች ጋራ በሚገኙበት በሰሜን ሸዋ ዞን የሚፈጸመው የነባር ጽላትና ቅርሶች ዘረፋና ቅሠጣ፣ ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ እንደ ኾነ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መረጋገጡ ተገለጸ።

በሀገረ ስብከቱ፣ ውስብስብ ኔትወርክ ዘርግቶ በከፍተኛ ምዝበራ ላይ የተሰማራ አደገኛ ቡድን መኖሩን የገለጸው የዞኑ አስተዳደር፣ ሀገረ ስብከቱ ራሱን እንዲፈትሽ አሳስቧል። ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በበኩሉ፣ ሀገረ ስብከቱን ከሚያምሰው የዘመድ አዝማድ መሳሳብና ቤተሰባዊ ሙሰኝነት ባሻገር፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመበረዝና ለመለወጥ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትና በወረዳዎች ድብቅ ተግባራትን የሚፈጽሙ የተሐድሶ ኑፋቄና የፕሮቴስታንት ኅቡእ ተላላኪዎችም እጅ እንዳለበት፣ አጣሪ ልኡኩ አረጋግጧል። በዚኽ ረገድ በተደጋጋሚ ሲቀርብ ለቆየው ስጋት መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ከማጣራት ሒደቱ መገንዘቡን አስታውቋል።

ሀገረ ስብከቱ፣ “የሀገሪቱን የታሪክ አሻራ ያለበት አንድ ክፍል ነው፤” ያለው አጣሪ ልኡኩ፣ የእኒህ የውስጥና የውጭ ፀራውያን አካላት ዝርፊያና ተጽዕኖ አንዱ ምክንያት፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጎበኙት አድባራቱና ገዳማቱ የሚያስገኙትና በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ ያለው ከፍተኛ የሰበካ ጉባኤ ገቢም ጋራ የተያያዘ እንደኾነ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ግላዊና ቡድናዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና ለሥልጣን ከሚካሔድ ሽኩቻና ሽሚያ እንዲኹም፣ ከቅርስ ዘረፋ እና ቅሠጣ ጋራ ተያይዞ በቀረቡ የምእመናንና የሠራተኞች አቤቱታዎች መነሻ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ባካሔደው ማጣራት፣ የሀገሪቱ የታሪክ አሻራ ያሉባቸው በርካታ ቅርሶች፣ የመንግሥት ለውጥ ከኾነበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ እየተዘረፉ እንዳሉ ለመረዳት መቻሉን፣ አጣሪ ልኡኩ ሰሞኑን ለጽ/ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል።

የቅርስ ምዝበራንና ቅሠጣን አስመልክቶ ከአቤት ባዮች የቀረበው አቤቱታ፣ እውነትነት ያለውና ችግሩ ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ እንደኾነ፣ አጣሪ ልኡኩ ባከናወናቸው ኹሉም የማጣራት ሒደቶች ተረጋግጧል። የጻድቃኔ ማርያም፣ የሸንኮራ ዮሐንስ፣ የሳማ ሰንበት፣ የሚጣቅ ዐማኑኤል፣ የዘብር ገብርኤል፣ የመልከ ጸዴቅ እና የእመጓ ገዳማትንና አድባራትን ጨምሮ ከኹለት ሺሕ በላይ አብያተ ክርስቲያናትን አቅፎ የያዘው ሀገረ ስብከቱ፣ ቅርሶቹን ለማስጠበቅ የአቅም ውሱንነት እንዳለበት፣ በመስክና በመድረክ በተደረገው በእያንዳንዱ ማጣራት ማሳያዎች እንደቀረቡ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

 • በሚጣቅ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የነበረ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የብራና ዳዊትና ከዐጤ ምኒልክ የተሰጠ መስቀል ተዘርፎ የደረሰበት አልታወቀም፤ ሀገረ ስብከቱም አልተከታተለውም፤
 • በመንዝ የቀያ ቅዱስ ገብርኤል ጽላት ተሰርቆ ሲፈለግ ቆይቶ፣ ጽላቱን የያዘው ሰው በቁጥጥር ሥር ውሎ በፖሊስ ከተጣራ በኋላ ሲመለስ፣ ነባሩ ቀርቶ አዲስ ጽላት ተለውጦ ነው የተመለሰው፤
 • ከተዘረፉት ቅርሶች ጅቡቲ ድረስ የተወሰዱ መኖራቸውንና ከእኒህም አንዱ የነበረውና ጠፍቶ የቆየው የዐጤ ዋሻ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም የተሰረቀው የመድኃኔዓለም ጽላት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቅርስ ጥበቃ መመሪያ ጋራ በመተባበር እንዲመለስ ተደርጓል
 • የሚዳ ኦሮሞ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፥ የሀገረ ስብከቱን ይሁንታ ሳያገኝና ማዕከሉን ሳይጠብቅ፣ “አዲስ ጽላት ለማስገባት” በሚል ኹለት ጽላት ከዐዲስ አበባ ድረስ በማስመጣት አግባብነት የሌለው ሒደት መፈጸሙንና ታቦታቱ እስከ አኹን በፖሊስ ጣቢያ በኤግዚቢት ተይዘው ይገኛሉ፤
 • በነጭ ገደል በኣታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን፦ የመንግሥት ባለሥልጣናት ነን ያሉና የወታደር ልብስ የለበሱ የተደራጁ ግለሰቦች፣ ቄሰ ገበዙንና የጥበቃ ሠራተኞችን በደጀ ሰላሙ አግተው ታቦተ ሕጉ ሲቀር ኹሉንም ንብረቶች ዘርፈው ወስደዋል፤ በሌላም ጊዜ ተደራጅተው ሊዘርፉ የመጡ ግለሰቦች ተይዘው በእስር ላይ ይገኛሉ፤ የጥበቃው አቅም አነስተኛ ነው፤
 • ደንባ ከተማ ላይ መሸኛ የሌለው ታቦት ተይዞ በሀገረ ስብከቱ አመራር ሰጭነት ተቀምጧል፤
 • ኹለት የቅዱስ ገብርኤል እና ኹለት የቅዱስ ሚካኤል ጽላት መሐል ሜዳ ተገኝተው ቢመለሱም የስርቆት ሙከራው ግን እስከ አኹን ቀጥሏል፤
 • በአፈር ባይኔ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጽላቱ ባይለወጥም የቅርስ ዘረፋው አልቆመም፤
 • በቁንዲ ቅዱስ ጊዮርጊስ፦ 14 የብራና መጻሕፍት፣ የብር ከበሮ፣ መስቀል፣ ኹለት ኩንታል የተቋጠሩ ንብረቶች ተዘርፈው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ አዋሬ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ቢመለሱም፣ ዘራፊዎቹ ለ8 ዓመት በሕግ ተፈርዶባቸው ሳለ 5 ዓመት ተቀንሶላቸው በ3 ዓመት እስራት ተፈትተዋል፤
 • በጃን አሞራ ተክለ ሃይማኖት፥ የብራና መጻሕፍት ጠፍተዋል፤ የአንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ደወል ተሰርቆ በክትትል ላይ ነው፤
 • ለፖሊስ ደብዳቤ ተጽፎ ክትትሉ ቢቀጥልም፣ ፍንጭ ያልተገኘላቸው እንደነሚጣቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እና አንጎለላ አካባቢ ከሚገኙ ሦስት አብያተ ክርስቲያናት የተሰረቁ ንዋያተ ቅድሳት በማጣራቱ ሒደት ከቀረቡት ማሳያዎች ውስጥ እንደሚገኙበት በሪፖርቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘርዝሯል።

በቅርስ ዘረፋውና ቅሠጣው ተይዘው የታሰሩ ቀሳውስትና ዲያቆናትም መኖራቸውንና በማረሚያ ቤቶችም ማየት እንደሚቻል አቤቱታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል። የወታደር ልብስ የለበሱና የጦር መሣሪያ ታጥቀው የተደራጁ ግለሰቦችም፣ የጥበቃ ሠራተኞችን በማገትና በማታለል ዘረፋ እንደሚፈጽሙም ለሀገረ ስብከቱ የሚደርሱ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ፣ ለ29ኙም የወረዳ አብያተ ክህነት ሓላፊዎች መመሪያ እንደሚሰጥና ምዝገባም እንደሚካሔድ የገለጹት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሣህል አባ ዘውዱ በየነ፣ “የቅርስ ዘረፋው ስልቱና ዝግጅቱ ግን ከእኛ አቅም በላይ ነው፤ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ነው የሚመጡት፤ ይህ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፤ እኛንም በእጅጉ አሳዝኖናል፤” ሲሉ ለልኡኩ አስረድተዋል። የሀገረ ስብከቱ ቅርስ ክፍል ሓላፊ ቄስ ዮሐንስ ታምሬም፣ “በርካታ ቅርሶች በኃይልና በአፈና ተዘርፈውብናል፤ ከተዘርፉት ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ ጅቡቲ ሲደርሱ ተይዘው የተመለሱ አሉ፤” ብለዋል።

የኹሉም ወረዳ አብያተ ክህነት ሓላፊዎች፣ በየወሩ በ29፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን በየወረዳቸው እየሰበሰቡ፣ መመሪያ እንደሚሰጡና እንደሚመዘግቡ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ከሚደርሱ ሪፖርቶች በመነሣት ክትትል እንዲደረግ ለፖሊስ ደብዳቤ ሲጻፍ መቆየቱን አውስተው፤ መንግሥትም፣ ከሞላ ጎደል መሣሪያ እየሰጠ ጥበቃው ቢካሔድም በቂ ሥራ ተሠርቷል ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል።

በልኡኩ የማጣራት ሥራ የተሳተፉት የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ምንውየለት ጭንቅሎ፥ የቀያ ቅዱስ ገብርኤል ነባር ጽላት በአዲስ መለወጡ እንደተረጋገጠ፤ ይኹንና ነባሩ ጽላት በአዲስ ጽላት እንዲለወጥ ስምምነት የተደረገው፣ በወቅቱ ጉዳዩን በተከታተለው ፖሊስና በሌሎች ካህናት እንደነበር አስረድተዋል። ፖሊሱ በወንጀል ተከሦ ከመታሰሩም በላይ ከሥራም እንዲሰናበት መደረጉን፣ ካህናቱም በእስር ላይ እንደነበሩ አውስተዋል።

ሪፖርቱ እንዳተተው፣ ለነባር ጽላት ስርቆትና ለቅርስ ለውጥ መንገድ የሚከፍተው ተጠቃሹ መንሥኤ፣ ሀገረ ስብከቱ “የታቦት እደላውን” በማዕከልነት አለማከናወኑ ነው። ይህም፣ ዐዲስ አበባ የሚኖሩ ካህናትም ኾኑ ምእመናን፣ “የአካባቢው ተወላጆች ነን” በሚል ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ግለሰቦች ጋራ እየተመሳጠሩ፣ “እኛ ጽላት አዘጋጅተን ብናመጣና ቢደረብ፤”  እያሉ በበጎ አድራጊነት ሽፋን ችግሩን ይፈጥራሉ። ለዚኽም የሚዳ ኦሮሞ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ ለሀገረ ስብከቱ ሳያሳውቁና ሊቀ ጳጳሱን ሳያስፈቅዱ ከዐዲስ አበባ ቀጥታ ኹለት ጽላት በማስመጣት የፈጸሙት ድርጊት በምሳሌነት ተጠቅሷል።

ጽላቱን ማስመጣታቸውን በማጣራቱ ወቅት ያመኑት የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ተከሥተ ደምስ፣ “በተደራቢነት እንዲገቡ እንጅ ነባሩን ጽላት ለመንካትና ለመለወጥ አይደለም፤” ሲሉ ክሡን ተከላክለዋል። ይህም፣ የምእመኑን ጥያቄ መነሻ በማድረግና ከሕዝበ ክርስቲያኑ በተሰበሰበ ፊርማ የተደገፈ ጥያቄ እንደኾነ ሥራ አስኪያጁ ቢገልጹም፤ ጽላቱን እንዲያመጡ የተላኩት ካህን፣ ከወረዳ ቤተ ክህነቱ የተጻፈውን ደብዳቤው ለሀገረ ስብከቱ ገቢ ሳያደርጉና ውክልናቸውን ሳይዙ በቀጥታ ወደ ዐዲስ አበባ ሔደው ጽላቱን ሲያመጡ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ እርሳቸውም ካህኑም ተይዘው ታስረዋል። በዚኹ ሳቢያ፣ በወረዳው ቤተ ክህነትና በወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተፈጠረው አለመግባባት፣ በወረዳው ዐቃቤ ሕግ የተመሠረተባቸው የክሥ ፋይሉ ቢዘጋም፣ ጽላቱ ወደተባለው ደብር ሳይገቡ አኹንም በፖሊስ ጽ/ቤት እንደሚገኙ ተመልክቷል።

“ዐዲስ ጽላት እናስገባለን፤ እንደርባለን፤” በሚል ሰበብ ነባር ጽላትና ቅርስ ይሰረቃል፤ ይለወጣል፤” የሚለውን ክሥ የሀገረ ስብከቱም ሓላፊዎች አስተባብለዋል። “ፎርጅድ የሚለው አባባል ትክክል አይደለም፤ ነባር ጽላት ይለወጣል የሚለውም አባባል ከእውነት የራቀ ነው፤” ብለዋል – የቅርስ ክፍል ሓላፊው ቀሲስ ዮሐንስ ታምሬ። ዐዲስ ጽላት ከማስገባት ጋራ ተያይዞ የሚቀርቡ ጥያቄዎችና የሚስተናገዱበትንም ሥርዓት እንደሚከተለው አብራርተዋል፡-

ዐዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተው ሲጠናቀቁና በነባሮች አብያተ ክርስቲያናትም፣ እንዲህ ዓይነት ታቦት ይደረብልን፤ የሚል ጥያቄ ደረጃውን ጠብቆ ሲቀርብ፣ በሀገረ ስብከቱም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ዕውቅና የተሰጣቸው አዘጋጆች እንዲያዘጋጁ እየታዘዘና አዘጋጅተው ሲያመጡ፣ ላዘጋጆቹ የአገልግሎት ክፍያ በመፈጸም ታቦታቱ በሊቀ ጳጳሱ ተባርከው ወደጠየቁት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በማስገባት አገልግሎት እንዲፈጸምባቸው ይደረጋል።

ሌላው ነባሮቹን ጽላቶች ላይ የሚቀመጠው ስመ አምላክ ትክክል ኾኖ ካልተገኘ፣ በደብሩ በቅርስነት ተመዝግቦ ከርሠ ሐመር በሚባለው ስውር ቦታ በክብር እንዲቀመጥ በማድረግ ስመ አምላክ በትክክል የተቀመጠበትና ዐዲስ የተዘጋጀው ጽላት በመንበሩ ላይ ኾኖ አገልግሎት እንዲከናወንበት ከማድረግ ውጭ፥ ይለወጣል፤ የሚለው አባባል ከእውነት የራቀ ነው።

ስለ ኹለቱ ጽላት፣ ሀገረ ስብከቱ በመጀመሪያ “ጉዳዩን አናውቅም” ብሎ ለፖሊስ እንደጻፈ የተናገሩት የቅርስ ክፍሉ ሓላፊ፣ በኋላ ግን ካህኑ ሊቀ ጳጳሱን ሳያገኙ በቀጥታ በማምጣታቸው በነበረው ክፍተት የተፈጠረ ችግር እንደኾነ አስረድተዋል፤ በሊቀ ጳጳሱም በተሰጠ አመራር ዳግመኛ ደብዳቤ ተጽፎ የታሰሩት ካህናት መለቀቃቸውን ገልጸዋል፤ የጽላቱ መዘጋጀት መነሻ ግን፣ “በበጎ አድራጊዎች የተከናወነ መኾኑን እንደሰሙ” አልሸሸጉም።

ከዞኑ ፖሊስ ጽ/ቤት የበኩላቸውን ምላሽ የሰጡት ኢንስፔክተር ንብረት ተጓድ፣ ሀገረ ስብከቱ “አናውቅም” ብሎ ደብዳቤ በመጻፉና ኹኔታው ጥያቄ በማስከተሉ ጽላቱ መያዛቸውንና ጉዳዩ በፍትሕ አካላት ታይቶ ውሳኔ እንደተሰጠበት ገልጸዋል። ከብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በተጻፈ ደብዳቤም እልባት አግኝቶ፣ ጽላቱ ወደ ቦታቸው እንዲገቡ መመሪያ አስተላልፈናል፤ ብለዋል።

ይህም ኾኖ፣ የአጣሪ ልኡኩ ሪፖርት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ ቀርቦ መታየቱን ተከትሎ፣ የሚዳ ኦሮሞ ወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱን ይኹንታ ሳያገኙና ማዕከልን ሳይጠብቁ፣ ጽላት ከዐዲስ አበባ እንዲመጣ በማድረጋቸውና ፈጥረዋቸዋል በተባሉ ሌሎች የሥራ ዕንቅፋቶች፣ ሀገረ ስብከቱ፥ ከማስጠንቀቂያ ጋራ ወደ ሌላ ወረዳ እንዲያዛውራቸውና አፈጻጸሙንም እንዲያሳውቅ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንደታዘዘ ታውቋል።

የቅርስ አጠባበቁን አስመልክቶ ሀገረ ስብከቱ መውሰድ ስለሚገባው ርምጃና በቀጣይነት እንዲያከናውናቸው ስለሚያስፈልጉ የተናጠልና የቅንጅት ተግባራት፣ አጣሪ ልኡኩ የሚከተሉትን አራት የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦች በሪፖርቱ አስቀምጧል፡-

 1. የቅርስ ምዝገባና የመለየት ሒደት፣ በሀገረ ስብከቱ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሠራ ኾኖ፣ ከዚኽ በፊት የተመዘገበ ቢኖር ወደ ዳታ ቤዝ እንዲገባ ቢደረግ፤
 2. ቅርስ ያለባቸው አብያተ ክርስቲያናትን የሚጠብቁ የጥበቃ ሠራተኞች በሚቀጠሩበት ጊዜ፣ ባለቅርሱ ደብር የመክፈል አቅሙ መጠነኛ እየኆነ እንደሚቸገር በማጣራት ሒደቱ በመስክ እይታ የተመለከትናቸውና አድባራቱም ያረጋገጡ በመኾኑ፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል፣ ሀገረ ስብከቱ የገንዘብ ድጎማ እንዲያደርግና በአቀጣጠሩም ሒደት ማኅበረሰቡን አወያይቶ ተአማኒነት ያላቸውን የጥበቃ ሠራተኞች የሚቀጠሩበትን ሒደት ቢያመቻች፤
 3. የቅርስ ስርቆትን ለመከላከልና ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንዲያስችል ሀገረ ስብከቱ ከዞኑ መስተዳድር ጋር ጥምር ኮሚቴ አዋቅሮ ቢሠራና በአጠባበቁም ሒደት ሥልጠና እንዲሰጥ አመራር ቢሰጠው፤
 4. ለቅርስ ለውጥ ምክንያት ይኾናል ተብሎ የሚገመተው፣ ዐዲስ ጽላት የማስገባት ሒደት በሀገረ ስብከቱ በማዕከል እንዲሠራና ከዐዲስ አበባ ከመንደር የሚመጡ ጽላቶችና የመለወጡ ሒደትም ሕገ ወጥ ተግባር በመኾኑ፣ ይህ ተግባር ዳግም እንዳይተገበር ጥብቅ መመሪያ ለሀገረ ስብከቱ እንዲሰጥ ኾኖ፣ ጥንታዊነት ያላቸው ጽላቶች ከተቀየሩ በኋላ ለውጡ በተደረገበት ደብር እንዲቀመጡ፣ ለሚመለከተው ኹሉ ሀገረ ስብከቱ ሰርኩላር እንዲበትን ትእዛዝ እንዲሰጠው ቢደረግ፣ የሚሉ ናቸው።

የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤም፣ በአጣሪ ልኡኩ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ተወያይቶ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንና ትእዛዞችን ለሀገረ ስብከቱ አስተላልፏል። ታቦት የሚያስፈልጋቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጥያቄን ሀገረ ስብከቱ በማዕከል ማስተናገድ እንደሚገባው፣ በውሳኔው አዘክሯል። ይኸው ማዕከላዊ አሠራር አለመኖሩ፣ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ ታቦታትን በቀላሉ ለመለወጥ መንገድ እንደሚፈጥር የማጣራቱ ሒደት ማስገንዘቡን ጠቅሷል። ከዐዲስ አበባ በመንደር ካሉ ነጋዴዎች ይመጣሉ ያላቸው ‘ጽላት’፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቁ፣ የመለወጡ ሒደትም ሕገ ወጥ ተግባር መኾኑን አስገንዝቧል። ይህን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሀገረ ስብከቱ ተከታትሎ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወስድ አዞታል፤ ውሳኔውንም ለመንግሥታዊ የወረዳ አመራሮችም በሰርኩላር ደብዳቤ አሳውቆ አፈጻጸሙን እንዲገልጽለት አሳስቦታል።

የዞኑ መስተዳድር ቅርስን ለማስመለስና ዘራፊዎችን ለመያዝ የሚያደርገው ጥረት እንደሚያስመሰግነው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገልጾ፤ በቅርስ ዘረፋ ወንጀል ተከሠው በሕግ የተፈረደባቸው አንዳንድ ዘራፊዎች፣ የቅጣት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ከእስር እየተለቀቁ ነው፤ ተብሎ በማጣራቱ ሒደት የተሰጠው አስተያየት፣ “አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ኾኖ ተገኝቷል፤” ብሏል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ የተካሔደውና ሰሞኑን ውሳኔ የተላለፈበት ይኸው የማጣራት ሒደት፥ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፤ የወረዳ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፊዎች፤ የዞኑና የከተማው አስተዳደርና የጸጥታ ሓላፊዎች በጋራ የተሳተፉበት እንደኾነ በሪፖርቱ ተገልጿል። የማጣራቱን ሒደት ለመቋጨት ተካሒዶ በነበረው የጋራ መድረክ ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ከሙሰኝነትና ቤተሰባዊ ትስስር ጋራ ተያይዘው የተነሡ ውዝግቦች ለመንግሥትም አሳሳቢ እንደኾኑና ሀገረ ስብከቱ ራሱን መፈተሸ እንደሚገባው አስተያየት ሰጥተዋል።

በሀገረ ስብከቱ በየጊዜው እየተከሠተ የሚገኘውን ችግር ለመፍታት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ልኡካን በተደጋጋሚ ሲመላለሱ መታዘባቸውንና ይህም ሀገረ ስብከቱ የሚሰማበትን ቅሬታ ለመፍታት ባለመቻሉ እንደኾነ ተናግረዋል። “ችግሩ ያለው በቤተ እምነቱ አመራሮች ውስጥ ነው፤” ያሉት አቶ ግርማ፣ የሀገረ ስብከቱን የችግር ፈጣሪዎች አሰላለፍ በሦስት በመመደብ የመንግሥትን አረዳድ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡-

አንደኛው ቡድን፥ ውስብስብ ኔትወርክ ዘርግቶ በከፍተኛ ምዝበራ ላይ የተሰማራና ሌሎችን የሚያጠፋ አደገኛ አካሔድ ያለው ነው። ኹለተኛው አካል፣ ቀደም ሲል ጥቅም ቀምሶ አኹን ግን ጥቅሙ ሲቀርበት ሀገረ ስብከቱን እየናጠ የሚገኝ ነው። ሦስተኛው አካል ደግሞ፣ በኹለቱ ዝሆኖች ፍትጊያ ራሱን ደብቆ አሸናፊውን አካል የሚጠባበቅ በፍርሃት የሚገኝ አካል ነው።

የዞኑ አስተዳዳሪ አያይዘውም፣ የተጠቀሱት ኹለቱ አካላት፣ ማለትም አንደኛውና ኹለተኛው በየደረጃው ማስተካከያ የማይደረግባቸው ከኾኑ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ እንደማይችሉና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ችግሩን ተረድቶ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ በመንግሥት ዘንድ አቋም መያዙን ጠቁመዋል። አካላቱ ስለሚያደርጉት የማያባራ ሽኩቻና ሽሚያም አስተዳዳሪው ተከታዩን ትንታኔ ሰጥተዋል፡-

እኒኽ ኹለት ቡድኖች ትምህርተ ወንጌል ለምን አልተስፋፋም፤ ለምን አልተጠናከረም ብለው አይጣሉም፤ አብያተ ክርስቲያናት ሲዘጉ ለምን ተዘጉ ብለው አይጣሉም፤ የአብያተ ክርስቲያናት መፍረስና የቅርስ ዘረፋው አያጣላቸውም፤ የልማት ሥራ ቆሞ ቢያዩት ለምን ብለው አይጠይቁም፤ አላግባብ የግል ተጠቃሚ ለመኾን የሚደረግ እሽቅድምድም ነው የሚያጣላቸው፤ ይህንንም ዞናችን በሚገባ ያውቀዋል።

የሥልጣን ሽሚያ፣ ሌላው የሚያጣላቸው ትልቁ ነጥብ ነው። ለዚኽም መነሻ አላቸው፤ አንዱ ከመሀላቸው በድንገት ባለሀብት ኾኖ ሲያዩት፣ ሀብቱ የተገኘበትን ስልት ስለሚያውቁት በቅናት መንፈስ ተነሣስተው ይጣላሉ። ባለሀብት የኾነው አካል በራሱ ላብ ቢኾን፣ ዞናችን ደስተኛ በኾነ ነበር። በድንገት ባለሀብት መኾን ግን እንድናስብ ያደርገናል።

የቅርስ ዘረፋውና ቅሠጣው ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ የኾነበት አንዱ ምክንያት፣ ለግላዊና ቡድናዊ ጥቅም የሚካሔደው የጥቅመኞች ሽኩቻና ሽሚያ እንደኾነ በዚኽ መልክ ያስረዱት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ፣ የቤተሰብ ትስስርና የዘመድ አዝማድ አሠራር አለ፣ የለም ለሚለው ሀገረ ስብከቱ ራሱን እንዲፈትሽ፤ የሚያገኘው ከፍተኛ ገቢና ወጪም በኦዲት ተጣርቶ ውጤቱ ሊታወቅ እንደሚገባ መክረዋል።

ዞኑን ለቱሪዝም እንቅስቃሴ አመቺ ለማድረግ አስተዳደሩ ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ እንዳለ አክለው የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚስችሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት እንዳሉትና የጋራ ተጠቃሚዎች ለመኾን ጥረት እንዲደረግ መልእክት አስተላልፈዋል። “ከደብረ ሲና ተራራ እስከ እመ ምሕረት አንኮበር ተራራ ድረስ የአየር ላይ የኬብል ማጓጓዣ ለማሠራት ውጭ ሀገር ድረስ እየተጻጻፍን እንገኛለን፤” በማለት አስታውቀው፣ ሀገረ ስብከቱም የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።