ለውጥ ያረገዙ መልካም አጋጣሚዎች፣ የአዋላጅ ያለህ እያሉ ነው!

Print Friendly, PDF & Email

 

ለውጥ ያረገዙ መልካም አጋጣሚዎች፣ የአዋላጅ ያለህ እያሉ ነው!

ነሃሴ ፪ ቀን ፪ሺ፱ ዓ.ም ቅጽ ፩ ቁጥር ፭

በየትኛውም መልኩ በሕዝብ ላይ የተጫነን አምባገነንና ዘረኛ አገዛዝ ለመጣል፣ ለውጥን አስፈላጊ የሚያደርጉ አጋጣሚዎች አሉ። ካሉት የለውጥ አዋላጅ መልካም አጋጣሚዎች ውስጥ የአገዛዙ የኢኮኖሚ ሥርዓት መናጋት አንዱና መሠረታዊው ነው። የአንድ  አምባገነን ሥርዓት የኢኮኖሚ መሠረቱ ሲናጋ የሚከተሉት ሁኔታዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ጎልተው ይታያሉ። የሥራ አጡ ሕዝብ ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ይጨምራል። የኑሮ ውድነት ከሚጠበቀው በላይ ይንራል። የገንዘብ የመግዛት አቅም ይቀንሳል። የማኅበራዊ ሰላም  ይናጋል። ሕጋዊ ሥርዓቱ ቦታውን ለሕግ-አልባው ይለቃል። መተማመን በጥርጣሬ ይዋጣል። ሕይዎት ዋጋ ያጣል። የአምባገነኑና የዘረኛው  የአፈና የመንግሥታዊ ተቋሞችና ቢሮክራሲ እንደ ጥንቱ የአፈናና የዕመቃ ተግባራቸውን ለማከናወን አቅም ብቻ ሳይሆን ፣ ወኔና የማድረግ ፍላጎቱ ይከዳቸዋል። በነዚህም ምክንያቶች የአገዛዙ ቁንጮዎች በመካከላቸው መተማመን ያቅታቸዋል። ለሚከሰቱ ችግሮች አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን ይቀስራል። በዚህም ትልቁ ዓሣ ትንሹን እንደሚውጠው፣ እርስ በራሳቸው ይዋዋጣሉ። የአገዛዛቸው ዕድሜ እያጠረ መምጣቱንም ስለሚገነዘቡ ኅሊናቸው ውጭ ያማትራል። በዚህም ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ወደውጭ ይልካሉ። ገንዘባቸውን ያሸሻሉ። ተፈርተው ይከበሩ የነበሩት፣ ክብራቸውን ያጣሉ። ሲያልፉና ሲያገድሙ ይሽቆጠቆጥላቸው የነበረው ሕዝብ ይንቃቸዋል፣ ያዋርዳቸዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖር አልፈው ሞልተው እየፈሰሱ ነው። የትግሬ ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ የኢኮኖሚ መሠረቱ ተናግቷል። የሥራ አጡ ቁጥር አገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ከመሆኑ የተነሳ፣ ወላጆች ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ልጆቻቸውን ለመጦር ተገደዋል። የኑሮውን ውድነት መግለጫ ቃል የለውም። የአንድ ኪሎ ሽንኩርት፣ የአንድ ሊትር ዘይትና የኪሎ ጨው ዋጋ በወያኔ መግቢያ፣ በደርግ የመጨረሻ ዓመት አንድ ትልቅ  የበግ ሙክት፣ ወይም አንድ ኩንታል የአዳ ማኛ ጤፍ ይገዛበት ከነበረው በላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ የወያኔው መቶ ብር፣ የደርግ ዘመኑን ሦስት ብር አይሆንም። በአገሪቱ ገበያ ከሃምሳና ከመቶ ብር በታች ባሉት ቁጥሮች መገበያየት ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በገበያው ዝውውር ውስጥ የቅንስናሽ ገንዘቦች ከአምስት ብር በታች ያሉት፣ ከገበያ በመውጥት ላይ ናቸው። ወያኔ ሲጀመር ጀምሮ ሕግና ሕጋዊነትን የማያውቅ ወንበዴ መሆኑ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ሕግ ብሎ ነገር የለም። በሕዝቡ መካከል ፣ከሁሉም በላይ ወያኔ ሆን ብሎ በዘራው የዘር ፖለቲካ ምክንያት፣ጥንት የነበረው የእርስ በርስ መተማመን አለ ከሚባልበት ደረጃ ላይ አይደለም። ከሁሉም በላይ ከወያኔ ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ  ሰዎችን ማመን ቀርቶ ሊያያቸው አይፈልግም። ይህ ሁሉ ተዳምሮ ሕዝባችን ለሕይዎት፣ ለሃይማኖት፣ ለእሳና ለይሉኝታ ይሰጣቸው የነበሩትን ዕሴቶች እያሟጠጣቸው በመምጣቱ፣ ለሰው ልጅ ሕይዎት ይሰጠው የነበረው ዋጋ እጅግ አቆልቋሏል። እምነት ለክህደት፣ ታማኝነት ለቅጥፈት፣ ዕውነት ለውሸት፣ ፍቅር ለጥላቻ፣ መከባበር ለመናናቅ፣ መተባበር ለመነጣጠል ወዘተ ቦታቸውን እየለቀቁ ነው።

ይህ በኢኮኖሚ ሥርዓቱ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ፣ የአገዛዙ ቢሮ-ክራሲና አፋኝ ተቋሞች እንደ አምና ታቻምናው ሕዝቡን አንቀጥቅጠውና አስፈራርተው የፈለጉትን ለማድረግ አልቻሉም። እንደጥንቱ ለማድረግም ወኔውና ፍላጎቱ ከድቷቸዋል። ሕዝቡም እንደድሮው ለመገዛት ፈጽሞ ፈቃደኛ አልሆነም።  ይህም በመሆኑ የአገዛዙ ቁንጮዎች ለተፈጠሩት ችግሮች አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን በመቀሰር የነበራቸውን አንድነት አጥተው፣ ለጊዜው ጠንካራ የሚመስለው ደካማውን እየበላ ነው። ሰሞኑን በሙስና ስም ዘብጥያ የወረዱ የወያኔ ባለሥልጣኖችና አጋሮች የዚህ ድርጊት ውጤቶች ናቸው። ነባር የሥርዓቱ አገልጋዮች ይዘውት ከነበረው ቁልፍ መንግሥታዊ የሥልጣን ቦታዎች ተነስተው አምባሳደር እንዲሆኑ ተሰጠ የተባለው ሹመት ያለመተማመኑ ሌላው ማሳያ ነው። በነጋዴው ላይ የተጣለው ግብር ምክንያቱ ወያኔ ለወታደሩና ለድኅንነት ሠራተኛው የሚከፍለው ገንዘብ በማጣቱና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ወደ ገበያ ያስገቡት ገንዘብ፣ የብሩን የመግዝት አቅም በማሳጣቱ የተነሳ ለእነዚህ ችግሮች ማቃለያ ይሆናል ተብሎ የተጣለ ግብር ነው። ይህም በራሱ ኢኮኖሚው ቀውስ ውስጥ የገባ መሆኑን አመላካች ከመሆኑም በላይ፣የገጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍ፣ አገዛዙ ችግርን በችግር ለማስወገድ የወሰደው የመጨነቅ ውጤት መሆኑን ያሳያል።

የወያኔ ቁልፍ ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ልዩ ጥቅም ማስገኛነት አዋጅ አንድ አቋም አለመያዝ፣ በወልቃይት ጉዳይ የትግሬ ሕዝብና የወያኔ ራስ ነን የሚሉት ተመሳሳይ አቋም አለመያዝ፣ የአገዛዙ ከሥሩ የመበስበሱ ማሳያዎች ናቸው። ይህ ሁሉ ተዳምሮ የአገዛዙ ቁንጮዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንዳለፉት 26 ዓመታት ሊቆዩ የማይችሉ መሆኑን በመገንዘባቸው ገንዘባቸውን፣ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን አስወጥተው የራሳቸውን መውጫ ቀዳዳ በማመቻቸት  ላይ እንዳሉ ሁኔታዎች ያስረዳሉ።

የእነዚህ ሁኔታዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ መከሰት፣ ሕዝቡን ያላንዳች አደራጅና መሪ የለውጥን አስፈላጊነት እንዲዘምር እያደረገው ነው። የከያኒዎቻችን ዜማዎች፣ «የእንከባበር»፣«ሂሳብ አለብን»፣ የቴዲ አፍሮ፣ የፋሲል ደሞዝ፣ የመሃሪ ደገፋው፣ የየዝጉብኝ ምሽቶች፣ የመዝንኛና የሆቴል ቤቶች የግጥም ቃናዎች፣ ቀረርቶና ሺለላዎች የለውጥን አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን፣ ለውጥን ያረገዙ፣ አዋላጁን የሚጣሩ  ናቸው። ከወያኔ ጋር ላለፉት በርካታ ዓመታት ተሰልፈው የነበሩ ሰዎች አገዛዙን እየከዱ ከሕዝብ ጎን ነን ማለታቸው፣ የአገዛዙ ዕድሜ እያጠረ መምጣቱን ማሳያ መስተዋቶችና ለውጥ አዋላጅ ጀግና ጠሪ ደወሎች ናቸው።

ባለመታደል ወይም በሌላ ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ለለውጥ የሚያግዙ ነባራዊና ኅሊናዊ ሁኔታዎች ቀድመው አቅደውና ተዘጋጅተው የመጠባበቅ አቅም አልባ ከመሆናቸውም በላይ፣ በነባራዊ ሁኔታዎች ግፊ ዕውን የሆኑ ለውጥ አዋላጅ የሆኑ ሁኔታዎችን ቀድመው ተረድተው፣ ለውጡን ዕውን የማድረግ ብቃ የሌላቸውን መሆኑን ባለፉት 26 የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ያመለጡን አጋጣሚዎች ማሳያዎች ናቸው። ካመለጡን የለውጥ አዋላጅ ሁኔታዎች መካከል  ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግሥት በወያኔ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት፣ የ1997ቱ የቅንጅ እንቅስቃሴ፣ ከ2007 እስከ 2009 ዓም የቆየው በኦሮሞ እና በዐማራ ነገዶች የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተጋድሎዎች የሚጠቀሱ ናቸው።

ዛሬም በተመሳሳይ ሁኔታ ለውጥን ያረገዘው ሁኔታ በምጥ ላይ ነው። ከ2007 ዓም ጀምሮ በኦሮሞ እና በዐማራ ነገዶች ብሦት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውስጥ ውስጡን እየጋመ ያስነሳው ማኅበራዊ አመጽ ፣ ወያኔን አስቸኳይ ወታደራዊ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል። ለስድስት ወር ጊዜ እንደሚቆይ ያወጣው ወታደራዊ አዋጅ፣ በወታደራዊ የኃይል ዕመቃ ያመጣል የተባለውን አስፈራርቶና አስደንግጦ ሕዝብን ተገዥ የማድረግ ዓላማ በሕዝቡ እንቢተኝነት ማሳካት ባለመቻሉ፣ ይኸውና ወታደራዊ አገዛዙ ድፍን ኦንድ ዓመት ሞላው። ወታደራዊ አዋጁ፣ ለይስሙላም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ ሰጠሁ ያላቸውን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በገሐድ የነፈገ መሆኑ ማሳያ ሆኖ በመቅረቡ፣ በዲሞክራሲና ሽብርተኝነት ለመዋጋት በሚል ያልተቆጠበ የገንዘብና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ይሰጡት የነበሩትን ምዕራባዊ መንግሥታት ድጋፋቸውን ፈጽመው ባያቋርጡ እንኳን፤ እንዲጠይቁ እያደረጋቸው ይገኛል።  የአውሮፓ ኅብረት ለወያኔ ይሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ መቀነስ፣የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ፣ በኒውጀርሲው ተወካይ ክሪስ ስሚዝ አማካኝነት የቀረበውን በወያኔ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲደረጉ የሚጠይቀውን ኤች አር 128 የተሰኘውን ረቂቅ ሕግ፣ በነሐሴ ወር 2009 ሦስተኛ ሳምንት መግቢያ ላይ በኮሚቴው ደረጃ በሙሉ ድምፅ ማለፍ፣ ምዕራባውያን  ከወያኔ አገዛዝ ጋር ገምደውት የነበረውን ግንኙነት እየተረተሩት መምጣቱንና አማራጭ ኃይል በማፈላለግ ላይ እንደሆኑ ያሳያል። ይህም ወያኔ ከኢኮኖሚው በተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊና የአጋር ቀውስ ውስጥ መግባቱን ያመለክታል። ይህም በምጥ ላይ ያለውን ማኅበራዊ አብዮት የሚገላግል ሐኪም እየፈለገ እንደሆነ ያሳይል።

በሌላ በኩል ዛሬ በአገራችን ውስጥ፣ የለውጥ አዋላጆች ነን የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው። ከ180 በላይ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች እንዳሉ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ ግን ከላይ የተጠቀሱትን መልካም አጋጣሚ ለውጥን ያረገዙና በምጥ ላይ ያሉ ሁኔታዎችን ተጠቅመው፣ ለውጡን ማዋለድ የቻሉ አይደሉም። ይህም የሚያመለክተው አገራችን የማኅበራዊ ለውጥ አዋላጅ የሆነ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ቅቡልና አዎናታዊ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ፖለቲካዊ ኃይል ያለመኖሩ መገለጫ ነው። ለማኅበራዊ ለውጥ ዕውን መሆን፣ የነባራዊ ሁኔታዎች መሟላት አስፈላጊነት ወሣኝ ቢሆንም፣ በራሱ ግን  ተፈላጊውን ለውጥ የማያስገኝ፣ በአንፃሩ ለጨቋኙ አገዛዝ የበለጠ መጠናከርና የአፈና መዋቅሩን ውስብስብ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው። ወያኔ ከክፍፍሉ በኋላ እና ከቅንጅት ውድቀት ቀጥሎ የነበረውን ለውጥ ያረገዘ ነባራዊ ሁኔታ፣ በጠንካራ ተቃዋሚ አለመኖር የተነሳ፣ የአፈና መዋቅሩንና አሠራሩን እንዲያጠናክርና እንዲያወሳስብ ዕድል ሰጥቶላል።

በሰሞኑም በኦሮሚያና በዐማራ ክልሎች በሚባሉት ጠቅላይ ግዛቶች ነዋሪ በሆነው ሕዝብ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ቁጣ፣ በነጋዴው ማኅበረሰብ በተጫነው የግብር ናዳ ምክንያት  በመላ አገሪቱ የተጀመረው ሥራ ማቆም አድማና ፈቃድ የመመለስ ጅምር፣ የነዳጅ ዋጋ መወደድ፣ የኑሮ ውድነት ሕዝቡ ከሚሸከመው በላይ መሆን፣ ማኅበራዊ ሰላምና መረጋጋት መጥፋት፣ ሙስናና አድልዎ ሕጋዊ በሚመስል ሁኔታ መንሰራፋት ወዘተ የማኅበራዊ ለውጥ ጥሪዎች ናቸው። ይህ ጥሪ የተቃዋሚ ኃይሉን ጎራ ጆሮ ሊያዳምጠውና ለጥሪው ሁነኛ መልስ ሊሰጠው ይገባል። የዚህ ጥሪ መልስ አዳዲስ ድርጅቶችን «ሰርገኛው መጣ በርበሬ ቀንጥሱ » ዓይነት በሆነ ሁኔታ መቀፍቀፍ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል የተደራጁትን  ድርጅቶች ዓላማቸው፣ ራዕያቸው፣ ተልዕኮዋቸውና ግባቸው ተቀራራቢ የሆኑትን ከተቻለ በአንድነት፣ ካልተቻለ፣ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ያረገዘውን የማኅበራዊና የሥርዓት ለውጥ ሊዋለድ የሚችለው ምን ምን ሥራዎች ቢሠሩ እንደሆነ በመለየት፤ በነዚያ ላይ የሰው ኃይልን፣ ገንዘብን፣ መረጃን ፣ ጊዜንና ዕውቀትን አቀነባብሮ ሁለንተናዊ ኃይል በመፍጠር ወያኔ የቆመበትን መሠረት ለመናድ፣ የተደገፈውን ምሰሶ ለመግፋት የሚያስችል ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የዐማራውን ኅልውና መጠበቅ አለበት ብለው ከሚያምኑና ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ፣ ለብሔራዊ ጥቅሟ መረጋገጥ፣ ለሕዝቡ ሉዓላዊነት፣ ለግለሰብ ነፃነት፣ ለሰዎች ዕኩለትና ለዲሞክራዊ ሥርዓት ግንባታ ከቆሙ ኃይሎች ጋር ያለውን የሰው ኃይል፣ የገንዘብና ሌሎች ሀብቶች አሟጦ፣ሕዝባችን የሚናፍቀውን ማኅበራዊና የሥርዓት ለውጥ ለማዋለድ ዝግጁ ነው።

የዐማራ ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!

Email-Aseuoipr@gmail.com