የአማራ ተጋድሎ ለኢትዮጵ አንድነት የገጠሙት የትግል ፈተናዎች!

Print Friendly, PDF & Email

(ከተስፋዬ መኮንን)

ዛሬ የአማራ ተጋድሎን እድገት ከሶስት አንጻር የሚፈታተኑት ክስተቶችን ማየት ይቻላል።

አማራ በቅድሚያ እራሱን ለማዳን ብሎም ኢትዮጵያን ለመታደግ ከትግሬ ነጻ አውጪ የሚሰነዘርበትን የዘር ማጥፋት ዘመቻን መክቶ በአሸናፊነት ለመወጣት ውስብስብ ትግል ውስጥ ገብቷል። ከዚህ ውስብስብ ትግል ድላማ ሁኖ መውጣት ማለት ኢትዮጵያዊነትን ያካተተ ትግልን ማራመድን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። በመሆኑም ይህ ትግል ድላማ ሁኖ ይወጣ ዘንድ ብቻውን በአማራነት ብቻ ተነጥሎ ድላማ ሊሆን እንደማይችል መቀበል ግዴታ ይሆናል። ይህንን የትግሉን የሁለትዮሽ ባህሪ እውነትነት ጠላትም በሚገባ ተቀብሎታል። የዚህ የአማራ ህልውና ከኢትዮጵያ አንድነት መረጋገጥ ጋር እንዳይላቀቅ ሁኖ አብሮ በታሪክ የተገመደ መሆን የቆረጡ ጠላቶች የሆኑትን ህወሀትን፣ ሸአብያንና ኦነግን አሰልፎበታል።

እነዚህ የርእዮት መሰረታቸውን ኢትዮጵያን እንደታሪካዊ ሀገር በመጥላት ላይ የገነቡና ግንባር የፈጠሩ የጥፋት ሀይሎች ምንጊዜም ቢሆን አማራን የሴራቸው ማርከሻ ደመኛ ጠላታቸው አድርገው ከመውሰድ አይመለሱም። አማራንም ሳያጠፉ ኢትዮጵያን ማጥፋት እንደማይችሉ በሚገባ የጨበጡት እውነት ነው። አማራም እነዚህን ሀይሎች ሳያጠፋ ህልውናውንም ላያራጋግጥ፣ የሱነቱ መግለጫ አድርጎ የሚመለከታትን ኢትዮጵያንም ከወደቀችበት ላያነሳ ነውና በሁለቱ መሀል የሚደረገው ትግል ውስብስብና ረጅም መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህ በግልጽ አማራን ለማጥፋት ፕሮግራም ነድፎ፣ ለሚደግፈው ነገዱ የጥላቻ ርእዮት አስጨብጦ፣ ጦሩን አሰማርቶ ፍጂት በመፈጸም ላይ የሚገኝ ሰፊ የጠላት ግንባር ነው። የአማራው ዋና የትግል ትኩረቱ በነዚህ ሀይሎች ላይ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ድልና ሽንፈቱም የሚወሰነው በነዚህ መሀል ይሆናል።

ሌላው የአማራ ተጋድሎን የገጠመው ተጻራሪ ሀይል በሰፊው የወገን ሀይል ውስጥ የተነሳው አድርባይ ፖለቲካ ነው። አድርባይ ፖለቲካ በገበሬ አዝመራ ውስጥ እህሉን ከሚያቀጭጭበት አረም ጋር የሚመሳሰል ነው። በእህሉ ውስጥ መስሎ ይበቅልና የእሸቱን ለምለም ንጥረ ነገሮች ስሩን ዘርግቶ እየበላበት እንዳያድግ አድርጎ በመጭረሻም አዝመራውን እንዳለ ያጠፋዋል። አድርባይ ፖለቲካም በአንድ አገር ውስጥ መስሎ አዳሪ ነው። ቁልጭ ያለና ግልጥ የፖለቲካ መስመር ነጥሮ እንዳይወጣ ከግራ ቀኙ እየተወራጨ የፖለቲካ መተራመስ ይፈጥራል። በመሸበት አዳሪ ነው። ከማይቧደነውና ከማይፋታው የለም። ዓላማው ፖለቲካውን የተጎለጎለ ልቃቂት ማድረግ ነው። በዚህ የጨለመና የተዘከዘከ የፖለቲካ ጉዞ የሚያተርፈው አድርባይ ፖለቲካ ነው። በዚህ ግርግር መሀል ባጋጣሚ ሊመጣ በሚችል የህበረተሰብ ተካፈት ተጠቅሞ ከፊቱ ከሚያገኘው ሀይል ጋር በመጣመር የስልጣን ሰገነት ላይ መፈናጠጥ የሚመኘውና የሚጠብቀው ጊዜ ነው። ይህ አድርባይ ሀይል የዚህ መሰሉ የስልጣን አጋጣሚዬ እንዳይመጣ የሚያደርጉ ሀይሎች ብሎ እንደጠላት የለያቸውን ሀይሎች ለማግለልና በጠላታቸው ለማስመታት ሌት ተቀን ይሰራል። ይህን ጎዳና የሚከትል አድርባይ ሀይል በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ላይ እንደ አዲስ ክስተት መነሳቱን ማንም ያውቀዋል። ስምን ተግባር ይገልጠዋልና ስሙን አላነሳም።

ይህ ሀይል ዛሬ ህወሀትን ቁርጥ በሚያስብል መልኩ የአማራን ተጋድሎ ቢችል ነጥሎ ለመምታት ባይችል ለወያኔ አቀብሎ ለማስመታት በመስራት ለይ ይገኛል። ቁርጥ እንደ ህወሀት የአማራውን ተጋድሎ ለብቻው ለማስቀረት ትግሉን ከሀገራዊ ወደ ክ/ሐገራዊ እንዲበታተንና ጎጥ ሰራሽ እንዲሆን ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። በዚህ ከህወሀት ጋር በግምባር በአንድ ላይ ሊያስቆም በሚያስችለው የጸረ የአማራ ተጋድሎ ውስጥ ይገኛል። ከዚህ የዓላማ አንድነት አኳያ ለአድርባይ ፖለቲካው ከህወሀት ጋር ግምባር ለመፍጠር እንቅፋቱ የህወሀት በልቶ አልጠግብ ባይነትና ለማካፈል ዝግጁ አለመሆን ብቻ ነው። የወደፊቱን እንጠብቅ። ይህም አይሆንም አይባልም። ለአማራው ተጋድሎና ለኢትዮጵ አንድነት እውን መሆን ስንል ባንድ በኩል ይህንን የህወሀትንና የአድርባይ ፖለቲካን በፊርማ ያልተገለጠ የአንድዮሽ የጋራ ትግላቸውን ለማክሸፍ መስራት፣ በሌላው በኩል ደግሞ በተግባር የአማራን ተጋድሎ ከኢትዮጵያ አንድነት ትግል ጋር በጥብቅ ለማሰር እንዲቻል ከመላው የአንድነት ሀይሎች ጋር የተባበረ የትግል መድረክ መፍጠር ለአማራው ተጋድሎ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ይሆናል። ይህ ከሁሉም የቋንቋ ማህበረሰብ ዘንድ የሚመጡትን የአንድነት ሀይሎችን ወደ ትግሉ እንዲገቡ ከማድረግ ትግላችን ጋር መቀናጀቱንም ማረጋገጥ ወሳኝ ይሆናል።

ለአማራው ተጋድሎ ሶስተኛውና ወሳኙ የትግል መስክ በራሱ በአማራው ወስጥ ያለ በሰላማዊ ትግል ልንፈታው የሚገባ መለስተኛ ልዩነት ነው። የአማራውን የተጋድሎ ፍልስፍናን አስመልክቶ ሶስት የሚታዩ መለስተኛና ተቻቻይ ልዩነቶች ይታያሉ። ዋናውና ወሳኙ አቋም በአማራ ተጋድሎ ዙሪያ የተሰለፈው ሰፊው የአማራ ህዝብና ከጎኑ ቁመው በፖለቲካ ተደራጅተው፣ ጠመንጃ አንስተው፣ በሰላማዊው ትግል ከጠላት ጋር እየተናነቁ በመታገል ላይ ያሉትን ያካትታል። ይህ ሰፊ የአማራ ህዝብ ተጋድሎ አማራን የመታደግንና ኢትዮጵያን አንድ የኮራች ሉዓላዊ ሀገር የማድረግ ግብን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ አድርጎ ተመልካች ወገን ነው።

ሌላው የወዳጅ ክፍል ይህንን የሁለትዮሽ የመሰለ የትግል ስልትን ያልተገነዘበው የአማራው ምሁር የተባለው የሚከተለው የቁሞ ተመልካችነት አባዜ ነው። ይህ ወገን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ነው። ይህ ሸጋ አቋምና የአማራ ተጋድሎ የሚፈልገውና እንዳይሸራረፍም አጥብቆ የሚታገልለት ነው። ይሁንና በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፣ የጎሳ ፖለቲካ ብቻ እንዲገን በተደረገበት፣ ኢትዮጵያዊነትን ማንሳት በሚያስቀጣበት፣ የአንድነት ጥያቄ በፈለገ የፖለቲካ ቅርጹ እንዲኖር በማይፈቀድብት የትግሬዎች አገዛዝ እንደ ቀድሞ በአንድነት ጥላ ስር የኢትዮጵያን ዳግም መነሳት እውን አደርጋለሁ ማለት ቅዠት ነው። ይህ የአንድነት ጠበቃ የሆነ ወንድማችን ከዚህ ቅዠቱ ነቅቶ የአማራውን ተጋድሎ በመቀላቀል የአንድነት ጸር የሆነ ህወሀትን ድባቅ በመምታት የፖለቲካ ህልሙን እውን እንዲያደርግ ማስተማር አስፈላጊ ይሆናል። ያለው ወደዚያ የሚወስደው መንገድ ይህ ብቻ መሆኑን ሳንታክት ልናሳየው እንፈልጋለን። ስለዚህም ሳትዘገይ ከአማራ ወገንህ የተጋድሎ ትግል ጋር ተቀላቀል። እንዲህ በማድረግም ወገንህንም፣ ሀገርህንና እራስህንም ነጻ አውጣ።

በመጨረሻ የምመለከተው ከአማራው ወጣት ውስጥ የማይናቅ ቁጥር ያለው ክፍል የሚከተለው የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ ነው። ዛሬ በጊዜ ካልታረመ ነገ ይዘገያል። ይህ የወጣት ክፍል በህወሀት የጭካኔ አገዛዝ ውስጥ ተወልዶ ያደገውንና ከልጅነት ጀምሮ በውስጡ ያደገውን ይጠቀልላል። በዘመዶቻቸው ላይ የደረሰውን ጭካኔ ተመልክተዋል። በነርሱም ላይ ብዙ ግፍ ተስተናግዷል። ይህ ሁሉ መዋረድ፣ መገፋት፣ መገደልና መሰደድ የሚፈጥረውን ንድመት ባይኑ ያየውና የከፈለው ብቻ ነው የሚያውቀው። በዚህ ግፊትና ከፖለቲካ ንቃት ጉድለት ምክንያት የአማራ አክራሪነት ዝንባሌ እስረኛ የመሆን አደጋ ውስጥ መውደቁ እየታየ ነው። እነዚህ ወገኖች እውነተኛ የአማራ ህዝብ ደህንነት የሚጠበቀውና ለእድገት የሚበቃው ከኢትዮጵያ ተለይቶ ለራሱ ለአማራው ብቻ የሚሆን ግዛት ባለቤት መሆን ሲችል ነው ብለው ያምናሉ። በተሳሳተ መንገድና የህወሀትን የተጋነነ የጸረ አማራ ድራማን ሁሉም ህዝብ የሚጋራው አድርጎ በመውሰድ ከኢትዮጵያ የመሸሽ የስሜት ግፊት ከፍተኛ አሉታዊ ሚና እንደተጫወተ ይታያል። ይህ ሊያሰፉለት የሚመኙት ጥብቆ ለታላቁ የአማራ ህዝብ የሚሆነው ልብስ አይደለም።

የአማራ ህዝብ ሰፊ ነው። በቁጥር አንገልጠውም። በሀገሪቱ ውስጥ የተዘራ ህዝብ ነው። የተዋለደ ነው። ውልደቱ በስጋ ብቻ አይደለም። በመንፈስም ኢትዮጵያን የያዘ ህዝብ ነው። ዛሬ በሀገሪቱ ውስጥ ወያኔና ኦነግ የዘሩት የጥላቻ ዘር ከላይኛው ቆዳ ዘልቆ የገባ አይደለም። ተማረ በተባለው ክፍል ውስጥ ሁነው ድምጻቸውን ለማሰማት በመቻላቸው ከሚጮሁት ዘረኛ ምሁራን ዘልቆ በህብረተሰቡ ውስጥ የገባ መልእክት አይደለም። በመሆኑም የአማራ ህዝብ ከሌሎች የቋንቋ ማህበረሰብ ወንድሞቹ ጋር እጅ ለጅ ተያይዞ ገና ያላለቅ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ የጋራ ትልእኮ እንዳለው ለነዚህ ወገኖቻችን ማስረዳት ይገባል። አማራ እንደ ህዝብ ጸንቶ የሚኖረው ከኢትዮጵያ በመሸሽ ሳይሆን የተለመደውን ታሪካዊ ድርሻውን ማበርከት ሲችል ይሆናል። ይህንን የአማራ ወጣት ካልጨበጠ ከፍተኛ የሆነ ታሪካዊ ወንጀል
በራሱ ህዝብ ላይ መፈጸሙ መሆኑን በግልጥ መንገር ይገባል።

የአማራ የህልውና ተጋድሎ ለኢትዮጵያ እንድነት ዋስትና ነው!!!