በኮሎኔል ደመቀ ላይ በሕይወት የሌሉ ሰዎች ለምስክረነት ተጠሩ

Print Friendly, PDF & Email

(ሙሉቀን ተስፋው)

በኮሎኔል ደመቀ ላይ በሕይወት የሌሉ ሰዎች ምስክረነት ተጠርተዋል፤ በምስክርነት ይቀርባሉ ከተባሉ ሰዎች መካከል እስካሁን ማቅረብ የተቻለው 13 ሰዎችን ብቻ ነው።

ትናንት ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓም በዐማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጎንደር ቋሚ ምድብ ችሎት የፌደራል ፍርድ ቤትን ወክሎ በዋለው ችሎት በቀጣዩ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ከታዘዘው ከ18ቱ ምስክሮች መቅረብ የቻሉት ሁለት ብቻ ናቸው። ባለፈው ወር በሰኔ 27 እና 29 ቀን በዋለው ችሎት በኮሎኔል ደመቀ ላይ እንዲመሰክሩ ከተጠሩት 11ን ሰዎች ጨምሮ መቅረብ የቻሉት 13 ሰዎች ብቻ ናቸው። ችሎቱ ቀሪዎቹን 14 ምስክሮች ነገ እንዲቀርቡ አዟል።

ኮሎኔል ደመቀ

የኮሎኔል ደመቀን የፍርድ ሒደት እየተከታተሉ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በኮሎኔል ላይ ይመሰክራሉ ተብለው ከታሰቡት ሰዎች መካከል ሁለቱ በሕይወት የሌሉ እንደሆነም ተናግረዋል። እስካሁን በነበረው ሒደት የቀረቡት ምስክሮች በኮሎኔሉ ላይ አሳማኝ ቃል መስጠት እንዳልቻሉም ተገልጧል።

የወልቃይት ዐማራ ማንነት ኮሚቴ ውስጥ ነበርኩበት ያለው አንድ ምስክር ‹‹ኮሎኔል ደመቀ የማንነት ጥያቄያችን እንዲመለስ ተወላጆችን እያሰባሰበ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ንግግር ይነግረን ነበር፣ ይህን በተደጋጋሚ አድርጓል›› የሚል ምስክርነት ሰጥቷል። እስካሁን ከተሰጡት ምስክሮች በኮሎኔል ላይ መስክሯል የተባለው ይኼው ምስክር ሲሆን የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ኮሎኔል ደመቀ ማድረግ የሚገባውን እንዳደረገና መብቱንም የተጠቀመ በመሆኑ ወንጀል ሊሆን የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

በ1966 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጸደቀው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት ኮሎኔል ደመቀ ጥያቄያቸው እንዲመለስ ሕዝብን ማደራጀትና መቀስቀስ መብታቸው መሆኑንና ይህም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የአገሪቱ ሕግ መሆኑንም ነው የተናገሩት ባለሙያዎቹ።

ኮሎኔል ደመቀ በሽብር ወንጀል ሰው ገድለዋል ተብሎ በቀረበባቸው ክስ በአገዛዙ ሰልጥነው የመጡት ምስክሮች እርስ በእርሱ የሚቃረን ቃል እንደሰጡም ተገልጧል።

በኮሎኔል ተገድለዋል ተብለው ከቀረቡት ሰዎች መካከል የትግሬውን አፋኝ ቡድን መሪ የነበረው ኮሎኔል ሐለፎም አንዱ ሲሆን አንደኛው ምስክር እንዳለው ኮሎኔሉ የተገደለው በሕዝብ መሆኑን ገልጧል። ምስክሩን የሰጠው ግለሰብ ኮሎኔል ሐለፎም የመከላከያ ልብሱን ለብሶ ከኮሎኔል ጋር ሲታኮስ ከቆየ በኋላ ሕዝብ ሲመጣ ሂዶ የሲቪል ልብስ ለብሶ ተመልሶ ሆኖም ግን አስቀድመው ያወቁት ሰዎች እንደገደሉት ተናግሯል።

ከኮሎኔል ሐለፎም ጋር አብሮ የመጣው ኮሎኔል ግደይ የጎንደሩ ጭፍጨፋ ካለቀ በኋላ ወደ ሽሬና አድዋ አስተባባሪ ተደርጎ መቀየሩም በዚሁ ችሎት በምስክሮች ተገልጧል።

እስካሁን ድረስ የምስክሮች ማንነት ለኮሎኔል ደመቀ ጠበቃም ሆነ ለተከሳሽ ያልተገለጹ ከመሆናቸውም ውጭ ተሸፋፍነው በመግባት ተሸፋፍነው እንደሚወጡም ታውቋል። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ውስጥ ማንኛውም ታዛቢም ሆነ ጠበቃዎች እንዳይገቡ ተደርገው ፍርድ ቤቱ በታጠቁ ወታሮች ታጥሮ የፍርድ ሒደቱ እየታየ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያዎች የተካሳሽ ሕገ መንግሥታዊ መበት የሚጋፋ መሆኑንም ጭምር ገልጠዋል።

የኮሎኔሉን የክስ ሒደት እተከታተሉ ያሉት ዳኞች በየጊዘው የሚቀያየሩ ሲሆን ከሁለት ጊዜ ባለይ ያየው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቴ የኔነህ ስመኝ ሕዝቡን ጥርጣሬ ውስጥ ጨምሮታል። አቶ የኔነህ በኃላፊነት ከተመደበ በኋላ የማንንም ክስ አይቶ እንደማያውቅ የሚናገሩት ምንጮች የኮሎኔሉን መዝገብ መያዛቸው ነው ጥርጣሬን የፈጠረው። ከዚህ ቀደም የኮሎኔሉን ክስ ይዘውት የነበሩት አቶ ሞገስ ቢተው ከቦታቸው የተነሱ ሲሆን አቶ ቢኒያም ዮሐንስ የተባሉ ዳኛ ደግሞ መታሰራቸው አይዘነጋም።

አሁን ላይ የኮሎኔሉን የክስ መዝገብ ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ አቶ ምስጋናው አበበ የተባሉ ዳኛ የያዙት ሲሆን ለሕሊናቸው እንዲያድሩ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዳዲስ ዳኞችን እየቀጠረ ሲሆን የኮሎኔልን መዝገብ ውሳኔ እንዲሰጡ አዲስ ከሚቀጠሩ ዳኞችም ሊመደብ እንደሚችል አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡት ቀሪዎቹ የወልቃይት የዐማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ከሳሽ አቃቢ ሕጉ ‹‹የሽብር ቡድኑ መሪ ከሆኑው ኮሎኔል ደመቀ ጋር›› እያለ በማቅረቡ ከጠበቃዎች በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል። ወንጀለኛነቱ በሕግ ያልተረጋገጠን ሰው መፈረጅ ከሕግ ውጭ መሆኑን በመጥቀስ።