ጣና ሐይቅን መታደግ ዐባይ እንደወንዝ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ተጠቃሚ አገሮች ኃላፊነት ጭምር ነው! – የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

Print Friendly, PDF & Email

ጣና ሐይቅን መታደግ ዐባይ እንደወንዝ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ተጠቃሚ አገሮች ኃላፊነት ጭምር ነው!

ቅፅ 1፣ ቁጥር 6
ሀምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም.

ጣና በአስደንጋጭ ሁኔታ ከመኖር ወደ አለመኖር በመሸጋገር ላይ ስላለ፣ ትውልዱ፣ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነው የኅብረተሰባችን ክፍል በሐይቁ ላይ የተከሰተውን ችግር ተገንዝቦ አፋጣኝ የመፍትሔ ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።

ጣና ታላቁ የአባይ ወንዝ በሚያስደንቅ ሁኔታ በላዩ ላይ አቋርጦ የሚያልፍበትና በኢትዮጵያ ከሚገኙት ሐይቆች ታላቁ ሐይቅ ነው። ስፋቱ 1,418 ስኳየር ማይል ወይም 3,673 ስኳየር ኪሎሜትር ነው። የሐይቁ ዙሪያ ርዝመት 4,500 ስኳየር ማይል ወይም 11,650 ስኳየር ኪሎሜትር ነው። የሐይቁ ከፍተኛው ጥልቀት 45 ጫማ ወይም 14 ሜትር ነው። ይህ ሁሉ ግን የነበረ እንጅ ዛሬ ነገሮች ሁላ ተለዋውጠዋል። ጣና ስፋቱም፣ ቁመቱም፣ ጥልቀቱም በነበሩት መልክ የሉም። ሐይቁ ቋሚና የክረምት ወቅትን ጠብቀው ወደሐይቁ የሚገቡ ወደ 60 የሚጠጉ ገባር ወንዞች አሉት። ይህ የተፈጥሮ ውብ ፀጋ የሆነ ሐይቅ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የጎንደርና የጎጃም ክፍላተሀገራትን የሚያዋስን ሐይቅ ነው። ጣና ከጎንደር በደንቢያ፣ አለፋ ጣቁሣ፣ ከምከም፣ ፎገራ እና ደራ ወረዳዎች ወይም በጎንደር ዙሪያ፣ ጭልጋ፣ ሊቦና ደብረታቦር አውራጃዎች፣ ከጎጃም በባህርዳር አውራጃ የተከበበ ነው። በሐይቁ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት መስብህ የሆኑ ጥንታዊ ገዳሞች የሚገኙበት በርካታ ደሴቶችን ያቀፈ ነው። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቡሾችና በቱርኮች በተወረረች ጊዜ የአገሪቱ ጠቃሚና ተነቀሳቃሽ ቅርሶች ከጥፋት የዳኑት በጣና ሐይቅ በሚገኙት ደሴቶች ውስጥ በመደበቅ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ጣና ለኢትዮጵያ፣ በውኃ ሀብትነቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሐይቁ ውስጥ በሚኖሩ ቀረሶ ወይም የፃድቁ ዮሐንስ ዓሣዎች የተባሉ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ዓሣዎች (endemic fish)፣ ጉማሬዎች፣ መሰል የውኃ ውስጥ እንስሶችና አእዋፋት የሚገኙበትና ለአካባቢው ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ የሕይዎት ዋስትና መሆኑ ግልጽ ነው። ጣና ከባሕርዳር ጎርጎራ፣ ቁንዝላ፣ ደልጊና መሰል ቦታዎች የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠቱ ባሻገር፣ የአገሪቱ የቱሪስት መስብህ ከሆኑት የሁለቱ ማለትም የጪስ አባይና የገዳሞቹ ባለቤት ነው። (በእርግጥ በአሁን ሰዓት ወያኔ ለትግራይ ፋብሪካዎች ማንቀሳቀሻ ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨትና የዐማራውን ክልል የተፈጥሮ ሀብት ሆን ብሎ ለማውደም ሲል ወደ ፏፏቴው የሚፈሰውን ውሃ ሙልጭ አድርጎ አዲስ ወደተጨመረው ተርባይን ስለጠለፈው ጪስ አባይን አድርቆታል። በመሆኑም ከቱሪዝም መስህብነቱ ወጥቷል ማለት ይቻላል።)

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ደግሞ የግብፅና የሱዳን ሕይዎት የተመሠረተው ከዚሁ ከጣና ሓይቅ ጋር ቀጥተኛ ትሥሥር ካለው ከአባይ ወንዝ ጋር መሆኑ ግልጽ ነው። ዐባይ የግብፅ የሕይዎትና የደም ሥር ነው የሚባለውም ያለምክንያት አይደለም። የግብፅ ኢኮኖሚም ሆነ የእያንዳንዱ ግብፃዊ የዕለት ተዕለት ሕይዎት የተመሠረተው በአባይ ውኃ ላይ ስለሆነ ነው። ይህም በመሆኑ ጣና፣ ከኢትዮጵያ ይልቅ ከከፍተኛ ጥቅም አልፎ፣ የግብፅ ኅልውና ብቸኛ መሠረት መሆኑ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም የጣና ሐይቅ ችግር ገጠመው ማለት፣ ከሁሉም ቀድሞ የችግሩ ተጠቂ የሚሆኑት የሐይቁ ተፈጥሮአዊ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያና በሐይቁ ዙሪያ የሚኖሩት ዜጎች ሳይሆኑ፣ ግብፅና ሱዳን እንደሚሆኑ ማስረጃ የሚያስቆጥር ጉዳይ አይሆንም።

ስለጣና ይኸን ያህል ለማለት የወደድነው አዲስ ግኝት ለማስተዋወቅ ወይም ስለጣና ታሪክ ለመዘከር አስበን ሳይሆን፣ ጣና ላይ ስለተደቀነው እጅግ አሳሳቢ አደጋ ለማውሳት ለሀሳባችን መንደርደሪያነት እንዲሆነን በማሰብ ነው።

የጣና ሐይቅ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የውኃ መጠኑ ከመቀነስ አልፎ በመድረቅ ላይ ነው። እነዚህም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ምክንያቶች ናቸው። ከሰው ሠራሹ ችግሮች ወስጥ ግንባር ቀደሙና የሐይቁን የውሃ መጠን በፍጥነት እንዲያሽቆለቁል ያደረገው ለጣና-በለስ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ውሃው በመሬት ውስጥ ለውስጥ ተጠልፎ በመወሰዱ ነው። ይህ በመሬት ውስጥ ለውስጥ የተቀበረው 43 ሜትር ስፋትና 11.5 ሜትር ከፍታ ያለው ቱቦ ወይም ቦይ የጣናን 9.1 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ወደ ጣና በለስ ተርባይን ይዞ ይጓዛል። ቱቦው ወይም ቦዩ ከመሬት ውስጥ ጠለቅ ብሎ የተቀበረ በመሆኑ የጣናን ውሃ ያለምንም ችግር ምጥጥ እያድረገ መውሰድ ችሏል። ይህ ከጣና የሚወጣው ውሃ ደግሞ ወደ ጣና ከሚገባው ውሃ በእጅጉ ስለሚበልጥ ጣና በፍጥነትና በአስደንጋጭ ሁኔታ መጠኑ እየቀነሰ ነው። ሌላው ሰው ሠራሽ ችግር ለሐይቁ ኅልውና መጠበቅ ምንም ዓይነት ትኩረት ሳይሰጥ በአካባቢው የሚገንቡ ፋብሪካዎች የሚለቁት ፍሳሽ በውኃው ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ለግብርና አገልግሎት ተብለው በሐይቁ ዙሪያ የሚሠሩ ሥራዎችም የራሣቸው የሆነ የውኃ ብክነትና መቀነስ አሳድረዋል።

በሁለተኛው ጎራ የተመደበውና ለጣና መድረቅ እንደምክንያት የሚቆጠረው ተፈጥሮ ያስከተለው ችግር ነው። ከዚህም ውስጥ አንዱ ከዓየር ንብረት መቀየር ጋር በተያያዘ የመጣ የውሃው መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመምጣቱ ሁኔታ ነው። ሁለተኛው የተፈጥሮ ችግር ደግሞ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ከአካባቢው ተራሮች እየተሸረሸረ ወደ ሐይቁ የሚገባው ደለል የሐይቁን ጥልቀት በመሙላት ሐይቁ መቋጠር የሚችለውን የውኃ መጠን በእጅጉ ስላሳነሰው ነው።

ከዚህ ሁሉ አልፎ አሁን ጣና የመድረቅ አደጋ የተጋረጠበት በተፈጥሮ ይሁን በሰው ሠራሽ ምክንያት በውል ተለይቶ እስካሁን ባልታወቀ ምክንያት “እንቦጭ” የተሰኘ አረም በሐይቁ ውስጥ በብዛትና በስፋት ስለበቀለበት ነው። ተክሉ በተፈጥሮው ውኃ መጣጭ በመሆኑ የሐይቁን የውኃ መጠን ከመኖር ወደ አለመኖር እያሸጋገረው ይገኛል። እንቦጭ የተባለው አረም (ተክል) የውኃውን መጠን ከመቀነስ አልፎ፣ በውስጡ የሚኖሩትን ለአካባቢው ሕዝብ በሁለንተናዊ መልኩ ጥቅም የሚሰጡት እፅዋትና እንስሳት እንዲያልቁም እያደረገ ነው። ይህ አጥፊ አረም አስቸኳይ መፍትሔ ካልተገኘለት በስተቀር ጣና ከሐይቅነት ወደ እርሻ መሬትነት መለውጡ አይቀሬ መሆኑን የውኃው መጠን የሚገኝበት ሁኔታ ያስረዳል።

ሀላፊነት ለሚሰማው ሰው ዛሬ ጣና የሚገኝበት ሁኔታ እጅግ፣ እጅግ አሳሳቢ ነው። ሐቁ ይህ ከሆነ፣ ታዲያ እኛ እንደ ዜጋ ምን ማድረግ እንችላለን? ምንስ ማድረግ ይጠበቅብናል? ለሚሉት ጥያቄዎች አስፈላጊና ተገቢ የሆኑ አማራጮችን በማፍለቅ በተሻለው ላይ የሥራ ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም።

በዚህ ረገድ ያገባናልና ይመለከተናል የምንል ወገኖች ሁሉ በጣና ጉዳይ የምንችለውን ልናደርግ ይገባናል እንላለን። በመሆኑም የጣና መድረቅ የቅርብ ተጠቂው የዐማራው ሕዝብ ነው። አባቶቻችን “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንደሚሉት፣ ሰዎቹ ተከዜን ገድበው ዓሣ እያሰገሩ ለሕዝባቸው ከመመገብ አልፈው ዛሬ ለባህር ዳር ሕዝብ አሣ እየሸጡ ነው። ዐማራው በተፈጥሮ የዓሣ ምንጭ የሆነው ጣና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት በሐይቁ የሚኖሩት ፍጡሮች ዓሣን ጨምሮ ለጉዳት ከመጋለጣቸው በላይ፣ የውኃ መጠኑ በእጅጉ ቀንሶ ወደ መድረቅ እያዘገመ ይገኛል። ይህን ችግር ለመቅረፍ በቅድሚያ “ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስም” ነውና በዐማራው ስም የተደራጁ የፖለቲካ፣ የሲቪክና የሙያ ድርጅቶች አቅማቸውን አስተባብረው ለችግሩ የመፍትሔ ሀሳብ ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም የዐማራ ሙያተኞች ማኅበር፣ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ዳግማዊ መዐሕድ፣ የጎንደር ኅብረት፣ የጎጃም ኅብረት፣ ወዘተ በአስቸኳይ ተገናኝተው ሌሎች አካሎች ሊሳተፉ የሚችሉበትን የአሠራር ዘዴ በመቀየስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተለይም የጣና መድረቅ ቀጥተኛ ተጠቂ ከመሆን የማይቀርላቸው ግብፅና ሱዳን የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መንገድ እንዲቀየስ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫዎቱ፣ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።

የጣና ሐይቅ መጠበቅ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ መጠበቅ ነው!
የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

Email: aseuoipr@gmail.com