አዲስ አበባ፣ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላው አፍካውያን ዋና ከተማ ናት!

Print Friendly, PDF & Email

አዲስ አበባ፣ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የመላው አፍካውያን ዋና ከተማ ናት!

ቅፅ 1 ቁጥር 5
ሀምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም.

ሰሞኑን “ያደቆነ ሰይጣን፣ ሳያቀስስ አይለቅም” የሆነባቸው የትግሬ-ወያኔዎች ቡድን፣ ኢትዮጵያውያንን የሚከፋፍል ብቻ ሳይሆን የሚያፋጅ አዋጅ አውጇል። አዋጁ አዲስ አበባ የኦሮሞ ነገድ ብቸኛ አንጡራ ሀብት እንደሆነችና በከተማው ላይም የኦሮሞ ነገድ ልዩ ጥቅም ማግኘት አለበት የሚል ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ከወያኔና አጋሮቹ በተሻለ የኦሮሞ ሕዝብ የሚጠቀም ቢሆን፣ ነገሩ፣ «ጥጃ ጠባ፣ ሆድ ገባ» በሆነ ነበር። ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም። የአዋጁ መነሻ መሠረታዊ ምክንያቱ በነገዶች መካከል በተለይም በዐማራውና በኦሮሞው ቀዝቅዞና በመለዘብ ላይ የነበረውን ወያኔ ሠራሽ ልዩነት አዲስ የመነጣጠያና የመቀያየሚያ አጀንዳ ሰጥቶ የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ማሰቡ ነው። ጎንደር ላይ «በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም!»፣ «የኦሮሞው ደም ደሜ ነው» የሚለው መፈክር ደምቆና ከፍ ብሎ መስተጋባት፣ በዚያው አንፃር በኦሮሞው ሕዝብ ተመሳሳይ ድምፅ መሰማት፣ ይህን ተከትሎም በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ በባሌ፣ በወለጋ ወዘተ በተከታታይ ለዓመታት የዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ የወያኔን ዘረኛና ከፋፋይ አገዛዝ ከመሠረቱ በማናጋቱ፣ አገዛዙ ሲመካበት የኖረውን ሕገመንግሥት ተብየ አግዶ ወታደራዊ አገዛዝ እንዲያውጅ አድርጎታል። ይህ የዐማራውና የኦሮሞው ድምፅ በአንድነት ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ መስተጋባት ወያኔ፣ እስከዛሬ ዐማራውንና ኦሮሞውን አጋጭቶና አለያይቶ በሥልጣን ለመቆየት ያለውን ሠፊ ዕቅድ ከማክሸፍ አልፎ እንዳልነበር አደረገው። ይህ ደግሞ ወያኔ በሥልጣን ለመቆየት ደልድሎት የነበረው መደላድል ጋሬጣና እሾህ አደረገው። የሥልጣን መደላድሉን ለማመቻቸት አዲስ የሕዝብ ማናቆሪያ ዘዴ መዘየድ ነበረበት። ዘዴውም የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ማስለወጥ የሚችል፣ በዐማራውና በኦሮሞው ብቻ ሳይሆን፣ በኦሮሞውና በሌሎች ነገዶች መካከል የማያቋርጥ የጠብ ምንጭ የሚሆን ነገር መፍጠር ሆኖ አገኘው። ይኸው ከኢትዮጵያውያን አልፎ፣ የመላው አፍሪካ መዲና በሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ተጠቃሚው ኦሮሞው ነው የሚል፣ ከወረቀት የማያልፍ አዋጅ ማውጣት ለአገዛዙ ዕድሜ መራዘም ጊዜ መግዣ ሊሆነው እንደሚችል አመነ። ለዕምነቱ ተግባራዊነትም አዲስ አበባ የኦሮሞ ብቻ አንጡራ ሀብት እንደሆነች የሚያስመስልና ተጠቃሚ መሆን ያለበትም ኦሮሞው ብቻ እንደሆነ የሚያሳይ አዋጅ አወጀ።

በእስከዛሬዎቹ አዋጆች ተጠቃሚዎቹ ወያኔዎችና አጋሮቻቸው እንደመሆናቸው መጠን፣ በዚህም አዋጅ ተጠቃሚ የሚሆኑት ወያኔዎች ብቻ ናቸው። የጥቅማቸው መሠረትም በነገዶች መካከል፣ በተለይም በኦሮሞውና በዐማራው መካከል አንድነት እስከወዲያኛው እንዳይፈጠር ማድረግ ነው። ይህን እስከዛሬ እንደሆነው ሁሉ፣ በዐማራውና በኦሮሞው መካከል ወያኔ ሠራሽ የግጭት ምንጮችን በማስፋት፣ወያኔ የአገሪቱን ባለቤቶች አገር አልባ በማድረግ፣ የአገዛዙን ዕድሜ ማራዘም ነው። የወያኔን ፕሮግራም፣ ዓላማ፣ ተልዕኮና የ43 ዓመታት የተግባር እንቅስቃሴዎች ላጤነ ሰው፣ ወያኔ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት፣ ዐማራውንና ኦሮሞውን ዓይንና ናጫ፣ ንብና ጭስ፣ እሳትና ውሃ፣ ወዘተ ማድረግ ግባቸው አድርገው መነሳታቸው እንደሆነ ይገነዘባል። የወያኔ ኅልውናና የመኖር ዋስትና የተመሠረተውም በዐማራና በኦሮሞ ነገዶች መነጣጠል ላይ እንደሆነ ከወያኔ ድርጊትና ከመሪዎቹ ንግግሮች የሰማነውና ያየነው ጉዳይ ነው። ይህንም ሟቹ መለስ ዜናዊ(ለገሠ ዜናዊ) ባንድ ወቅት፦ እንዲህ ማለቱ የሚዘነጋ አይደለም። “ዐማራውና ኦሮሞው አብረው መቆም ከጀመሩ ድርጅቴ ሕወሓት ያኔ ማቅ ትለብሳለች። የትግራይ ሕዝብ ኅልውና በዐማራውና በኦሮሞው ሕዝብ ፍቺ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ላፍታም መዘንጋት የለብንም። ኦሮሞውና ዐማራው መልሰው ጋብቻ የሚፈጥሩበት ፕላት ፎርም ካገኙ የሕወሓት ኅልውና ያን ጊዜ በይፋ ያከትማል”ሲል ለትግራይ ሕዝብ መቀሌ ላይ በትግርኛ መናገሩን እናስታውሳለን፤ እናውቃለንም።

ይህ የመለስ ንግግር በድንገት የተባለ አይደለም። የድርጅቱ ቋሚ መመሪያና መርሕ ነው። አምና የጎንደር ሕዝብ “በኦሮሚያ ጎዳናዎች የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድሞቼ ደም የእኔ ደም ነው” ሲልም ጌታቸው ረዳ በቴሌቭዥን ቀርቦ ያለምንም ይሉኝታ፦ “እሣትና ጭድ የሆኑ ነገዶች ሊቀራረቡ አይገባም። ይህ የሚያሳየው የቤት ሥራችንን በደንብ አለመሥራታችንን ነው” በማለት በቁጭት ተናግሯል። አዎ፣ የሰሞኑ የኦሮሞ ነገድ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ይኑረው የሚለው አዋጅ፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ታስቦ ሳይሆን፣ ኦሮሞውን ከሌሎች ነገዶች ጋር በማጋጨት፣ ወያኔ ገላጋይ መስሎ በመግባት ግጭቶቹን በማባባስ የአገዛዝ ዕድሜውን ለማራዘመም መሆኑን ማንም ይስተዋል አይባልም። የአዋጁ ዓላማ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ አዋጁ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት መውጣት ነበረበት። በሌላ በኩል አዲስ አባባ የአንድ ብቸኛ ነገድ መኖሪያና ልዩ ጥቅም ማስገኛ ልትሆን አትችልም። አዲስ አበባ የተገነባቸው በሁሉም ኢትዮጵያውያን ኅሊናዊና ቁሣዊ ሀብት ነው። ከተማዋም የአንድ ነገድ መኖሪያ ሳትሆን፣ ከተቆረቆረችበት ከ1879 ዓም ጀምሮ ባሉት 130 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ የሚገኙ ነገዶችና ጎሣዎች የወል ቤት ናት። አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና ሌሎች ዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ድርጅቶች በመዲናዋ ከተቋቋሙ ጀምሮ የአፍሪካ ዋና ከተማ ሆናለች። ዓለም እየተቀራረበ ባለበት በዚህ ዘመን፣ አዲስ አበባን በመሰል ታሪካዊና ጥንታዊ ከተማ ቀርቶ፣ ጥቃቅን የሚመስሉ ምድራዊ አካባቢዎችና ሕንፃዎች፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ቅርሶች የዓለም ማኅበረሰብ የጋራ ሀብት መሆን ከጀመሩ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከዚህ አንፃር አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የወል ቤት እንጂ፣ የአንድ ነጠላ ነገድ ብቸኛ ቤት አይደለችም። ልትሆንም አይገባም።

ወያኔ እንዳሰበው በዚህ ድርጊት የሚደሰቱ ካሉ፣ እነርሱ ወያኔና የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላቶች ብቻ ናቸው። ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብም ልክ እንደ አባ ዶዮ፣ እንደ ራስ ጎበና ዳጬ፣ እንደፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዲና እንደ ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ የሚያስቡ የኦሮሞ ልጆች፣ በዚህ ከፋፋይና አጥፊ የሤራ ተግባር ይደሰታሉ፣ አዋጁንም ከልብ ይቀበሉታል ለማለት አያስደፍርም። የምንጠቀመው በአንድነት ስንቆምና የከተማይቱ ጥቅም የወል ተጋሪዎች ስንሆን እንጂ፣ አንዱን ልጅ፣ ሌላውን የእንጀራ ልጅ በማድረግ እንዳልሆነ ማንም ይስተዋል አይባልም።

ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ተጠቃሚ የኦሮሞ ሕዝብ ይሆናል የሚለው አዋጅ፣ «ዶሮን ሲያታልሏት፣ በመጫኛ ጣሏት» ከሚባለው የተለየ እንደማይሆን ኦሮሞው አይስተውም። ወያኔን ከማንም የበለጠ ማንነቱንና ተግባሩን ተጠግተው ሳይሆን፣ ከውስጥ ሆነው ልጆቹ አይተውታል። ወያኔ ኦሮሞውን የሚፈልገው በተለያዩ ምክንያቶች የተጋመደውን የዐማራውና የኦሮሞ ሕዝብ ለማፋታት፣ አጥፊና ጠፊ ሆነው እንዲቆሙ መሳሪያ እንዲሆኑት እንጂ፣ የዘላቂ ጥቅምና መብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዳልሆነ ያለፉት 26 ዓመታት የወያኔ አገዛዝ ከሚገባው በላይ አሳይቷል። እናም በዚህ አዋጅ የሚታለል የኦሮሞ ልጅ ይኖራል ለማለት ያስቸግራል። ቢኖርም የሻዕቢያና የወያኔ ምርኮኛ የሆኑትን እነአባዱላ ገመዳና መሰሎቹ ብቻ እንደሚሆኑ መጠራጠር አይቻልም። እነዚህ ደግሞ ለራሳቸው ነፃነት የሌላቸው ለሌሎች ነፃነት፣ ጥቅምና መብት ይቆማሉ ተብሎ አይታሰብም።

ለዚህ የትግሬ ነፃ አውጭ ነኝ ባይ፣ በአሁኑ ሰዓት የአዲስ አበባን ከተማ የባለቤትነትና የጥቅም ጉዳይ አንስቶ አዋጅ ያስነገረው መሠረታዊ ምክንያት፣ ኅሊና ላለው አገር ወዳድ የተሰወረ አይሆንም። ዛሬ የትግሬ ነፃ አውጭ በቡችሎቹ አማካኝነት ባለፉት 26 ዓመታት ሲገዛ፣ ሲረግጥ፣ በዘር ሲመነጥርና ዕልቂት ሲፈጽም፣ ሲዘርፍና ሲያፈናቅል የመጣበት ሥርዓቱ ከሥሩ እየተናደበት መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ሕዝቡ በዘረኛው የትግሬ ነፃ አውጭ አልገዛም ብሎ ዱር ቤቴ ማለቱ በየቀኑ የምንሰማውና የምናየው ነው። ዐማራውና ኦሮሞው የአባቶቹን የአርበኝነት የትግል ሥልት ከጀመረ ውሎ አድሯል። ይህም የከፋፍለህ ግዛውን ታላቅ ሤራ፣ በአደባባይ በተገለጠ የሕዝብ አንገዛም የአንድነት መፈክር አረጋግጦ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፎ አረመኔውን ሥርዓት ግብዐተ መሬት ለማስገባት ቆርጦ ተነስቷል። በአሁኑ ሰዓት ሕወሓት የቀረው የመጨረሻ ግብዓተ መሬቱን የሚያቀላጥፍ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕዝብ ምት ነው። ወያኔ የዚህ አይቀሬ ምት የሥራዓቱን ዋልታዎች እየመታቸውና ክፉኛም እያቆሰላቸው እንደሆነ በሚገባ ተረድቷል። ይህ አዋጅ በዚህ የመጨረሻ የወያኔ የጣር ዘመን ላይ መውጣት፣ ባወጣ ያውጣው ዓይነት በሕዝባችን መካከል ልዩነቶችን አራግቦ የጣረሞት ሞቱን ዕድሜ ለማራዘም ታስቦ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ማንም አይስተውም።

ሕዝባችን፣ በተለይም ሊሸነገል የተፈለገው የኦሮሞ ማኅበረሰብ፣ የዚህን የወያኔ ሤራ በሚገባ ስለሚያውቀው የሤራው ተባባሪ ይሆናል ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም። ለዚህ ሤራ ድጋፋቸውን በመለገስ ላይ ያሉ ቢኖሩ፣ ቀደሞም ሕዝቡ የሚያውቃቸው የወያኔ ተባባሪዎች ብቻ ናቸው። እኛ ለዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሕዝቡ መሠረታዊ መብቶች፣ ነፃነትና ዕኩልነት የቆምን፣ አሁን የዘረኛው አገዛዝ ባለቀበት ሰዓት ላይ ደርሰን እያለ፣ የግዛት ይገባናል ጥያቄን ብናነሳ፣ የወያኔ ተባባሪነታችን ከማሳየቱ አልፎ፣ የታሪክ ተጠያቂዎች ከመሆን አናልፍም።
ሕዝቡ በትግሉ ጎዳና በቁርጠኝነት እየተዋደቀ ባለበት ሰዓት፦ “አዲስ አበባ የማናት” በሚል ወያኔ በሰጠን የማደናቆሪያና የመካፋፈያ ሤራ ውስጥ መግባት፤ ሕዝቡ እየከፈለው ያላውን መራር የመኖርና ያለመኖር ትግል ጭቃ መቀባት፣ አራሙቻ ማልበስ ይሆናል። የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ሕዝባችን ከዚህ ወያኔ ካጠመደለት የእርስ በእርስ ግጭትን ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋግር ወደ ሚችል ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ አበክሮ ያሳስባል። የትግላችን አንኳር ለሽርፍራፊ ጥቅሞችና መብቶች ሳይሆን፣ የተነጠቅነውን የመላዋ ኢትዮጵያ ባለቤትነታችን፣ ነፃነታችን፣ መብቶቻችንና ጥቅሞቻችን መልሰን የእኛ የኢትዮጵያውያን በማድረግ የሁሉም ነገሮች ባለቤቶች ለመሆን ነው። ከዚህ በመለስ ከወያኔ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር የለም። እኛ የምንታገለው ኢትዮጵያውያንን የጋራቸው የሆነች ሀገር ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ከዚህ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ውስጥ አንዱም ”የልዩ ጥቅም” ባለቤት የሆነ ሕዝብ የለም፤ አይኖርምም፤ መኖርም የለበትም።

ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከበው በቅብብሎሽ፣ በተጋድሎና በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገነባች አንዲት ኢትዮጵያን ነው። ሥሪቷም የአባቶቻችን የሆነች፣ ከተሞቿም በነርሱ የተገነቡ የጋራ መነኸሪያቸው፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የማኅበራዊ ሥነልቦና ማሳያ የሆኑ የአንድነታችን መስታዋቶች ናቸው። በመሆኑም ከተሞቻችን የወል ማንነቶቻችን መግለጫዎች በመሆናቸው የጋራችን ናቸው። እነዚህ የወል ሀብቶቻችን የሆኑ፣ ግን በወያኔ በኃይል የተነጠቁብን ውርሶቻችን በትግል የምናስመልሳቸው ንብረቶቻችን መሆናቸው ግልጽ ነው።

ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን የወል ጥረቶቻቸው ሁነኛና ልዩ መገለጫቸው የጋራ ቤታቸው ናት። የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ሀገራዊ ነፃነትና ለሕዝቡ ዕኩልነት ቆመው ለሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የትግሉን ጊዜ ለማሳጠር፣ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመቀነስና የሕዝባችን ሥቃይ ለማቃለል የሚረዳ የተባበረ ጥረት የሚደረግበት ዘዴ በጋራ እንዲቀየስ የትብብርና የአንድነት ጥሪ በዚህ አጋጣሚ ያቀርባል። የጥሪያችን ፍሬ ነገር፣ በወያኔ የማደናገሪያና የግርግር ወጥመድ ውስጥ ሳንገባ፣ ቢቻል በተቀናጀ፣ ካልተቻለም በመሰለን መንገድ ሁሉ የምናደርገው ትግል፣ ሕዝቡ የጀመረውን ትግል ሳያሰናክል የሚቀጥልበትን መንገድ በጋራ በመሻት ሁላችን የአቅማችን ለትግሉ አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክረን እንድንቀጥል የሚያስችል በሁሉም የአንድነት ኃይሎች ይሁንታን ያገኘ ስልት እንቀይስ የሚል ነው።

ኢትዮጵያ እንደአገር፤ ሕዝቧ እንደ ዜጋ ባለፉት መልካም ዕሴቶችና ግንኙነቶች ላይ በመመሥረት ወደ ተሻለ የዕድገትና የብልጽግና ጎዳና እንድታመራ ብሩኅ ራዕይ ያላቸው ዜጎች ይህን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መነጣጠያና መጠፋፊያ የሆነውን አዋጅ እንዳለፉት የከሸፉ አዋጆች ሁሉ ማክሸፍ ይጠብቅብናል። ከሁሉም በላይ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የሚኖሩ የዐማራ እና ሌሎች ነገዶች ከኦሮሞ ወንድም እህቶቻችን ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት በዚህ አዋጅ የተነሳ እንዳናደፈርሰው ልዩ ጥንቃዌ ልናደርግ ይገባል። በዚህ አዋጅ በመሠረተ ሀሳቡም ሆነ በአፈጻጸሙ ላይ የሚነሱ ችግሮች ሁሉ የትግሬ ወያኔ እንጂ፣ የኦሮሞው ነገድ እንዳልሆነ ከወዲሁ በቂ ግንዛቤ ልንጨብጥ ይገባል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የኦሮሞ ወንድሞችና እህቶች፣ኢትዮጵያና አዲስ አበባ የማንም ሳይሆኑ፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር እና ዋና ከተማ መሆናቸውን አምነው፣ በነበረን መልካም ግንኙነቶቻችን ላይ በመመሥረት ወደ ተሻለ ዕድገት ልናመራ የምንችልበትን ሥልት በመቀየስ፣ የአገራችንና የሕዝባችን ጠላት የሆነውን የትግሬ ወያኔ አገዛዝ ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ መንጭቀን ለመጣል በኅብረት ልንነሳ ይገባል።

ሕዝባችን የወያኔን የመከፋፈያ ሤራ በአንድነት ቆሞ ያመክናል!
የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት።

Email: aseuoipr@gmail.com