የአየር ጠባይ የሚያመጣውን አደጋ አስጠንቃቂዎች!

Print Friendly, PDF & Email

(ፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ )

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

የአየር ጠባይ የሚያመጣውን አደጋ አስጠንቃቂዎች ለሰው ልጅ ባለ ከፍተኛ ውለታ ናቸው። “ዐውሎ ነፋስ ሊመጣ ነውና ተደበቁ”፤ “ወንዙ ጐርፍ ሆኖ ሕይወት የሚያጠፋ ሆኗልና ዳር ዳሩን መገደብ ጀምሩ”፤ “ራስ የሚፈነክት በረዶ ሊወርድ ነውና ቶሎ መጠጊያ ፈልጉ”፤ “ነጐድጓዱ መብረቅ የሚጥል ስለ ሆነ ከዛፍ ስር ራቁ” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ብዙ ሰውና ንብረት ያድናሉ። በሀገራችን ብዙ እረኞች በጎርፍ ተወስደዋል። ከላይ መዝነቡን ሳያውቁ ከወንዝ ዳር ሲጫወቱ ድንገት እየደረሰ ወስዷቸዋል። ብዙ ሰዎች ዛፍ እየተጠጉ በመብረቅ ተመትተዋል። አውሎ ነፋስ እንኳን በሀገራችን ብዙ ኃይል የለውም። እዚህ አሜሪካ ግን ዋና የሕይወት ጠሮ ነው። ታዲያ አስጠንቃቂ ባለመኖሩ አልተጐዳንም?
“የአየር ጠባይ አስጠንቃቂዎች ሥራ አስፈላጊ አይደለም” የሚል ሰው ያለ አይመስለኝም። ማስጠንቀቂያቸውን የማይሰማውን “ሞኝ”፥ የሚሰማውን “ብልህ” ብል፥ ጸላኤ ሠናይ (ደግ ነገር የማይወድ) ከሚባለው ከዲያብሎስ በቀር ምንም ዓይነት ሰው አባባሌን አይነቅፍም። የሚነቅፍ ካለ፥ “ዐውሎ ነፋስ ይውሰዳችሁ፤ በረዶ ይፈንክታችሁ፥ ውሓ ይውሰዳችሁ” የሚል ተንኮለኛ ክፉ ሰው ብቻ ነው።

በዚሁ አስተሳሰብ፥ ሰይጣን (ወያኔ) አይስማውና፥ ለምሳሌ ጉራጌዎችን ለማጥፋት አንድ ኃይል እንደ ዐውሎ ነፋስ፥ እንደ ጐርፍ፥ እንደ ነጐድጓድ ተነሥቶ ማውደም ሲጀምር፥ ጉራጌዎች ከሞት ለመዳን ቢደራጁ ከጸላኤ ሠናይ በቀር ምንም ዓይነት ሰው አይነቅፋቸውም? “ዝም ብለው መውደማቸውን ትተው አንወድምም አሉ” ብሎ የሚታዘባቸው ይኖራል ወይ? እንደሚመስለኝ ከሆነ (መሆንም አለበት)፥ጉራጌዎች የሚሳቅባቸው በእንደዚህ ያለ አደጋ ላይ መሆናቸውን እያወቁ ራሳቸውን ከውድመት ለማዳን ባይደራጁ ነው። ከተደራጁና “ሞረሽ” ብለው ከጮኹ ጎረቤትም ይደርስላቸዋል። ከመውደም ይድናሉ። እርዳታ ሲጠይቁ ሰው የሚደርስላቸው፥ጉራጌነት የግል ቢሆንም፥ ሰውነት፥ ከዚያም ኢትዮጵያዊነት፥ የጋራ ስለሆነ ነው። ካልተረዳዳን፥ ያንድ እናት ሀገር ልጆች መሆናችን ዋጋ የለውም።

ጉራጌዎች መደራጀት የጀመሩት በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው። ከአዲስ አበባ ወደነሱ አገር የሚወስደውን መንገድ ያሠራው የነሱ ጅርጅት ነው። ተጠቅመውበታል፤ተመስግነውበታል። ሌሎችም ተጠቅመውበታል። የተደራጁት “የግል የምናደርው አገር ተከልሎ ይሰጠን” ብለው ቢሆን ኖሮ፥ ግብራቸውን ዲያብሎሳዊ አገር ከፋፋይ ሐሳብ ያነገቡ እንላቸው ነበር።

አማራው ቢደራጅስ? የአማራ መደራጀትማ፥ ለምን እንደተደራጀ እንኳን ሳይጠየቅ በብዙ መንገድ ይነቀፋል፤ “ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖቹ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ሊነሡ ነው”፥ “አማሮች የቀድሞውን አስተዳደር ሊመልሱብን ነው”፥ “አማራውም በወያኔ ወጥመድ ገብቶ በዘር መደራጀት ጀመረ” ይባላል። ታዲያ የተዘመተበትን የጥፋት ዘመቻ እንዴት ይቋቋመው? “ክርስቲያን ስለሆንክ ቀኝ ፊትህን ሲመታህ ግራህን አዙርለት” ለማለት ይሆን? አሁን ሳስበው ምስጢሩ “ዝም ብለህ እለቅ፤ አንተ ካላለቅህ የኛ ማንነት ደብዝዞ ይቀራል፤ እለቅና ወይም ከፊታችን ዞር በልልንና መኖራችን ይታወቅልን። ጤነኛ እያለ ጎባጣ አይመለመልም” የሚሉ ራሳቸውን ከአማራው በታች ዝቅ አድርገው የሚያዩ ወገኖች ሴራ ነው።

“ትምክሕተኛ” ሲሉት ሰምታችሁ የለም? ምስጢሩ ምን መሰላችሁ? “ከኛ በልጠህ ትታያለህ” ነው። “አማራውን የሚያስከብረው ታሪክ የጋራ ታሪክ ነው፤ አብረን እንኵራ፤ አብረን እንመካ” ቢባሉም፥ ጥሪው ሽንገላ ይመስላቸዋል። የሚቀርብላቸውን ማስረጃ ሰው-ሠራሽ ተረት ያደርጉታል። በዚያ ላይ ወያኔዎች አማራ እየመሰሉ ሌሎችን የሚያናድድና በአማራው ላይ ጥላቻ የሚፈጥር ቃል ጣል ያደርጉላቸዋል። በቋፍ ያሉ ስለ ሆነ፥ በቀላሉ ከወጥመዳቸው ይገባሉ። ከወጥመዳቸው አልገባ ብለው ካስቸገሩ፥ የሌላውን (በተለይም የአማራውን) ጥቅምና መብት ወስደው ሲሰጧቸው ይሸነፋሉ። ዲሞክራሲ ለሰብአ ትካት እንግዳ ነገር ስለሆነ፥ ከዘራፍነት (ዘርፎ ከመብላት) ባህል መውጣት አልተቻለም። ሰብአ ትካት በግጦሽና በመስኖ ውሓ ይጣላሉ። አማራው ለዲሞክራሲ ሲታገል እነዘራፍ ዘመቱበት። አሁን ሲነቃ እንዳንቀላፋ ለማስቀረት አዲስ ዘዴ አመጡ።

አዲስ ያመጡት ዘዴ፥ የሞረሽን እያየለ መሄድ ሲያዩ፥ በወያኔ መንገድ ሊያዳክሙት ፈለጉ። ታስታውሱ እንደሆን፥ ወያኔዎች ተቃዋሚዎቹን ሲያጣጥል፥ “ብዙዎች ፓርቲዎች እንጂ አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የለባቸውም” ይላሉ። በዚያው ዘዴ፥ “አማራው ሊስማማ አልቻለም፤ ብዙ የአማራ ድርጅቶች አሉ እንጂ አንድ ጠንካራ የአማራ ድርጅት የለም” እያሉ የአማራውን አልሞት ባይ ተጋዳይነት ያጣጥላሉ። የትኛው የአማራ ድርጅት ነው ሞረሽን የሚወዳደር? የትኛው የአማራ ድርጅት ነው እንደ ሞረሽ ስለ አማራው እልቂት ጥናት ያቀረበ? የትኛው የአማራው ድርጅት ነው እንደ ሞረሽ ከትግሉ ሜዳ ጋር ግንኙነት ያለው? ከዓሥር የማይበልጡ ሰዎች ተጠራርተው “የአማራ ማኅበር ነን” ቢሉ እነሱን ፍሬ ካሳየው ሞረሽ ጋር ማስተካከል አለማወቅ ወይም ተንኮል ነው።

ሌላው ትችት፥ “የአማሮችን ትግል መደገፍ ሌሎችን ያገላል፥ ያስቀይማል” የሚል ነው። ለዚህ ምን ዓይነት አጸፋ ይሰጧል? አንድ ሰው ቤቱ ሲቃጠልበት ለማዳን በሚያደርገው ጥረት ጎረቤቱ ይረዳል እንጂ፥ ምን ሆንኩ ብሎ ነው ቅሬታ የሚሰማው?

ይሄ ትችት አላስኬድ ሲል፥ “ለመሆኑ አማራው ማን ነው?” ይላሉ። አማራው ማን እንደሆነ ለማወቅ ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው አልተቸገሩም፤ እያሳደዱት ነው። አማራውም ማን እንደሆነ ለማወቅ አልተቸገረም፤ሻዕቢያና ኦነጎች ምጽዋ ላይ የተማረኩትን ወታደሮች ሰብስበው፥ “አማራ የሆንክ ተለይ” ሲሉት ተለይቷል። አማራ ገዳዮች፥ “ከአውቶቡስ ላይ አማራ የሆንክ ውረድ” ሲሉት ወርዷል፤ ተገድሏል። ግራኝ መሐመድ (አሕመድ) ወታደሮቹን “አማራ መስላችሁ ተሰለፉ” ሲል፥ መስለው ተሰለፉ እንጂ፥ “አማራ ማነው?” “አማራ ምን ይመስላል?” አላሉም።

የሞረሽን መልክትና ራእይ የማይቀበል ጠላትነቱ ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጭምር ነው። ሞረሽ የሚታገለው አማራንና ኢትዮጵያን (የኦርቶዶክስ ሃይማኖትንም) ሊያጠፉ የተነሡትን ለመመከት ነው። ለሰብአዊ መብት እቈረቈራለሁ የሚል አማራን ለማዳን የሚደረገውን ትግል ካልደገፈ፥ ውሸታም ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት እታገላለሁ የሚል ሁሉ፥አማራው የሚያደርገውን ትግል ካልደገፈ፥ ውሸታም ነው። ምክንያቱም አማራው የሚታገለው ራሱን ለማዳን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከወያኔ ነፃ ለማውጣት ጭምር ነው። አማራው፥ “ከኢትዮጵያ መሬት ላይ በሰፊው ከፍለን እንሰጥሃለን፤አርፈህ ተቀመጥ” ቢሉት፥ አርፎ አይቀመጥም። መላዋ ኢትዮጵያ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ናት፤ ነፃነቷን ካልተጐናጸፈች አማራው ከወያኔ ጋር ተስማምቶ አይኖርም። ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ሁሉ፥ አማራው የሚያደርገውን ትግል ካልደገፈ፥ ውሸታም ነው። ምክንያቱም አማራው የሚታገለው

ራሱን ለማዳን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲሰፍን ጭምር ነው። ማንኛውንም ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዲሞክራሲ የሚታገልን ድርጅት መደገፍ ግዴታችን ነው። ሴቶች በሴቶች ላይ የተሰነዘረ በደልን ለመታገል ቢደራጁ እንደግፋቸዋለን። በሃይማኖት ላይ የተሰነዘረ በደልን ለመታገል የሚደራጅን ቡድን እንደግፋለን።

የአንድ ድርጅት ትግል የራሱን ክልል ለማስፋፋትና ነፃ ለማውጣት ብቻ ከሆነ ማንኛውንም ድርጅት፥ አማራም ቢሆን ሌላ፥ እንቃወማለን። መቃወም አባታዊ እናታዊ ግዴታችን ነው። ኢትዮጵያን ከወላጆቻችን የወረስናት ለልጆቻችን ልናወርሳት እንጂ፥ በጣጥሰን ልንጥላት አይደለም። ወያኔዎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት የኦሮሞ ፖለቲከኞችን መጠቀሚያ እንዳደረጓቸው አማሮችን ሊጠቀሙባቸው አይችሉም። እንዲያውም ይኸ ወያኔን እምቢተኝነት ሳይሆን አይቀርም ብዙዎች አማሮች በአማራነት የተደራጀውን ሞረሽን ደፍረው በይፋ ከመደገፍ የሚያወላውሉት። አማሮች፥ የኢትዮጵያ አንድነት ጠላቶች ሲጨርሷችሁ ዝም ብላችሁ አትለቁላቸው። ከሞረሽ የተሻለ ድርጅት ልታቋቁሙ ስለማትችሉ ሁሉን እርግፍ አድርጋችሁ ሞረሽን ደግፉ፥ አጠናክሩ። ድጋፍ ብዙ መልክ አለው፥ የገንዘብ፥ የተሻለ ሐሳብ ማቅረብ፥ የማበረታታት፥ ደጋፊ የማብዛት፥ እነዚህ ሁሉ በእርዳታ አንዱ ከሌላው አያንስም።

ለሞረሽም አንድ ሁለት ቃላት አሉኝ፤ጠላታችሁ ወያኔና ደጋፊዎቻችሁ ብቻ ናቸው። ሌላ ጠላት የላችሁም። ወያኔን የሚያዳክም ድርጅትም ሆነ ግለሰብ በምንም ምክንያት ጠላታችሁ ሊሆን አይችልም። ቢሆንም ሊጐዳⶭሁ አይችልምና ከእንዲህ ያሉ ወገኖች ጋራ ግብ ግብ አትግጠሙ። ለምሳሌ፥ አስመራ ላይ የአማራ ድርጅት ተቋቁሟል ሲባል ሰምተናል። የሞረሽን ተቃውሞ ወይም ድጋፍ ሳይፈልግም ሽልም እንደሁ ይገፋል፥ እህልም እንደሁ ይጠፋል። እኛ አዳማጮቻችሁም ስለሚሆነው ነገር ሁሉ የናንተን አስተያየት ሳንሰማ የራሳችን አስተያየት ለመፍጠር እንችላለን። አፈሙዛችሁን ለአንዳች ቅጽበት ቢሆን ከወያኔ ላይ አንሥታችሁ ወደሌላ አታዙሩት፤ ጥይታችሁን አታባክኑ። ውጤቱ ደጋፊዎቻችሁን መቀነስ ይሆናል።