ኅልውናችን ለማትረፍ ስንል በመደራጀታችን የሚቃወሙንን ከገዳዮቻችን ለይተን አናያቸውም!

Print Friendly, PDF & Email


ኅልውናችን ለማትረፍ ስንል በመደራጀታችን የሚቃወሙንን ከገዳዮቻችን ለይተን አናያቸውም! ( pdf )
ቅጽ 1፣ ቁጥር 3
ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም.

አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ኦዚ ደርሶ መልስ” የሚል ፀረ-ዐማራ መጣጥፍ እ.ኤ.አ ግንቦት 18 ቀን 2017 በድረገጽ ላይ በይፋ ማሰራጨታቸው የሚታወስ ነው። ያ የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ ጽሑፍ ሁሌም “ነፍጠኞች” እያሉ ከሚያዘውትሩት አሽሙርና ፀያፍ ንግግራቸውም የከረረም ቢሆን ለእርሳቸውም ይሁን ለድርጅቱ ግንቦት 7 መልስ ከመስጠት ይልቅ በዐማራ ባህላችን “ንቆ መተው ይሻላል” በሚል “የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)” መልስ ላለመስጠት ወስኖ ነበር። ሆኖም ግን ይሄውና አሁን ደግሞ የ”ኦዚ ደርሶ መልስ” ቅጥያ የሆነውን በቃላት ጨዋታ ከሽነው ተራ ሽንገላቸውን “ከቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ” በሚል ርዕሥ እ.ኤ.አ ጁን 1 ቀን 2017 አሁንም በድረገጽ ላይ አሰራጭተዋል። አቶ ኤፍሬም ከኦዚ ደርሶ መልስ ጽሑፋቸውን በግሌ የጻፍኩት ነው ቢሉም፣ ድርጅታቸውን ወክለው በየአዳራሹ ባደረጓችው ንግግሮቸ ሁሉ በጽሑፋቸው ከገለፁት ባልተለየ እንዲያውም በባሰ ሁኔታ በዐማራው ላይ ዘምተዋል። በመሆኑም ወክሎ የላካቸውን ድርጅታችውን ለመጥቀስ የተገደድነው ከዚህ አኳያ እንደሆነ በቅድሚያ እንዲታወቅልን እንሻለን።

አቶ ኤፍሬም በሁለቱም ጽሑፎቻቸው የአፄ ቴዎድሮስን ሥምና ጀግንነት ደግመው ደጋግመው ማንሳታቸው ባይከፋም፣ የዐማራ ልጆች ለኅልውናቸው የሚያደርጉትን መሰባሰብ ግን አሁንም “በጭቃ ጅራፍ መግረፉን” አጠናክረው ቀጥለዋል። እንዲያውም የአቶ ኤፍሬም አፄ ቴዎድሮስን አሞናሙነው ለማቅረብ እየሞከሩበት ያለው ቅኝት ግን ከልብ ላለመሆኑ በአፄ ምኒሊክ ላይ ያላቸው ሥር የሰደደ ክፉ ጥላቻና ሥም ማጥፋት የቆየ ተግባራቸው ጥሩ አድርጎ ያሳብቅባቸዋል። በመሆኑም የጀግናው የአፄ ቴዎድሮስ ሥም የተነሳበት ዐብይ ምክንያቶች ሁለትና ሁለት ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ መገመት አይከፋም።

አንደኛውና የመጀመሪያው ምክንያት በግንቦት 7 ውስጥ ያሉ የዐማራ ነገድ ተወላጆችን የሚወዱትን የአፄ ቴዎድሮስን ስም አሁንም አሁንም ደጋግሞ በማነሳሳት በቃላት ለመሸንገል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ “ያለ ተግባር በቴዎድሮስ ዝና ብቻ” ጎንደርና ጎጃም ድልድይ ሆነው እርሳቸው “ሸገር” ወደሚሉት ከተማ አልጋ ባልጋ ለመሻገር የሚያስችል ብልሃት ነው ተብሎ ታስቦበት የቀረበ የብልጣብልጥ መጣጥፍ ይመስላል። ያ ባይሆን ኖሮ በአፄ ቴዎድሮስ እጅ አድገው፣ የአፄ ቴዎድሮስን ራዕይ አንግበው ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን ዳግማዊ አፄ ምኒሊክን ልክ እንደ ወያኔዎች ሁሉ በትቢያ ላይ ባልጎተቷቸው ነበር። አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ንፁህና ከጥላቻ ነፃ የሆነ ኅሊና ቢኖራቸው ኖሮ ሀገር ገንቢውንና ሀገር አንድ አድራጊውን ምኒልክን ከሀገር አጥፊውና ፀረ – አንድነቱ መለስ ዜናዊ ጋር “አንድ ናቸው” ብለው ባልፈረጇቸው ነበር።

እርግጥ ነው አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ከኦሮሞ ወረራ በፊት ወደ ነበራት ታላቅ የግዛት ስፋትና ሉዐላዊነት እንዲሁም ታሪካዊ ዝናና ቦታዋ ለመመለስና ይበልጥ ደግሞ በስልጣኔ ለማዘመን እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ራዕይ ይዘው የተነሱና በታሪክ ባለሙያዎች “ከጊዜያቸው ቀድመው የተወለዱ መሪ” ተብለው የተመሠከረላቸው መሪ ነበሩ። እርሳቸው ሀገርን አንድ ለማድረግና ለማዘመን በተነሱበት በዚያ ዘመን እጅግ በጣም ደካማዋ ጣሊያን – በካሚሎ ዲ ካቮዩር (Camillo di Cavour) እንዲሁም ጀርመን – በኦቶ ቮን ቢስማርክ (Otto von Bismark) እ.ኤ.አ (ከ1850 – 1871) በተመሳሳይ ሁኔታ የተበታተኑ አገሮቻቸውን ወደ አንድነት ለማምጣት ሲሉ ከፍተኛ በሆነ የጦርነት ቋያ ውስጥ ይነዱ ነበር። ያ የጣሊያንና የጀርመን መሪዎች ጠንካራ አገር የመፍጠር ምኞታቸው ተሳክቶላቸው አንድነታቸውን አጠናክረው ለመጠበቅ ያለፈውን የእርስ በእርስ ጦርነት ረስተው በአዲስ መንፈስና በአዲስ ራዕይ ከአካባቢያቸው ርቀው በመሄድ አዲስ ቅኝ ግዛት አገር ለማፈላለግ ምክንያት ሆኗቸዋል። ኢትዮጵይ ግን ከራሷ ታሪካዊ ግዛት አልፋ ልትሄድ ይቅርና ባለመታደል ሆኖ ታላቁን መሪዋን አፄ ቴዎድሮስን ገና በጠዋቱ አጣችና አባቶቻችን ለዘመናት በደማቸው ያቆዩትን የራሷን የግዛት ወሰን በሚፈለገው መልኩ ለማደራጀት እንኳ ገና ጊዜ አላገኘችም ነበር።

አዎ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ሁለት መሠረታዊ ጉዳዩችን የያዘች ዕለት ነበረች። ሆኖም ግን ሁለቱም ምክንያቶች አቶ ኤፍሬም ለማስቀመጥ እንደ ሞከሩት አልነበረም። ይልቁንስ የመጀመሪያውና ራሳቸው አፄ ቴዎድሮስ ቃታውን ከመሳባቸው በፊት ቃል በቃል የተናገሩት እንደሚከተለው ነበር። “የጠላት ጦር ሠራዊት የንግሥቲቱን ትዕዛዛ ለመፈፀም አገር አቋርጦ እኔን ለመግደልና አገሬን ለመውረር ሲመጣ የኔዎቹ ሰዎች ግን ክፉኛ ከዱኝ፣ በእኔ ላይ ከጠላት ጋር ሆነው አሴሩ፣ መንገድ መሩ፣ ድሮም ቢሆን በቴዎድሮስ ሕይወት ማንም አያዝዝም፤ ወሳኙ እሱው ራሱ ቴዎድሮስ ብቻ ነው” ብለው የደጃዝማች ካሣ ምርጫ (የኋላውን አፄ ዮሓንስን) የከሃዲነት ተግባራቸውንባንደበታቸው ተናገሩና ምላጩን ሳቡት! እናም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአገራችን ኢትዮጵያና በንጉሧ ላይ በዓይነቱ የተለየና ወደር የማይገኝለት ክህደት በዚያች ዕለት የተፈፀመባት ዕለት ስትሆን፣ ይህን ተከትሎ በደጃዝማች ካሣ ምርጫ ሰፈር ደግሞ የደስታ ተኩስ ሲንዷዷ፣ ወያኔና እርስዎን መሰል የወያኔ ግርፎች (ጃዋራዊያን/Jawarist) በወራሪነትና በጡት ቆራጭነት በፈጠራ ወሬ ስማቸውን የምታጠፏቸው በወቅቱ የሸዋው ንጉሥ ምኒሊክ ግን ጥቁር የሃዘን በርኖሳቸውን ለብሰውና እልፍኛቸውን ዘግተው ከምርና ከአንጀት ጀግንነትን አስተማሪ አባታቸውን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያም ደግሞ ቆራጥ መሪዋን በማጣቷ ከምር ሐዘን ላይ ነበሩ።

እንግዲህ በአፄ ቴዎድሮስና በኢትዮጵያ የተፈጸመዉ ክህደት ይህን ያህል ታላቅ ሆኖ ሳለ አቶ ኤፍሬምም ሆኑ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም በአፄ ቴዎድሮስና በኢትዮጵያ ላይ ስለተፈፀመው ታሪካዊ ክህደት አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሲሉ አልተደመጡም። ለዚህ ደግም ምስጢሩ አንድና አንድ ብቻ ነው። ያም ወያኔዎች እንዳይከፋቸው ብቻ ሳይሆን ስር የሰደደው ወያኔአዊ ባሕሪና አቋም ከውስጣቸው ስላለ ይሆናል።

ሌላው ሁለተኛው በሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም የተከሰተውን ጉዳይ ደግሞ ፕ/ር መሥፍን በሲያትል የወያኔ ቅኝት አራማጅ ኮንፍረስ ላይ “ቴዎድሮስን በፍርሃት ራሱን ገደለ” እንዳሉት ሳይሆን ሃቁ አፄ ቴዎድሮስ ፍርሃትን በሞታቸው ገለው፣ ክብርና ድፍረትን በገሃድ ለትውልድ አውርሰዋል። ለዚህ ደግሞ ምሥክሩ የቴዎድሮስ ጀግንነት ለቀጣዩ ኢትዮጵያዊ ትውልድ በደም ዉስጥ ዘላለም የሚኖር የጀግንነት ውርስ ሆኖ ይሄውና በገሃድ እያየነው ነው። በተለይ ደግሞ በየካቲቱ 23 በዕለተ ጊዮዎርጊስ በዕለተ ሰንበቱ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዓድዋ ላይ ለተመራው የኢትዮጵያ አርበኛ ጦር (የአፄ ቴዎድሮስ ጀግንነት) ጥሩ የሞራል ስንቅና ትጥቅ ሆኖ ለአርበኞች ማገልገል የመቻሉ ጉዳይ ነው። እናም ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የአፄ ቴዎድሮስ ፈለግ የተከተሉ ሌላው ባለትልቅ ራዕይ ብልህ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩ እንጅ ወያኔና የወያኔ ግርፎች እንደሚሉት ወራሪም፣ ጡጥ ቆራጭም አልነበሩም።

ምኒሊክ አይወድም ሰንጢ መታጠቅ፣
ምኒሊክ አያውቅም ጩቤ መሸጎጥ፣
ምኒሊክ አይወድም በሰንጢ መቁረጥ፣
ያስከብራል ድምበር በርዕቱ አንደበቱ — አልያም በከዘራ ወይም በሽጉጥ!!

እውነተኛው ታሪክ ይህ ሆኖ እያለ፣
በወያኔ ግርፎች ጡጥ ቆራጭ ተባለ፣
በወያኔ ግርፎች (በጃዋራዊያን) ወራሪ ተባለ!!

ይህ ከላይ ለማሳየት የሞከርነው አቶ ኤፍሬም ባለፈው “ኦዚ ደርሶ መልስ” ከተባለው ጽሑፋቸው ተከታይ በሆነው “ከቴዎድሮስ እስከ ቴድሮስ” በሚለው መጣጥፋቸው ላይ በድጋሜ ያነሷቸውንና የዐማራውን ሕዝብ “ይውጋህ ብለው፣ ይማርህ” ያሉበትን ለመቃኘት ነው እንጅ ትኩረታችን ከ”ኦዚ ደርሶ መልስ” ላይ ነው። በእርግጥ ይህንንም ንቀን ትተነው ነበር። አቶ ኤፍሬም ግን አማርኛና የነገር ብልት ለዐማራው እንደማይገባው በተሽሞነሞነ ዐማርኛ ሊሸነግሉት ሲነሱ ብዕራችንን ለማንሳት ተገደድን። አቶ ኤፍሬም እኛ ዐማሮች እንኳንም ሲሸጡን ሲያስማሙን እናውቃለንና ሽንገላዎት አልያዘልዎትም።

“ሆድ ያባውን ጌሾ ያወጣዋል” እንዲሉ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ምን ሲቀምሱ የሆዱቸውን አውጥተው እንደሚናገሩ ባናውቅም በተለያዩ ጊዜያት በዐማራ ነገድ ላይ የሚያደርጓቸውን “ዛቻና ጥላቻ” ይበልጥ አጠናክረው ወደ አደባባይ ማውጣት ከጀመሩ ቆይተዋል። ይህንን ዐማራ ጠል አቋማቸውንም መጀመሪያ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያንፀባርቁት የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ይባስ ብለውና የልብ ልብ ተሰምቷቸው ይሄውና በተለያዩ ድረገፆች ላይና በየአዳራሹ “ዐማራ መደራጀት የለበትም” እያሉ ዘመቻ ከፍተዋል። በስመ “የአንድነት ታጋይነት” ጭምብል ውስጥ ተደብቀው ከሚያታልሉን፣ እነ አቶ ኤፍሬም እንዲህ በአደባባይ ወጥተው ዐማራው ተደራጅቶ ራሱን ማዳን የለበትም፣ እጁን አጣጥፎ ማለቅ እንጅ፣ ብለው መስበካቸውና አቋማቸውን እንዲህ ግልፅ አድርገው ማሳየታቸው ለዐማራው በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ጭቃ ውስጥ የተደበቀ እሾህ ወይም የጠርሙስ ስባሪ የአንድን ሰው እግር ይወጋ ይሆናል እንጅ፣ በግላጭ የሚታይ እሾህም ሆነ የጠርሙስ ስባሪ አይወጋም። ምክንያቱም ግልፅ ሆኖ ስለሚታይ መንገደኛው አይረግጠውም፤ ካልረገጠው ደግሞ አይወጋውም። እነ አቶ ኤፍሬምም እንዲህ በገሀድ ዐማራ መደራጀት የለበትም በማለታቸው በግልፅ እንድናያቸውና እንድናውቃቸው እረድቶናል። በመሆኑም ከዚህ ተነስተን አረማመዳችንና አሰላለፋችን እንድናስተካክል ግድ ይለናል።

የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ኦዚ ደርሶ መልስ” መጣጥፍ “ከአርበኞች መንደር” ሆኜ ብሎ ይጀምራል። ልብ በሉ “ከአርበኞች መንደር” ነው የተባለው! መቸም ነገሩ “ለስሟ መጠሪያ፣ ሰፋች ወስከምቢያ” እንደሚባለው ሁሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ክቡር ሕይወታቸውን የገበሩበትንና ዛሬም ድረስ በተለያየ ምክንያት እየገበሩበት ያለውን “የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር”ን ጮሌዎቹ የግንቦት 7 አመራሮች “ከእኛ ጋራ ካልተዋሃዱ አስጠጊው ሀገር ከለላም ሆነ ስንቅ መስጠት የለበትም” የሚል ውትወታ በማቅረብና ተፅዕኖ በመፍጠር “አርበኞች” የሚለውን ስም መነተፉና ግንቦት 7ቶች በአንድ ጀምበር “አርበኞች ግንቦት 7” ተባሉ። አቶ ኤፍሬም ማዴቦም ትንሽ እንኳን ይሉኝታ ሳይዛቸው ራሳቸውን አርበኛ አድርገው ቁጭ አሉ። ከአሜሪካ-አውሮፓ፣ ከአውሮፓ-አሜሪካና ሌሎች አገሮች በአየር በረራና በገንዘብ ስብስባ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት የግንቦት ሰባት ሰዎች ጭብጥ ቆሎ ይዘው ከአሻሮ ተጠጉና አርበኛ ሆኑ። አሁን ደግሞ የጎንደር አማራ ታጋዮች የሚያስቆጥሩትን ድል ሳያፍሩ ባልዋሉበት አየር በአየር እየመንተፉ የግንቦት ሰባት ድል ነው እያሉ የተለመደ ማጭበርበራቸውን ተያይዘውታል። አቶ ኤፍሬምማ እንዲያውም እርሳቸው ራሳቸው ገና ያኔ ኤርትራ እንደ ደረሱ በድረገጽ ላይ ባስነበቡን መጣጥፋቸው ላይና እኛም እንደምንገምተው እርሳቸው ሻወር እስከሚወስዱ ድረስ ሠራተኛቸው ሰላማዊት ቁርስና ቡና አዘጋጅታ በምትጠብቅበት የተቀማጠለ የኑሮ ሁኔታ ላይ ሆነው “ከአርበኞች መንደር” ሲሉ አይገርምም!? ተግባርና ስያሜ ያልተገናኙበት ዘመን!

በጣም የሚገርመው ደግሞ ምንም እንኳን ሻዕቢያ ሜዳ በነበር ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት አገሮች አስፈላጊውን አቅርቦት በገፍ ቢያቀርቡለትም ቅሉ “የትጥቅ ትግሉ ባሕሪ” ግን እንዲህ አቶ ኤፍሬም እንደሚሉት አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ሻዐቢያዎች በሚገባ ስለሚያውቁት እነሱ እንኳ ይታዘቡኛል አለማለታቸው እጅግ በጣም አስገራሚም አስቂኝም ነው። እንዲያውም ጀብሃም ይሁን በሂደት ሻዐቢያ በትግሉ የመጀመሪያው ምዕራፍ ወቅት (“At the formative Stage” ብለው በጻፉት ሰንድ ላይ) ትግሉን ለመቀላቀል ሲባል አንዳንዶች በማጋነንም ይሁን ለፖለቲካው ቁማር ብለው ደርግ በጦርነት ልጆቻችንን ከሚገድልብን “ሕፃን ልጆቻችንን ራሳችን ገድለን ወደ ሜዳ ሄደናል” ብለው የሚናገሩ ሰዎች ባሉበት ከተማ እየኖሩ፣ ከአገረ አሜሪካ የ16 ዓመት ጎረምሳ ልጃቸውን ትተው ወደ አሥመራ ስለሄዱና አሥመራ ስለተቀመጡ ብቻ እርሳቸው ራሳቸው አልቅሰው የቢጤዎቻቸውን አንጀት ለመብላት የተወኑት ተውኔት የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው!

በዚሁ ከኦዚ ደርሶ መልስ ጽሑፋቸው፣ በገጽ 5 ላይ “ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ መሰማት የተጀመረ አንድ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ስብከት አለ —- እሱም የ’አማራው አማራ ሆኖ መደራጀት የአማራንም የኢትዮጵያንም ነፃነት ያፋጥናል’ የሚለው ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው ስብከት ነው” ብለው ባስቀመጡት መሠረታዊ ጉዳይ ዙሪያ እየተሽከረከሩ የአማራን የመደራጀት ሙከራ እራስ እራሱን ማለታቸውን አበክረው ተያያዙት። ምን ያላሉት አለ? በዐማራነት መደራጀት የራስ በሽተኝነት ነውም ብለውናል።

በመጀመሪያ ነገር “ውኃን ከጥሩ ነገርን ከሥሩ” እንዲሉ መቸም ስለ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የቆየ ፀረ-ዐማራነት አቋም ወደ ኋላ ሄደን ተንትነን ለማሳየት ብንሞክር እጅግ በጣም በወደድን ነበር። ሆንም ግን “ያን ለጊዜ ትተን” ለዋቢነት በአንድ ወቅት እንኳን በሰሜን አሜሪካ የኤርትራዊያን ማህበረሰብ ስብስባ ላይ ተጋብዘው ያደረጉት ንግግር ከነሥብሃት ነጋ ያልተለየ ፀረ-ዐማራ ንግግራቸው ከአዕምሮአችን ሳይወጣ፣ እንሆ አሁን ደግሞ በሌላ መንገድ ዞረው ትናንት የገደሉትንና ሰብዕናውን የገፈፉትን ዐማራ አዲስ ዛቻና አዲስ ዘመቻ ከፈቱበት።

እርግጥ ነው ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ ሆነና ነገሩ፣ ከግንቦት 7 አመራሮች ውስጥ ፀረ-ዐማራ ያልሆነን የአመራር አባል እንፈልግ ብንል የትኛውን አንስተን የትኛውን መተው እንደማንችል ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ብቅ ያላቸሁ ሁሉ በሚገባ እንደምትገነዘቡልን ስለምናውቅ ይህ የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ ፀረ-አማራ መጣጥፍ ብዙም አላስገረመንም። ለዚህ ደግሞ ከራሱ ከድርጅታዊ አቋሙ እንኳን ወረድ ብለን የድርጅታዊ አመራር መመልመያ መሥፈርቶቹን (ለአመራር አባልነት ለመመረጥ፣ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ አንድ ሌላ ቋንቋ መቻል ግድ እንደሚል) አይተናል። ይህ መሥፈርት ማንን ለማግለል ተብሎ እንደተቀመጠ የማይገባው አማራ ግንቦት ሰባት ውስጥ ካለ፣ እርሱ ምንጊዜም አይገባውና ዝም ብሎ የጫኑትን ተሸክሞ ይቀጥል። አማራው ግንቦት 7 ውስጥ አመራር ላይ እንዳይወጣ በቋንቋ መስፈርት ከተገደበ፣ የሚፈለገው ለተዋጊነት፣ ለአገልጋይነትና ለገንዘብ ምንጭነት ብቻ ነው ማለት ነው። በሬ ካራጁ ይሏል ይህ ነው።

ይህንን የመሰለው ዐማራ ጠልና ዐማራ አግላይ ድርጅት ከፍተኛ የአመራር አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም በዐማራ ላይ ከድርጅታቸው የተለየ አቋም ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም የግንቦት 7 ከፍተኛው አመራር አባል የዐማራን መደራጀት ቢኮንኑ አይደንቀንም። የአንድ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ለመሆን ቀርቶ፣ ተራ አባል ለመሆንም የድርጅቱን ዓላማና አቋም መቀበል ቅድሚያ ግዴታ ነው። ስለሆነም አቶ ኤፍሬም የግንቦት 7 አመራር ከፍተኛው ሰገነት ላይ ሆነው ይህን ቢሉ “ድርጅታዊ አቋማቸው ነው” ከማለት ውጭ ከቶ ምንም ማለት አንችልም። ስለሆነም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከአቶ ኤፍሬም ማዴቦም ጋር ይሁን ወይም ከግንቦት 7 አመራሮች ጋራ አላስፈላጊ አተካራ ውስጥ በመግባት የሥራ ጊዜ ለመግደል ተፈልጎ ሳይሆን የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ የዐማራ መደራጀት “የቅርቡ አደገኛ ስብከት” ሆኖ ዐማራን በጠላትነት ያስወነጀለበት ዋና መነሻ ምክንያቱና ፊት ለፊት ፈጦ የመጣው እውነታ ምን እንደሆን ቢያንስ በጥቂቱም ቢሆን “የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)” ግልጽ መሆን አለባቸው የሚላቸውን ዐበይት ጉዳዮች ደግሞ ደጋግሞ ለማብራራት ነው!!

ኢትዮጵያን በዐማራ – ዐማራን በኢትዮጵያ እየቀያየሩ፣
ስንቱን ሰው ገደሉ ስንቱን አባረሩ?

ተናገር ወልቃይት – ተናገር ሑመራ፣
ተናገር ተከዜ – ተናገር ቃሌማ፣
ተናገር መተከል – ተናገር ቢቸና፣
ተናገር አሩሲ – ተናገር ወለጋ – ተናገር ድፍን ሸዋ፣
ተናግሮ የለም ወይ? መስክሮ የለም ወይ? በቱትሲዎች አገር፣
በውኃ ላይ አንሳፎ ሰውን በሰው እልቂት እጅግ ዘግናኝ ነገር?

የተከበራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን ሆይ፣ በዐማራ ነገድ ላይ እይተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ይህ ከላይ በስንኝ መልክ የተቋጠረው እውነታ በደንብ ይገልፀዋል። ዐማራ በነገዱ ምክንያት ብቻ ከማንም ተነጥሎ እየተፈፀመበት ያለውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ተግበር ለማስቆም ደግሞ የግድ ዐማራ መሆን ሳይሆን ሰው መሆን ብቻ ይበቃል። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮች ግን ሐቁን አናይም ብለውና ከሰውነት ተራ ወርደው ይህን ያህል ከወያኔ ያላነሰ ጨካኝና ፀረ-ዐማራ ዘመቻ በነገዳችን ላይ ለምን እንደከፈቱበት ፈፅሞ ሊገባን አልቻለም።

የዐማራ ሞቱ ኢትዮጵያውነቱ ሆኖና፣ ዐማራ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ስለወደደ ብቻ ወያኔና ተከታዮቹ በጠላትነት ፈረጀው ላለፉት 40 ዓመታት በተለይ ደግሞ ወያኔ ምኒሊክ ቤተመንግሥት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ፣ ንብረት ነጠቃና አጠቃላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ኢሰባዊ ድርጊት ገሃድ የወጣ ወንጀል ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት ቆሜያለሁ የሚል እንደ ግንቦት 7 ያለ ድርጅት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ አካል የሆነውና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ የማይታማው የዐማራ ሕዝብ ይህንን የመሰለ የዘር ፍጅትና የዘር ማፅዳት ዘግናኝ ወንጀል ሲፈፀምብት ከማንም ቀድሞ ሊያሳስበው በተገባ ነበር። ባለመታደል ግን የግንቦት 7 አመራሮቸ ዐማራው የመጀመሪያው የነገድ ድርጅት ሆኖ የተቋቋመና እገነጠላለሁ ያለ ይመስል፣ “የዐማራው መደራጀት ኢትዮጵያን ያጠፋል፤ ከወያኔ ያልተለየ አደገኛ አካሄድ ነውና ልናወግዘው ይገባል” ይሉናል። እነ አቶ ኤፍሬም በአንድ በኩል፣ “ኢትዮጵያ ቅኝ ገዣችን ናትና ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ እንገነጥላለን” የሚሉትን እነ ኦነግንና መሰል ተገንጣይ የጎጥ ድርጅቶችን በጥምረት ስም አቅፈው ከበሮ እየደለቁ፣ በሌላ በኩል ግን ኅልውናው አደጋ ላይ በመሆኑ ሕይዎቱን ለማትረፍ ሲል ገና አሁን መደራጀት የጀመረውን የዐማራውን ሕዝብ አጥብቀው ይኮንናሉ። ይህ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት የችግሩ ሰለባ የሆነውን የዐማራ ሕዝብ ቀርቶ ማንም ንፁህ ኅሊና ያለውን የሰው ልጅ ስሜት ምን ያህል እንደሚጎዳ እነአቶ ኤፍሬም በቅጡ የተረዱት አይመስልም። እነ አቶ ኤፍሬም እባካችሁ ቁስላችንን በወንድምነት ባታክሙልንም እንኳን ላዩ ላይ ጨው እየነሰነሳችሁ ይበልጥ አታሳምሙን።

አቶ ኤፍሬም በኦዚ ደርሶ መልስ መጣጥፋቸው በአውስትራሊያ ከሚኖሩ የወልቃይት ተወላጆች አገኘሁት ያሉትን በወልቃይት ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ወንጀል የሚያሳይ መረጃ በጽሑፋቸው ለመግለፅ አልደፈሩም። ምክንያቱም የተፈፀመው ኢሰባዊ ወንጀል እጅግ ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ ለሕዝብ በጽሑፍ ለመግለፅ አልደፍርም ብለው በአፅንዖት ገልፀዋል። ለአቶ ኤፍሬም ይህንን ዘግናኝ መረጃ የሰጧቸው የወልቃይት ተወላጆች በምን ምክንያት ያ ሁሉ ወንጀል እንደተፈፀመባቸው እንደሚነገሯቸው አንጠራረርም። ያ ሁሉ አሰቃቂ ወንጀል የተፈፀመባቸው በማንነታቸው (በዐማራነታቸው) እንደሆነ ነግረዋቸዋል። ይህንን መረጃ በጆሯቸው የሰሙት ጨካኙ አቶ ኤፍሬም ግን እነዚህ በዐማራነታቸው እጅግ አሰቃቂ ወንጀል የተፈፀመባቸው ዐማራዎች በዐማራነታቸው ተደራጅተው ኅልውናቸውን ለማትረፍ በመንቀሳቀሳቸው ከወያኔ አስበልጠው ይኮንኗቸዋል። አቶ ኤፍሬም አውስትራሊያ ውስጥ ለግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ንግግር ሲያድርጉ “በዐማራ ሥም ለመደራጀት የሚሞክሩትን ከወያኔ ነጥላችሁ ማየት ስለሌባችሁ በምንም ዓይነት ሊሰባሰቡ የሚችሉበት ሁኔታ በአካባቢያችሁ ሊኖር አይገባምና ዕድል እንዳትሰጧቸው” ብለው በአጽንዖት መመሪያ ሰጥተዋል። አከታትለውም “በተለይ በተለይ ገንዘብ እንዳታዋጡላቸው፣ ገንዘብ ወደ ሜዳ መሄድ ያለበት በአንድ መሥመር ሲሆን፣ እሱም በአርበኞች ግንቦት 7 በኩል ብቻ ነው” አሉ። ይህ የለየለት ጭካኔና ጠላትነት ነው። ዐማራው ቢደራጅ አደጋ ላይ ያለውን ኅልውናውን ለማትረፍ እንጅ በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ጊዜም ሆነ ችግር የማይለውጠው የፀና አቋም ያለው ሕዝብ ነው። በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እንዲህ የፀና አቋምና ዕምነት ያለውን ሕዝብ ደግሞ ይንከባከቡታል እንጂ እንዴት ከጠላት ባልተናነሰ ሁኔታ እንዲጠፋ ያሤሩበታል? አዎ! ዐማራው ለኅልውናው ሲል የሚያደርገው መሰባሰብና መደራጀት አደገኛ አካሄድና ኢትዮጵያን እንደማፍረስ እርምጃ ተደርጎ መተርጎሙ ከጠላት እንጂ ወገን ነኝ ከሚል አካል ወይም ግለሰብ የማይጠብቅ ፍፁም የተሳሳተ እይታ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጨካኝና በነገዳችሁ ተለይታችሁ ስትገደሉ ተደራጅታቸሁ መመከት ሳይሆን እንደበግ አንገታችሁን ስጡ የሚሉንን ከገዳዮቻችን ለይተን እነደማናያቸው እነ አቶ ኤፍሬምና ድርጅታቸው እንዲያውቁልን እንፈልጋለን። ሁሉም የዐማራ ልጅ በዐማራው ነገድ ላይ እንዲህ ዓይነት ጨካኝ እርምጃ ሲወሰድበት፣ ድርጊቱን ሊያወግዝና የኃይል አሰላለፉን ከወዲሁ እንዲያስተካክል ማስገንዘብም እጅግ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል!

አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በአውስትራሊያ ጉዞአቸው ይዘውት የቀረቡት በዋናነት በወልቃይት ጉዳይ ላይ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነበር። የጽሑፉም ዋና መልዕክት የወልቃይት ሕዝብ ከወያኔ መውደቅ በኋላ “ሕዝበ-ውሳኔ” ሊያደርግ እንደሚችል የሚያሳይ ነበር። ይህ አቋም ደግሞ ከወያኔ ያልተሻለ አካሄድ ነው። ይሁን እንጅ የአቶ ኤፍሬም ጽሑፍ በዚያው መጠን ደግሞ በዕለቱ የሚፈለገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ታስቦ አቀራረቡ እንቅፋት እንዳይፈጥር በጥንቃቄ የተሰራ ጽሑፍ ነበር ማለት ይቻላል።

ሆኖም ግን፣ እውነት እንነጋገር ከተባለ የወልቃይት ሕዝብም ይሁን በአጠቃላይ የዐማራ ልጆች እንደዚያ ያለውን ዲስኩርና “የሕዝበ-ውሳኔ” ወያኔአዊ ስብከት መስማት አይፈልጉም ነበር። ምክንያቱም ጎንደርና ትግራይ በተፈጥሮ ድንበር በተከዜ ወንዝ የተለዩ ሁሉት ለየብቻ ያሉ የኢትዮጵያ ክ/ሀገሮች መሆናቸውን ጠላት ይሁን ወዳጅ ያውቀዋልና። አውስትራሊያ ወስጥ ከተደረጉ ስብሰባዎች በአንዱ ከተማ ለአቶ ኤፍሬም ከቀረቡላቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የሚከተልው ነበር፦ “በወልቃይትና አካባቢው ጉዳይ ላይ ይህን ጽሑፍ ከማቅረባችሁ ባሻገር አርበኞች ግንቦት 7 በጉዳዩ ላይ ያለው ድርጅታዊ አቋሙ ምንድን ነው? በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በፊት የነበረው አቋም ግልጽና የማያሻማ መሆኑን በሚገባ የምናውቀው ቢሆንም ቅሉ በውኅደት ሽፋን የአርበኞች ግንባር እጅግ በጣም ጠንካራና ኢትዮጵያዊ አቋሞቹ በሂደት በግንቦት 7 እጅ በተናጠል እየተወሰነባቸው ነውና አሁን አርበኞች ግንቦት 7 ያለው ድርጅታዊ አቋም ምንድን ነው?” አቶ ኤፍሬም ሲመልሱ፦ “የለም በወልቃይት ጉዳይ ላይ ድርጅቱ አቋም አይዝም” ብለው ነበር ያለፉት። ለነገሩ ግንቦት 7 ያኔ “ፊሽካው ተነፍቷል፣ የትጥቅ ትግሉ ተጀምሯል” ብሎ ሲደሰኩር የወልቃይትን ስም ማንሳት ተጠይፎ፤ “የምዕራብ ትግራይ” መሬት አድርጎ መዘገቡን ስናስታውስ የድርጅቱ አቋም በወልቃይት ላይ ከወያኔ የተለየ አለመሆኑን ያወቅነው አሁን አቶ ኤፍሬም ሲነግሩን ሳይሆን ገና ያኔ ነበር።

እርግጥ ነው ግንቦት 7 ወያኔና ኦነግ ዐማራውን አግልለው በ1983 ዓ.ም በሕገወጥ መንገድ ለራሳቸው እየከነዱ የወሰዷቸውን የዐማራ መሬቶችና በተናጠል የወሰኗቸውን አገራዊ ውሳኔዎች ምንም ሳያቅማሙ መቀበል እንጅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎትና ታሪካዊ እውነታዎችን ተከትሎ አቋም መያዝ ማለት የውስጥ ድርጅታዊ ተልዕኮአቸውን ተፃርሮ መቆም ስለሚሆንባቸው ግንቦት 7ቶች ይህን አያደርጉትም! የትግርኛ ቋንቋን እንደተጨማሪ ቋንቋ በመናገራቸው ብቻ የወልቃይትና የራያ ዐማራዎች ትግሬዎች ናችሁ ተብለው ወደትግራይ በግድ ተከልለዋል። ይህንን በቀላል ምሳሌ/ አመንክዮ ብናየው ፈረንሣይኛ ቋንቋ የሚናገሩ የአጎራባች አገሮች ነዋሪዎች ሁሉም ዜግነታቸው ፈረንሣያዊ እንዳላይደሉ ወያኔም ሆነ ግንቦት 7 ሊረዱ አለመፈለጋቸው ነው።

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) የሚታገለው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እንደሚሉት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም አይደለም። ዐኅኢአድ ሁለት የትግል ምዕራፎች ያሉት ድርጅት ነው። በምዕራፍ አንድ ትግሉ የዐማራን ነገድ ወያኔና መሰሎቹ ከከፈቱበት የዘር ማጥፋት ጦርነት መታደግ ነው። በሁለተኛው የትግል ምዕራፉ ደግሞ በኢትዮጵያዊነታቸው ከሚያምኑና ከሚኮሩ ሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር በመሆንና በመተባበር ኢትዮጵያን ከወያኔ መንጋጋ ፈልቅቆ በማውጣት ሉዐላዊነቷና ዴሞክራሲያዊ አድንድነቷ በሁሉም ዜጎች እኩልነት ተጠብቆ ዳግም በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ቀድሞ የነበራትን ታሪካዊ የክብር ቦታዋን እንድታገኝ ማድረግ ነው። ምንም እንኳን ዐኅኢአድ ዐማራው በተከፈተበት የዘር ፍጅት ምክንያት መጀመሪያ የዐማራውን ኅልውና መታደግ ቀዳሚ ተግባሩ ቢሆንም ቅሉ፣ ድርጅቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ልጆችና ማኅበረሰብ አባላት ላይ ታላቅ አክብሮትና አመኔታ አለው። ኢትዮጵያም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገር መሆኗን አበክሮ ያምናል። በመሆኑም ዐኀኢአድ አንዳንድ ለዐማራው በጎ አመለካከት የሌላቸው (እንደ እነ አቶ ኤፍሬምና መሰሎቻቸው) ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ሊከስሱት እንደሚሞክሩት “ዐማራው ከሌሎቹ የበለጥኩ ኢትዮጵያዊ እኔ ነኝ፤ ኢትዮጵያንም ብቻየን ነፃ አወጣታለሁ” ብሎ የሚታበይ ግብዝ ድርጅት አይደለም።

የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ ግንቦት 7 ግን እንዲያውም ዐማራነት እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የዐማራ ልጆች በየድርጅቶች አመራር ውስጥ እንዳይካተቱ የሚያደርግ አግላይ ድርጅት ነው። ይህም ሆኖ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ያለፋል የሚለውን ብሂል ሆን ብለው ተቀብለው ገንዘባቸውንና ጊዜአቸውን መሪ ነን ለሚሉት እየሰጡ ብዙ ዓመታት ቢጠብቁም የነገዳቸው ኅልውና ይባስ ብሎ ከዓመት ዓመት ወደ አደገኛ ሁኔታ ሄደ እንጅ ሲሻሻል አልታየም። ይህም በመሆኑ እጅግ በጣም ዘግይቶም ቢሆን የዐማራ ልጆች በሚደርስባቸው መጠነ-ሰፊ ግፍ ተገድደው በነገዳቸው ዙሪያ ለኅልውናቸው ሲሉ መደራጀት ጀመሩ። ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ አቶ ኤፍሬም አሁን ደርሰው ኢትዮጵያዊነትን ለዐማራ ልጆች ለማስተማር መሞከራቸው “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማራች” እንዳይሆንባቸው እንሰጋለን። ዐማራው ኅልውናን ለማዳን ሲል በሚያደርገው መሰባሰብ ላይ ተጨማሪ መሰናክል የሚሆንበትን ማንም ይሁን ማንን የማይቀበልና አምርሮ የሚያወግዝ መሆኑን ዐኅኢአድ ግልጽ ማድረግ ይፈልጋል።

ተድራጅተን ራሳችንን ከጥፋት መታደግ የሰው ሠራሹ ሕግ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ሕግም ይፈቅድልናል። በመሆኑም ይህንን ላለመጥፋት የምናደርገውን ተደራጅቶ መታገል የሚኮንንም ሆነ ሊያሰናክል የሚመክረውን ሁሉ እቅድ ነድፍው እያጠፉን ካሉ የለየላቸው ጠላቶቻችን ለይተን እንደማናየው አበክረን ልንነግረው እንወዳለን።

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ወሳኝ ነው!!
የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)