የአማራ የማንነት ትግል ለአማራ ህልውና አስፈላጊነት..(ዲሲ ጉባኤ የቀረበ ጽሁፍ ጭምቅ ሀሳብ)

Print Friendly, PDF & Email

(ምስጋናው አንዱዓለም)

ምስጋናው አንዱዓለም

የአማራነት እንቅስቃሴ የማንነትና የታሪክ ማስከበር ነው። ዋና ግቡም የአማራን ህልውና ማስከበር ነው። ህለውናውን ካረጋገጠ በኋላ ሙሉ ጥቅሞቹን፣ መብቶቹን፣ ደህንነቱንና ህልውናውን የሚያስጠብቅለትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተክለሰብእና መገንባት ዋና ስራው ይሆናል። አማራ በማንነቱ ባለመደራጀቱ አሁን ለደረሰበት ጥፋት መንስኤ ነው።በአማራ ማንነት መደራጀት ጥቅሞች፡ የህዝብ መሰባሰብን፣ መተሳሰብን፣ መረዳዳትንና ፍቅርን ያመጣል። አንዱ ለአንዱ ለጥቃቱ እንዲደርስለት ያደርጋል።

በኢትዮጵያዊነት ትግል እንዳየነው አማራው ለራሱ ሊደርስ አልቻለም። ምክንያቱም

አንድ፡ አማራው በኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ውስጥ ስለሚታቀፍ ተነጥየ ለአማራው ልቁም ቢል ችግር ነው።

ሁለት፡ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሊደርሱለት አይችሉም። ምክንያቱም አንዳንዶቹ አማራን እንደጠላት የሚቆጥሩ በመሆናቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በአማራው ላይ የማንነት ጥቃት እየተፈጸመበት እንደሆነ መረዳት ስለማይፈልጉ ማለትም ልክ ሌላው ላይ እንደሚደርሰው የመብት ጥሰትና የኢኮኖሚ ጥያቄ ስለሚወስዱት። እንደገናም በኢትዮጵያ ስም የተደራጁት ድርጅቶች ለአማራው የተለየ ከለላ ለማድረግ አደረጃጀታቸው ስለማይፈቅድላቸው።

የአማራ የማንነት እንቅስቃሴ መጀመር የነበረበት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ነበር። በዛ ጊዜ አማራውን አገሪቱ ላይ ለደረሰው ችግር ሁሉ ተጠያቂ ማድረግ ሲጀመር የአማራ ልጆች መዘዙን አስቀድመው መገንዘብ እና ያንን የሚሞግት፣ ለአማራው ወገን የሚቆም እንቅስቃሴ ማድረግ ነበረባቸው። አሁን እያደረግን ያለነው እጅግ ዘግይተን፡ ከ40 አመት በኋላ ነው።

ብንዘገይም አልቀረንም የሚል የአርፋጅ እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው። በ40 አመት የዘገየ ጥያቄ ለመመለስ፣ ወይም የአርባ አመት ችግር ልንፈታ ነው የተነሳነው።

በእርግጥ ይህ አዲሱ የአማራ እንቅስቃሴ ከአርባ አመት ወዲህ ያለውን አንገብጋቢ ችግር ከመፍታት ባሻገር በታሪክ ወደኋላ ሄዶ ካለፈው ታሪክ በመማር ለሚመጡት ዘመናት አማራው ዳግም ለጥቃት እንዳይጋለጥ ለማድረግ ሀላፊነት አለበት። ምክንያቱም የአማራ ችግር የተጀመረው ከአርባ አመት በፊት ሳይሆን ወደኋላ አራትና አምስት መቶ አመታት ቀደም ብሎ ስሆነ። ስለሆነም አሁን በግልጽ ከ40 አመት በፊት መጀመር የነበረበትን እንቅስቃሴ ስንጀምር ለምን በአማራነት ትደራጃላችሁ ብለው አምባጓሮ የሚፈጥሩ አሉ። አነዚህ ለአማራ ፍቅር የሌላቸው፣ በደሉ የማይሰማቸው፣ ለአማራ ጥላቻ ያላቸው፣ አማራውን የገጠመውን ችግር ለመገንዘብ ውስን የማስተዋል አቅም ያላቸው፣ ግዴለሽና ሰብአዊ ርህራሄ የማይሰማቸው ናቸው ብለን ልንዘረዝራቸው እንችላለን።

የአገሪቷ ሲሶ ህዝብን ጥያቄ መመለስ የኢትዮጵያን ጥያቄ ቢያንስ በሲሶ እጅ መመለስ ስለሆነ የአማራውን ትግል ሁሉም አማራ በግንባር ቀደም ሊታገልለት፣ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በቁርጠኝነት እንዲደግፉት ያስፈልጋል። ለአማራ መታገል ማለት ሌላ ተአምር መፍጠር ሳይሆን ለአገሪቷ ሲሶ ህዝብ መታገል በመሆኑ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንደቅዱስ ተግባር ሊቆጠር ይገባል።

የአማራ በአማራነቱ አለመቆም ኢትዮጵያን ፈተና ላይ ጥሏል። ዛሬ ከባድ ችግር እየፈጠሩ የሚገኙት የብሄር ፖለቲካ ግንባሮች የአማራውን በኢትዮጵያዊነት መቆም ወይም የአማራውን በአማራነት አለመቆም እንደመልካም እድል በመጠቀም የጎለመሱ ናቸው። ስለየራሳቸው ብሄር መገንጠልም ሆነ የበላይነት በሚታገሉበት ጊዜ ዋናው የመጫወቻ ሜዳው በነጻ የተገኘው የአማራ ሜዳ ነው። የእኔ የሚሉት መሬትና ሀብት በእብዛኛው የአማራ ታሪካዊ ይዞታ ነው። አፈጣጠርና ጉልምስናቸው አማራ በኢትዮጵያዊነት ሰበብ አሰረን በማለት አማራውን በመወንጀል ነው። አማራው የራሱን ጥያቄ ባለማንሳቱም እነዚህ ወገኖች የሚመኙትን የአማራውን ይዞታ ሁሉ እንደራሳቸው እንዲቆጥሩት አደረገ። አማራው ላይ የደረቱት የሀሰት ክስ እንደእውነት እንዲቆጠርላቸው አደረገ። ይሄም ህዝቡን ማለትም በየፊናቸው ቆምንለት የሚሉትን ህዝብ በአንድነት ለማንቀሰቃስና አማራውን እና ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ መጠጊያ የሌላቸውን ባለብዙ ብሄር ማንነት ያላቸውን ወገኖችና በቁጥር አናሳ ነገዶችን ፈተና ላይ ጣለ።

ከዚህም ተነስተን እነዚህ ጽንፈኛ የብሄር እንቅስቃሴዎች የአማራውን ሜዳ ተጠቅመው በመፋፋት ራሱን አማራውን እና የተጠቀሱትን የህብረተሰብ ክፍሎች አደጋ ላይ ጣሉ እንላለን። ነገር ግን አማራው በአማራነቱ ተነስቶ ቢሆን ኖሮ የራሱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የታሪካዊ ይዞታ ጥያቄዎች ስለሚያነሳ እነዛ ብሄረተኞች ያንን ያህል እንዳይጎለብቱ ያደርግ ነበር። ምክንያቱም አማራው በአማራነቱ የሚገባውን ጥያቄዎች ሁሉ ካነሳ እነሱ የእኛ የሚሉት ነገር ስለማይኖር በቶሎ አቋማቸውን በቀየሩና ቀጭጨው በቀሩ ነበር። የአማራው በአማራነቱ መነሳት ሌላ የውድድር ትግል ስለሚፈጥርባቸው እስካሁን ተሸንፈው ከሜዳው ይወጡ ነበር። እስካሁን ግን ጎልብተው የቆዩት የአማራውን ሀብትና መብት ሁሉ ለራሳቸው በመቀራመት ነው። አማራው ጥያቄ እንደሌለው፣ ብሶት እንደሌለው ተቆጥሮ፣ እንደአማራ የሚናገርለት በመጥፋቱ እነዚህ የብሄር ቡድኖች እንደልባቸው በመፈንጨት የአማራውን ህልውና አደጋ ላይ ጥለዋል፣ የአገሪቷንም ህዝብ መልሶ ለማግባባት ከባድ ወደሆና ማህበራዊ ቅራኔና መለያየት ወስደዋል።

የአማራው የአማራነት ጥያቄዎች ግን ይሄንን እንደልብ ሲፈነጭ የቆየ የአክራሪ ብሄረተኞች አደጋ ሚዛን በመስጠት ያረግበው ነበር። አማራው ራሱን ችሎ እንደ አንድ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሀይል ብቅ ማለት የእነዚህ አክራሪ ብሄረተኞች ህልውና መክሰም መንስኤ ነው። ለዛ ነው ብንዘገይም እንኳ አሁንም በቶሎ አማራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ይሄንን ሁሉ ለአርባ አመት የተዛባ ሚዛን ማስተካከል ታሪካዊ ግዴታችን የሆነበት ጊዜ ላይ ነን የምንለው።

የአማራ ማንነት እንቅስቃሴ የግድ አስፈላጊ የሆነባቸው ምክንያቶች፤
አንደኛ የአማራ ትግል የህልውና ትግል ነው። ህልውናው አደጋ ላይ ወድቋል። ስለዚህ ህልውናው አደጋ ውስጥ የወደቀ ህዝብ ማድረግ ያለበት ቅድሚያ ህልውናውን ማረጋገጥ ነው።

ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀባቸው ሁኔታዎች፡- የትግሬ ሪፑብሊክ ጽነሰ ሀሳብ የአማራን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል። እንደሚታወቀው ትግሬ በታሪክ አለማቀፍ ድንበር የለውም። ከቀይ ባህር ጋር አይገናኝም፤ ከሱዳን ጋር አይገናኝም። ለወደፊቱ ነጻ አገር መሆን ከፈለገ ከሱዳን እና ቀይ ባህር ጋር መገናኘት አለበት። በሱዳን በኩል አማራ ከኤርትራ ጋር ስለሚጎራበት ትግራይ መሀል ላይ ተገልሎ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ስለዚህ ያንን በሱዳን እና በአማራ መካከል ያለውን መሬት ለራሳቸው በመውሰድ የትግራይ አካባቢ አድርጎ ከሱዳን ጋር ድንበርተኛ መሆን ያስፈልጋቸዋል። የወልቃይት እና ጠገዴ ችግርም መነሻው ይሄ ነው። በቀይ ባህር በኩል ያለው በአሁኑ ስሌት እጅግ የተወሳሰበ ነው። ቢሆንም እነሱ እንቅስቃሴያቸውን አላቆሙም። የወሎን ታሪካዊ ግዛት ነጥለው አፋር በሚል ክልል ያቋቋሙበት ምክንያት አማራን በዛ በኩል እንዲሁ መሀል ላይ ቆርጦ ለማስቀረት እና ለትግራይ የተስፋፋ መንገድ ለመፍጠር ነው።

ይህ የትግራይ አገርነት ሀሳብ የአለማቀፍ ድንበር ብቻ ሳይሆን የሀብትም ጥያቄ አለበት። ብዙ ትግሬ የራሱን አገር ይመሰርታል ሲባል ቀድሞ የነበረውን ክፍለ ሀገር ብቻ ይዞ ይመስለዋል። ያ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው። የትግሬ ነጻ መንግስት ማለት አብዛኛውን የአማራ ምድር ሁሉ ወርሮ በመያዝ የትግሬ አካል ማድረግ ነው። ዛሬ ጎንደር ውስጥ በቅማንት ስም የሚፈጥሩት ትርምስም ጎንደርን ለዛው አላማ የማመቻቸት አንዱ ሂደት ክፍል ስለሆነ ነው። በወሎ በኩል የተወሰደው ግዛት የዚሁ ክፍል ነው። በጎንደርና ወሎ ሳይገታ በጎጃም በኩልም የትግሬን ግዛት ለማስፋፋት ሴራ እንዳለ የሚታወቅ ነው።

የትግሬ የበላይነት በአማራ ላይ የህልውና አደጋ ደቅኗል። ከላይ የተዘረዘረው የትግሬ ነጻ መንግስትነት ህልም ከሀብትና ድንበር ጋር በተያያዘ አማራው ላይ የህልውና ችግር ደቅኗል። ነገር ግን ምናልባት ነጻ አገርነት ባይሳካ የትግሬ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖር ይሰራሉ። ይሄም አማራው ላይ ከባድ የህልውና ስጋት ፈጥሯል። የትግሬ የበላይነት እንዲረጋገጥ አማራ የበታች መሆን አለበት። ትግሬ ትልቅ እንዲሆን አማራ ማነስ አለበት። በስነተዋልዶ ሰበብ አማራው ላይ የሚደረገው ዘመቻ በሌሎች ክልሎች እንደሌለ የታወቀ ነው። ትግሬ እዲበለጽግ አማራ መደህየት አለበት። ትግሬ እንዲማር አማራ በማይምነት ጥላ ስር መውደቅ አለበት። የትግሬ የባህል የበላይነት እዲረጋገጥ የአማራው መንቋሸሽና መወገዝ አለበት። ትግሬ እደህዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው አማራው መጥላላት ነበረበት። ትግሬ ሰላም እዲያገኝ አማራው ሰላም ማጣት አለበት። የወያኔ ማፌስቶ አንዱ አላማ አማራን ማህበረሰባዊ ረፍት መንሳት መሆኑን እናስታውሳለን። ይህ ሁሉ በአማራው ኪሳራ ላይ ትግሬን የመገንባት ስራ ላለፈው ሩብ ክፍለዘመን ሲሰራበት የቆየ ነው። ስለዚህ ይህ ትግሬ የበላይ የሆነባት ኢትዮጵያ ለመመስረት የሚደረገው ጥረት በራሱ አማራን አደጋ ውስጥ ከቶታል።

አማራው በአማራነቱ መቆሙ እንግዲህ፡ በዋናነት የህልውና ማስጠበቅ ትግል ነው። አማራው በማንነቱ ካልቆመ በብርታትና በስፋት ለመታገል አይችልም። በኢትዮጵያ ስም የሚያደርገው ትግልም መልህቅ አልባ ሆኖ በታሪክ ተፈትኖ ወድቋል። ይህ አማራው ባለፈው ሩብ ክፍለዘመን የተበላበት ጨዋታ ነው። ስለአንድነት የሚደረግ ትግል ሁሉም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍች ስለዚህ አላ አንድ አይነት አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል። በተቃራኒው ግን አማራው ራሱ ከየብሄረሰብ ከሳሽ ልሂቃን የሚያደርገው የመሳ ለመሳ ትግል የሞኝ መንገድ መሆኑ ተረጋግጧል። የአማራው ችግር በድርጅታዊ ስራ ብቻ የሚፈታ አይደለም። ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው የአማራነት አስተሳሰብ ሲሰፍን እና ሲጠነክር ነው። መአሕድ ሲፈርስ ሌላ ለአማራው የቆመ ድርጅት ለመተካት ይሄንን ያህል ረዥም ጊዜ የወሰደው የአማራነት ስሜት ስላልዳበረ ነው።

ጠንካራ ማንነት ሲኖር የድርጅት መጎልበት ይኖራል። ድርጅት ባይጎለብትም አሳሳቢ አይሆንም። ጠንካራ ማንነት ስሜት እስካለ ድረስ ወይ ሌላ ድርጅት ይፈጠራል፣ አልያም ያለው ይጠናከራል። ጠንካራ ማንነት ስሜት ከሌለ ግን አንድ ድርጅት ሲዳከም ተዳክሞ ይቀራል፣ ሲፈርስም ፈርሶ ይቀራል። የተጠቀሰው ታሪክም ይሄንን ያስረዳል። ስለዚህ የአማራ ማንነት አስተማማኝነቱ ለራሱ ለድርጅቶቹም ጭምር ስለሆነ የግድ አስፈላጊ ነው። የአማራው የማንነት መጠናከርም ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ የህልውና አደጋ እንዳይከሰት ያደርጋል። ይሄ የማንነት ማደግ ህዝቡ ለራሱ ያለው ፍቅር እንዲጨምር ያደርገዋል። የህዝቡ ፍቅር ለራሱ መጨመሩ ደግሞ በጋራ ለመታገል ትልቅ እና አመች በር ይከፍታል። ማንኛውንም ህዝብ ላይ የሚደቀን አደጋም ተረባርቦ ለመቀልበስ ያስችላል። የማንነት ማደግ ለእያንዳንዱ አማራ ማንኛውም አማራ ጠበቃ የመቆምን እድል ይፈጥራል። ይህም የጥቅም፣ የደህንነት እና የህዝባዊ እንክብካቤ እድል ይፈጥራል። እስካሁን የተነፈግነውን እድል በዚህ መልኩ እናገኘዋለን ማለት ነው። ማንነቱ ጠንካራ ህዝብ የተከበረ፣ የታረማ የተፈራ ይሆናል።

ይህ የአማራ በአማራነት መቆም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመወሰን ትልቅ አቅም ይፈጥራል። እስካሁን የመጣንበትን መንገድ ስናይ አማራው የራሱ ፖለቲካዊ ተክለ ሰብእና ኖሮት በፖለቲካዊ አውዱ ልተሳተፈም። ይሄም ትልቅ ጎደሎ ክፍተት ከመፍጠሩም በላይ የአማራውን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፣ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል።

አማራው ሲከሰስበት የነበረውን የጎደፈ ፖለቲካዊ ውዥንብር ለማጥራት እና የአማራ ህዝብ ምንም አይነት ብሄራዊ በደል ያላደረሰ መሆኑን የምናረጋግጥበት አንዱ እና ዋናው መንገድም ይሄው ነው። እስካሁን ድረስ አማራው ለሚከሱት አክራሪ ብሄረተኞች አማራው እንደ አማራ በቆመ ፖለቲካዊ ተክለ ሰብእና ተመልሶ አያውቅም። ሲደረግ የነበረው ምንድነው ልክ እንደ ውጫሌ ውል አንቀጽ አስራ ሰባት ለአማራው በትክክል ያልቆሙ ምናልባትም አማራውን በመቀየም እና አማራው ላይ በማሴር ከአክራሪ ብሄረተኞች ያላነሰ ሚና ያላቸው አካላት በአንድነት ሰበብ ሲያድበሰብሱ ነው የቆዩት። እንደ አማራ ሆኖ የሚመጣውን ጥያቄ ለመመለስ፣ እና የህዝቡን ስም በአጉል መጥፋት ለመቀልበስ የአማራ በአማራነት መቆም ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። አማራ ላይ የሚሰነዘሩ ማናቸውንም ነገሮች እንደአማራ ሆኖ መከራከር ይገባል። የአንድነት ፖለቲካ ኢትዮጵያን ወክሎ ወይም በኢትዮጵያዊነት ስም እንጅ ለአማራው በእጅ አዙር ሊናገርለት አይችልም። የአንድነት ቡድኑ ለአማራው መናገር እና የአማራን ጥቅም ማስከበር አይችልም። አግባብ አይደለም። አደረጃጀቱና አሰላለፉም አይፈቅድም። በዚህም ምክንያት የአማራን ችግር በአንድነት ስም ማዳፈን ትልቅ ስህተት ነው።

የአማራ በአማራነት መቆም አማራ ላይ የሚደርሰውን ክስ የሚያስቆምበት እና ህዝቡ ሳያፍር ሳይፈራ መብትና ጥቅሙን እንዲያስከብር ያደርገዋል። የኢትዮጵያ ፍሬዋ ብቻ ሳይሆን መከራዋ ለሁሉ መከፋፈል አለበት። ሁሉም የድርሻውን ጸጋ፣ የድርሻውን መከራ መካፈል አለበት። ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአለሙም በደስታውም እኩል ተሳትፎ ሲኖራቸው ለሀገራቸው የሚኖረውን ዋጋ ይጨምረዋል። የአማራ አገር እያሉ ለጥቃት ማጋለጣቸውም ይቆማል። በዚህ ረገድ የአማራ የራሱን ድርሻ ብቻ መውሰድ ሌሎችም በጋራ እንዲተባበሩ ስለሚያደርግ ለወደፊት ገንቢ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

እዚህ ላይ ግን መጠቀስ ያለበት አንድ ነገር አለ። በአማራነት እንቁም ሲባል የሚደነብሩ ብዙ አካላት አሉ። አክራሪ ብሄረተኞች በፍርሀትና በስጋት ይጠሉታል። አማራ የራሱን አጀንዳ ይዞ ከተነሳ የእኛ ስኬት ችግር ላይ ይወድቃል በሚል ይፈሩታል። እንደፈለጉ የሚፈነጩበት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ አውድም ይጠባቸውና ወደእውነተኛው ንግግር እንዲመጡ ያስገድዳቸዋል። በኢትዮጵያ አንድነት ፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱትም ይፈሩታል። የአማራው በአማራነት መነሳት የእነሱን ይዞታ ያሳሳዋል ብለው ስለሚሰጉ። በጣም የሚገርመው አማራ ሆነው አማራነቱን የሚፈሩት ሰዎች ጉዳይ ነው። አማራ ስትል ኢትዮጵያስ ይላሉ። በእውነት በአማራነት መቆም የትግል መንገድ እንጅ የዜግነት ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ዜግነት እንጅ ከአማራነት ትግል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። እነሱ ግን ዜግነትና ትግል በመቀላቀል ብዙ ውዥንብር ሲፈጥሩ ይስተዋላል። አማራነት በቀጥታ ኢትዮጵያዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ይመስላቸዋል። የሚስቱት ነገር ግን አለ። አንደኛ የአማራን ትግል የፖለቲካ ትግል አድርገው ይረዱታል። ሁለተኛ አማራው ያለበትን ነባራዊ ችግር አይገነዘቡትም። ከዚህ የተነሳ ይፈሩታል። ይሄ ፍርሀት ግን መሰረተቢስ ነው።

በአማራነት መቆም አስፈላጊነቱ የሰብአዊነት ጉዳይ ነው። እንኳን የተወለድንበት ህዝብ ሌላ ማኛውም ህዝብ አማራ የገባበትን አይነት መከራ ውስጥ ሲገባ አብረን መሰለፍ ይገባናል። ለአማራነት መታገል ለሰው ልጆች ደህንነት መታገል ነው። በአማራነት መቆም ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው። ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች እንደሚባለው ማንም ከሰው ውጭ የሆነ ፍጥረት ሁሉ የገዛ ወገኑ ችግር ላይ ሲወድቅ ይከላከላል። ለአማራ መቆምም በዚህ አይነት የፍጥረት ማስቀጠል ህግ የተመሰረተ በመሆኑ ትክክለኛ ነው። እዚህ ላይ መወቀስ ያለበት በአማራነት የቆመው የተፈጥሮን ህግ እየፈጸመ ያለው ሳይሆን ከተፈጥሮ ህግ ውጭ ሆኖ ዳር ቆሞ የሚመለከተው ብቻ ነው። ከተፈጥሮ ህግ አንጻር የእነዚህ ራስ ወዳዶች እና ለሌላው የማይቆሙ ተደርገው ይወሰዳሉ።