ዐምሐራ – ነፃ ህዝብ!

Print Friendly, PDF & Email

(ቬሮኒካ መላኩ)

ዛሬ ስለ አማራ ልፅፍ ተነሳሁ ምክንያቴ ደሞ እንደ ራስ ደጀን ተራራ የገዘፈውንና የጠነከረውን የአማራ ስነልቡና እንሰብረዋለን ወይም ሰብረነዋል ብለው የሚያስቡ ደካሞች ካሉ ምኞታቸው ከንቱ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው ። ዘፋኙ “ይሞክሩኛ” እንዳለው አማራን ስነልቡና ይሰበራል ብሎ ማሰብ እና መሞከር እንቁላልን ቋጥኝ ላይ ወርውሮ ነጥሮ ይመለስልኛል ብሎ እንደ ማሰብ የሚቆጠር ነው።

” የወደፊቱን መተንበይ አልፈልግም ፣ ግን አንድ ነገር ብቻ ማለት እፈልጋለሁኝ ።አራት ወራት ሙሉ ከዚህ በአለም ወደር ከማይገኝለት የአማራ ህዝብና ሰራዊት ጋር ስኖር የራሱ የሆነ ከፍተኛ ክብርና ድስፕሊን ያለው መሆኑን እመሰክራለሁ ። ይህ ህዝብ የውጊያ ቅልጥፍና ፣ የዘመቻ ኑሮና የጦር ታክቲኮች ከደሙ ጋር ተዋህደዋል ። ይሄን ህዝብ እግዚአብሄር ይርዳው ። “ አሌክሳንደር ቡላቶቪች ( With the army of Menilik) .

አንባቢዎቼ ረዘም ያለ ፅሁፍ ሊያሰለቻቸው ይችላልና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ ። “ስምን መለአክ ያወጣዋል” የሚባል ብሂል አለ ። ለካ ይሄ አባባል ለግለሰብ ስም ብቻ የተባለ ሳይሆን ለህዝብም ነው። በተለይ ለአማራ (አምሃራ) ህዝብ ።

አምሐራ ወይም አማራ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰው ከ 3000 አመታት በፊት ሲሆን” “አምሐራ” የሚለው ስም ከሁለት ቃላት ማለትም “ዐም” እና “ሐራ” የተፈጠረ ነው ።

“ዐም = ሕዝብ ማለት ሲሆን “ሐራ = ነፃ” ማለት ነው ። አምሐራ (አማራ) ማለት “ነፃ ህዝብ ” ማለት መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል ።

የአማራ ህዝብ የስሙ ትርጓሜ እንደሚያመለክቱት ነጻነት በገንዘብ የማይተምኑት፣ በስጦታ የማይደለሉለት የሰው ልጅ ፍላጎት ነው ብሎ በፅኑ ያምናል። ድህነት፣ ማጣት፣ ችግርና የመሰለው ምንም አይነት መከራ ቢመጣ አማራዎች ነጻነትን ለድርድር እንዲያቀርቡ አያደርጋቸውም። ነጻነት ክብር ነው፤ ክብር ደግሞ በምድር ላይ ለሰው ልጅ የተሰጠ ጸጋ ነው። ይህን ደግሞ ከምንም ከማንም በላይ አማሮች ያውቁታል።ለዘመናት ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋ ግንባሩ ታጥፎ የማያውቀው ጦረኛው የአማራ ህዝብ በነፃነቱ ድርድር እንደማያውቅ አስመስክሯል ።

ታሪክ ምስክር ነውና የአማራን ህዝብ የነፃነት እና የአይበገሬነት ስነልቡና እየነቀስን እንተርከው ። በ 19ኛው ክዘ አጋማሽ ላይ ለአፍሪካ የወደፊት እድል ወሳኝነት ያላቸው ሁኔታዎች በመከሰት ላይ ነበሩ ። በዚህ አንገብጋቢ ወቅት አፍሪካ በነጮች ተከፋፍላ ስትያዝ በብቸኝነት ነፃነቷን ያስከበረችው አገር ኢትዮጵያ ነበረች ። በዚህ የኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ ውስጥ የአማራ ህዝብ የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ የአገሩን ነፃነት አስከብሯል ። በዚህ ወቅት ነበር እንግድህ የተለያዩ የምእራባውያን ፖሊሲ አውጭዎች “የአማራ ህዝብ ካልጠፋ ወይም የነፃነት ስነልቡናው ካልተሰበረ ኢትዮጵያን መጠቅለል አይቻልም” በማለት የደመደሙት።

በ 1930 ዎቹ በአዲስ አበባ ተመድቦ የነበረው የምእራባውያን ወኪል የነበረው ባሮን ሮማን ፕሮችዝካ ለአውሮፓውያን ባቀረበው ሪፖርቱ እንድህ በማለት ገልፆት ነበር :…

“አውሮፓውያን መንግስታት ልብ ብላችሁ ስሙኝ። በምሳራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አማራ የተባለው ህዝብ በፍጥነት መፍትሄ ካልፈለግንለት ለአውሮፓውያን ህዝቦች ከፍተኛ አደጋ ነው። በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የእኛ የነጭ ዘሮችን ፍላጎት ካለምንም ችግር ለማሳካት ከተፈለገ በአማራ ላይ የምንከተለው ፖሊሲ ማውጣት አለብን።” የሚል ሪፖርት ለአውሮፓ መንግስታትና ለአሜሪካው የመረጃ ድርጅት ልኳል።

ባሮን ሮማን ፕሮችዝካ ( Abyssinia the powder Barrel , Publisher British International news Agency 1936)።

ሌላው ለዘመናት የአማራ ህዝብን የነፃነት ስነልቡና ለመስበር አውሮፓውያን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንና ያደርጉ እንደነበር የሚያሳየን መረጃ የሚገኘው ከታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ስባኪ መፅሃፍ ነው ።

አልቤርቶ ሰባኪ Ethiopian under Mussoloni and Fascist experience በሚል ርእስ በፃፈው መፅሃፉ እንደሚከተለው ይላል :…

“ኢትዮጵያን በኢጣልያ መያዝ ለማፋጠን ሲሉ ኢጣልያኖች የውስጥ ቅራኔንና ጥላቻንና ግጭትን ለማባባስ አማራ ያልሆኑ ጎሳዋችን በማሳመፅ ለመጠቀም ብዙ ሞክረዋል ።”

መፅሃፉ ይቀጥልና መጀመሪያውኑ ኢጣልያ ከአማሮች ተቃውሞ እንደሚኖር ጠብቀዋል ። ለዚህ የኢጣልያ ስጋት አንዱ ምክንያት አማሮች አላቸው የሚባለው የወታደራዊ ጀግንነት ታሪክ ነው ።

ግራዚያኒ …… “አማሮች ምንም እንኳን ለጊዜው ያመኑ ቢመስሉም አመች ጊዜ መርጠው ለማጥቃት አድብተው ይጠባበቃሉ” በማለት የየአካባቢው ገዥወች አማሮችን እንዳጠፉ መመሪያ ሰጥቷል። ይሄ ሁሉ ግፍ በአማራ ላይ ተፈፅሞበት የአማራ ህዝብ ስነልቡና ጢም እንዳለ ነበር። ይሄን የነፃነት ስነልቡና ፈፅሞ መስበር አልቻሉም ።

አልቤርቶ ስባኪ ይቀጥላል

ኢጣልያኖች አማሮችን በኦሮሞዎች ፊት ለማሰቃየት ቢሞክሩም እንኳን ጥቂቶች አማሮች በነበራቸው የፖለቲካ ብስለት የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ችለዋል። እንደ እውነቱ አማሮች ችላ ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች አልነበሩም። በነበረባቸው ተፅእኖ ሳይዳከ መንፈሰ ጠንካሮች ሆነው በህብረተሰቡ ውሥጥ የነበራቸውን እንዳለ ለማቆየት ችለዋል።

ሌሶና ኢትዮጵያን በጠቅላይ ግዛት ሲያዋቅር አማሮችን በመንግስት መስሪያ ቤቶች መቅጠር ከልክሎ ነበር (ወያኔም የሌሶናን ፖሊሲ ተከትላለች)።

ኢጣልያኖች አማሮችን ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ቅራኔ ውስጥ በማሥገባትና ፀረ አማራ ፖሊሲ በመከተል በመከተል በራሳቸው ላይ ተቃውሞ አጠናክረዋል።” እያለ የዚህን ተአምረኛ ህዝብ አይበገሬነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገር ዘንድ ከትቦት አልፏል።

የፋሽስት ሙሶሎኒን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሸምድዶ በኢትዮጵያ ላይ የተገበረው አምባገነኑ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም፡ በአንድ ወቅት

“ኦርቶዶክስንና አማራን ካላጠፋን መሪት ትክበዳቸውና መቸም አገሪቷን በምንፈልገው መንገድ መምራት አንችልም።” በማለት የአማራን አይበገሬነት ተንፍሶ ፍግም ብሏል። ይሄ የመለስ ንግግር ከባሮን ሮማን ፕሮችዝካ እና ሩዶልፍ ግራዚያኒ ስለ አማራ ከተናገሩት የተኮረጀ እንደነበር በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

አሁን ወደ ፅሁፌ መደምደሚያ እየደረስኩኝ ነው። የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ከአራት ሺ በላይ ዓመታት ባስቆጠረው ያልተቋረጠ ረዥም ታሪኩ በርካታ የጨለማ እና የብርሃን ዘመናትን አሳልፏል። ብዙ ጊዜ ወድቆ ተነስቷል። አለቀለት ሲባል አገግሟል። ጠላቶቹ ቀብረነዋል ሲሉ ነፍስ ዘርቷል። ያን ሁሉ ዘመን በውጣ ውረድ ሲያሳልፍ አንድም ቀን ለአንድም ሰከንድ የስነልቡና መውደቅ አጋጥሞት አያውቅም። እንደውም ለሌሎች መሰል ህዝቦች በአርአያነት የሚጠቀስ የአይበገሬ ስነልቡና ተምሳሌት ሆኗል።

አማራ ድሮም በፋሽስት ጣሊያን ዛሬም በፋሽስት ወያኔ በደል ቢደርስበትም ሚስማር ሲመቱት እንዲጠነክር በደሉ የህዝቡን ወኔ ይባስ ቀሰቀሰው እንጂ ወደኋላ አልመለሰውም።

ተስፋ ሊያስቆርጡ የሚችሉ እጅግ በርካታ ምክንያቶች ቢደረደሩም ክብርና ነጻነትን ማቆየት ግን ከሁሉ በልጠው አመዘኑ። የአማራ አይበገሬ ስነልቡና እንደ አልማዝ አንፀባራቂና የማይሰበር ሆኖ ወጣ ።

ዛሬስ?

ዛሬም ቋንቋ ያልተደባለቀባቸው፣ ቀለማቸው ያልደበዘዘ ባቸው፣ ባህል ያልተሰወረባቸው፣ ውበታቸው ያልተበረዘባቸው የራሳቸው ማንነት ያልጠፋቸው ልጆቻቸው ያለአንዳች ሃፍረት አንገታቸውን አቅንተው በኩራት እንዲቆሙ ሆነዋል። እነዛ ብርቱ አማሮች የኢትዮጵያዊ መልክ ይቀየር ዘንድ ለጠላት እጅ አልሰጡም፤ አልፈቀዱምና። እንደ ስማቸው ነፃ ህዝቦች ናቸውና ። እመኑኝ! ይህቺ በደም የቆየች የአማራ የነፃነት አይበገሬ ስነልቡና መቼም አትሰበርም ።

ታሪክ ሙት አይደለም።አይሞትም።ታሪክ የሚሞተው በታሪክ ሰሪው ትውልድም ሆነ በተከታዮቹ በወጉ ተመዝግቦ ሳይቀርብና ተረካቢ ትውልድ ሲያጣ ብቻ ነው። የአማራ ህዝብ ታሪክ ደሞ ትናንትም በአባቶቻችን ቀለም ተበጥብጦ ብራና ተፍቆ ዛሬም በውድ ልጆቻቸው ዘመኑ በሚፈቅደው ላይጠፋ ከዘመን ወደ ዘመን ሊሸጋገር ተከትቧል ። አኩሪ ታሪካችን የጠንካራው ስነልቡናችን አንዱ ምንጭ ነው ። የአማራ ታሪክ እና ስነልቡና ሁሌም ዘመን ተሻጋሪ ነው።