ወያኔ አማሮቹን መቀሌ ላይ አፍኖ በመደብደብ ምን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አሰላ?

Print Friendly, PDF & Email

በትግሬ ወያኔ በመቀሌ የተደበደቡ የአማራ የእግር ኳስ ተጫዋቾች

(ሸንቁጥ አየለ)

መግቢያ

መጀመሪያ መግባባት ያለብን ነጥብ አለ። አሁን አማሮቹን የሚደበድባቸዉ እና የሚያስደበድባቸዉ ማን ነዉ በሚለዉ ጥያቄ ላይ መግባባት ያስፈልጋል። ከጥቂት ወራት በፊት የኦሮሞ ተጫዋቾችን ባህርዳር ላይ በአማራ እንደተደበደቡ አድርጎ ድራማ የሰራዉ ወያኔ መሆኑን በወቅቱ ብዙ ወገን አብራርቶ አቅርቦታል። በዚያዉ ጉዳይ ላይ እኔም አንዲት አጭር ጽሁፍ አቅርቤ ነበር።

ወያኔ ሳያዉቅ አንዳችም እንቅስቃሴ በሀገሪቱ አትከናወንም። በሜዳም ሆነ በጓዳ። ለምሳሌ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አንድ አስገራሚ ምስክርነት ሰጥተዋል። በ1984 ዓም ወያኔ በአርሲ፣ በሀረር እና በመላ ሀገሪቱ ላይ ይታረዱ ይፈጁ እና ይፈናቀሉ የነበሩ አማሮችን የገደላቸዉና ያፈናቀላቸዉ ኦነግ ብቻዉን ነዉ እያለ የነዛዉን ፕሮፖጋንዳ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከወያኔ ፕሬዝዳንትነት ሲባረሩ እዉነቱን ፍርጥ አድርገዉ አዉጥተዉታል። እሳቸዉ እንዳብራሩት “አማሮቹን የፈጃቸዉ ኦነግ ብቻ ነዉ የሚባለዉ ሀሰት ነዉ።”

ሲያብራሩም “የኢህአዴግ ሰራዊት አማሮቹን በማፈናቀል፣ በመግደል እና በመረሸን ዋናዉ ተዋናይ ነዉ። በዚህ ሂደትም ዉስጥ እኔም እራሴ ስለነበርኩበት ስላጠፋሁት ጥፋት ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሀላፊነቴንም እወስዳለሁ” ሲሉ አብራርተዉ ነበር። ወያኔ አሁን ድረስ የሚያናፋዉ አማሮቹን ኦነግ ብቻዉን እንደገደላቸዉ ነዉ። ሆኖም ለኦነግ መመሪያዉን የሰጠዉ፣ አማሮቹንም ከቦ በመጨፍጨፍ ዋናዉን ስራ የሰራዉ ወያኔ እራሱ ነዉ። በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩ ሰዉ ቁልጭ አድረገዉ መስክረዋልና።

ወያኔ ሳይፈቅድ እና ሳያዉቅ አንዳች ነገር በኢትዮጵያ ጥላ ስር አይደረግም። በደቡብም፣ በምስራቅም፣ በጦር ሜዳም፣ በፍጅትም፣ በሰላምም ሆነ በኳስ ሜዳ ወያኔ ሳያስተባብረዉ እና ሳያቅደዉ ብሎም ሳያጸድቀዉ የሚከናወን አንዳች ነገር የለም።

ግን ጥያቄዉ ለምን? የሚል ነዉ። ወያኔ ከአማሮቹ መገፋት፣ መፈናቀል እና ስቃይ ምን ያተርፋል? የሚል ነዉ።

ወያኔ እንደ ወያኔ ለመቀጠል ከፈለገ ይሄን ከማድረግ የተሻለ ሌላ አማራጭ የለዉም። እንዴት?

ወያኔነት በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነዉ።

1. ጸረ አማራነት፣ ጸረ የአማራ መደብ እና አማራነትን የመታገል ምሠሶ

ወያኔ በ1968 ዓ.ም. የቀረጸዉ ማኒፌስቶዉ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግስት ሲቆጣጠርም የቀረጸዉ ህገመንግስትም በዋናነት የሚያጠነጥኑት ጸረ አማራነት፣ ጸረ የአማራ መደብ እና አማራነትን የመታገል ምሠሶ ላይ የቆመ ነዉ። ይሄ መርህ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ በወያኔ ደጋፊዎች እና አባላት ዉስጥ አይሰርጽም። ትግሉ ከጸረ አማራነት፣ ከጸረ የአማራ መደብ እና አማራነትን ከመታገል ጋር ነዉና ዋና የወያኔ ህልዉና የተንጠለጠለዉ በዚችዉ ስትራቴጅ ላይ ነዉ።

በዋናነትም አማራዉ በአባቶቹ ሀገር ኢትዮጵያ ላይ ወራሪ ነዉ ተብሎ እንዲፈረጅ የሚያስችል ህገመንግስት መቀረጹ እና አማራዉን ሙሉ ለሙሉ በጠላትነት የፈረጀ ስትራቴጅ በሀገሪቱ መቀረጹ አንዱ ነዉ። ለምሳሌ አንድ የዋህ በ1998 ዓ.ም. እነ ተፈራ ዋልዋ እና እነ አዲሱ ለገሰ በሚመሩት የህገመንግስት ዉይይት መድረክ ላይ አንድ ጥያቄ ጠዬቀ። “ለምን መሬት የህዝብ አይሆንም? መንግስት መሬት የህዝብ ቢሆን ምን ይጎዳል?” አቶ ተፈራ የሚባለዉ ሰዉዬ ለዚህ ጉዳይ መልስ ሲሰጥ በጣም እርግጠኛ እና ፈጣን ሆኖ ነበር። “እኛ ህገ መንግስታችንን የጻፍነዉ አማራዉ ወደ ስልጣን ተመልሶ እንዳይመጣ በሚያስችል መልኩ ነዉ። አሁን ለምሳሌ መሬት የህዝብ ይሁን ብንል በከተማ የሚኖርዉ ገንዘብ ያለዉ አማራ እንዲሁም ብር በጁ ላይ ያለዉ ጉራጌ መሬቱን እየገዛ ሀብታም ይሆንን እና መልሶ በሂደት ወደ ስልጣን ይመጣል።” አቶ ተፈራ ዋልዋ የሚባለዉ ሰዉዬ በእርግጠኝነት ለዚያ የዋህ ሰዉ መለሰለት።

እናም ከህገመንግስት እስከ ማኒፌስቶ ብሎም እስከ እያንዳንዱ ድርጊት የሚወሰደዉ እርምጃ ጸረ አማራነት፣ ጸረ የአማራ መደብ እና አማራነትን የመታገል ምሠሶ የሚሉትን እስትራቴጅ በሚያረጋግጥ መልክ ነዉ። ይሄ ስትራቴጅ በደጋፊዎቹ ዘንድ አሁንም እየተተገበረ መሆኑን ለማስታወስ ልዩ ልዩ ተግባራት ይተገበራሉ። የኳስ ሜዳዉ እርምጃም አንዱ ነዉ። ደጋፊዎቹ እንዳይዘናጉበት። ልባቸዉ ከጸረ አማራ ትግል እንዳያርፍበት።

2. ኢትዮጵያዉያን አብረዉ እንዳይቆሙ ማረጋገጥ እና ጸረ ኢትዮጵያዊነት ስትራቴጅን አስፋፍቶ ማራመድ

ወያኔ ኢትዮጵያዊነት እርሱን ካልጠቀመዉ አፈር እንዲበላ የወሰነዉ ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ ብቻ ሳይሆን ቀደም ባሉት የቀዳማይ ወያኔ እና ሁለተኛዉ ወያኔ እንቅስቃሴዉ ጭምር ነዉ። ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ብሎ ሲወስን የትግራይ ህዝብ መገንጠል እናዳለበት፣ ኢትዮጵያም መፈራረስ እንዳለበት የወሰነዉ ከ1968 ዓ.ም. ማኒፌስቶዉ በፊት ነዉ። እናም ኢትዮጵያዉያን አብረዉ እንዳይቆሙ ማረጋገጥ እና ጸረ ኢትዮጵያዊነት ስትራቴጅን አስፋፍቶ ማራመድ ዋናዉ የወያኔ የቤት ስራዉ ነዉ።ኢትዮጵያዉያን የማይግባቡበት ታሪካዊ እርምጃ እየተጠና ይተገበራል።ህዝቡ እንዲቃቃር እና እርስ በርሱ በጥርጣሬ እንዲተያይ ወያኔ ሳያሰልስ ይሰራል። ይሄ አስተሳሰብ እንዳይዘነጋ በህዝቡ መሃከል በርካታ ተንኮሎች እየተገመዱ ይተገበራሉ። አሁን የተድረገዉም ይሄዉ ነዉ። ጎንደር ላይ አማሮች ያልነኩትን የትግራይ ማህበረሰብ ወያኔ እራሱ አንዳንድ አርምጃዎችን በመዉሰድ አማሮች የትግራይን ህዝብ አጠቁ የሚል ፕሮፖጋንዳ በመንዛት በሁለቱ ማህበረሰብ መሃከል አስተማማኝ የጥላቻ ድልድዩ አሁንም እንደቆመ ማስረገጫ ጊዜአዊ ስትራቴጅ ወስዷል። በዚያዉም አሳቦ የትግራይን ተፈናቃዮች ካስኳችሁ እኔ ከሌለሁ ትግሬ አለቀልህ በሚል ፕሮፖጋንዳ የትግራይን ህዝብ በጥቅሉ ከጀርባዉ ማሰለፉን የዳሰሳ ጥናት አድርጎበታል።

3. በማህበረሰቦች መሃከል ቋሚ የሆነ የጥላቻ ሀዉልት መስራት

ወያኔ በጣም እርግጠኛ መሆን የሚፈልገዉ የትግራይ ህዝብ ከቀሪዉ ኢትዮጵያ መነጠሉን ነዉ። ለዚህም ወያኔ ለትግራይ አዲስ ታሪክ ጽፏል። ለምሳሌ በወያኔ አባባል የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ፣ የአክሱም ታሪክ እና የቀደሙ ነገስታት ታሪክ በሙሉ አማራ የፈጠራቸዉ ተረት ተረት ናቸዉ። በወያኔ አስተምሮት መሰረት አማራ የትግራይን ህዝብ ታሪክ ነጥቆ እንጅ አማራዉና ትግሬዉ የጋራ መሰረታዊ ታሪክ የላቸዉም። ወያኔ እንደሚሰብከዉ አማራ የሚባለዉ ህዝብ መጤ ሲሆን ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንንም አይነት ታሪካዊ ትሥር የለዉም። በወያኔ የሀሰት ታሪክ መሰረት አማራዉ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ብሄሮች ጠላት ሲሆን ሁሉ ብሄረሰብ ሊያጠፋዉ ይገባል።ይሄ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ብሄሮችም ጋር ምንም አይነት የታሪክ ትስሥር የለዉም።በወያኔ ፍልስፍና መሰረት ኢትዮጵያ መበታተን ሲኖርባት መበታተን የሚኖርባት የጎሳዎች ስብስብ ነች። የወያኔ ህገመንግስት አንቀጽ 39 የዚሁ አስተሳሰብ መገለጫ ነዉ። እናም ወያኔ በዋናነት በየወቅቱ በሚተገብራቸዉ ስትራቴጅዎቹ ማረጋገጥ የሚፈልገዉ ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች እርስ በርሳቸዉ በጥላቻ መተያዬታቸዉን ሲሆን በዋናነትም የትግራይ ህዝብ ከወያኔ ጉያ እንዳያመልጥ አስተማማኝ ስልት መቀዬሱን ነዉ።

እና ኳስ ሜዳ ለምን ? አሁንስ ምን ለማግኘት ነዉ?

ወያኔን ሆነን ስናስበዉ በዚህ የአማሮች በመቀሌ መደብደብ ወያኔ ብዙ ያተርፋል። ይሄዉም

1. አማራዉ እና የትግራይ ህዝብ በአስተማማኝ መነጣጠላቸዉን ማረጋገጥ አለበትና እያደረገ ነዉ።

2. የትግራይ ህዝብ አሁንም በወያኔ የሀሰት ስብከት እንደተማረከ እንዲቀጥል የአማራን የጠላትነት ስብከት መልሶ ማደስ አለበት። በዚህም የትግራይ ፖለቲከኞች እና ምሁራን በአንድ በመሰባሰብ ከወያኔ ዉጭ አማራጭ የለንም የሚለዉን ድምዳሜያቸዉን በማደስ ከወያኔ ዙሪያ እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል።

3. እያንዳንዱ ብሄረሰብ በአስተማማኝ መለያዬቱን እርገጠኛ መሆን ይፈልጋል። ለምሳሌ ወያኔ የራሱን ካድሬዎች በባህርዳር እግር ኳስ ሜዳ አሰማርቶ ኦሮሞዎቹን ተጫዋቾች በመደብደብ አማራ ደበደባቸዉ በማለት የኦሮሞ ህዝብ እና የአማራ ህዝብ መለያየቱን ማረጋገጥ ነበረበት።

ሌላዉ ማሳያ አዲስ አበባን ሆን ብሎ ለኦሮሞ ብቻ እንደሆነች የሚያሳይ አዋጅ ነገር በጎን ለቆ ሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች እና ኦሮሞዉ እንዲጠላሉ፣ እንዲጨቃጨቁ እና የጎሪጥ እንዲተያዩ ብሎም ከተቻለ እርስ በርስ እንዲጫረሱ የተራቀቀ የቤት ስራዉን እየሰራ ነዉ። በተመሳሳይም በአሁኑ ሰዓትም በርካታ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎችን ለሶማሌ በመሰጠት ሶማሌዉ እና ኦሮሞዉ ከፍተኛ ጥላቻ እና ፍጥጫ ዉስጥ እንዲገቡ እየሰራ ነዉ።ወያኔ አንድ ነገር ማረጋገጥ አለበት። ይሄዉም ሌሎች ማህበረሰቦች እርስ በርሳቸዉ ስለመፋጠጣቸዉ እርግጠኛ መሆን።

4. አቅጣ ማስቀዬሻ አጀንድዳዎችን በጭካኔ እና በድፍረት ይተገብራቸዋል። ወያኔ አንድ ልዩ ችሎታዉ ማንኛዉንም ጨካኝ እና ደፋር አቅጣጫ ማስቀየሻ ስትራቴጂ እና ታክቲክ ያለማወላወል መተግበሩ ነዉ። በአሁኑ ወቅት በህዝባዊ አመጽ ተቀስፎ የተያዘዉ ወያኔ አስተማማኝ የአቅጣጫ ማስቀዬሻ መፈለግ እንዳለበት ያዉቃል። በተለይም የአማራ ወጣቶች ማህበራዊ ሚዲያዉን በመቆጣጠር ወያኔን በስነ ልቦና ጦርነት መተንፈሻ እያሳጡት ነዉ።

ይሄም ወያኔን አስጨንቆታል ብቻ ሳይሆን አሳስቦታል። ስለዚህ የሆነ የቤት ስራ መስጠትና ከመሰረታዊ ጉዳዮች ይልቅ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ይፈልጋል።በዚሁም የትግራይ ወጣቶች በሙሉ ጉልበታቸዉ ከአማራ ወጣቶች ጋር ግብ ግብ እንዲገጥሙለት ፈልጓል። ለምሳሌ በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ተጋድሎ እና በኦሮሞ ተቃዉሞ መሀከል የመግባባት ዝንባሌ በታዬበት ጊዜ እና ወያኔ በተወጠረበት ወቅት ኦሮሞዎቹን እራሱ ወያኔ ባህርዳር ላይ በካድሬዎቹ በማስደብደብ አማራ ደበደባችሁ በማለት የሀሰት ወሬ ሲነዛ በርካት አማራ እና ኦሮሞ ታጋዮችን አቅጣጫ በማስቀዬስ የርስ በርስ ጭቅጭቅ ዉስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዉ ነበር። ወደ አንድ ሊመጣ እያቅማማ የነበረዉም ትግል በዚህ ወቅታዊ የወያኔ ማስቀየሻ ስልት እንዲሁም የኦነግ ሰዎች ኢትዮጵያን እንበትናታለን ብለዉ ይዘዉት የመጡት አጀንዳ የአማራዉን እና የኦሮሞዉን መግባባት ድራሹን አጥፍቶ ለወያኔ በቂ እፎይታ ሰጥቶታል።

ወያኔ ሞኙ ተንኮል አማኙ?

የሆኖ ሆኖ የወያኔ ደባ እና ተንኮል እራሱን ወደ መቀመቅ የሚከት እንደሆነ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። አሁንም አማሮቹን ተጫዋቾች መቀሌ ላይ በመክበብ የደበደበበት እና ያስደበደበት የተንኮል ስልቱ እራሱን ወያኔን የሚበላዉ ይሆናል። በአጭሩ ወያኔ ሞኙ ተንኮል አማኙ ብሎ መዝጋት ይቻላል። ጥበብ እና ማስተዋል: ህዝባዊ ፍቅር እና ሁል አቀፍ ህዝባዊነት ከወያኔ ልብ የተነጠቀች ናትና የወያኔ መነሻዉም፣ መድረሻዉም ያችዉ ተንኮሉ ነች። ይህች ተንኮሉ ግን እራሱን ትበላዋለች። በሀዋርያት አንደበት እንደተባለዉም፡-

“አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፣ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፣ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? (ሐሥ. 13: 10)” ተብሎ ቢገሰጽም ወያኔ ከተንኮሉ ጋር እስኪጠፋ ከቶም አያርፍም።

በኢትዮጵያ ህዝብ መሀከል አንገትህን ቀና አድርገህ የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ መጨረሻዉ የመጠፋፋት ጠርዝ ለመዉሰድ የተሰለፍክ የዲያቢሎስ መንፈስ እና የዲያቢሎስ ፈረሶች ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እና ሀይል የተመታችሁ ሁኑ። የእግዚአብሄር ስዉር ጣት እናንተን ቀድማ ታጠፋለች እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብስ ወደ እርስ በርስ መጠፋፋት አይገባም !

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አይዞህ! የተሰበረ ልብህን እግዚአብሄር ይጠግነዋል!