“ቆስቋሽ—” – የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)

Print Friendly, PDF & Email


ቅጽ 1፣ ቁጥር 2    ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም

“ቆስቋሽ—” ( pdf )

“በዕውቀት ሥልጣኔ ግሎ ለመነሣት፣
ቆስቋሽ ይፈልጋል፣ የሰው ልጅ እንደ እሣት።”

ይህን ዘመን ተሻጋሪ እና የመሪን አስፈላጊነት በተመጠኑ ቃላቶች፣ በማይወይብና ጊዜ በማይሽረው መልኩ ከሽነው ለትውልድ እንዲተላለፍ ያደረጉት ከስልሳዎቹ ትውልዶች ጀምሮ ወደታች ያለውን ትውልድ በቀለም ኮትኩተው ካሳደጉት የዕውቀት ቀንዲሎች መካካል አንዱ የሆኑት ከበደ ሚካኤል ናቸው። የጽሑፉ ዓላማ ከበደ ሚካኤልን ለማስተዋወቅ አይደለም። ከበደ በሥራዎቻቸው “ጃፓን እንዴት ሰለጠነች፣ ታላላቅ ሰዎች፣ የዓለም ታሪክ፣ የዕውቀት ብልጭታ፣ ታሪክና ምሳሌ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ” መጽሐፎቻቸው ይታወቃሉና ከነዚህ ሥራዎች በተሻለ ከበደ ሚካኤልን የሚያስተዋውቅ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ርዕሱ ለተነሳንበት ዓላማ መነሻ እና መንደርደሪያ ለማድረግ ተስማሚ በመሆኑ የሀሳቡን አመንጭ አስታውሶ ለማለፍ ሙከራ የተደረገበት ነው።

ለማንኛውም አዎንታዊ ለውጥና ሕዝብ አሳታፊ ለሆነ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ፣ የሕዝቡን ፍልጎት በሚገባ ተረድቶ፣ ለውጤት በሚያበቃ መልኩ ወደፊት ዓላማውን ለመግፋት፣ የተቀጣጠለ እሣት እንዳይጠፋ፣ መንደዱን እንዲቀጥል ለማድረግ፣ መቆስቆስና እየነደደና “ብርሃን እየሰጠ” ያለው ምድጃ መልሶ ድርግም እንዳይል አስፈላጊውን ሁሉ ማገዶም ይሁን ነዳጅ እንዲያገኝ ማድረግ አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፣ የተቀጣጠለን፣ የተነሳሳን፣ ጭቆና እና አድልዎ በዛብን፣ ለውጥ እንሻለን ብሎ የተነሳን ሕዝባዊ እንቢተኝነት፣ ወደ ተፈላጊው ግብ ለማድረስ፣ የጎደለውን እየሞላ፣ የተጣመመውን እያስተካከለ፣ የጎበጠውን እያቃና፣ ያደፈጠውን እየቀሰቀሰ፣ ያልሰማውን እያሰማ ወዘተ ትግሉን እንዲቀላቀል የሚያደርግ ቆስቋሽ ድርጅትና መሪ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።

ጣፋጩን ማር የሚሠራውን የንብ ሠራዊት አበባ ቀስሞ፣ ውኃ ቀድቶ ማሩን ለመጋገር አውራ ያስፈልገዋል። ንብ ያለአውራው እንኳን ማር ሊጋግር አብሮ መኖር አይችልም። ሁሉም ባፈተተው “ጢዝዝ” እያለ በንኖ ጠፊ ነው።
በደረሰበት ተደራራቢ ችግር ከውስጥ ተገፍቶ የተቀጣጠለ ሕዝባዊ እንቢተኝነትም ለድል እንዲበቃ ከተፈለገ፣ እንቅስቃሴውን በጊዜ ቅደም ተክተል አካትቶ፣ ዘላቂውን ከጊዜአዊ፣ ረጅሙን ከአጭሩ፣ ታሪካዊውን ከወቅታዊው፣ ወዳጅን ከጠላት አበጥሮ ለይቶ ከየወቅቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር እያገናዘበ ለትግሉ ግለትና ለድል መብቃት አቅጣጫ እያመላከተ የሚመራ ድርጅት መኖር ምርጫ ሳይሆን፣ የግድ አስፈላጊ ነው።

የግራኝን ወረራ ለማክሸፍ ከልብነ-ድንግል እና ከተከታዮቹ ባለቤታቸው ሰብለወንጌልና ከልጃቸው ገላዲዎስ ቆራጥ አመራር፣ ዘመነ መሣፍንትን ለማስወገድና የኢትዮጵያን አንድነት ለማረጋገጥ ካለቴዎድሮስ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ብልኅነት እና አርቆ ተመልካችነት፣ የዐድዋን ድል ከአባዳኘው ምኒልክና ዕቴጌ ጣይቱ ብልኅ አመራርና ኢትዮጵያዊነት ስሜት መላበስ ውጭ የሚታሰቡ አይደሉም። ለሁሉም ድሎች ሕዝቡ በዙሪያቸው እንዲሰባሰብና ሁሉም የሚችለውን እንዲያደርግ ጥበብ፣ ትዕግሥት፣ ቆራጥነት እና አስተዋይነት የተመላበት ተከታታይ አመራርና ትግሉ እንዳይቀዘቅዝ፣ ኅሊናቸው ሳይረሳ፣ ክንዳቸው ሳይዝል ባደረጉት ቁስቆሳ/ ማነሳሳት፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የተገኙ ሕዝባዊ ድሎች ናቸው።

ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓም በጎንደር የፈነዳው ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንቅስቃሴ ላለፉት 26 ዓመታት የትግሬ ዘረኛ ቡድን በዐማራው ሕዝብ ላይ ያደረሰውና እያደረሰ ያለው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የጎንደር ሕዝብ፣ በተለይም የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ነዋሪ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተቀጣጠለ ሕዝባዊ እንቢተኝነት መሆኑ ግልጽ ነው። ይህም በመሆኑ እንቅስቃሴው ግብታዊ ነው። እንቅስቃሴውን ግብታዊ ነው የሚያሰኘውም፣ በታቀደ፣ በታለመ፣ ግልጽ ዓላማና ግብ፣ ራዕይና ተልዕኮ ኖሮት ባንድ አመራር ሥራ የሚመራ አለመሆኑ ነው። በሌላ አባባል፣ እንቅስቃሴው በነባራዊ ሁኔታዎች መመቻቸት፣ ነገር ግን በኅሊናዊ ሁኔታ አለመሟላት የተፈጠረ እንቅስቃሴ ነው ማለት ነው።

በነባራዊ ሁኔታዎች መመቻቸት የተቀጣጠለ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ግፍ የወለደው፣ ከግፉ ለመላቀቅ ምን ማድረግና እንዴት ማድረግ እንዳለበት በቅጡ ለይቶ የማያውቅ ፣ ለአዎንታዊ ለውጥ ወይም ለተፈላጊው ድል ይበቃል ለማለት አያስደፍርም። እንቅስቃሴውና ተቃውሞው ለተፈላጊው ድል እንዲበቃ፣ ግልጽ ዓላማ፣ የማያሻማ ግብ፣ ከዛሬው ተነስቶ ነገን እንደመስታውት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ተልዕኮና ራዕይ ያለው ድርጅታዊ አመራር ያሻዋል።

ድርጅት ሲባል የሀሳብ አንድነት የወለደው የተግባር አንድነት፣ የማድረግ ብቃትና ቁርጠኝነት፣ የድል አድራጊነትና የብሩኅ ተስፋ ምንጭ የሆነ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ፣ የመረጃ፣ የዕውቀትና የጊዜ ሀብት ውሕድ እንቅስቃሴ ማለታችን ነው። ለአስተማማኝ ድል የሚበቃ ድርጅት የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የመረጃ እና የዕውቀት ሀብት በበቂ መጠን ሊኖሩት ይገባል። እነዚህ ግብዐቶች በአስተማማኝና በበቂ መጠን የሌለው እንቅስቃሴ ካሰበው ግብ ይደርሳል ተብሎ አይታሰብም።

ጊዜ የሁሉም ነገሮች መሽከርከሪያ ምሕዋር ነው። ያለጊዜ ምንም ነገር ሊከናወን አይችልም። ከዚህ ላይ ጊዜ ስንል እንቅስቃሴውን የሚመሩት ሰዎች በትርፍ ጊዜ ሳይሆን በሙሉ ጊዜ ሥራዬ ብለው እንዲሠሩ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ወይም ማመቻቸት ማለታችን ነው። የሕዝብ ነፃነት በትርፍ ጊዜ ተሠርቶ የትም ሊደርስ አይችልም። በመሆኑም ለዚህ ዓላማ የቆሙ ሰዎች ራሳቸውን ያሞኙ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ራስን ማሞኘት ስንልም፣ ልጄ፣ ቤቴ፣ ትዳሬ፣ ንብረቴ የማይሉ፣ አገሬ፣ ወገኔ የሚሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ባንድ ጊዜ ከሁለት ዛፍ ላይ መውጣት እንደማይቻል ሁሉ፣ ቤቴ፣ ትዳሬ፣ ንብረቴ ብሎ አገሬና ወገኔ ማለት በፍፁም ለውጤት አያበቃም። አንዱን መምረጥ የግድ ነው። የዐማራው ጠላቶች ያደረጉት ይህንን ነው። ትምህርታቸውን አቋርጠው፣ ጫማቻውን አውልቀው፣ ትዳራቸውን ፈትተው፣ ከዘመድ አዝማዶቻቸው ተነጥለው «የትግራይ የበላይነት ወይም ሞት» ለሚለው ዓላማቸው ቁርጠኛ ዓላማ ይዘው በርሃ በመግባት ነው ለዚህ ለጨበጡት ሥልጣንና ዐማራውንና ኢትዮጵያን ለማጥፋት ስጋት ለመሆን የበቁት። ከጠላትም መማር ይቻላልና፣ እኛም «ኅልውናችንና ማንነታችን፣ ወይም ሞታችን» ብለን ለወገናችን ቤዛ ለመሆን፣ መቁረጥና አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቅብናል። ያለመስዋዕትነት ድል የለምና!

ገንዘብ ስንል ደግሞ የሁሉም የማድረግና የድል አድራጊነታችን ሞተሩ ገንዘብ ነው ማለታችን ነው። «አባቶቻችን ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ» የሚሉት ያለምክንያት አይደለም። ገንዘብ ጤና ነው፤ ጤንነት ይገዛበታልና! (ሁልጊዜም ባይሆን ቅሉ።) ገንዘብ ኃይል ነው፤ ዕውቀት፣ መሣሪያ፣ ጥበብ፣ የሰው ኃይል፣ መረጃ፣ ወዘተ ይገዛበታልና! ገንዘብ የማድረግ፣ የድል አድራጊነትና የአሸናፊነት መገለጫም ነው። ስለሆነም የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴም ሆነ፣ ይህን ለመምራትና ለማስተባበር የሚያስቡ ቡድኖችና ኃይሎች ለእንቅስቃሴው መልካም ቆስቋሽ፣ አቀጣጣይ ነዳጅ ለጋሺ ለመሆን፣ በቂ የገንዘብ ቋት ያስፈልጋቸዋል።

መረጃ ስንል፣ የእንቃስቃሴዎች ኮምፓስ፣ የማድረጋችን ትክክለኛነት ማረጋገጫ፣ የዓላማችን መዳረሻ አመላካች ሚዛን ማለታችን ነው። እያንዳንዱ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለሚወስዳቸው ርምጃዎች ውጤታማ መሆን፣ ሊወሰድ የታሰበው ርምጃ በተጠናና በተጨበጠ መረጃ ላይ መመሥረት ይኖርበታል። መረጃ የሕይዎት፣ የአካል፣ የንብረት ጥፋትን ተከላክሎ፣ ዓላማን ወደፊት ማራመድ የሚያስችል ሁነኛ መሣሪያ ነው። የሩቁን አቅርቦ፣ የተደበቀውን ግልጽ አውጥቶ፣ የታቀደውን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል አመላክቶ፣ የጠላትን ዓላማ ማርከሻ የሆነውን አስቀድሞ ለማከናወን የሚረዳ፣ የብስሉ ከጥሬው፣ የሐቁ ከሀሳቱ የሚለይበት ወንጠፍት ነው። ስለሆነም የጠላቶቻችን እንቅስቃሴ፣ ዕቅድ፣ ፈጻሚና አስፈጻሚዎችን ማንነት አበጥሮ ማወቅ የግድ ይላል። የዚህ መለያ ወንጠፍቱ ደግሞ የተጠናከረ የመረጃ መረብ ዘርግቶ፤ የሚገኙትን የተበጣጠቁ መረጃዎች ገጣጥሞ፣ ተንትኖና ትርጉም ሰጥቶ፤ አፀፋ ለሚያስፈልገው አስፈላጊውን አፀፋ መስጠት፣ ማጥቃት ለሚሻው ጊዜ ሳያባካኑ፣ ዒላማ ሳይስቱ ጥቃቱን መሰንዘር የሚያስችለው ሁነኛ የመረጃ መሰብሰብና የመመዘን ሥራ ሲሠራ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ለዐማራ ኅልውናና ማንነት እታገላለሁ የሚል የመረጃ ሰብሳቢ መሆን ይጠበቅበታል። መረጃ የሚገኘው የትም ቦታ ነው። ሰዎች በዋሉበት፣ ባደሩበት፣ በተጫዎቱበት፣ በሠሩበት፣ በተዝናኑበት ሁሉ የሚደረጉ ጭውውቶች፣ ፌዞች፣ ቀልዶች፣ ንግግሮች፣ ወዘተ ተገቢ ትርጉም ከተሰጣቸው መረጃዎች ናቸው። ለመረጃ ስብሰባ ደግሞ የግድ ልዩ ሙያ አይጠይቅም። የሚጠይቀው ማን ምን አለ? መቼ? የት ቦታ? እንዴት አለ? በምን ምክንያት አለ? ለሚሉት ጥያቄዎች ሁነኛ መልስ መያዝ ብቻ ነው። «ጅራቷ ያደርሳል ካናቷ» ነውና በዚህ መልክ የተሰባሰቡ መረጃዎች ባንድነት ተያይዘው ሲተነተኑ ወደ ተፈላጊው ውጤት ያደርሳሉ። የመረጃ ሙያተኛ የሚያስፈልገው እነዚህን የተበጣጠቁ መረጃዎች አገጣጥሞ ሙሉ ሥዕል እንዲሰጡ ተገቢ የማያያዝ፣ የመተርጎም እና የመመዘን ሥራ ለመሥራት ነው። በዚህ ረገድ፣ ለዐማራው ኅልውና ትግል ሁሉም የዐማራ ልጅ መረጃዎችን የመሰብሰብና ለሚመለከታቸው በወቅቱ ማድረስ ከግዴታዎቹ አንዱና በጣም ቀላል ተግባሩ አድርጎ ሊወስደው ይገባል። የድላችን መፋጠን ወይም መዘግየት በመረጃ ሥራ መሰባሰብና የተገኘውን መረጃ በሥራ ላይ በማዋል አቅማችን ይወሰናል።

በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥይት አብሪነት ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓም የተቀጣጠለው የዐማራ ሕዝብ የኅልውናና የማንነት ተጋድሎ ግለቱ ሳይበርድ፣ ከአቅጣጫው ሳይዛነፍ፣ ዓላማውን ሳይለቅ፣ ወደ ትክክለኛ ግቡ እንዲያመራ ለማድረግ፣ የትግሉ ቆስቋሽ ኃይል መሪ የፖለቲካ ድርጅት ማስፈለጉ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህም በመሆኑ፣ የዐማራውን ታሪክ፣ ባህል፣ ሥነ-ልቦናና ማንነት በቅጡ የተገነዘበ፣ በዐማራውና በኢትዮጵያዊነት መካከል ያለውን ማንም ሊበጥሰው የማይችል ዙሪያገብ ቁርኚት በሚገባ ያወቀ፣ ኢትዮጵያዊነት እና ዐማራነት እንደ ዋሰራ ዱቄት ተፈጭቶ የተቦካና የተጋገረ ኅብስት መሆኑን በቅጡ የተረዳ «የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት» የተሰኘ «የዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!» የሚል መሪ መታገያ መፈክር ያነገበ፣ በዐማራው ወጣቶች፣ ምሑራን፣ ገበሬዎችና ሴቶች ንቁ ተሳትፎ፣ በኅቡዕ ተደራጅቶ በተለያየ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎና የሸዋ አውራጃዎች፣ ወረዳዎችና በሌሎች አካባቢዎች ጭምር «ዱር ቤቴ፣ ማንነቴ ወይ ሞቴ» ያሉትን የጎበዝ አለቆች እያስተባበረ፣ የትግሉ ግለት እንዳይበርድ እየቆሰቆሰ ይገኛል። ይህ የ26 ዓመታት የትግሬ ወያኔ የግፍ አገዛዝ የወለደው ሕዝባዊ እንቢተኝነትና የኅልውና ትግል ለድል እንዲበቃ፣ ቆስቋሹ ኃይል ሊቆሰቁሰው የሚችል የገንዘብ፣ የመረጃ፣ የዕውቀት፣ የጊዜ አቅርቦት በበቂ መጠንና በአስፈላጊው ሰዓት እንዲያገኝ ለማስቻል፣ የአገር ቤቱ ድጋፍ ሰጭ የሆነ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ድርጅት በውጭ በሚገኙት የዐማራ ልጆች ተመሥርቶ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የዐማራ ልጆችና የኢትዮጵያ አንድነት አፍቃሪዎች ባለፈው በቁጥር አንድ “የዐማራ ኅልውና ለምን” በሚል መግለጫችን አብሥረናል፤ አሁንም በድጋሚ የምሥራች እንላለን።

መጀመር ቀላል ባይሆንም፣ የጀመሩትን እንደመጨረስ አስቸጋሪ አለመሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም ለመጀመር ብንቸገርም፣ የበለጠ የሚቸግረን የጀመርነውን ዳር ማድረሱ እንደሆነ እንገነዘባለን። የችግሩን ስፋትና ጥልቀት፣ ወርድና ቁመት በሚገባ መረዳቱ ደግሞ ለሚገጥሙን ችግሮች መሻሪያ ወይም ማርከሻ የሚሆነውን አስቀድመን እንድናዘጋጅ ስለሚያደርገን ችግሮቹ የቱንም ያህል ይክበዱ፣ ዐማራውን የሚያህል የሁለንተናዊ ሀብት ባለቤት ከኋላችን አሰልፈን የማንፈታውና ድል የማንነሳው ችግር ይኖራል ብለን አናምንም። ስለሆነም ትግሉን በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው ግለቱ እንዳይበርድ ለሚቆሰቁሱት ኃይሎች ሊቆሰቁሱት የሚችሉት ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ መረጃና ጊዜ ለማቅረብ ሁሉም የዐማራ ልጅ ራሱን ዝግጁ እንዲያደርግ ጥሪአችን እናቀርባለን።

በእርግጥ ይህም ለዐማራው አዲስም እንግዳም አይደለም። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የጣሊያን ወራሪና ቅኝ ገዥ ኃይል ዐድዋ ላይ ለመፋለም ለሕዝባቸው የክተት አዋጅ ሲያውጁ፣ «ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፣ አቅም የሌለህ በፀሎትህ እርዳኝ» ነበር ያሉት። የሆነውም ይኸው ነው። ዛሬም አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ወርረው የያዙት በተለይ ደግሞ የዐማራውን ነገድ በዕቅድ እያጠፉ ያሉት እኒሁ የጣሊያንን የወደቀ መርሓግብር አንስተው ነፍስ እየዘሩበት ያሉት የእናት ጡት ነካሾችና ባንዳ የባንዳ ልጆች ናቸው። ይህም በመሆኑ በነጭ ጠርሙስ ቀርቦ የነበረው የቀድሞው ወይን በአዲስና ጥቁር ጠርሙስ ቀረበ እንጅ ዐማራውንም ሆነ ኢቶጵያን አስመልክቶ የቀድሞውን የሚለውጥ ሁኔታ አልተፈጠረም። ስለሆነም እያንዳንዱ የዐማራ ልጅ፣ ለኅልውናችንና ለማንነታችን ቆስቋሽ ሆነው በግራ በቀኝ ከሚንቀለቀለው የወያኔ አፈሙዝ ፊት የቆሙት ወንድም እህቶቻችን የምኒልክን ጥሪ ዳግም አቅርበዋልና በምንችለው የአቅማችን እንድናደርግ አደራ እንላለን።

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!
ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

Email: aseuoirp@gmail.com