እንደ ደርግ አፈቀርናት ብላችሁ ነክሳችሁ እንዳታፈርሷት!

Print Friendly, PDF & Email

(ምስጋናው አንዱዓለም)

የአማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት በማለት የአማራውን ትግል ላለመቀበል ግትር አቋም የሚያንጸባርቁ ወገኖች እስከመቸ ነው የትግልን ስልት እና ዜግነትን እያደባለቁ ደንቃራ የሚሆኑት? አወ፡ የአማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት። ቢያንስ ወረቀት ላይ የተጻፈው እንደዛ ነው። በአማራነት መታገልን ከዚህ የወረቀት ዜግነት ጋር ምን ያገናኘዋል? አማራ አገሩ ኢትዮጵያ ናት፤ ስለሆነም አማራነት አያስፈልገውም፤ ይልቅም ኢትዮጵያዊነት እንደመታገያ አጀንዳ ብቻ በቂው ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ከባድ ህጸጽ ይሰራሉ። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች በሌላ ክልሎች የሚኖሩ አማሮች ከተወሰኑ አስርት አመታት በኋላ ተቀላቅለው እንደሚጠፉ አያውቁም? ባለፈው አመት እንኳ ሐረርጌ ውስጥ መፈናቀልን በመፍራት 80 000 አማራ አማራነትን ጥሎ ኦሮሞነትን ተቀብሏል (ቦታው ላይ ቀጥታ መረጃ ያለው ሰው ያጫወተኝ)። አማሮች አሁን በብዙ ክልሎች ላለመገለል እና ላለመፈናቀል አማራነታቸውን እየደበቁ እየተለወጡ ነው እኮ። ዛሬ የኦሮሞ ማንነትን አምኖ ተቀብሎ የምናየው አብዛኛው ህዝብም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእንዲህ ያለ ሂደት ያለፈ አማራና ሌሎች ነባር ህዝብ ነው። አሁንም ከጥቂት አመታት በኋላ ማለትም አማራው በአስቸኳይ ተንቀሳቅሶ ለውጥ ካላመጣ በሌላ ክልል ያለው አማራ ወገናችን የአማራ ማንነቱን ይዞ የማይቀጥልበት ደረጃ ይደርሳል። አሁንም በየጊዜው ከባድ የለውጥ ሂደት ላይ ነው። በግልጽ ከሚታየው ማፈናቀልና ማሳደድ ውጭ ከባድ የማንነት ቅየራ (Ethnocide) ስራ እየተሰራ ነው። ይሄ ደግሞ በረዥም ርቀት የኋላ የኋላ አማራው ድልን በሚቀዳጅበት ጊዜ የአማራውን ስርጭት እና የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ያሳንሰዋል። በዚህ እሳቤ በአማራነት ማንነት ሊቆይ የሚችለው የአማራው “ክልል” እና አዲስ አበባ ብቻ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ለዛውም አዲስ አበባ ላይ በህግ ሽፋን ከባድ የአማራ ጠረጋ ዘመቻ ታቅዶ ቀን እየጠበቀ መሆኑን በአይናችን እያየን ነው። ቶሎ ካልታገልን አዲስ አበባ ራስዋ የአማራ አሻራ የሌላት ከተማ መሆኗ የማይቀር ነው።

ከላይ በኩል የትግሬ ማንነት ከባድ ወረራ እያካሄደ ነው። የትግሬ ተስፋፊነት የፖለቲካ የበላይነትና የኢኮኖሚ የበላይነት ብቻ ሳይሆን የትግሬ ማንነትም ጭምር ነው። ከታች በኩል የኦሮሞ የማንነት ወረራ በአደገኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው። ሌሎች ብሄሮች የየራሳቸውን ብሄር ማንነት በማጠናከር በውስጣቸው ያለውን ብሄር ሁሉ እየዋጡ ነው። ይሄ ሁሉ የሚያመለክተው በተለይ አማራውን በተመለከተ Ethnocide (ማንት ቅየራ፣ ነገድ ቅየራ፣ ብሄር ቅየራ) እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየተሰራበት እና እየሰራ መሆኑን ነው። አማራው ለግለሰባዊ ህልውናው ሲል አማራነቱን እየደበቀ በየአካባቢው በእርሱ ላይ የበላይነት ያላቸውን ማንነት እየተቀበለ ማንነቱን እየቀየረ ማህበራዊ ህልውናውን እያጠፋ ነው። እና ኢትዮጵያን እንደማታገያ ርእዮተ አለም ስንወስድ አማራውና ኢትዮጵያ ዘላለማዊ የማይለወጥ ቁርኝት እንዳላቸው አናስመስል ለማለት ነው። ይሄ አክቲቭ የሆነ ኢትኖሳይድ እየተካሄደ ባለበት ሰአት አማራው አገሩ ኢትዮጵያ ናት የሚለው ፍልስፍና ወደባዶ ቅዠትነት ይለወጣል። ስለዚህ በፍጥነት እየተለወጠ ያለውን የአማራ የስነ-ህዝብ ማሽቆልቆል ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማገናዘብ አዋጭ ማታገያ ርእዮት መከተል ይገባል።

በዛ ላይ በአሁኑ ሰአት አማራ በምን ቅልጥሙ ነው ኢትዮጵያን የሚያድነው? ይሄን ማለቴ ህዝቤን አቅም ማሳጣቴ ሳይሆን ቅድሚያ ራሱን ያላዳነ ህዝብ እንዴት ሌላውን ሊያድን ይችላል በማለት የማያወላዳ ጥያቄ ለመጠየቅ ነው። ይህም እውነታ የረጅም እና የአጭር ጊዜ እቅድ መንደፍ እንዳለብን ያስገነዝበናል። በአጭር ጊዜ የቱን አስመዝግበን በረጅም ጊዜ ምን እናስመዘግባለን ብሎ አቅምን ከነባራዊው ሁኔታ ጋር አሰናስሎ መራመድ ብልህነት ነው። ዝም ብሎ ቃሉ ለምላሳችን ስለቀለለ ብቻ እንደልባችን እየተናገርን በተግባር ጠቀሜታ የሌለው አባባል በመሰንዘር አማራውን ለባሰ መከራ ባንዳርገው መልካም ነው።

በዚያውስ አማራን ብቸኛ የኢትዮጵያ አዳኝና ባለቤት እንደሆነ ማስመሰሉ ለሌላ ብሄሮች የእይታ ክፍተት ወይም ልዩነት የፈጠረ መሆኑ እና ያንን ተከትሎም ከባድ ጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ሲሰራበት መቆየቱ ለምን አይታሰብበትም? ይሄ ከመጠን በላይ ኢትዮጵያን እናድን አካሄድ ሌላውን ይሄው እንደ ድሮው ሊጨቁኑን መጡ አላልናችሁም ወይ? ስልጣን ፈልገው ነው እንጅ ችግር አልገጠማቸውም ለሚለው ፕሮፓጋንዳ አያጋልጠንም ወይ? አማራ ለኢትዮጵያ አንድነት ከታገለም ከሌሎች ብሄሮች ጋር እየተመካከረ የጋራ አጀንዳ እየቀረጸ፣ ስትራቴጅክ አሊያንስና ታክቲካል ትብብር እየነደፈ መታገል ይገባዋል እንጅ በብቸኛነት የኢትዮጵያ አንድነት ትግል ሻምፒዮን ሆኖ መቅረቡ በውስጡ የወራሪነትና የአገር አቅኝነት ይዘት አለው ተብሎ ውግዘት ሊያደርስ ይችላል። ለዛስ ምን መልስ ልናዘጋጅ ነው? በአሁኑ ሰአት የጎላ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ድርጅቶች ከትህዴን በቀር የኢትዮጵያ አጀንዳ ያለው አለ? እሱም ቢሆን በብዙ ኮንስፓይረሲ ውስጥ የሚታይ ድርጅት ነው። ታዲያ ሌላው ለየራሱ ሲሮጥ አማራው ምን ቤት ነው ለኢትዮጵያ እሮጣለሁ የሚለው? ችሎ እንኳ የሚሮጥ ቢሆን ይበጅ ነበር። እንዲህ ያለው ብስለት የጎደለውና ሀላፊነት የራቀው አስተሳሰብ 50 አመት ሙሉ “ከአማራ ለማምለጥ” ሲታገሉ ለኖሩት ብሄሮች ልሂቃን የበለጠ የብሶታቸው ትክክለኛነት ማረጋገጫ አይሰጥም ወይ? አማራ ለኢትዮጵያ ብቻውን ይታገላል ብሎ በአደባባይ ማወጅ ሌላው ብሄር አማራው እንዲታገለው በር የሚከፍት መሆኑን መገንዘብ ይከብዳልን? በአሁኑ ሰአት በአማራ ጥላቻ የተገነቡ የየብሄር ድርጅቶች አማራው ኢትዮጵያ ብሎ ሲነሳ መጣብን ሳይቀድመን እናጥፋው ወደሚል እሽቅድድም እንዲገቡ ያደርጋል። ይሄም የአማራን መከራ ያፋጥናል። ሌሎች አገዛዙን ተቃዋሚ የብሄር ድርጅቶችም የአማራው ካሁን ቀደሙ የከፋ ደንቃራዎች እንዲሆኑ እድል ይሰጣል።

የየብሄር ድርጅቶች የተቀረጹት ከአማራ ወይም ከኢትዮጵያ በማምለጥ አስተምህሮት ነው ብለናል። በየቦታው የሚታገሉት እኮ ከዚህ በአንድ ጊዜ አማራና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያና አማራ ከሚመስላቸው አስተሳሰብ ነው። ታዲያ ለማምለጥ እየታገሉ ያሉት አስተሳሰብ እንደገና አማራው አንግቦት ሲያዩ የቀደመ ንድፈ-ሀሳባቸው እውነታዊ ሆኖ ለበለጠ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራ ትግል ያነሳሳቸዋል። አሁን ኢትዮጵያ የሚለው ከመጠን ያለፈ ጩኸት እንደማታገያ አጀንዳ ሲወሰድ በራሳችን ምላጭ መቆረጣችን ነው። ማለትም አማራ የኢትዮጵያ ባለቤት አልነበረም፤ የሚከሰሰው ክስ ሁሉ ሀሰት ነው ስንል ቆይተናል። ታዲያ አሁን ይሄን አጀንዳ ከፊት ማሰለፍ ውሸት ያልነውን አፍርሰን ለምንከሰስበት ነገር እውነትነት እየመሰከርን መሆኑ ለምን አይታሰብበትም? ኢትዮጵያን የአማራ በጎ ፈቃድ ውጤት አስመስሎ ምንም በሌለበት መንቧቸር የተከመረብንን የሀሰት ክምር እውነት ነው ብሎ የሀሰት ምስክር ከመስጠት የዘለለ ሚና የለውም። ያ አይነት ነገር ደግሞ አገር አፍርሷል። አደብ ካልገዛን አሁንም ያፈርሳል።

በዋናነት ይሄ አለቅጥ የተለጠጠ ኢትዮጵያ ኢትዮጰያ መዝሙር አማራው ላይ ጠላት ያበዛል፤ አማራውን እንደወራሪ ያሳያል፤ አማራውን በድሮ ስርአት ናፋቂነት ሁሉም ጦር እንዲሰብቅበት በር ይከፍታል፤ አማራው በአገሪቱ ላይ ከሌላው የተለየ ድርሻ ያለው ያስመስላል፤ አማራ ላይ የሚደርሰውን በደል ሌላው ወገን እንዳይገነዘበው ግርዶሽ ይጋርዳል፤ የአማራ አጀንዳ ከራሱ አልፎ ስለሌላ ጉዳይ መሆኑን ያስገምታል፤ ይሄም የህልውና ትግል እያልን የምንጮኸው የአጭበርባሪ ቋንቋ እንደሆነ ያሳብቃል፤ ሌላው ብሄር ኢትዮጵያን የአማራ ጉዳይ ብቻ አድርጎ በማየት ለኢትዮጵያ በጋራ እንዳይታገል ምክንያት ይሰጠዋል፤ ሌላው ብሄር ስለወደፊቱ ኢትዮጵያ እኩላዊ ስሜት እንዳይኖረው ያደርጋል፤ ይሄም ሰበብ ሆኖ አገሪቱን እንድትበታተን ያግዛል።

አሁን አማራው በሚገኝበት አስቸጋሪ የሆነ ወቅት አማራውን ሌላው እንዲፈራው ማድረግ በእውነት የወዳጅ ስራ አይደለም። አሁን ማድረግ ያለብን ሌላው አማራውን እንዳይፈራው፣ እንዳይጠራጠረው ማድረግ እና ከዚህ ቀደም የተሰራበትን ማጠልሸት ሀሰትነት በማስረዳት ስሙን ማደስ ነው። ለአማራው ጓደኛ የሚያበዛ አካሄድ ብቻ ነው የሚጠቅመን።

“ደርግ ኤርትራን ከመጠን በላይ ከማፍቀሩ የተነሳ ሳምኩ ብሎ ነከሳት” ይል ነበር ጓደኛየ። ደርግ ኢትዮጵያን የጅል ፍቅር አፍቅሮ ሳምኩ ብሎ ነከሳት የሚሉም አሉ።

*******

የግርጌ ማስታወሻ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ አንድን ቡድን ወይም ድርጅት አይመለከትም። በሁሉም ቡድን ወይም ድርጅቶች ላሉ ተመሳሳይ ሀሳብ ለሚራምዱ ወገኖች እንደአስረጅ የቀረበ ጽሁፍ ነው።