አስደሳች ዜና – የዳግማዊ መዐሕድና የቤተ አማራ መድኅን የቅድመ ውህደት ስምምነት

Print Friendly, PDF & Email

የዳግማዊ መዐሕድና የቤተ አማራ መድኅን የቅድመ ውህደት ስምምነት
ሚያዚያ 26 2009 ዓ.ም.

ዳግማዊ መዐሕድና ቤተ አማራ መድኅን የአማራን ህዝብ ህልውና ለመታደግና ለዘመናት ሲደርስበት የነበረውን ጥቃት ለማስቆም ብሎም ማህበራዊ፣ ኢኮሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትህን ለማስፈን በተለያዩ ደረጃዎች ስንንቀሳቀስ የነበርን የፖለቲካ ድርጅቶች በተናጠል እያደርግነው ያለነው ትግል የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የመረጃ፣ የዕውቀትና የቁሳቁስ ብክነትን እያስከተለና የህዝባችንን መከራም እያራዘመ እንደሆነ ይታወቃል።

በአማራው ላይ የተከፈተውን መጠነ ሠፊና የተቀናጀ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመከላከል የሕዝባችንን ህልውና ለመታደግ ብሎም መብቱና ብሄራዊ ጥቅሞቹን ለማስከበር እየተደረገ ያለውን የተናጠል ትግል በጥምረት እና በውህደት ማቀናጀት ፈጣንና አስተማማኝ ድል እንደሚያስገኝ የታነመ ነው።

በመሆኑም የሁለቱ ድርጅቶች የጋራ አመራሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ሰፋ ያለ ውይይት ስናደርግ ቆይተን ሚያዚያ 26 2009 ዓ.ም. (እ.አ.አ. May 5 2017) ባደረግነው የጋራ ጉባዔ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመዋሃድ የቅድመ ውህደት ስምምነት አድርገናል። የሁለቱ ድርጅቶች ውህደት ተግባራዊ የሚሆነው የሚከተሉት ሶስት መሰረታዊ መርሆዎች መሰረት አድርጎ እንደሚሆን ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል።

1ኛ. የአማራን ሕዝብ ህልውና እና ብሄራዊ ጥቅምን የሚያስከብር፣ እንዲሁም ወቅታዊውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ያገናዘበ የፖለቲካ ፕሮግራም ይኖረዋል።

2ኛ. የውህዱ ድርጅት አርማና ስም የውህድን ድርጅት ራዕይና አላማን መሰረት ባደረገ መልኩ በውህደት አመቻች ኮሚቴው በጋራ ተዘጋጅቶ ቀርቦ በውህደቱ ጥምር ጉባዔ ይፀድቃል።

3ኛ. ሙሉ ውህደቱ እስከሚፈፀምበት የአንድ ወር ጊዜ ድረስ ሁለቱ ድርጅቶች “ዳግማዊ መዐሕድ – ቤተ አማራ መድህን” በሚል ጥምረት ይቆያሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ድርጅቶች በጋራና በተናጠል ከሌሎች የአማራ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራትና የአማራ ኮሚቴዎች ጋር የጀመርናቸውን የትብብር እንቅስቃሴዎች በአንድነት አጠናክረን የምንቀጥልበት መሆኑን እየገለጽን፣ የአማራን ሕዝብ ህልውና ለመታደግና የህዝባችንን መብቶችና ጥቅሞች ለማስከበር እየታገላችሁ ያላችሁ የአማራ ድርጅቶና “አክቲቪስቶች” አዲሱን ውህድ ድርጅታችንን ተቀላቅላችሁ በአንድነትና በተቀናጀ መንገድ የጋራ ትግል ማድረግ እንችል ዘንድ የወገን አድን ጥሪያችንን በታላቅ እክብሮት እናቀርባለን።

አዲሱ የአማራ ትውልድ ታሪኩን ያድሳል!
የአማራ ተጋድሎ ያሸንፋል!

ተፈሪ ቸርነት – ዳግማዊ መዐሕድ (ሊቀመንበር)
ካሳው ታፈረ – ቤተ አማራ መድኅን (ሊቀመንበር)