የኤፍሬም ማዴቦ ንግግር ሲፈተሽ

Print Friendly, PDF & Email

(ቬሮኒካ መላኩ)

ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራር አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በአውስትራሊያ ሜልቦርን አደረገው የተባለው ” የወልቃይት ማንነት የሚወሰነው በመንግስት ወይም በሌላ አካል ሳይሆን በወልቃይት ህዝብ ነው ” በማለት ጋዜጠኛ ደረጄ ሃብተወልድ በኩራት ፅፎ በመመልከቴ ይሄን ፅሁፍ ለመፃፍ ምክንያት ሆነኝ ። እስኪ ይሄን በፖለቲካዊ አይታ አደገኛ የሆነ ንግግር ገለጥለጥ አድርገን እንፈትሸው።

ጋዜጠኛ ደረጄ ሃብተወልድ ለመዝናኛ ጋዜጠኝነት ተሰጥኦ እንዳለው አውቃለሁ ነገር ግን በተደጋጋሚ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ችግር እንዳለበት አስተውያለሁ።

በመሰረቱ ግንቦት 7 በወልቃይት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም ይሄ ከላይ የተጠቀሰው ከሆነ ከህውሃት አቋም ያልተለየና ለወልቃይት አማራ ህዝብ በኩራት የሚነገር ሳይሆን ይልቁንስ ድርጅቱ ከአማራ ህዝብ አንፃር ያለው አመለካከት እና ፖሊሲ መፈተሽ ያለበት እንደሆነ ይሰማኛል ።


የወልቃይት ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛው እንደሆነና ሁሉም ነገር በዝርዝር ታይቶ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በፊት ወደነበረበት በመቀላቀል በትክክል አስካልተፈታ ድረስ ብቼኛው ምክንያት በመሆን አገሪቱን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ ስለመሆኑ የውጪ ዜጎችና ምሁሮች ሳይቀሩ እያስጠነቀቁ እያሉ የግንቦት 7ን የተውለሸለሸ የወልቃይት ፖሊሲ በየፌስቡኩ መለጣጠፉ ድርጅቱን የበለጠ ቅርቃር ውስጥ እንደሚከተው እነ አቶ ደረጀ ሃብተወልድ የተረዱት አይመስልም።


በመጀመሪያ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ከመግባቴ በፊት ግምቦት 7ቶችን የተወሰኑ ጥያቄዎችን ልጠይቅ :

1~ ህውሃት በ 1983 የመንግስት ስልጣን መያዙን ተከትሎ ወልቃይትን ከጎንደር በመውሰድ ወደ ትግራይ ያካለለው በወልቃይት ህዝብ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ነበር ወይ ?


2~ በጉልበት እና በማናለብኝነት የተካለለን መሬት በህዝበ ውሳኔ ይመለስ ማለት አግባብ ነው ወይ ? ከህግ አንፃርስ ያስኬዳል ወይ?


3~ የወልቃይት ጉዳይ በወልቃይት ህዝብ ( እዚህ ላይ የወልቃይት ህዝብ ሲባል ወደትግራይ በተካለለው የወልቃይት መሬት የሚኖር ህዝብ ማለት ነው) ነው የሚወሰነው ካላችሁ ከወያኔ አቋም በምን ተለያችሁ?

ወያኔ ለአለፋት በርካታ አመታት የወልቃይት አማራን እያሰረ እየገደለ እንዲሰደዱ በማድረግ ከህዝቡ ግማሽ በላይ የሚሆነው የወልቃይት ህዝብ በሌለበት እና ወያኔ ከሰራዊቱ ተቀናሽ በማድረግ እና ከትግራይ የተለያዩ ወረዳዎች የሚኖሩቱን ትግሬዎችን እያሰባሰበ እንዳሰፈራቸው እየታወቀ እንዴት ነው የወልቃይት ጉዳይ ለወልቃይት ነው የሚተወው በማለት ህዝብ የሚያሸማቅቅ ንግግር ለመናገር ሞራሉን ከወደየት አገኛችሁት ?


በማንኛውም ህግ ሆን ብሎና አምኖበትና ሳይታይ አየተጠነቀቀ ከሌላ ቦታ በመሄድ የሰረቀውን የሱ ያልሆነን ሀብትና ንብረት ሌባ ይመልስ ዘንድ ራሱ ሌባው ይፈርድ ዘንድ ዳኛ አይፈርድም፡፡

ህወሀትም የአማራን ህዝብ በመናቅ፣ በመጥላትና በማዋረድ ሰበብ ተነሳሰቶ ለራሱ ጥቅም ለማድረግ በጉልበትና በህገወጥ መንገድ የወሰደውን ቦታ በተመለከተ “የወልቃይት ህዝብ ራሱ ይወስን ” በሚል አስመሳይ ንግግር አጅቦ በወልቃይት የሰፈረ ህወሀት ትግሬ ህዝቦች መወሰን እንዳለበት ግንቦት 7 በመግለጫ መልክ ለህዝብ ማሳወቅ ምን ያህል ብቃት የሌለው፣ ራሱን ያጣና በደምሂት አሻጥር የታጀበ ለሀገር እደጋ እየሆነ መምጣቱን የሚያመለከት አሳዛኝና አሳፋሪም ነው፡፡


ከተከዜ ማዶ ወልቃይትን ጨምሮ ምን ጊዜም ጎንደር ሲሆን በታሪክ ውስጥ ለአንዴም ትግራይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ትግሬ አንጂ ተከዜን እየተሻገረ ለስራ ሲመጣ የኖረ ትግራይ ግን በምንም መንገድ ስለማይቻለው አስቦትም አያውቅም ።

አሁን እናንተ በምትሉት ሪፈረንዴም ወልቃይት ህዝብ ትግሬ ነን ቢል እንኳን መሬቱ የአማራ እንደሆነ መሰመር አለበት ። የተጠየቀው ጉዳይ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ነው በዚህ አስተሳሰብ ወልቃይት ትግሬ ነን ቢሉም ሳይፈናቀሉ መኖር ይችላሉ መሬቱ የአማራ ሁኖ የአማራ ህዝብ በወልቃይት ላይ እየታገለ ያለው መሬቱ የአማራ ስለሆነ ነው ስለዚህ ትግሬወች በኦሮሞ፣በደቡብ በጋምቤላ ሂደው እንደሚኖሩት ወልቃይትም መኖር ይችላል።


በመሰረቱ ግንቦት 7 በወልቃይት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም ከዴምህት ፣ ከወያኔ ፣ እና ከአረና አቋም የተለየ ምንም ነገር የሌለው ነው። የወልቃይትን ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ ይፈታ ከተባለ በህገ-ወጥ መንገድ ወልቃይት ላይ የሰፈሩ ትግሬዎች ቁጥራቸው ከአማራው ስለሚበልጥ የreferendum ውጤቱ ለትግራይ እንደሚያደላ ግልፅ ነው። ግ7 ይህን በሚገባ ያውቃል። እኛም ቢሆን ከደምህት ጋር ጥምረት ፈጥሮ የሚንቀሳቀሰው ግ7 በምንም ሁኔታ በወልቃይት ጉዳይ ላይ ከደምህት ጫና ወጥቶ በነፃነት የተለየ አቋም ያንፀባርቃል ብለን አንጠብቅም ። ነገር ግን በየሄዱበት ስለወልቃይት መዘባረቁ ዋጋ ያስከፍላችሁ እንደሆነ እንጅ አይጠቅማችሁም።


ግንቦት 7ን ጨምሮ ለማንም ግልፅ መሀን ያለበት ግን ከማንም ጋር ሳይነጋገርና ሳይስማማ በራሱ ትቢትና በአማራ ህዝብ ላይ ንቀት ተነሳሰቶ ወንዝ ተሻግሮ በመምጣት ለምና ሀብታም የሆነን የጎንደር ተፈጥሯዊ አካል ወልቃይትን ለራሱ ለማድረግ የሚሞክር ህወሀት ይቅርታ በመጠየቅ ወንዝ ተሻግሮ ወደ ትግራይ ከመመለስ ውጪ ሌላ የፈለገውን ይናገር ወይም ያድርግ በምን መንገድ ተቀባይነት እንደሌለው ነው።


ይህም ችግር ከአካባቢው አልፎ የሀገር ችግር እየሆነ ነው፡፡ በመሆኑም የወልቃይት ጉዳይ መፈታት ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ሰላም፣ አንድነት፣ እድገትና ጥቅም መሆኑ ታውቆ ሌላ ሌላ መዘባረቃችሁን ትታችሁ ነገሩን አፍረጥርጣችሁ በማውጣት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደነበረበት መመለሱ ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ ማስገንዘቡ ይሻላል።