“እብዱ” ንጉስ እና “ከኦሮሞ ያልተወለደው ቡዳው ጎጃሜ”

Print Friendly, PDF & Email

ወፈፌው ምሁር ተብዬ ዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀ

(ቬሮኒካ መላኩ)

ለዚህ አጭር ፅሁፍ ይሄ ሞገደኛ ርእስ ይገባው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ አላውቅም። ለማንኛውም ሰሞኑን በአንድ የታሪክ ምሁር ነኝ ባይ የተጠቀመበትን “እብዱ ንጉስ” የሚል ነውረኛ አገላለፅ እኔ ርእስ ይሆን ዘንድ ተጠቅሜበታለሁኝ።

አሁን በአለንበት ዘመን የማንሰማው ጉድ የለም። አፄ ቴዎድሮስ “እብድ ነበር”፣ አፄ ምኒልክ “አገር ሻጭ ነበር” ፣ መለስ ዜናዊ “ጀግና ነበር” የሚሉ ምሁራንን በየሚዲያው እየሰማን እየተመለከትን ነው።

“ዘመነ ግርምቢጥ ውሻ ወደ ሰርዶ አህያ ወደ ሊጥ ” የሚባለው ተረት አየደረሰ ይመስላል። ጀግናውን “እብድ” ። የአገር ድንበር አስከብሮ የመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነን ንጉስ “አገር ሻጭ”። አገር ቆርጦ ወደብ አልባ ያደረገውን ” ጀግና ” የሚሉ ምሁራን መመልከት አስገራሚ ነው።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ኢሳት ላይ የቀረበው የታሪክ ተንታኝ አፄ ቴዎድሮስን “እብድ” ነበር በሚል የገለፀበት ነውረኛ እና ሃላፊነት የጎደለው አገላለፅ ወስውሶኝ ነው።

በጥቁር አህጉር ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በቀላሉ የማይገመት ሚና ተጫውታለች። አፄ ቴዎድሮስ በዘመነ መሳፍንት እንደ እህል ዘር የተበተነችውን ኢትዮጵያን አንድ በማድረግ እና ስልጣኔን በማስጀመር ውጥኑን ሲጀምሩ በአንፃሩ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ህልውናና ክብር ለማስጠበቅ ከጣሊያን ጋር መራራ ትግል አድርገው አኩሪ ድል በመቀዳጀት በአፍሪካ ውስጥ ለራሱ መቆም የሚችልና ነፃ ሆኖ ለመኖር መብት ያለው የጥቁር ዘር እንዳለ በማያጠራጥር ሁኔታ አስመሰከሩ።


አሁን ሃላፊነት በጎደላቸው የወረቀት ምሁራን ስማቸው የሚዘነጠለው ብርቅዬ መሪዎቻችን የነበሩት አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒልክ በህይወት ዘመናቸው የተስፋፊ ኢምፔሪያሊስቶችን ሤራ ለማክሸፍ ብዙ መስዋእትነትን የከፈሉ ነበሩ። አገሪቷ የውጭ ጠላትን በመቋቋም ነፃነቷን ለማስከበር፣ በስልጣኔ ጎዳና ወደፊት ለመራመድ የምትችለው አንደነቷ በተጠናከረ ሁኔታ ሲገኝ መሆኑን ተገንዝበው ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት ገንብተው ኢትዮጵያን ሃያል ያደረጉ መሪዎች ነበሩ።


አለም ለዘመናት ታላላቅ ሰዎቿን እና ከዘመኑ ቀድመው የሚያስቡ ግለሰቦችን “እብድ” እያለች ስትጠራ ኖራለች። ሶቅራጥስ ፣ ፑሉቶ፣ አሪስቶትል ፣ ደዮጋን “እብዶች ” ተብለው ዋጋ ከፍለዋል።

ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከ 1847 እስከ 1983” በሚል ርእስ ባለው መፅሃፋቸው አፄ ቴዎድሮስን “ቴዎድሮስ ከጨረቃ የመጣ ሰው ሳይሆን ከዚቹ ከኢትዮጵያ የተፈጠረ ሰው ነበር” በማለት ጥሩ አድርጎ ገልፆታል። በተጨማሪም በመቅደላ እስር ቤት ለአመታት ታስሮ የነበረው ሄነሪ ብላንክ “ቴዎድሮስ ከዘመኑ ቀድሞ የሚያስብ መሪ ነው” ብሎ ምስክርነቱን ፅፎ አልፏል።

የፌስቡክ ወዳጄም Tesfaye ስለዚህ ጉዳይ በሚከተለው መልኩ በደንብ ገልፆታል።


በእርግጥ ማሰብ-ለተሳናቸው ቴዎድሮስ “እብድ” ነው ቢሉም ልንፈርድባቸው አይገባም። አፄ ቴዎድሮስን ለመከተል አይደለም ሀሳቡን ለመረዳት ጂኒየስ መሆንን ይጠይቃል። ጥቁር ህዝብ በተፈጥሮው የIQ መጠኑ ዝቅተኛ ነው ይባላል። ሁሉም ባይሆንም ይህንን ለመቀበል የሚገፋፉኝ ብዙ ነገሮች አሉ። እናም የፈረንጅ ታሪክ አጥኚዎች እንኳን ቴዎድሮስን ከዘመኑ 200 አመት ቀድሞ የተወለደ ጂኒየስ ነበር ይሉታል። ይታያችሁ፡ ቴዎድሮስ ከተወለደ 200 አመት አልሞላውም። ስለዚህ አይደለም ያ ትውልድ፤ የእኛ ትውልድ እንኳን በቴዎድሮስ ለመመራት የአዕምሮ ብቃት የለውም ማለት ነው።


አፄ ቴዎድሮስ ትውልዱን በምዕተ ዓመት ቀድሞ ተወልዶ ስቃዮን አዬ። አፄ ምኒሊክ ከዘመናቸው ፊት ፊት እየሔዱ በብቃት አገር መሩ። አፄ ኃይለ ስላሴ ደግሞ በወጣት ትውልዳቸው ተቀድመው ነበር ማለት እንችላለን። የአፄ ቴዎድሮስ ተፅዕኖ በሚኒሊክ ላይ እንኳን ሰርጾ ነበር። ምኒሊክ ስርዓተ መንግስትን የተማረው በ12 ዓመቱ የቴዎድሮስ ግዞተኛ ሆኖ መቅደላ በታሰረበት ሰዓት ነው።

አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን የዘመናት ችግር የፈታ የጥበብ ሰው ነው። የኢትዮጵያ ህልውና በቱርክ መድፍና በአህመድ ግራኝ ጦር ክፉኛ ከተፈተነ በኀላ አገሪቱ ማገገም ባለመቻሏ ብዙ ታሪክ ስልጣኔና ሀገር አጥተናል።

ይህንን የዘመናዊ ጦር መሳሪያ ችግር ለመፍታት ከ500 ዓመት በኀላ ብቃቱን ያሳየና መድፍ በአገር ውስጥ የሰራው ንጉስ ቴዎድሮስ ብቻ ነው።


ቴዎድሮስ በጣና ሃይቅ ላይ 300 ሰው የሚይዝ መርከብ በራሱ ንድፍ ያሰራ ድንቅ ሰው ነው፡፡ 300 ሰው የሚይዝ መርከብ/ ጀልባ አሁን ራሱ ለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ቴዎድሮስ ብዙ ዘመናዊ ነገርችን በአገር ውስጥ ሰርቷልም አሰርቷልም።

ቴዎድሮስ እዚች ያልታደለች አገር ላይ ተወለደ እንጂ፤ አሜሪካ ተወልዶ ቢሆን እሱ የሚሆነው መሪ ሳይሆን በአዕምሯቸው ጭማቂ አለምን እንደለወጡት እንደነ ቶማስ ኢድሰን የአዲስ ግኝት ባለቤት ይሆን ነበር።


በአሁኑ ጊዜ እንኳን ቴዎድሮስን መረዳት የሚችሉበት የአእምሮ እድገት ደረጃ ላይ ያልደረሱ “ምሁራን” ና ጋዜጠኞች ያሉበት አገርና ዘመን ላይ ስላለን ልናፍር ይገባል።

የወፈፌው እና  የምሁር ነኝ ባዮን የዶ/ር ዮሐንስ ዘለቀን ቃለ መልልስ ሙሉውን ከዚህ ላይ ያድምጡ።