እስቲ ዶሴው ይውጣ … የማን? የኢሕአፓ

Print Friendly, PDF & Email

(አቻምየለህ ታምሩ)

እስቲ ዶሴው ይውጣ [ክፍል ፮]

ይህ ጽሁፍ ምናልባት አስተያየት የሚያጭሩ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ኢሕአፓን በሚመለከት የምንጽፈው የመጨረሻው ክፍል ይሆናል። ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች ኢሒአፓ የሚባለው የ ያ ትውልድ ድርጅት ከምስረታው ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሰራጫቸውን ዶሴዎች ብቻ በማገላበጥ የኢሕአፓን ፀረ–ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቫይረስነት በማያሻማ ሁኔታ ለማሳየት ሞክረናል።

ዛሬ በምናትማቸው ዶሴዎች ደግሞ ማቅረብ የምንፈልገው ኢሕአፓ የዚያድ ባሬ ሎሌ ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ደባና የአገር ክዳት ታሪክ ነው።

የሶማሌው ዚያድ ባሬ ጥጋብ ልቡን ንፍት አድርጎት በግፍ የወረብንን የኦጋዴን፣ የባሌን፣ የሲዳሞን፣ የአርሲንና የሐገርጌን የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች ልክ ወያኔ ልክ በኤርትራ እንዳደረገው ሁሉ ኢሕአፓም “የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል” በሚለው የግራ ፖለቲከኞች ትርክት በመመስረት ኢሕአፓ የኢትዮጵያ መንግስት ሲሆን አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቶ እንደነበር ዚያድ ባሬ ራሱ የተናገረውንና ዊክሊክስ ያሾለከውን ሚስጥርና ሌላ ተያያዥ ታሪካዊ ሰነዶችን በመመርመር ያገኘነውን እውነት እናቀርባለን።

ከታች የታተመው በዊክሊክስ የሾለከ ሚስጥራዊ ነሰድ እንደሚያሳየን ዚያድ ባሬ አዲስ አበባ ውስጥ ከነበረው ኢሕአፓ ጋር ግንኙነት እንደነበረውና ኢሕአፓ የመንግስቱ ኃይለ ማርያምን አገዛዝ ተክቶ የኢትዮጵያ መንግስት ሲሆን ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ የነበራትን የግዛት ይገባኛል ጥያቄ እንደሚያስተናግድ በልበ ሙሉነት ተናግሯል። ዚያድ ባሬ ስለኢሕአፓ አገር ሻጭነት ይህንን የተናገረው ኢትዮጵያን በእብሪተኛነት ወርሮ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች በባሌ፣ በኦጋዴን፣ በሐረርና በሲዳሞ ከወራሪው የሶማሊያ ሰራዊት ጋር ሲፋለሙና መስዕዋት ሲሆኑ በነበረበት በ1969 ዓ.ም. ነው።

ዊክሊክስ ባሾለከው በዚህ ሚስጥራዊ ሰነድ እንደሰፈረው ዚያድ ባሬ ኢሕአፓ የሻለቃ መንግስቱ ኃይለ ማርያምን አገዛዝ ተክቶ መንግስት እንዲሆን የፈለገው ለኤርትራ፣ ለኢትዮጵያ ሶማሌ፣ለኦሮሞ፣ ለትግራይ፣ ወዘተ መገንጠል ይተጋ ስለነበር ኢሕአፓ መንግስት ከሆነ በኋላ ኦጋዴን፣ ባሌን፣ ሐረርጌ፣ባሌና ሲዳሞን ከኢትዮጵያ በመውሰድ፤ አልፎም የኤርትራ ተገንጣዮችን በማደፋፈርና ኤርትራን በማስገንጠል ኢትዮጵያን አዳክሞ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገና ተገነጣጥላ የተፈችዋን ኢትዮጵያ የሚገዛ ዚያድ ባሬ እንደፈለገው የሚያሽከረክረው የኢሕአፓ መንግስት ኢትዮጵያ እንዲኖራትና ኢትዮጵያ ከካርታ ላይ እንድትጠፋ ነበር። ከነግብጽና ሳውዲ አረቢያ ጋር የሚጋራውን ይህንን አላማውን ሳያፍር ተናግሮታል። ኢሕአፓ የሚባለው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቫይረስ የዚያድ ባሬን ፍላጎት በዚያ ደረጃ በኢትዮጵያ ላይ ለማስፈጸም የቆመ አደገኛ ተውሳክ ነበር።

አዲስ አበባ የነበረው የሶማሊያ ኢምባሴ የኢሕአፓ ፋኖዎች መፈንጫ ነበር። የአምባሳደሩ መኖሪያም የኢሕአፓ ጽሕፈት ቤት ቤት ነበር ማለት ይቻላል። ደርግ ኢሕአፓ አዲስ አበባ ውስጥ የዘረጋውን መረብ ለማወቅ የቻለው የሶማሊያው አምባሳደር ወደ አገሩ ይዞት ሊሄድ በሳምሶናይ ሞልቶት የነበረውን የኢሕአፓ ሰነድ በመቀማት ነበር። በአዲስ አበባ የሶማሊያ አምባሳደር የነበረው ሰው አዲስ አበባ ከነበረው የአምባሳደሩ መኖሪያ ተነስቶ ወደ ሞቃዶሾ ለመብረር ቦሌ አየር ማረፊያ እንደደረሰ የመንገደኞች ማረፊያ ተቀምጦ አውሮፕላኑን ይጠባበቅ በነበረበት ወቅት የደርግ ደህንነቶች ያልተጠበቀ ፍተሻ አካሂደው የአምባሳደሩ ሳምሶናይት በመንጠቅ ባካሄዱት ምርመራ ሳምሶናይት ሙሉ የኢሕአፓን የአገር ውስጥ አደረጃጀት፣ እቅድና ተያያዥ የኢሕአፓ ሰነዶችን ማግኘት ችለዋል። ደርግ በአዲስ አበባ የሶማሊያን አምባሳደር የነበረውን ሰው ወደ አገሩ ሊሄድ ከአዲስ አበባ ሲነሳ ሶስት ጊዜ ሳምሶናይቱን ቀምቶ የኢሕአፓን ሰነዶች አግኝቷል። ልብ በሉ! በሶማሊያው አምባሳደር ሳምሶናይት ተሞልቶ ከአዲስ አበባ ወደ ሞቃዲሾ ሊጓዝ ሲል በደርግ የደህንነት ሰዎች የተቀማው የኢሕአፓን ሚስጥራዊ አደረጃጀትና ትልግ የሚያሳዩ ዶሴዎች ናቸው። በወቅቱ ኢትዮጵያን ለመውረር ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ዚያድ ባሬ ከኢሕአፓ የሚላክለት ሚስጥራዊ ነሰድ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ የወዳጅነትና ሁለቱን ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ የትብብር ስምምነት ነው የሚል የዋህ ያለ አይመስለኝም።

ሌላኛው የኢሕአፓ አምበል ተስፋየ ደበሳይ ደግሞ አዲስ አበባ የሚገኝው የግብጽ ኢምባሲ ቤተኛ ነበር። የግብጹ አምባሳደር የተስፋየ ደበሳይ የቅርብ ጓደኛ ነበር። የአምባሳደሩ መኖሪያ ደግሞ ተስፋየ ደብሳይና ጓደኞቹ በፈለጉ ጊዜ ሳይሰጉ የሚሰበሰቡበት አዳራሻቸው ነበር። ተስፋየ ደበሳይ በደርግ የተገደለው ከአምባሳደሩ ቤት ወጥቶ ኪዳኔ ህንጻ ተብሎ ይጠራ በነበረው ቦታ እንደደረሰ ነበር። አንዳንድ የመኢሶንና የኢሕአፓ አባላት ተስፋየ ደበሳይ እንዲገደል በተገደለበት እለት ከየት ተነስቶ ወዴት ይሄድ እንደነበር ሚስጥር ያሾለኩ ክፍሉ ታደሰና የወቅቱ ፍቅረኟው የአሁኗ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ጋዜጠኛ የሆነችው አዳነች ፍስሀዬ እንደሆነች ጽፈዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከኢሕአፓ መስራቶች ዋነኛው ሰው የሆነው ኢያሱ አለማየሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለ አዲስ አበባ በሚገኝው የጥሊያን ኢምባሲ አይጠፋም ነበር። አውሮፕላን ጠልፎ ከአገር ከወጣ በኋላ ለረጅም ጊዜ ኑሮው ሮም ነበር። ሮም እየኖረ የኢሕአፓ አመራር በነበረበት ወቅት ይኖር የነበረው የጥሊያን የጥሊያን ሶሻሊት ፓርቲ አመራርና እንደራሴ የነበረ ጥሊያናዊ ጓደኛው በሰጠው ቤት ውስጥ ነበር። ፋሽዝምና ኮምኒዝም ስላላቸው ግንኙነት የምትጠይቁኝ አይመስለኝም። እንግዲህ! እያሱ አለማየሁ ሮም ይኖርበት የነበረው ቤት የፋሽስት ጥሊያን መንፈስ ወራሽ የነበረው የጥሊያን ሶሻሊት ፓርቲ አባል የነበረ እንደራሴ በሰጠው ቤት ውስጥ ነው ማለት ነው። እንደራሴ ወይንም የምክር ቤት አባል ወይንም ምክር ቤት ሶስተኛው የመንግስት አካል ተደርጎ ይወሰዳል።

እንደሚታወቀው መንግስት ህግ አውጭ፣ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ የሚባሉ ሶስት አካላት አሉት። ፓርላማ የመንግስት ህግ አውጭ አካል ነው። ይህ ማለት እያሱ አለማየሁ ሮም ተቀማጥሎ ይኖርበት የነበረበት ቤትና ወጭውን ሁሉ ይሸፈንለት የነበረው የጥሊያን መንግስት ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኢያሱ ሮም ከመከተሙ ከሰላሳ አመታት በፊው አገራችንን በግፍ ወርራ የነበረችው ጥሊያን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን እያሱንና ኢሕአፓን ታጥቃ ትደግፍ ነበር ማለት ነው። ኢሕአፓና የመንፈስ ወራሾቹ ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ያስተጋባውን ፕሮፓጋንዳን ይዘው ፖለቲካ ውስጥ የገቡት ሮም ቤት መንግስት ውስጥ የተጠነሰሰውን ጸረ ኢትዮጵያ ሴራ ነው ማለት ነው። ለዚህ ውለታቸው ደግሞ እነ እያሱ ሮም ሲኖሩ አዲሱ የጥሊያን መንግስት ቤት ተሰጥቷቸው ቀለብ እየተሰፈረላቸው ፋሽስት ጥሊያን ጀምሮ የተወውን ኢትዮጵያን በዘርና በጎሳ የመከፋፈል ፕሮጀት ከግብ ለማድረስ የኢትዮጵያን የገበሬ ልጆች ያላስከፈሉት ዋጋ የለም።

ኢሕአፓ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቫይረስ እንደሆነ የሚያሳየን ዛሬ የምናቀርበው ሁለተኛው ሰነድ ደግሞ የኢሕአፓው አምበል ክፍሉ ታደሰ በጻፈው “ያ ትውልድ” መጽሀፍ ቅፅ አንድ ምዕራፍ ፭ ላይ የነረገን የኢሕአፓ ውሎ ነው። ክፍሉ ታደሰ እንደጻፈው በሚያዚያ 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የዛሬው ችግር በጀመረበት ወቅት ኢሕአፓን የወለደው ኢሕአድ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሂዶ ነበር። ክፍሉ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው ይህንን የኢሕአፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከሁለት የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በስተቀር ሁሉም ተሳታፊ እንደነበሩ ነግሮናል። የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ካልተሳተፉት የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ደስታ ታደሰ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እያሱ አለማየሁ ነው። ደስታ ታደሰ በሚያዚያ 1966 ዓ.ም. የተካሄደውን የኢሕአፓን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ያልተሳተፈው ድርጅት ቀይሮ ወደ መኢሶን “በመዛውሩ” ነው።

እያሱ አለማየሁ ግን የስዊዘርላንዱን የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮምቴ ስብሰባ ያልተሳተፈው በድርጅቱ በኢሕአፓ ተልዕኮ ተሰጥቶት ወደ ሶማሊያ ተጉዞ ስለነበር ነው። አስተውሉ! ኢትዮጵያ ችግር ላይ በወደቀችበት በዚያ ወቅት የኢሕአፓው የማዕከላዊ ኮምቴ አባልና የድርጅቱ አመራር ኤርትራዊው ኢያሱ አለማየሁ በድርጅቱ ታዝዞ ከዚያድ ባሬ ተልዕኮ ለመቀበል ሞቃዶሾ ነበር። ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረችበት በመከራ ሰዓቷ ከጠላት ተልዕኮ ለመቀበል ዚያድ ባሬ ቤተ መንግስት የሰነበተው ኢሕአፓ ለኢትዮጵያ እንደታገለ ሳያፍር የጠላት ተልዕኮ በመቀበል ሊያጠፋው የተነሳውን ስሟን እየጠራ “ኢትዮጵያ ሆይ!” በማለት እያላዘነ በሚደርተው ክታብ ያደነቁረናል! አንድ አገር ችግር ላይ እያለች ከሀገሪቱ ቀንደኛ ጠላት ተልዕኮ ለመቀበል ወደ ጠላት ቤተ መንግስት ያመራ ድርጅት ለሀገር እንደታገለ ራሱን በመቁጠር የተዋደቁላት ጀግኖች ልጆቿ በጠሩት ታላቅ ስሟ “ኢትዮጵያ ሆይ” እያለ መጽሐፍ የሚጽፍ ቢኖር ኢሕአፓና ኢትዮጵያን የከዷት የርዕዮተ አለም ወራሾቹ ብቻ ናቸው።

በሶስተኛ ደረጃ ዛሬ የምናቀርበው ኢሕአፓ ፀረ–ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቫይረስ ሆኖ የዚያድ ባሬ ተላላኪ እንደነበር የሚያሳየን መረጃ ደግሞ የኢሕአፓ ክፋይ የሆነው የመብርሀቱ ገብረ ሕይወቱ ኢሕህዴን ለወያኔ አድሮ አዲስ አበባ እንደገባ “ማለዳ” በተሰኘው ልሳኑ ያወጣው መግለጫው ነው። የኤርትራዊው የመብርሀቱ ገብረ ሕይወት ወይንም በሚንስትር ስሙ የበረከት ሰምዖን ድርጅት የሆነው ኢሕዴን ወያኔንና ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የወያኔ በየነ መንግስት ተሳታፊ እንደሆነ በመጀመሪያው የ”ማለዳ” መጽሔት እትም ላይ ባወጣው የድርጅቱ መግለጫ “ለሶማሊያ መበታተብ ተጠያቂዋ ኢትዮጵያ ናት” ሲል ኢትዮጵያን ይከሳል። ኢሕዴን ይህንን “መንግስታዊ” መግለጫው ያወጣው “እኛ ከኢሕአፓ ተለይተን የወጣን ትክክለኛ ኢሕአፓዎች ነን” የሚለውን የታምራት ላይኔ ቃለ ምልልስ ባሳተመበት በዚያው የ”ማለዳ” መጽሄት ቅጽ 1 ቁጥር አንድ እትሙ ነው።

ልብ በሉ! “ኢትዮጵያ ሶማሊያ እንድትበታተን ተጠያቂ ናት” ያለው ለወያኔ ያደረውና ኢሕአዴን በሚል የማታለያ ጭምብል ስም ኢትዮጵያን ለመምራት በኢትዮጵያ መንበረ መንግስት የተሰየመው የኢሕአዴግ አካል የሆነው ኢሕዴን ወይንም የዛሬው ብአዴንና ታምራት ላይኔ “እኛ ከኢሕአፓ ተለይተን የወጣን ትክክለኛ ኢሕአፓዎች ነን” ያለለት ድርጅት ነው። ሶስት ነገሮች እናስተውል። ኢሕአፓ ለሻዕብያና ለጀብሐ አድሮ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለማስገንጠል ታግለ።

ኢሕአፓ ለዚያድ ባሬ አድሮ ኦጋዴን፣ ባሌን፣ ሐረርጌ፣ባሌና ሲዳሞን ለዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ለመስጠት ታገለ፤ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረችበት ጊዜ ከኢትዮጵያ ጠላት ሞቃዲሾ ድረስ ሄዶ ተልዕኮ ተቀበለ። ለወያኔ ያደረውና “እኛ ከኢሕአፓ ተለይተን የወጣን ትክክለኛ ኢሕአፓዎች ነን” ያለው በበረከት ሰምዖን የሚመራው ኢሕአፓ ደግሞ በመንግስትነት ወንበር ላይ ተሰይሞ “ኢትዮጵያ ሶማሊያ እንድትበታተን ተጠያቂ ናት” ሲል የሚገዛትን አገር በልሳኑ በማለዳ መጽሔት የመጀመሪያ እትሙ ከሰሰ።

በአለም ላይ የሚገዛትን አገር በወንበሯ ተቀምጦ ሌላ አገር ተበታትና እንድትፈርስ አድርጋለች ብሎ በክስ ደረጃ መግለጫ ያወጣ ቢኖር “እኛ ከኢሕአፓ ተለይተን የወጣን ትክክለኛ ኢሕአፓዎች ነን” የሚለው የታምራት ላይኔና የበረከት ሰምዖን ኢሕአፓ ብቻ ነው። ኢሕአፓውያን ሳይማር ባስተማራቸው አርሷደር ላይ ያንን ሁሉ ክህደትና በደል መፈጸማቸው ሳያንሳቸው “ለኢትዮጵያ እንደታገሉ” የሚተርኩ የሐጢዓት ድርሳናት እየደረቱ ዛሬ በድጋሚ ይዋሹናል! የሁላችንም እውቀት በአንድ ለናቱ የመንግስት ሬዲዮና ቴሌቭዥን የሰማነው ብቻ እየመሰላቸው ነሰድ አገላብጦ የሚያጋልጣቸው ሰው ያለ አይመስላቸው። ኢሕአፓ በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸመው በደልና የአገር ክህደት የሚጠየቅበት ጊዜ ይመጣ ይሆን??