ውሸት ሲደጋገም . . . አቶ አበበ ቦጋለ ስለሚባለው የግንቦት 7 አፈ-ቀላጤ

Print Friendly, PDF & Email

(አቻምየለህ ታምሩ)

ውሸት ሲደጋገም. . . [ ክፍል ፪]

አንዳንድ ሰዎች አደባባይ ላይ የሚናገሩትን ንግግር በአንክሮ የሚመለከትና የሚመረምር ሰው ያለ ስለማይመስላቸው የተለመዱ የሚመስሉ ውሸቶችን እንደ ሀቀኛ ታሪክ በድፍረት ያስተጋባሉ።

አቶ አበበ ቦጋለ ሰሞኑን ከ EthioTube ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያን የኤርትርራን ፌድሬሽን በማፍረስ ከሰዋል። ለወትሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣትና አገር ለማስተዳደር የሚታገል አንድ ሰው እታገልላታለሁ የሚላትን አገር ምንም ቢሆን ምንም መክሰስ አልነበረበትም። የሆነው ሆኖ አቶ አበበ ኢትዮጵያን ለመክሰስ ያበቃቸው በተደጋጋሚ በወሬ የሰሙትን የግራ ፖለቲከኞች የሀሰብ ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው በማመናቸው አልያም እነ ወያኔ፣ ኢሕአፓ፣ ሻዕብያና ሌሎች የግራ ድርጅቶች በፕሮግራማቸው የጻፉትን አንብበው እንደ እውነት በመውሰዳቸው ነው። የኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት ጥናት ያደረጉ ሰዎች የጻፉትን መጽሀፍ ቢያነቡ አሊያም ከጉዳዩ ጋርአጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የተጻፉትን ቢያነቡና የተናገሩትን ቢያደምጡ ኖሮ ግን የተሳሳተውን የወያኔ፣ የኢሕአፓና የሻዕብያ ፕሮፓጋንዳ በመድገም ራሳቸውን ትዝብት ውስጥ አይጥሉም ነበር።

የኤርትራን ፌድሬሽ መፍረስ በሚመለከት አምባሳደር ዘውሬ ረታ የጻፉትን ዝነኛውን «የኤርትራ ጉዳይ» መጽሀፍ ለጊዜው እንተወውና ስለፌድሬሽኑ መፍረስ ፌድሬሽኑ ሲፈርስ የኤርትራ እንደራሴ የነበሩትና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት ቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል የተናገሩትን ቃል ማዳመጥ በቂ ነው። ስለፌድሬሽኑ መፍረስና ይህንን ተከትሎ በግራ ፖለቲከኞች ስለተስተጋባው ጉዳይ አይደለም አቶ አበበ ቦጋለ፤ የሻዕብያው አምበል ኢሳያስ አፈወርቂም ከቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል በላይ ሊያውቅና ምስክር ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ «ማን ያውራ የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ» ነውና ብሂሉ የኤርትራን ፌድሬሽን በማፍረስ ረገድ ተጠያቂው ማን እንደሆነ ባለጉዳዩና የኤርትራ ፌድሬሽን ሲፈርስ የኤርትራ አስተዳደር እንደራሴ ወይንም ገዢ የነበሩት ቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል እውነቱን ይነግሩናል።

ቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል እንደሚነግሩን የኤርትራ ፌድሬሽን ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል የተወሰነው ሐሙስ ህዳር 6, 1955 ዓ.ም. ሲሆን ይህም ውሳኔ የኤርትራ ምክር ቤት 62 አባላት፤ ሙስሊም ክርስቲያን በሚል ሳይለያዩ ያለ አንድ ተቃውሞ ባደረጉት ምርጫ መሰረት ነው።

ከታች በታተመው የቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል ንግግር፤ ፌድሬሽኑ እንዲፈርስ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጫና ተደርጎባቸው እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ «ውሸት፣ ሀሰት፣ ሀሰት. . . ፌድሬሽኑ እንዲፈርስ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጫና ቢኖር ኖር መጀመሪያ የምሸፍተው እኔ ነበርሁ፤» ሲሉ የኤርትራ ፌድሬሽን የፈረሰው «ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት መሆን በሚያስገኝው የኤርትራ ጥቅም ላይ ብቻ በመመስረት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ መዋሀዷ ይጠቅማል? ወይንም አይጠቅምም? በሚል ኤርትራውያን ወደው ያደረጉት ነጻ ውሳኔ» እንደሆነ በአንደበታቸው ይናገራሉ። ቀጠል አድርገውም አጼ ኃይለ ሥላሴ የፌድሬሽኑን መፍረስ ፈጽሞ የማይናፍቁት እንደነበሩ በግንባር ቀደምትነት የሚያቁትንና የወቅቱን እውነት ለዛ ባለውን አንደበታቸው ይነግሩናል!

እንግዲህ! በደተጋጋሚ እንዳልነው ዘመኑ የማይዋሽበት ነውና የኤርትራ ፌድሬሽን መፍረሱ የኤርትራውያን የራሳቸው ሙሉና ነጻ ፈቃድ ሆኖ የተፈጸመ እንጂ የግራ ፖለቲከኞች ሲያስተጋቡ እንደኖሩት የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ውጤት አለመሆኑን በክምችት ክፍላችን ሙሉ ንግግራቸው የሚገኘው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ እ.ኤ.አ. በ1997 ዓ.ም. በመዲናችን በአዲስ አበባ ከዚህ አለም የተለዩት የቀድሞው የኤርትራ አስተዳደር እንደራሴ ቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል ሀቁን ፍንትው አድርገው ይነግሩናል።

ስለዚህ የአርበኞች ግንቦት ሰባቱ አቶ አበበ ቦጋለ የኤርትራን ፌድሬሽን መፍረስ አስለመክቶ የተናገሩትን የተለመደ ውሸት ከዋናው ምስክር ከቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል በላይ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው እውነተኛ ምስክር ሊኖር አይችልምና ሲደጋገም የኖረውን የተለመደ ውሸት ከታች የታተመውን የከቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤልን መልስ አዳምጠው በህዝብ ፊት የሳቱትን ስህተታቸውን ማረም ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ አበበ ቦጋለ የኤርትራ ችግር የጀመረው ፌድሬሽኑ በመፍረሱ እንዳልሆነ ማወቅ አለባቸው። የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር [ELF] ፋኖዎች ኤርትራን «ነጻ ለማውጣት» በረሀ የወረዱት ኤርትራ በፌድሬሽን ትተዳደር በነበረበት ወቅትና የኤርትራ ፌድሬሽን ከመፍረሱ ከአመታት በፊት ነው። ስለዚህ ኤርትራን «ነጻ የማውጣቱ» የነጀብሃ እንቅስቃሴ መጀመር ከኤርትራ ፌድሬሽኑ መፍረስ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለምና የተለመደውን ውሸት ስንደግም መኖር የለብንም።

የኤርትራ እንደራሴ ቢትወደድ አስፍሀ ወልደ ሚካኤል   —   አቶ አበበ ቦጋለ የሚባለው የግንቦት 7 አፈ-ቀላጤ