ጠቃሚ ምክሮች በውጭ ለምንኖር የአማራ ሕዝብ ማህበርሰብ አባላት በሙሉ

Print Friendly, PDF & Email

ገና ብዙ መንገድ ስላለብን የሚከተሉትን የግድ ልናደርግ ይገባል!

(ምስጋናው አንዱአለም)

1. አንድን የአማራ ድርጅት፣ የጽዋ ማህበር እንኳ ቢሆን የጎሪጥ እንኳ ማየት ፈጽሞ እንዲቆም መጣር፡፡ በአማራ ስም የተሰባሰቡ ወገኖቻችንን ድርጅት ወይም ማህበር ስንነካ በውስጡ ያሉትን ወገኖች ሞራል መንካት መሆኑን ማወቅ፡፡ በሌላው የአማራ ድርጅትም ሆነ ማህበር ላይ አለማሴር፡፡ ማኛውንም ስብስብ ከአማራ ህዝብ አጠቃላይ ትግል አንጻር እንጅ ከራስ ፍላጎትና ከድርጅት ፍላጎት ብቻ አለማየት፡፡ ነገር ግን የድርጅቶች አላማ ለህዝብ የማይጠቅም ከሆነ፣ አካሄዳቸው ስህተት ከሆነ በድፍረት፣ በግልጽ መተቸትና ለማስተካከል መሞከር፤ የማይስተካከሉ ከሆነ ለማስቆም መሞከር፡፡

2. አንድን የአማራ ተቆርቋሪ ወገን በምንም ተአምር አለመንካት፤ ይልቅም መደገፍ፣ ማበረታታትና መንከባከብ፡፡ በአሉባልታ ስም ከማጥፋት መቆጠብ፡፡ የሁሉንም ሰብእና ገድለን ብንጨርስ ነገ ራሳችን ነን መሪ የምናጣው፡፡ አንድ አማራ 50+ ጠንካራ ጎን ካለው እሱ ላይ በማተኮር የተቀረውን ደካማ ጎኑን በማረምና በመገሰጽ ማስተካከል እና የበለጠ ጠቃሚ ወገን ማድረግ፡፡ ነገር ግን ከአማራ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ተጻራሪ የሆነ አላማ የሚራምዱትን ፊት ለፊት መጋፈጥና እኩይ አላማቸውን ለህዝብ ማሳወቅ፡፡

3. የተሳሳተን ለመተቸት ደፋር መሆን፡፡ ይህ ግን ክብረ ነክ ስድብን አይጨምርም፡፡ መሪውን የሚፈጥረው ህዝብ መሆኑን አውቀን ያለ ይሉኝታ መተቸት፣ መምከርና መገሰጽ ጥቅሙ ለራሳችን ነው፡፡ ዛሬ በይሉኝታ ብናልፈው ነገ ሌላ ከባድ ችግር እንደሚያመጣብን አውቀን በጊዜ ማስተካከል፡፡ ይህ ሲሆን ግን በእውነተኛ መረጃ ተመስርተን እንጅ በአሉባልታ ተመስርተን ሊሆን አይገባም፡፡

4. የአማራ ህዝብ የሚያስፈልገው አንድ ማእከላዊ ድርጅታዊ አመራር ነው፡፡ በተለይ በውጭ አገር ህዝቡ ከአንድ በላይ ድርጅት ለመሸከም ይከብደዋል፡፡ ምክንያቱም በውጭ የሚኖረው ወገናችን ኑሮው ራሱ ከባድ ጦርነት ነው፤ በዛ ላይ ሁለትና ሶስት ቦታ ልናዋክበው አይገባም፡፡ በተግባር ሲታይ ብዙ ድርጅት በውጭ አገር ለወገናችን አይጠቅምም፡፡ ወደአንድ መምጣት አለበት፡፡ ህዝቡም በየቦታው በየአጋጣሚው ይሄንን አቋሙን ቅልብጭ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ በነገራችን ላይ ህዝባችን ለመታገል በጣም ዝግጁ ነው፤ ግን መስመሩ አንድ ብቻ እንዲሆንለት ይሻል፡፡ ይሄ ደግሞ የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ የምናደርገው ትግል እንዲሳካ በአንድነት እንድንቆም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል መስራት፡፡