የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት የዘጠንኛው ማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ የአቋም መግለጫ

Print Friendly, PDF & Email

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ቅዳሜ ጥር ፳፯ ቀን ፪ሺህ ፱ ዓ.ም. ቅፅ፭፣ ቁጥር ፲፩

የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት የዘጠንኛው ማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ የአቋም መግለጫ (pdf)

እኛ የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ዛሬ ጥር ፳፯ ፪ሺ፱ዓ.ም[ ፌብሩዋሪ 4/2017 ] በአካልና በዘመናዊ ቴክኖሎጅ በመታገዝ ባደረግነው የአንድ ቀን ስብሰባ፣ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የቀረበውን የምክር ቤቱን የ፮ ወር የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የድርጅቱ የቁጥጥርና ፍተሻ ሪፖርት፣ የአካላት ሪፖርትን አዳምጠን፣ ባደረግነው ውይይት፣ ድርጅቱ በ፰ኛው ምክር ቤት በሚቀጥሉት ፮ ወሮች እንዲሠሩ ብሎ የተስማማባቸው ዕቅዶች መቶ ለመቶ ሊባል በሚችል ደረጃ መከናወናቸውን ከሪፖርቱና በተጨባጭ ከሚታዩት የሥራ ውጤቶች ተረድተናል። ይህም ሞረሽ ወገኔ ለዐማራው ድምፅ የመሆንና ዐማራውን ከፈጽሞ ጥፋት የመታገድ ዓላማውን በተግባር እያረጋገጠ የመጣ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል።

በሌላ በኩል፣ በሪፖርቱ በሚገባ እንደተብራራው፣ የዐማራውን ኃይል ሆኖ መውጣት የማይሹ ወገኖች፣ ዐማራውን በክፍለሀገራት በመከፋፈል ለማደራጀት የሚደረው ጥረት ታላቅ ሤራ መሆን ምክር ቤቱ ግንዛቤ ጨብጧል። ይህንም እንቅስቃሴ በትዕግሥት፣ በማስተዋልና በጥበብ በዚህ ከፋፋይ ዓላማ የተሠማሩ ወገኖችን በማስረዳት የዐማራውን ኅልውና የማስጠበቅና የኢትዮጵያን አንድነት የማረጋገጥ ጥረት ሂደት ተካፋይ እንዲሆኑ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለብን የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰናል።

ምክር ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከተወያያባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የዐማራው የተጋድሎ እንቅስቃሴና ይህን እንቅስቃሴ ወያኔ በኃይል ለመደፍጠጥ እያደረገ ስላለው የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው። በመሆኑም ምክር ቤቱ ዘረኛው የትግሬ ወያኔ ዐማራውን ሳያጠፋ እንቅልፍ የማይወስደው መሆኑን ባለፉት ፳፮ ዓመታት በዐማራው ነገድ ላይ የወሰደውና እየወሰደ ያለው የጅምላ ጭፍጨፋ የሚያረጋግጥ እንደሆነ በመተማመን፣ ዐማራው ከተደገሰለት የዘር ዕልቂት ብቸኛ መውጫው ራሱን አደራጅቶ ኅልውናውን በማስጠበቅ፣ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ማስከበር እንደሆነ ታምኖበታል። ለዚህም የዐማራውን ትግል የሚመጥን የፖለቲካ ድርጅት መሠረቱን አገር ቤት ያደረገ፣ በአስቸኳይ ተመሥርቶ ለተጀመረው የዐማራ ተጋድሎ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስነናል። ለነዚህ ሁሉ ዳብሮ መቀጠልም፣ የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት አካላትና አባላት ያለፈ ጥረታቸውን በእጥፍ ድርብ በማሳደግ የዐማራውን ኅልውና የማረጋገጥ ጥረቱ የተሳካና የሰመረ እንዲሆን የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል።

፩ኛ/ በዐማራው ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖችና ግለሰቦችን ለፍትሕ ለማቅረብ የተጀመረው የፍትሕ አፈላላጊ ፕሮጀክት አካል የሆነው የጥናት ውጤት በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ፣ አሕጉር አቀፍና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲደርስ የሚያስፈልገውን የገንዘብ፣ የዕውቀት፣ የመረጃና መሰል ተግባሮችን ከምንጊዜውም ሁኔታ በላቀ ደረጃ ኃላፊነታችን ለመወጣት ቃል እንገባለን።

፪ኛ/ ለዐማራው ነገድ የሀሳብ መለዋወጫ፣ የመማማሪያ፣ የመረጃ መለዋወጫና የማሳወቂያ አንደበት የሆነው የዐማራ ድምፅ ራዲዮ የቆመለት ዓላማ የሰመረ እንዲሆን፣ የሚያስፈልጉትን የሰው ኃይል፣ የመረጃ፣ የገንዘብና የቁሣቁስ ድጋፍ፣ በየምንኖርበት አገሮችና ከተሞች የዐማራ ድምፅ ራዲዮ ድጋፍ ሰጭ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ተፈላጊዎቹ ግባቶች ያላማቋረጥ ፈሰስ እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።

፫ኛ/ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የተመሠረተበትን ለዐማራው ድምፅ የመሆን፣ በማንነቱ ወንጀል የፈጸሙበትን ለፍትሕ የማቅረብና የዐማራውን ሁለንተናዊ ዓቅም የመገንባት ትግል በቋሚነት የምንገፋበት ሆኖ፣ ዐማራው ማንነቱን አስጠብቆ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁነኛ ቦታውን እንዲይዝ ለማስቻል በቅርብ መሠረቱን አገር ውስጥ ላደረገ የፖለቲካ ድርጅት በመረጃ፣ በሰው ኃይል፣ በቅስቀሳና መሰል ተግባሮች የጀርባ አጥንቱ ሆነን ለመቆም በቁርጠንነት ተነስተናል።

፬ኛ/ ከሁሉም በላይ እኛ የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት አባሎች ዐማራውን በክፍለሀገር፣ በፆታ፣ በዕድሜና በመሳሰሉ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች በመከፋፈል አንድነቱን ለማሳጣትና የተከፈተበትን የዘር ጥቃት ባንድነት ቆሞ እንዳይመክት የሚደረገውን ሤራ በቸልታ የማናየውና ይህ ዓይነቱ ተግባር ዐማራው እንደትናንቱ በዝምታና በይሉንታ የማናየው መሆኑን ወዳጅም ጠላትም እንዲያውቁት እንሻለን።

፭ኛ/ ባለፉት ፳፮ ዓመታት የትግሬ ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በዐማራው ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ገደፉን ጥሶ መፍሰስ በመጀመሩ የተነሳ፣ በወላቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ያስነሳው ሕዝባዊ ቁጣ፣ ወያኔ ሰጠሁት ያለውን ሕገ- መንግሥቱን አግዶ ፣በዐማራው ላይ የጅምላ ግድያና አፈና ማካሄድ ከጀመረ ወራቶች ተቆጥረዋል። ይህን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለመደፍጠጥ ወያኔ ያለ የሌለ ኃይሉን በዐማራው ነገድ ላይ አሰማርቶ ሕዝቡን ሲዖል ከተውታል። ጭቆና በበዛ ቁጥር ተጨቋኙ ወገን እንብተኝነቱን የበለጠ ማጠናከሩ የኅብረተሰብ ዕድገት ሕግ በመሆኑ፣ ዐማራው የተጫኑበትን ያፈና መዋቅሮች በጣጥሶ ትግሉን በማጧጧፍ ላይ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ይህ ትግል ወደ ተፈላጊው ግብ እንዲበቃ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የቆመለትን የዐማራ ድምፅ የመሆንና ዐማራውን ከፈጽሞ ጥፋት የመታደግ ዓላማ ለማሳከት ለዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንገባለን።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!