እንደ በለሴውም ሆነ እንደ ወገሬው፤ እንደ ፋርጣውም ሆነ እንደ መንዜው፤ እንደ አገውም ሆነ እንደ ወልቃይቴው – ቅማንትም አማራ ነው፤ በቅማንት ላይ የሚደርስ ጉዳት በአማራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው! – ዳግማዊ መዐሕድ

Print Friendly, PDF & Email

ጥር ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓም (05 February 2017)
ዳመዐሕድ 007/2009/2017

እንደበለሴውም ሆነ እንደ ወገሬው፤ እንደ ፋርጣውም ሆነ እንደ መንዜው፤
እንደ አገውም ሆነ እንደ ወልቃይቴው – ቅማንትም አማራ ነው፤
በቅማንት ላይ የሚደርስ ጉዳት በአማራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው!

የዐማራ ሕዝብ፤ በብዙ ዘርፍ የዘር ግንድ የተገነባ፤ ተመሳሳይ የሆነ ስነልቡና፣ ወግ፣ ልማድ፣ ባህልና ቅርስ በውልጠት ያበለጸገ ሕዝብ ነው። አንዳንድ ጊዜ አሁን በብዛት በሚኖርባቸው መልክዓ ምድር ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ሸዌ፣ ወሎዬ በሚል የተለምዶ አጠራር ሲታወቅ በተጨማሪ ደግሞ ማህበራዊ ውልጠት ቋንቋን በተለየ ባሳደገበት አካባቢ ቅማንት፣ አገው፣ አርጎባ፤ ወይጦ፤ ቤተ እስራኤል ወዘተ በመባል ይታወቃል። በመልክአ ምድርም ሆነ በቋንቋ ማንነቱ የሚገለጸው ዐማራ ከአንድ የዘር ግንድ ቅርንጫፍ የተፈጠረ እንጅ ምንም ዓይነት መሰረታዊ የስነልቡና ልዩነት በመካከሉ እንደሌለ ቢታወቅም፤ ራሱ ዐማራው ሳይሆን ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚቋምጥለትን የታላቋ ትግራይ ተስፋፊ አላማ ለማሳካትና አላማውን በተከታታይ ያከሸፈበትን ጀግና የዐማራ ህዝብ ለመከፋፈል፣ ለማዳከምና ለመበቀል፤ ለራሱ ጥቅም ሲል ሰው ሰራሽ ልዩነቶችን በመፍጠር በዐማራው የህልውና ተጋድሎ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ለመቸለስ አሁንም የተለመደውን ቅማንትና ዐማራ ብሎ የመከፋፈል ዕኩይ ስራውን መጀመሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ለዘመናት በደም ተሳስሮና ተዋህዶ፤ አገሩን በጋራ ከወራሪም ሆነ ከውስጥ ጠላት ተከላክሎ፤ ለረዥም ዘመናት

በተለምዶ መኖሪያወቹም ሆነ ከዚያም ወጣ በማለት በመላ ኢትዮጵያ ተሰማርቶና ተሰባጥሮ የሚኖረው ዐማራ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የደረሰበት ግፍ አልበቃ ብሎ ዛሬ እንደ አንድ ሕዝብ የህይወቱ ቅድስና፤ የንብረቱ ባልቤትነት ተከብሮለት በነጻነት የመኖርና የመቀጠል መብቱ በመገፈፉ፤ የሞት ወይም የሽረት፤ የህልውናና ሉዓላዊነት ትግል ውስጥ ይገኛል። ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በዐማራው ሕዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል ዕልቂት፣ ግፍና በደል እየፈጸመ ይገኛል። ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ሊያጠፋው የሚፈልገው የዐማራው ዘር (ወገሬውን፤ ፋርጣውን፣ በለሴውን፤ መንዜውን፤ ጣቁሴውን፣ ደምቤውን፤ ጋይንቴውን፤ ዳሞቴውን፤ ላኮመንዛውን፤ ላስቴውን፤ ሰቆጤውን፣ ቅማንቱን፣ አገውን፣ ቡልጌውን፣ ሸንኮሬውን፤ ይፋቴውን ወዘተ..) መሆኑን በግልጽ አውጆ ዛሬ በከባድ መሳሪያና በብዙ ጦር በመውረር በጅምላ እያስጨነቀ፣ እያሰረ፣ እየረሸነ፣ እየጨፈጨፈ፣ እያሳደደና እያንገላታ፣ ቁም ስቅሉን እያሳየው ይገኛል። አሻፈረኝ ባዩ፣ ለነጻነቱ ቀናዒ የሆነው የዐማራ ሕዝብም ከአያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ጀግንነት ስንቁ አድርጎ፣ ለነጻነቱና ለህልውናው በቆራጥነት፤ በጁ በያዘውና አቅሙ በሚፈቅደው ሁሉ በቅማንት፣ በአገው፤ በበለሳ፤ በወገራ፣ በሰሜን፤ በወልቃይትና ጠገዴ ዐማራ ጎበዝ አለቆችና ጀግኖች ልጆች መሪነት እምቢ እያለና እየተፋለመ ይገኛል። ከመተማ እስከ ደሴ፣ ከደባርቅ እስከ ደብረ ማርቆስ፤ በእያንዳንዷ ከተማ፣ ቀበሌ፣ ወረዳና አውራጃ የደም ግብር እየከፈለ ይገኛል።

ይህን የሞት የሽረት ትግል የዐማራው ህዝብ በአሸናፊነት እየተወጣው ነው። ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ከጭንቀቱ ብዛት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ቅማንት ዐማራወች ከዚህ በፊት ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የጠነሰሰላቸውን ዕልቂት ተቋቁመው፤ ከሌሎች ዐማራ ወንድሞቻቸው ጎን በመቆም የጠላትን ሴራ ከማክሸፋቸውም በላይ በነጋዴ ባህር፣ በመተማ፣ በቋራና ማህበረ ስላሴ በአጋዚ ጦር ላይ ከፍተኛ ድል ተቀዳጅተዋል። አሁንም ዐማራዊ ጀግንነታቸውን እያስመሰከሩ ናቸው።

ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ፋሽስታዊ ህገ መንግስቱን በመጠቀም “የማንነትና ራሥን በራሥ የማሰተደደር” ጥያቄ በሚባል መሰሪ አስተሳሰብ የዐማራውን ሕዝብ በሰው ሰራሽ ልዩነት ከፋፍሎ ለመግዛት፤ በዐማራው ተጋድሎ ዙሪያ አዲሱ ትውልድ እያዳበረ የመጣውን ትግል ለማኮላሸትና ለትግራይ ክልላዊ ጥቅም ሲል ይህንን ፍጹም አንድ የሆነ ሕዝብ ቅማንትና ዐማራ ብሎ በመከፋፈል ወንድማማቾችን እርስ በርስ ለማጫረስ እያወናበደ ይገኛል። ባለፉት አምስት አመታት በዚህ ጣልቃ ገብነት ብጥብጥ ሲፈጥር የቆየው እንቅስቃሴ በመጨረሻ በዐማራው ህዝብ አንድነት ክንድ ሴራው ሲከሽፍበት አሁንም በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በሕዝበ ውሳኔ የቅማንት ዞን እፈጥራለሁ እያለ ከፍተኛ ውዥንብር እየፈጠረ ይገኛል።

ዳግማዊ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት ይህንን እኩይ ተግባር በጽኑ እያወገዘ የዐማራው ሕዝብ ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተልና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተቃውሞውን እንዲገልጽ፣ እምቢተኝነቱን እንዲያሳይና በቀደመ ታሪኩ ሲያደርግ እንደቆየው በአንድነትና በጽናት የመጣበትን የጠላት ሴራ እንዲመክት ጥሪ ያደርጋል። የዐማራን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ የዐማራ ሕዝብ ብቻ እንጅ ከአሁን ወዲያ ማንም ሊወስንበትም ሆነ ሊነግድበት አይችለም። ለትግራይ ክልላዊ ጥቅም ሲባል የአማራ መሬት የጦር ሜዳ የሚሆንበት አንዳችም ምክንያት የለም። እንዲህ ያለው ህገወጥ የማናለብኝነት ጸረ ህዝብ ሴራ ውሎ አድሮ በአማራ ህዝብ እና በትግራይ ህዝብ መካከል ሊያገግም የማይችል ታሪካዊ ቁስል ጥሎ እንዳያልፍ ዳግማዊ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት በጽኑ ያሳስባል።

ቅማንት ዐማራ ነው!
ዐማራውን የሚከፋፍለው ምድራዊ ሃይል የለም!
ድል ለዐማራ ሕዝብ!