አማራነቱን የካደ አፍሪቃዊነቱን ያላወቀ ምሁር ምን ተብሎ ይጠራል ? (መልስ ለፈቃደ ሸዋ ቀና)

Print Friendly, PDF & Email

(ታምሩ ሁነኛው)

ፈቃደ ለሄኖክ የሽጥላ ኢካድፎሩም በሚባለው የግንቦት ሰባት አቀንቃኝ ድረገጽ መልስ ሰጥቷል። የድረገጹ አዘጋጅ ፈቃደን ባማራነቱ እንዳንጠራጠርና ለጽሁፉም ክብደት እንድንሰጠው በማሰብ ከጽሁፉ አናት ላይ ”ኢዲተር፣ አቶ ፍቃደ ሸዋቀና ሕወሃት ስልጣን በተቆናጠጠ ማግስት ከአማራ ብሄር በመሆናቸው ብቻ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩት ከ40 በላይ መምህራን ውስጥ አንዱ ናቸው። ” የሚል ማስታወሻ አስቀምጧል። ማስታወሻው የድረገጹን ወገንተኛነት እንጅ የፈቃደን ወያኔን ተቃዋሚነት የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም። አዘጋጁ ፈቃደ ከብርሃኑ ነጋ ጋር በመሆን መለስ ዜናዊን፡ አባይ ፀኃየንና ሌሎችንም ባንዳዎች አሜሪካ ሲመጡ አስተናጋጅና ምክር ሰጭ እንደነበረ ቀጠል ቢያደርግበት ኖሮ ሚዛናዊነት ይኖረው ነበር። ለማንኛውም አንድን ሰው አማራ የሚያሰኘው ከአማራ መወለዱ ብቻ ሳይሆን የአማራን ስነምግባር መሰረቱ አድርጎ ለአማራው የሚያበረክተው አስተዋጽኦና ተግባሩ ነው። አማራ ነኝ ብሎ አማራን የሚያስጠቃና ለጥቃት የሚያዘጋጅ የሚመደበው ከአማራው ጠላቶች ጎራ ነው።

ፈቃደ አወቅሁ ባይነቱ ብዙ ችግር ውስጥ የዘፈቀው ይመስለኛል። ለሱም ሆነ ለአማራው እጅግ አደገኛ የሆነ ዘመቻ ውስጥም ከቶታል። እንደዚህ ዓይነት የማንነት ችግር ያለበት ሰው አንዴ የተሳሳተ አቋም ከያዘ በሙግትም ሆነ በውይይት ስህተቱን ማሳመን አይቻልም። የሱ ኃሳብ እንጅ የሌላው ትክክል ሊሆን እንደሚችል አይታየውም። በሙግትና በሰድብ መካከል ያለውን ልዩነትም አይገነዘበውም። በመሆኑም እሱ ሲሳደብ ለሙግቱ ማስረጃ ያቀረበ ይመስለዋል። በተጻራሪው በሱ ላይ የሚቀርቡ ትችቶች ለሱ ስድብ እንጅ ሙግት አይደለም።

የአማራውን መደራጀት እንደማይቃወም ተናግሮ ሳይጨርስ እንዲህ ይላል ” እኔ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ከወረድኩ አፍሪካዊ እሆን እንደሆን እንጂ ጎሳ ከረጢት ውስጥ እልገባም አልኩ።” እንዴት ነው የአማራውን መደራጀት የጎሳ ከረጢት እያለ መደራጀቱን አልቃወምም የሚለን? እንዴት ነው በጎሳ ከረጢት የማያምን ሰው አማራውን ከጎሳ አሳንሰው በጏጥ እናደራጅህ ለሚሉት ደጋፊ የሚሆነው? የሚያስበው በምኑ ነው? ምነው ታዲያ የጎሳ ከረጢትን ፈጥራ ራሷን ነጻ ካወጣችውና ኢትዮጵያን በጎሳ ከፋፍላ በመበታተን ላይ ካለችው ኤርትራ ጋር ወዳጅ ሆነ? የሚገርመው ደግሞ ”አፍሪካዊ እሆን እንደሆን እንጂ” የሚለው ነው። ምነው እስከዛሬ አፍሪቃዊ መሆኑን ሳያውቅ ነው እንዴ የኖረው? ኢትዮጵያዊነትን ማጣት ይቻላል። አማራነትና አፍሪቃዊነት ግን የማንመርጠውና የማንቀይረው በተፈጥሮ ያገኘነው ማንነት መሆኑን እንዴት ምሁሩ ሳተው ወይስ አረብ ነኝ ብሎ ያስብ ነበር? ከዚህም ዘሎ አማራነት የመነገጃ ፖለቲካ ሆኗል ይለናል። መስታውት ቤት የሚኖር ቀድሞ ድንጋይ አይወረውርም ይባላል። ነጋዴዉና የአማራውን ኪስ አውላቂ ማን እንደሆነ እናውቀዋለን። በደመቀ ዘውዴ ፎቶግራፍ ማን እንደሚነግድ እናውቀዋለን። ግንቦት ሰባት አርበኛ መስⶀአቸው በለጋ እድሚያቸው ለመታገል ኤርትራ ገብተው አህያ አማራ ተብለው የተጨፈጨፉትና በስር ቤት የሚማቅቁት እንዲሁም አረም አራሚዎች ሆነው የቀሩት ስንት እንደሆኑ አታውቅም? ለራሱ ዜጎች የማይራራ ኢሳያስ አህያ ለሚለው አማራ አጋር ነው የሚለው አስተሳሰብ እንዴት መጣላችሁ?

አወቅሁ ባይነት ካመጣብን ችግር አንዱ እንደ ኢሳያስ ያሉትን ሊያጠፉን የተዘጋጁ ኃይሎች የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዋነኛ አጋር ናቸው ብላችሁ ተቀበሉ መባላችን ነው። አንቀበልም ካልን የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፈትብናል። በባድመ ጦርነት ጊዜ ኢሳያስን ለመውጋት ዘመቻ ያደርግ የነበረ ሰው ዛሬ ምን ታይቶት ነው በኤርትራ ላይ አታቅራሩ የሚለን? ስለኢሳያስ ባህሪና የኢትዮጵያ ጠላት መሆን ተጨማሪ ሃተታ አያስፈልገውም። ሁሉም ያውቀዋል። ግንቦት ሰባት የኢሳያስን ወንጀል ለማጠብ ዘመቻ ቢያደርግም ሃቅን መቀየር አይቻልም። ኢሳያስ የውሸት ታሪክ እንደጻፈው ኢሳትና ግንቦት ሰባትም ስለኢሳያስ የውሸት ታሪ ቢያወሩ ተቀባይነት የለውም። እንደዚህ የተዛባ ግንዛቤ ያላቸው ምሁሮች ነገ ወያኔ የትግራይን ሪፓብሊክ ሲያውጅና የቀረችው ኢትዮጵያ በማንፈልገው ጉልበተኛ ስር ብትወድቅ እነፈቃደ ትግራይ ወዳጃችን ናት ከትግራይ ተነስተን ቀሪዋን ኢትዮጵያን እናድን እንደሚሉ አንጠራጠርም።

ያማራው ክብር በጀግናው አማራ ይረጋገጣል!