እያዳነን ያለውን መድሀኒት ተውት ብሎ ምክር አለ እንዴ???

Print Friendly, PDF & Email

“የአማራን ሕዝብ ከነባር አመለካከቱ አታውጡት” የሚል ሀተታ ዘ አበሻ ላይ ታትሞ አየሁ። ያው የአማራ በብሔር መደራጀት እረፍት ከነሳቸው ሰዎች አንዱ የፃፈው መሆኑ ነው። ሀተታው የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት የደከመውን ድካም፣ እንደ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የዋለውን ውለታ በዝርዝር ያስቀምጣል። በሂደቱም ለሀገሩ ከመቁሰልና ከመሞት ባሻገር ምንም ያገኘው ጥቅም አለመኖሩን፤ እንደውም ከሌሎቹ በተለየ ተጎጂ መሆኑን ይገልፃል።

ከፅሑፉ እንደተረዳሁት ፀሀፊው ከፊት መስመር ባይሆንም ከ60ዎቹ ፖለቲከኞች አንደኛው የነበረ ይመስላል። የዘር ፖለቲካ እንዴትና በነማን እንደተጀመረ፣ ዘረኛው ቡድን ሕብረ ብሔራዊ ድርጅቶችን እንዴት እየቀረጣጠፈ እንደበላቸውና አሸናፊ ሆነ እንደወጣ ታዝቦል። ዘረኞቹ ለአማራ ሕዝብ ያላቸውን ጥላቻ በደንብ እንደሚያውቅ ገልፆል። ህውሃት በሃያ አምስት የአገዛዝ ዘመኑ የአማራ ሕዝብ ላይ ያዘነበውን የግፍ አይነት በፅሑፉ ዘርዝሯል። ከዚህ ሁሉ አተታ በኋላ ሲደመድም “አማራን በብሔር አታሰባስቡት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” የሚል ጅል ድምዳሜ ይሰጣል። ከዛም የብሔር ፖለቲካን አማራ የፈለሰፈው አዲስ ግኝት ይመስል የአማራ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅን ወንድምና እህቶችን ያብጠለጥላል። የብሔር ፖለቲካን ኋላ ቀር እንደሆነ፣ ደካማነት እንደሆነ፣ የአማራ ብሔርተነት የተሸናፊነት ስነ ልቦና ባላቸው ሰዎች የሚስተጋባ ሀሳብ እንደሆነ ይደመድማል። ሀሳቡን የሚገፉት የአንድነትን ጥቅም መረዳት የማይችሉ እፃናት እንደሆኑ ለማስረዳት ብዙ ቃላቶችን አባክኖል። የተወሰኑት ደግሞ በህውሃት ቀለብ የሚሰፈርላቸው ሰርጎ ገብ ቅጥረኞች እንደሆኑ ይፈርጃል።

ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ የአማራ ምሁራን በጣም የሚያናድዱኝ ይህ አይነት አቋማቸው ነው። ሁኔታውን አልተረዱም እንዳይባል የአማራ ሕዝብ ያለበትን ሁናቴ በጣም መርዳታቸውን የሚያሳይ ትንታኔ ሲሰጡ ይታያል። የመረጃም ሆነ የታሪክ ክፋተት የለባቸውም ።በአንድነት ስም የአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን መከራ ሲቸከችኩ ይውሉና አማራ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ምንድነ ነው፣ አማራ በዘር መደራጀት የለበትም፣ በዘር መሰባሰብ ኋላቀርነትና ወያኔነት ነው፣ ሌላም ሌላም እያሉ ሲዘባርቁ ይገኛሉ። ለአምሳ አመታት ችግር ከማውራት ባለፈ አንዳች የተለየ የመፍትሄ ሀሳብ ሲያፈልቁ አይታዩም። ሌላው ቢቀር እነሱ ያልታያቸውን የመፍትሄ ሀሳብ አዲሱ ትውልድ ሲያፈልቅ ሲያዩ እሰየው ብሎ እንደማበረታታት ተመልሰው ያንኑ አምሳና ስልሳ አመት ያቦኩትን ጭቃቸውን ያቦካል።

የአማራ ብሔርተኝነት ውጤቱ መሬት የረገጠና እየሰራ ያለ የመፍትሄ ሀሳብ ነው። በአማራ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘሩ ፀያፍ አንደበቶችን የዘጋ የአማራ ፅንፈኝነት ነው። እነሱ በእንዝላልነት ያስነጠቁትን የአማራ መሬት የማስመለሱን ስራ ቢያንስ እንዲጀመርና አማራ ለእርስቱ እንዲሞት እየቀሰቀሰ ያለው የአማራ ብሔርተኝነት ነው። የትግሬና የኦሮሞ ፖለቲከኞች አማራ የለም እስከማለት ደፍረው እርስቱ ላይ እጣ ሲጣጣሉበት የነበረውን የውርደት ሁናቴ በመቀልበስ መልክ እንድይዝ እያደረገ ያለው የአማራ ብሔርተኝነት ነው። የለም ብለው እርስቱን ሊወርሱ ለሀጫቸውን ሲያዝረከርኩ የነበሩ የኦሮሞና የትግራይ ፅንፈኞች ዛሬ አንደኛው ለእራሱም እኩይ አላማ ቢሆን የአማራን ብሔርተኝነት ሲደግፍ ያየነው የአማራ ብሔርተኝነት ስራ ውጤት ነው። ሌላውና ሰዶ ማባረር ላይ ያለው ህውሃት በኢትዮጵያዊነት ስም ሲያሳድደው የነበረውን አማራ ዛሬ በ180 ድግሪ በመዞር አንድነት አንድነት እንዲል ያደረገው የአማራ ብሔርተኝነት የስራ ውጤት ነው። የአማራ ብሔርተኝነት በጠነከረ ቁጥር የሌሎችን ሕዝቦች ባሕል፣ ልምድ፣ እምነት፣ ቋንቋ በሀይል እየጨፈለቁ ኦሮሞ የሚል የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባቱ ሂደት አፈር ይለብሳል። የሌሎችን እርስት እየነጠቁና ሕዝቦችን እያጠፉ “ኦሮሚያ” የሚል ምናባዊ ሀገር የመመስረቱ ሂደት ይኮላሻል።የአማራ ብሔርተኝነት በጠነከረ ቁጥር “የአማራን ሕዝብ አጥፍቸ ታላቋ ትግራይን እገነባለሁ” የሚለው የህውሃት ሕልም ሰሞኑን እንዳስተዋልነው ወደ ጠዋት ቅዠትነት ይቀየራል። ሌላም ሌላም።

የብሔር ፖለቲካ አዲስ ዛሬ የተከሰተ ነገር ሳይሆን አሮጌ ሀሳብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በዘር መደራጀት ከተጀመረ ወደ ሁለት የሚጠጋ ትውልድ አልፎል። ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ (ጀብሃ) 1961 ዓ.ም, ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) 1973 ዓ.ም, ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ 1975 ዓ.ም። የሻብያን 55+ ዓመታት አስቆጥሯል። ቁራጩን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረውን ሕውሃት ደግሞ 40+ ዓመታትን አስቆጥሯል። ከላይ እእንደተጠቀሰው እነዚህ ድርጅቶች በአንፃራዊነት ስኬታማ ናቸው። ሀገር መገንባት የፈለገው ያሻውን ቆርሶ ሀገር ሆኖል። ሁለተኛው ደግሞ ካርታውን ስሎ፣ ትውልዱን በሚፈልገው መልኩ ቀርፆና አዘጋጅቶ ጉልበት ቢያጥረው ለተግባራዊነቱ የፊተኛውን ልምድ በመቅሰም አረቦችን ልመና ላይ እየተጋ ነው። ሶስተኛው ደግሞ አነሳሱ የራሱን ሀገር የመመስረት ቢሆንም ባለቤት አልባ ሀገር አግኝቶ ዘረፋ ላይ ተሰማርቶል። የነገዋን ነፃ ሀገር ግንባታ እውን ለማድረግ ሳር ቅጠሉን እያጎዘ ነው። በተቃራኒው ደግሞ የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣብቆ ሀብቱን፣ ንብረቱን፣ እርስቱን እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቹን አስበልቷል።

አማራ እንደ ሕዝብ የዘር ፖለቲካን ሲቃወምና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሲያቀነቅን ቆይቷል። ይሄ እውነት ነው። በደርግና ከዛም በፊት በነበሩ ስርሀቶች እንደማንኛውም ዜጋ በገዢዎች ብሔራዊ ጭቆና ቢኖርበትም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ መድረኮች ላይ ሁሉ ከፊት መስመር በመሰለፍ ታግሎል። እስከ ደርግ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ሀገሪቷን የሚያስተዳድሯት መሪዎቿ ሕዝቦቿን ቢበድሉም የሀገር ልዋላዊነት ላይ የፀና አቋም የነበረቸው ነበሩ።የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዱ ነገሮች ላይ ድርድር ብሎ ነገር አያውቁም። መድፍና መትረየስ ይዞ የመጣን የነጭ ወራሪ ከወንዝ ላይ ድንጋይ እየለቀሙም ቢሆን ለመመከት ወደ ኋላ የማይሉ ድንቅ አባቶች ነበሩ። ስለዚህ የአማራ ሕዝብ በነዚያ ስርሀቶች በዘር አለመሰባሰቡ እንደ ብሔር ተጎጂ ቢያደርገውም የዘርን አደረጃጀት እምቢኝ ማለቱና ሕብረ ብሔራዊን መዘመሩ ቢያን ቢያስ ስርሀቶቹ የሚከተሉት ሪወታለም ይደግፈው ስለነበር ለህልውናው አስጊ አልነበረምና ችግር አልነበረበትም።

ዛሬ ሀገር የማፍረስ ስራው የሚሰራው ሀገር እየገዛሁኝ ነው በሚለው አካል ነው። የስርሀቱ ሪዎታለም የተተከለው የሀገር አንድነት ላይ አይደለም። ልዩነት ላይ ነው። ዘር ላይ፣ ቋንቋ ላይ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያዊነት፣ብሔራዊ አንድነት፣ የሀገር ልዋላዊነት፣ ዳር ድንበር ጅኒ ቁልቋል ቦታ የላቸውም። የዛሬው የአማራ ብሔራዊነት፣ አንድነት አቀንቃኝነት ጠላትነቱ ለተገንጣይ አማፂያን ብቻ አይደለም። መንግስት ነኝ ለሚለውም አካልም ነው። መገንጠልን በሚደግፍና በሚያበረታታ ስርሀት፣ መገንጠልን በሚደግፍና በሚያበረታታ ሕገ መንግስታዊ ሰነድ በምትመራ ሀገር የአማራ ብሔራዊነት ፀረ መንግስት፣ ፀረ ሀገር ነው።ስለዚህ የዛሬው የአማራ ብሔራዊነት፣ ኢትዮጵያዊ አንድነት አቀንቃኝነት እንደ ትላንቱ የመንግስት ከለላ ያለው አይደለም። የአማራ ትግል የሕልውና ነው የሚባለውም ለዚህ ነው። ስለዚህ የአማራ ሕዝብ እንደ ትላንቱ በኢትዮጵያዊነቱ ይንገታገት እንጂ ብሔርተኛ መሆን የለበትም የሚል በጣም ጅል የሆነና ሁኔታዎችን ያላገናዘበ አስተያየት ነው።

Gizenew Demelash

#ቤተ አማራ ወደፊት!!!!!