በዐማራ ሕዝብ የሕልውናና የማንነት ትግል ዙሪያ ሊስተዋልና ሊታሰብበት የሚገባ ክስተት፣ የተደራጀ፣ የግል ትግልና መንደር ተኮር ወቅታዊ ሂደቶች

Print Friendly, PDF & Email

(ፈለገ አስራት)

የዐማራን ሕዝብ በማደራጀት  ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ ተደቅኖ ያለው  ሃላፊነትና ውጣውረድ እልህ አስጨራሽ መስዋዕትነቱም እጅግ ከባድ መሆኑ በትግሉ ውስጥ የሚስተዋል ጉዳይ ነው። ስለ ዐማራ ሕዝብ ሰቆቃ  መናገርና በማህበረሰቡ ላይ  እየተካሄደ ያለውን የስነልቦና ጥቃት መመከት የሚያስችል  ዕውቀትና ዕውነት ላይ የተመረኮዘ  ግንዛቤ ማስጨበጥ የእያንዳንዱ የዐማራ አክትቪስትና የፖለቲካ ስብዕና የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን የሚገባ ነው። በዚህ ዙሪያ እየተካሄደ ያለው ተግባር የሚያበረታታ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስለዐማራ ሕዝብ ሰቆቃና የሰቆቃው መንስዔ ግንዛቤ  ያገኘው  የህብረተሰቡ ክፍል ህልውናውን ከጥፋት ለመከላከል በመደራጀት ብሄራዊ ግዴታውን  መወጣት፣ የጥፋቱን መጠን የሚቀንስና  የግድ  መሆን ያለበት ተግባር ነው። ይህን ትግል  ለመጀመር ለማካሄድና ከግብ ለማድረስ ልዩ ስብዕና የሚጠይቅ አይደለም። አንዳንዶች እንደሚሰብኩት ልዩ ስብዕና ያላቸው ታጋዮችና መሪዎች እንፍጠር ብንልም ሃሳባዊ ከመሆን ያለፈ  ተግባራዊ የማይሆን ውጤት አልባ ቅዠት ከመሆን አያልፍም ። ልዩ ታጋይ ማፍሪያ ማሕበራዊ ፋብሪካ ሊኖረን አይችልም።  

እውነታው ግን  በአንድ ህብረተሰብ ወይም ሕዝብ ላይ የሚደርስ ግፍና በደል ሲበዛ፣ ለጋራ ብልጽግናና ዕድገት የአገዛዙ ስርዓት ደንቃራ ሲሆን ፣ወይም የግልና የጋራ ነጻነት ሲገፈፍ ፣ለህሊናቸው ያደሩ ሰዎች ሊታገሉት የግድ መሆኑ ላይ ነው።ታዲያ ይህንን ለማከናወን እኔነትን የሚጠይቀው የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ ጋር ህሊና እየተናነቀ ለመታገል ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራል። ይህም ትግል በግል፣በቡድን ወይም በብቃት በተደራጀ መልኩ ሲቀጥል አንዱ ሌላውን በመደገፍ ወይም በመጎተት መልኩ ይከናወናሉ። በሰለጠነ  የፖለቲካ ዑደት ውስጥ ይህም የሚጠበቅ ክስተት ነው።

በግል የሚደረጉ ትግሎች የተበላሸ ስርዓትን ለመለወጥ ባያስችልም በሰዎች ስነልቦና ላይ ያለው ተጽእኖ   ግምት ውስጥ የሚገባ ነው። ለምሳሌ ሰዎች በወቀሳ፣ ወይም በትችት በመገለጥ እራሳቸውንም እንደምሳሌ ባማቅረብ ለመታገል ይሞክራሉ። ይህም  በዐማራ የህልውና ትግል  ዙሪያ ይሰተዋላል። በሌላ በኩል  ይህ ሁኔታ ከአሁን ቀደም  የኢትዮጵያ ብልሹ ስርዓቶችን ለመለወጥ  ተደራጅቶ መታገል ከመጀመሩ በፊት የስርዓቱን መለወጥ አስፈላጊነት  በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማስረዳት በግል የሚደረጉ የተቃውሞ ሃሳብ ማሰማትን ማስተዋል ይቻላል። ይህ በወቅቱ  ተደራጅቶ በመታገል ስርዓቱን ለመለወጥ ምቹ ሁኔታዎች  ባልተሟሉበት  የተከሰተ በመሆኑ ስለሚሆን ለምንም ነገር ደንቃራነት አልነበራቸውም። እንዳውም አካባቢውን በአስተማሪነቱ በበጎ ጎኑ ሊታይ ይቻላል። አንዳንዴም ከሕብረተሰቡ አድናቆትን ይገለጽለታል ከስርዓቱ አቀንቃኞች ደግሞ እንደ እብደት ወይም በወቅቱ እንደ ቀልድ ሊታይ ይችላሉ።

ይኽው የግል ተቺነትና ፖለቲካዊ ተንታኝነትን  እንደ ጥሩ የትግል መንገድና ሙያ ተወስዶ ተደራጅቶ ከመታገል ይልቅ ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂን በመጠቀም  ስራዬ ተብሎ ተያይዟል። አልፎ ተርፎም  በፖለቲካ መደራጀት አያስፈልግም ፣ በመሀበር መልክ መደራጀቱ ይጠቅማል፣ እንኛ የምንፈጥረው ድርጅት እውን እሰከሚሆን  ሌሎችን  አትከተሉ ፣ አለያም  ዐማራው እንዳይጠቃ  የመሳፍንት ዘመን አካባቢያዊ  አደረጃጀትን መከተል  ይበጃል ወዘተ የሚሉ ቀላልና  የዋህ አካሄዶች የሚመስሉ ነገር ግን ፖለቲካዊ  መሰሪነት የተሞላቸው የዐማራው የሰቆቃ ምንጮች (የትግሬ ፋሽስቶች ከደደቢት  እስከ ምኒሊክ ቤተመንግስት ጉዞዋቸው  መሸጋገርያ ርዕዮታቸው  ሁኖ ያገለገላቸው ይኸው የመሳፍንት የመንደር ፖለቲካዊ ስሜት ነበር ፣ ውጤቱ ግን  መራራ ሁኖ ትውልድ እየገበርን እንገኛለን)ቀጣይ ደባ  ሲከናወን ይስተዋላል።

አንዳንዶቹም  ከዚህ ቀደም  የትኛውም  ድርጅት አባል ያልነበርኩ ወይም ከዚህም ከዚያም ያልወገንኩ ንጹህ እየተባለ ለመንቀሳቀስ ይሞከራል። ታዲያ ይሄ ከየዋህነት፣ ተደራጅቶ መታገል ከሚያመጣው ውጣ ውረድና መስዋዕትነት ፍርሃት፣ ከስንፍና ፣ ወይም ከተስፋ መቁረጥ ሊመጣ ይችላል። ምክንያቱ በውል ባልተነገረለት ተቀናቃኝነትና የጠለቀ የዐማራ ጥላቻ  መሰረት አድርጎ  ዐማራን ለማጥፋት የሚከናወን  መሰሪነት ይገኝበታል። የነኚህን ኃይሎች ችግርና  በሽታቸውን በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ እነዚህ ግለኛ መንገደኞች አማራጭ ለሌለው ተደራጅቶ የመታገል ስልት በአራያነታቸው የሚጫወቱት አፍራሽ ሚና ቀላል አይደለም፣ በሌላ መልኩ  በአጋጣሚ ሊያቀርቡዋቸው የሚችሉት ጥሩ ሃሳቦች ቢኖሩ እንኳን ርካሽ ተወዳጅነት ለማግኘት ካልሆነ በስተቀር በተነደፈ ፕሮግራም ተከታታይነት ባለው መንገድ ተንቀሳቅሰው ትርጉም ያለው ውጤት ሊያመጡ አይችሉም።ተደራጅቶ የሚሰራውን ኃይል ደግሞ ከማጥቆር አልፎ ድርጅቶች ለሚያደርጉዋቸው ውስጣዊና የውጭ የትግል ትንቅንቅ በአመዛኙ አፍራሾች ሆነው እናገኛቸዋለን። መጨበጫ ውል የሌለው  መልዕክት የሚያሰራጩ ፣ ትግሉ በወሬ ተጀምሮ በወሬ የሚያልቅ ይመስል ፣ ከአክትቪስቶቹ መስፈርትና  ፈቃድ ውጭ  ተዳራጅቶ መታገል ዋጋ እንደሌለው  የሚነገረው ሁኔታ፣ ሰዎች ለግል ትምክህታቸው ሲሉ ትግሉ ላይ የሚፈጥሩት ጫና በመሆኑ ሊገታ ይገባል።የዐማራ ሕዝብ የህልውናና የማንነት ትግል  ፖለቲካዊ ውሳኔን የሚጠይቅ ዋና ጉዳይ መሆኑ ክርክር የሚደረግበት ጉዳይ አይደለም።  

ፖለቲካዊ ጉዳዮች በአግባቡ ለማሕበረሰቡ  ጠቃሚ ውጤቶችን ለማስጨበጥ ከቡድን ተነስቶ ወይም ከአጀማመሩ በብቃት ተደራጅቶ መታገል  በየትኛውም መመዘኛ አማራጭ የሌለው ነው።በርግጥ  የተደራጀው ትግል ውስጣዊ  ሁኔታውን እየመረመረ ለታለመለት የዐማራ ሕዝብ  የህልውናና የማንነት   መብት መረጋገጥና መከበር  ሳይሆን ተድበስብሶ የዐማራ ሕዝብ ችግርና ሰቆቃ የማይቀርፍ  ሁኔታዎችን  እንዳይፈጥር  ወይም  የዐማራን ሕዝብ የሰቆቃ  ዘመን እንዳያራዝም  ክትትል ማድረግ ላፍታ እንኳን ቸል የምንለው  ሊሆን አይገባም። ለዐማራ ሕዝብ የህልውናና የማንነት  ትግል ውጤታማነት ከልብ የተነሳን  እርስ በርስ በረባ ባልረባው  መላተም አስወግደን  ግዜያችንንና  ትኩረታችንን ወደ ቆምንለት  ዓላማ  ላይ ማተኮር ይገባናል። ጭብጨባና ግርግር  ወደ ነጻነት የሚወስድ ሳይሆን  እንዳውም  አንዳንድ አክቲቪስቶችና  ፖለቲከኞችን  ስሜታዊ በማድረግ ከነባራዊ ፖለቲካዊ ዑደት ሊያስፈነጥራቸውና ትግሉን ከሚጎዱበት ጀብደኝነት ላይ ያደርሳቸዋል፣  ስለዚህ በዐማራ የህልውናና የማንነት ትግል ዙሪያ  እዩኝ እዩኝ ባይነት ፣ጭብጨባና  ግርግር አጥብቀን ልንጠየፈው የሚገባ ፖለቲካዊ ባህላችን ሊሆን ይገባል።   

በመጨረሻም የዚህ ሁሉ  ማርከሻ  የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሁለንተናዊና ቁሳዊ ግንዛቤያቸው ከፍ ብሎ በመካከላቸውና በሚመሩት  የሕብረተሰብ ክፍል ያለውን ግንኙነትና እምነትን በማጠናከር ተግባራቸውን ገሃድ በሆነ መንገድ ከተከታዮቻቸው አጠቃላይ ስሜት እንዳይለይ መጣር ይገባቸዋል።

አሮጌውን የአውሮፓውያን ዓመት  ጨርሰን፣ አዲሱን ዓመት ለመቀበል እየተንደረደርን ባለበት በመጨረሻዎቹ ቀናት  በትግራይ ወራሪና ፋሽስታዊ አገዛዝ የመከራ ዝናም የሚወርድባቸውን  ወገኖቼን  ስቆቃ እያሰብኩ፣  እየጨረስን ያለውን አሮጌ ዓመት  የትግል ሂደት ውጤታማነት በመቃኘት አዲሱን ዓመት ለተሻለ የትግልና የድል ዘመን እንጠቀምበት ዘንድ  ለዐማራ የህልውናና የማንነት ታጋዬች ፣ለዐማራ ጉስቁል ሕዝብ ጥሪዬን አቀርባለሁ። በማያያዝም  ለዐማራ ወዳጆች  ኢትዮጵያውያን  አዲሱ ዓመት የድልና በመፈቃቀድና በመከባበር በጋራ የምኖርበት ድል ላይ እንዲያደርሰን እመኛለሁ !!!  

 ድል ለዐማራ ሕዝብ !!!

 ፈለገ አስራት