“መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ” አቶ ማሙሸት አማረ

Print Friendly, PDF & Email

የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ – “መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ”

(ሸንቁጥ አየለ)

ልክ ከእስር ቤት እየወጣ ሳለ የመኢአድ ፕሬዝዳንትን አቶ ማሙሸት አማረን እንኳን ደስ አለህ ልለዉ ስልክ ደዉዬ ነበር:: የመለሰልኝ መልስ በጣም አስደመመኝ:: አሁንም ለትግል ያለዉ ወኔ አለመብረዱም ገረመኝ::ከአስራ ሶስት አመታት በላይ ሲታሰር ሲፈታ የኖረ ሰዉ አለወንጀሉ ታስሮ ሲፈታ ምን ሊሰማው እንደሚችል እኔ ማወቅ አልችልም:: ሆኖም እንኳን አብሮ ደስ ያለን ይለኛል ብዬ ነበር የጠበቅሁት::ሆኖም እሱ “መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ” ብሎ መለሰልኝ:: ማሙሸት አማረ አስከትሎም የሚከተለዉን ተናገረ::

አቶ ማሙሸት አማረ

“ደስተኛ ልሆን የምችለዉ ሁሉም የመኢአድ አመራሮች እና አባላት ሲለቀቁ ነዉ:: ደስተኛ የምሆነዉ ሁሉም የተቃዋሚ ሀይላት ሲለቀቁ : ሁሉም የሰበአዊ መብት ታጋይ ሲፈቱ: ሁሉም ጋዜጠኞች ሲፈቱ ብሎም በመጨረሻ ዲሞክራሲ እና ሰላም የናፈቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን ሲጎናጸፍ ብሎም ኢትዮጵያ ወደ በለጸገ ሀገርነት ደርሳ ህዝቧ ደስተኛ ሲሆን ነዉ::መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ::

አሁን እኔ ተፈታሁ ብዬ ደስታ የለኝ::ምን ደስታ ይኖረኛል? መጀመሪያዉንም የታሰርሁት ያለ ወንጀሌ ነዉ::ስለ ህዝቤ ዲሞክራሲ እና መብት በመታገሌ ብቻ ነዉ የታሰርኩት::
አሁን የእኔ መፈታት ህዝቤም አብሮ ዲሞክራሲን ካላገኘ ምንም ዋጋ የለዉም::የኔ መታሰር እና መፈታት ቁምነገር አይደለም:: ስታሰር እና ስፈታ የኖርኩት ለህዝብ ዲሞክራሲ እና ሰላም ነዉ:: እናም አሁን መፈታቴ ደስተኛ ሊያደርገኝ አይችልም::ምክንያቱም ህዝባችን ዲሞክራሲ: እና እፎይታን ገና አላገኘም እና::

መኢአድን በህጋዊነት ተመርጠን እየመራን ያለን በርካታ አመራሮች አለጥፋታችን ታስረናል::ተሰደናል::መከራ ተቀብለናል::የተገደሉብንም አሉ:: ባለን ያልተጣራ መረጃ መሰረትም ከ120 በላይ የመኢአድ አመራሮች ታስረዋል::እጅግ በርካታ የመኢአድ አባላት እስር ቤት ናቸዉ:: አሁንም በርካታ አመራሮቻችን እና አባላታችን እንደታሰረ ነዉ:: እጅግ ብዙ ተቃዋሚ እና የሰበአዊ መብት ታጋይ እና ጋዜጠኞች እስር ቤት ናቸዉ:: እንደ እኔ እስር ቤቱን አይቶት የወጣ ሰዉ ይሄ ሁሉ ወገን ታስሮ ሳለ ምንም ደስተኛ ሊሆን አይችልም:: አጠቃላይ ኢትዮጵያ ከእስር መፈታት አለባት::ያኔም ህዝባችን ደስተኛ ሲሆን: ዲሞክራሲ ሲሰፍን እና ብልጽግና ያለዉ ማህበረሰብ ሲኖረን ከህዝባችን ጋር ደስተኛ እንሆናለን::”

አቶ ማሙሸት አማረ

የምታስተላልፈዉስ መልዕክት አለህ? ስል ጠየቅቅሁት::ፈጠን ብሎ ሶስት ነገሮችን እንደሚከተለዉ ተንትኖ አብራራልን::

1ኛ. ኢህአዴግ አሁን ያለዉ ብቸኛ አማራጭ አጠቃላይ እስረኞችን በመፍታት: የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ በማድረግ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲና መረጋጋት እንድትገባ ማድረግ መሆኑን መረዳት አለበት::
2ኛ. ተቃዋሚዎች እዚህ እና እዚያ ተበታትነን አሁንም በደካማ አካሄድ ህዝብ እንመራለን የምንለዉን አካሄድ ትተን: ትናንት የገባንበትን መቃቃር አስወግደን አብረን በመስራት የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ የሚያገንበትን እና ዲሞክራሲን የሚጎናጸፍበትን ሂደት ማፋጠን አለብን::

3ኛ. አስመሳይ ተቃዋሚዎች ከአምባገነኖች ጋር በመሞዳሞድ: የአምባገነኖች ሰላይ በመሆን እና እዉነተኛዉን ትግልን ጠልፎ በመጣል የሚያደርጉትን ጸረ ህዝብ አካሄድ እንዲተዉ መገደድ አለባቸዉ:: የኢትዮጵያን ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ማዳከም እና ማጓተት በህዝብ እንደሚያስጠይቃቸዉ ማወቅ አለባቸዉ::

***********

ማሙሸት ብርቱው ሰው እንኳን ከመከራ ቤት አወጣህ!! – Yilkal Getnet

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በገዥዎቻችን የተመሰረተበት የፈጠራ ክስ ተቋርጦ እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው ታጋዮች አንዱ ሁኖ “ለስልጠና” ከእስር ቤት መውጣቱን ሰማሁ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ውስጥ የሚከፈለው መስዋዕትነት እስከ ዛሬዋ ሰዓት ድረስ ለማሰብም የሚዘገንን ነው። በዚህ የፖለቲካ ትግል የመጨረሻውን የህይወት መስዕዋትነት የከፈሉትን ሳይጨምር በህይወት ውጣ ውረድ ለትግሉ ሲሉ የተገረፉትን፣ከስራ የተፈናቀሉትን ፣ቤተሰባቸው የተበተነባቸውን፣ በእስር እየማቀቁ ለጋራ ጉዳያችን ሲሉ የግል ህወታቸው የተሰናከለውን ለሃገራችንና ለእያንዳንዳችን ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማስታወስ እና ምስጋና ለማቅረብ ባሰብኩ ጊዜ እቸገራለሁ። ለዚህ ምክንያቴ በአብዛኛው በእስር የሚሰቃዩት የቅርብ ጓደኞቸ፣ የትግል ጓዶቸ፣ በቅርብ ባላውቃቸውም እንኳ የእኔን ዓላማ በመጋራታቸው የሚሰቃዩ ናቸው። ይህም በመሆኑ አንዳቸውን ከሌላው ለይቸ ማመስገን በታጋዮች መካከል አድሎ ያደረኩ ስለሚመስለኝ ምርጫየ ዝምታ ሆኗል። በዚህ ሁሉ የስሜት መረበሽ ውስጥም ሆኘ የአቶ ማሙሸት አማረ ጉዳይ ግን በልዩ ሁኔታ ባለእዳነትና የአቅመ ቢስነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ማሙሸት ከለጋ የወጣትነት እድሜው ጀምሮ አሁን እስካለበት የጎልማሳነት እድሜ ያለው ጊዜ በሙሉ ምንም አይነት የግል ህይወት ሳይኖረው ለኢትዮጵያ ሲል በመከራና በሲቃይ ቤት ያሳለፈ ሰው ነው። ማሙሸት በሲቃይ ያሳለፈው ጊዜ በሰው ልጅ እድሜ ምዕራፍ ውስጥ በጣም ብርቅዬ የሆነ በትምህርት እራሳችንን የምናሰናዳበት፣ ትዳር መስርተን ልጅ የምንወልድበት፣ ሃብት ንብረት የምናፈራበት አፍላ የህይወት ጊዜ ነው። ይህንን ሁሉ ቁም ነገር ለህይወቱ የሚያከናውንበትን እድሜ ማሙሸት ለእኛ አሳልፎ ሰጥቶናል። ይህንን የማይተካውን ወሳኝ የህይወቱን ምዕራፍ ለሰዋልን ሰው ውለታውን በምን መመለስ ይቻላል? ድካምህና የተቀበልከው መከራ ሁሉ ለሃገርህ በጎውን በማሰብ ስለሆነ እግዚአብሔር የሃገርህን ትንሳኤ ያቀርብልህ፤መንፈስህንም ያበርታህ።ማሙሸት በድጋሜ እንኳን ከሲቃይ ቤት አወጣህ!!!

Yilkal Getnet