“ለምን አሁን?” – (ነፃነት ዘለቀ)

Print Friendly, PDF & Email

ይቺ “ለምን አሁን?” የሚሏት ጥያቄ በጣም ወቅታዊና ተገቢ ጥያቄ ናት፡፡ አብርሃም ያዬህም እንደሚወዳት በቅርቡ ባደረገው አንድ ቃለ ምልልስ ገልጧል፡፡ እኔም “ትመቸኛለች”፡፡ ሲጀመር እኔ ራሴስ “ለምን አሁን” ጻፍሁ? እስካሁን ዝም ያልኩት የሚጻፍበት ጉዳይ ጠፍቶ ነው? አይደለም! ታዲያስ? “ታዲያስ?” ብለህ ከጠየቅኸኝማ የሚጻፍ ነገር ጠፍቶ ሣይሆን የሚጻፈውን ነገር አንብቦ ወደ ተግባር የሚለውጥ ዜጋ በመጥፋቱ ነበር – “አንተን ጨምሮ!” አልከኝ ልበል? ትክክል ነህ፤ ሀገርና የሀገር ጉዳይ የሁሉም እንጂ የአንድ ወይም የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ አይደለም፡፡ ሀገር፣ ሀገር የምትሆነው ሁሉም የኔ ናት ብሎ ሲያስብላትና ሲንሰፈሰፍላት ነው፡፡ እንጂ እንደ እናት ገዳዮቹ ወያኔዎች ባወጣች እየቸበቸቡና “እህ!” ብላ አምጣ የወለደቻቸውን ልጆቿን ባልተወለደ አንጀት በካራ እየዘነጣጠሉ የአንዲት ሀገር ልጆች መባባል አይቻልም፡፡ ብዙዎች ይጽፋሉ፤ “አሁን ታዲያ ምን አዲስ ነገር ተገኘና መጻፍ አስፈለገ?” ተብሎ ሊጠየቅም ይችላል፡፡ ይሄም ጥያቄ ትክክል ነው፡፡ ወረድ ብሎ ማየት ነው፡፡

ሲቀጥል “ ወያኔዎች ሽብርተኛ ብለው ከፈረጁት ኦብነግ ጋር በኬንያ ‹ድርድር› የሚያካሂዱት ለምድነው? ‹አሁን ለምን?› ፤ በውነቱ ኦብነግ በሀገራችን ላይ ‹የደቀነው› ችግር ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ እያስከተለው ካለው ችግር የባሰ ነውን? ወያኔና ‹ጃዝ!› ብለው የላኩት የታችኛው መንግሥት ጌታዎቹ ከመጋረጃ በስተጀርባ ለኢትዮጵያ ምን እየደገሱላት ይሆን?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው – ጥሎባት ለኢትዮጵያ የመከራ ድግስ የማይደግስ የለም፡፡ ምነው የታሪክና የተፈጥሮ ሀብት ድሃ ሆና ተፈጥራ ቢሆን ኖሮ! ድሃ ምን ምቀኛ አለው? ከጀርባው ሌላ ነገር ከሌለው እንግዲያውስ “ድርድሩ” ለምን ቀደም ሲል አልተደረገም? ለምን አሁን? ሀገር በምጥ በተያዘችበት ሰዓት ምን አቻኮላቸው? ብዙ የ“አሁን ለምን?” ጥያቄዎችን መደርደር ይቻላል፡፡

የዚህችን የኦጋዴንን ጉዳይ በተመለከተ ዛሬ ጧት አንዱ ስለሀገሩ የሚንገበገብ ዜጋ በኢሜል አድራሻየ የላከልኝ መልእክት ከነከነኝና የተውኩትን ነገር አስታወስኩ – እናም መጻፍ አማረኝ፡፡ የምጽፈው በትንሹ ነው፡፡ አጠሬራ ዓይነት፡፡ ጊዜው የተግባር ነዋ!

ትንሽ ልጎርር መሰለኝ፡፡ ብዙዎች ተኝተው በነበረበት ወቅት ጥቂቶች ብዙ ለፈለፍን – እንደሰነፉ እረኛ፡፡ እኛ ግን እውነታችንን ነበር፡፡ ይህ ዘመን እንደሚመጣ በሚገባ እናውቅ ነበር – ጥሎብን ምናባዊው ዐይነ ኅሊናችን እያስገደደን እንጂ የተለየን ሆነን አልነበረም፡፡ ለማንኛውም ዛሬም ቢሆን ያን ያህል አዲስ የሚባል ነገር አልተፈጠረም፡፡ እያየን ያለነው ጅምር ነው፡፡ የጫፉን ግርጌ ብቻ! “አባይን ያላዬ ምንጭ ያመሰግናል” እንዲሉ ነው፡፡ እኔን መሰል ለፍላፊዎች ሦርያን በደንብ ያውቋታል – እዚያ ሳይሄዱ፡፡ ሶማሊያን ጠንቅቀው ያውቋታል – እዚያም ሳይጓዙ፡፡ የመንን ያውቋታል – እዚያችም ሀገር ድርሽ ሳይሉ፡፡ የመካከለኛው አፍሪካ “ሪፓብሊክ”ን ፣ ኢራቅን፣ ሊቢያን፣ ዩጎዝላቪያን፣ … ምን አለፋችሁ እንደሞተ ፀጉራም ውሻ ያሉ መስለው የሌሉና የፈራረሱ ሀገራትን አስቀድመው በሦስተኛው ዐይናቸው ጎብኝተው አሳምረው ያውቋቸዋል፡፡ “ጮኹ ጮኹ እንዳልጮሁም ሆኑ” ይለዋል መጽሐፉ በንዴት፡፡ “ነባይነ ነባይነ ከእምዘምነባይነ ኮነ” ይል የለም? አዎ፣ አሁን ግን መጮኹ የነሱ ተራ አይደለም፤ እነሱ ፈዘዋል፤ ዕንባቸውንም ጨርሰዋል፡፡ “የፈሩት መድረሱ፣ የጠሉት”ም መንገሡ ያለና የነበረ ነውና ከአሁን በኋላ የሚመጣውን ነው ክፉኛ መፍራት፡፡ ልብ በሉ – አሁን ምንም አልሆነም፡፡ ወያኔም ዝምቡን እንኳን “እሽ” አልተባለም፡፡ እየተጎዳ ያለው ምስኪኑ ዜጋ ነው፡፡ ምስኪኑ ዜጋም የሞተው ተገላገለ፤ ነገን ስለማያይ የታደለ ነው፡፡ በቁማችን ለምንሰቃየው ነው አምርሮ ማዘን፡፡ ቀባሪ እያለ መሞት ፀጋ ነው፡፡ ነገ የሚፈጠረው ሀገራዊ ትርዒት ለጅብና ለተኩላ የአሥረሽ ምቺው ዳንኪራ የተመቸና ከየትኛውም የዓለማችን ታሪክ የሚለይ ልዩ ዕልቂት ነው – ሌላ ጩኸት!!

“የጨው ተራራ ሲናድ ብልኅ ያለቅስ ሞኝ ይስቅ” ይባላል፡፡ ግሩም ተረት፡፡ እናስተውለው፡፡

በቋንቋችን ትንሽ ልባልግ – ለበጎ መሆኑ ታውቆ ይፈቀድልኝ ታዲያ፡፡ ከፈስ ቀጥሎ ምን እንደሚመጣ ሽንት ቤት ድረስ ሄዶ ማዳመጥን አይጠይቅም፡፡ [ከወንድና ሴት] ፍቅረኛሞች መሳሳም ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል አልጋ ብሶቱን እስኪያሰማ ድረስ ጆሮን እግድግዳ ላይ ለግጦ መጠበቅ ለራስ ስሜትም አለማሰብ ነው፡፡ ዳመና ሲጠቋቁር ምን ሊከተል እንደሚችል አለመገመት ገሣውን ወርውሮ የጣለ እቡይ እረኛ እንደመሆን ነው፡፡ የገረረ የፀሐይ ሙቀት ከሚያስተናግደው በጋ ቀጥሎ የክረምት ቆፈን እንደሚመጣ አለመረዳት የወቅቶችን መፈራረቅ ያለመገንዘብ ችግር የሚያስከትለው ነፈዝነት ነው፡፡ ይህን ተጠየቃዊ ጉዞ አንተው ቀጥልበት….

እሳት ላይ የተጣደ ወተት ለስ ሳይል አይሞቅም፤ ሳይሞቅ አይፈላም፤ ሳይፈላ አይንተከተክም፤ ሳይንተከተክ ከድስቱ ገንፍሎ አይወጣም፤ ከድስቱ ገንፍሎ ካልወጣ ለዚያ ደረጃ ያበቃውን እሳት መልሶ አያጠፋም፡፡ ወያኔም ሆነ የወያኔ ጌቶችና ተላላኪዎቻቸው ያላወቁት ነባራዊ እውታ ይህንን ነው፡፡ ጎበዝ – “የጭንቅላት ሥጋ መብሰሉ ለማይቀር እንጨት ይፈጃል፡፡”

ገበሬ ጥሩ ምርት የሚያፍሰው እንዴትና መቼ ነው? ብለህ ጠይቅ፡፡ መልሱ ቀላል ነው፡፡ መሬቱን በደምብ አርሶ፣ ጎልጉሎ፣ አለስልሶና የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ሲዘራና ሲበቅልለት ደግሞ አርሞ፣ ኮትኩቶ፣ ሸልሽሎና ከወፍና ከጅንጀሮ ጠብቆ … ሲያጭድና ሲወቃ ነው፡፡ ገበሬ ያልዘራውን አምርቶ አያውቅም፡፡ ይህም እውነት ዘመናትን አልፎ የሚሄድ ዘላቂ እውነት ነው፡፡ But people with chronic problem of myopia never understand such realities. They bother not about tomorrow; the sole purpose they live for is to fill their tummy and satisfy their carnal wishes in the whimsical world they have invented for themselves.

በነገራችን ላይ ወያኔም ጎበዝ ገበሬ ነው፡፡ ከተቋቋመበት ከ1968 ለካቲት 11 ወዲህ ሌት እንቅልፍ ሳያምረው፣ ቀን ረፍት ሳያሰኘው ይሄውና እስካሁኒቷ ቅጽበት ድረስ ተግቶ በመሥራት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰው ነፍሶችን አጠፋ፤ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብትና ንብረት ከሀገርና ከምስኪን ዜጎች በመቀማት ከበረ፤ በብዙ ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚገመት የኢትዮጵያ መሬት ገንጥዬ ለራሴ አደርገዋለሁ ብሎ ወደሚቃዥበት ክልልና ወደ ውጭ ሀገራት ይዞታነት አሸጋገረ፤ አማራንና ኦርቶዶክስን ካላጠፋሁ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ በድፍረት ማኒፌስቶው ላይ በመጻፍ ጭምር የጌቶቹን ቀልብና ሁለንተናዊ ድጋፍ ገዛ – (የላኪዎቹን ደጀንነት በግልጽ የሚመሰክረው ይህ ድፍረታቸው ብቻውን እኮ ወያኔዎችን ዘሄግ ላይ ይገትራቸው ነበር – ግን “አንበሣ ምን ይበላል” ቢሉ “ተበድሮ” “ምን ይከፍላል?” ቢሉ ማን ጠይቆ”… እንዲሉ ሆነና ፍርዱን ለታሪክ ሰጥተን ቁጭ ብለናለ) ፤ … ባጭሩ በጌቶቹ የተማመነው ቀበሮው ወያኔ የኢትዮጳያን አናብስት ላለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ደፍቆ ሰይጣን ራሱ እንኳን የማያውቃቸውን ወንጀሎችና ግፎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ፈጸመ፡፡ አሁን ግን ሥፍሩ ሞላ፡፡ ጊዜው ደረሰ፡፡ ግን ግን ገና ምኑም አልተነካም፡፡ የሚታዩ ነገሮች፣ የሚሰሙ ነገሮች ቢኖሩም ወደነዚያ አንገባም፡፡ የነጋበት ጅብ ብዙ ጥፋት እንደሚያስከትልም ልብ በሉ፡፡ እንደማንኛውም አምባገነን መንግሥትና ዐረመኔ የወሮበሎች ቡድን ወያኔም የመጨረሻውን መራራ ጽዋ መጨለጡ ባይቀርም የነፃነትን ጮራ ለማየት ብዙ ድካምና ልፋት ይጠብቀናልና በዱባ ጥጋብ መዘናጋት አይኖርብንም፡፡ ትግሉ ጀመረ እንጂ 25 በመቶ እንኳን የተጓዘ አይመስለኝም፡፡

ይልቁንስ አስደንጋጭ ነገር ልንገርህ፡፡ ወያኔና ጌቶቹ በተለሙለት ጎዳና እየተመመ ራሱንና ወገኑን መቀመቅ ለመክተት የሚራወጠው ኃይል ብዙ ነው፡፡ መጥራቱ ባይቀርም አሁን ዙሪያ ገባውን ሲያዩት ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ ወያኔ ያከፋፈለን የዘርና የሃይማኖት ቁርቋሶ ወደማይቀለበስ ደረጃ ወጥቶ ከመቆራረጣችን በፊት እንምከርበት፡፡ “አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” ይባላል፡፡ ጥሩ ተረት ይመስላልና እናስብበት፡፡

ሰሞኑን በሚደረጉ ሕዝባዊ ዐመፆች ልዩነቶች ጎልተው ይታያሉ፡፡ ልዩነቶቹን ማንም ይፍጠራቸው ማን፣ ለምንም ዓላማ ይፈጠሩ የዞረ ድምራቸው ግን ማንንም አይጠቅምም፡፡ በተመሳሳይ አዙሪት የሚደፍቁንና ለሌላ 30 ዓመታት በአዙሪታቸው የሚያንከራትቱን ናቸው፡፡ አሁን ያለው ነገር ወያኔንና ላኪዎቹን በደስታ የሚያስፈነጥዝ ነው፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳትኖር አድርጎ ቢሳካለት ወደዋሻው መፈርጠጥ ይፈልጋል፡፡ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ጠፍቶ ሰማንያ ቁጫጭ መንግሥታት በ“ቀድሞዋ ኢትዮጵያ” ውስጥ እንደሚሠረቱ ነው ወያኔን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጠላቶች እየሠሩና እያሤሩ ያሉት – እኛ ግን አላወቅንም ወይም አልገባንም፡፡ በዚያ ላይ ቀደም ሲል ከአንድ ሰውዬ የተሰጠንን የመቶ ዓመት የቤት ሥራ መዘንጋት የለብንም፡፡ የቤት ሥራዎች በተከታታይ እየተሰጡንና እነሱን ካለመታከት እየሠራን መጃጃል ከቀጠልን መቼም ልብ የሚባል ነገር መግዛት አልቻልንም ማለት ነውና ከአሁኑ ተመካክረን በየፊናችን ጎጆ መቀለስ ይኖርብናል – የብልጦች መሣሪያ ሆኖ ዕድሜ ልክ በሸረኛ ወጥመድ እየገቡ ከማለቅ በየራስ ጓዳ ገብቶ ጊዜን ማሣለፍም ሞኝነት አይመስለኝም፡፡ እንጂ ቄሮ ብለህ የኦነግ ባንዲራ፣ ፋኖ ብለህ የኢትዮጵያ ባንዲራ፣ ወይን ብለህ የተሓህት ባንዲራ፣ ዴምሕት ብለህ አክሱማዊ ባንዲራ … የትም አያደርሰንም፤ ደግሞስ “አሁን ለምን?”፡፡ የጅልነታችንን መጠን ሳስበው ይደንቀኛል፡፡

ሰው ሆነን እንደሰው በጋራ ሀገር ላይ መኖር ከፈለግን የተሰጠንን የቤት ሥራ የሡልጣን አሊ ሚራን ምክር ተከትለን በርግጫ እንምታው፡፡ ችግራችን ከቋንቋ በላይ ነው፤ ችግራችን ከጎሣና ነገድ በላይ ነው፤ ችግራችን ከምንከተለው ሃይማኖት የዘለለ ነው፡፡ ችግራችን እንደዜጋ ብቻም ሣይሆን እንደሰውም በመቆጠርና ባለመቆጠር መካከል ያለ ነው፡፡ ወያኔ እንደተናጋሪ እንስሳ ቆጥሮ በፈለገው መንገድ እያላጋ ሀገርንም ዜግነትንም ሰብኣዊነትንም አሳጥቶናል፡፡ ይህን ከሰው በታች ያደረገንን ዕኩይ ኃይል አስቀምጠን በቄሮና በፋኖ መቧደን፣ ኢትዮጵያ የትግሬ፣ የአማራና የኦሮሞ ብቸኛ ንብረት የሆነች ይመስል ሌሎቹንና በብዙ አሥራዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ጎሣና ነገዶችን ወደ ጎን መተው፣ ከዚህም በተያያዘ አንድ ቀን የፋኖ ሌላ ቀን የቄሮ ዐድማ መጥራት በርግጥም ያለፉት 27 ዓመታት ምንም ነገር አላስተማሩንም ማለት ነው፡፡

የተጣለብንን አፍዝ አደንግዝ አስወግደን ትግላችንን በአንድ ላይ ካላስተባበርን ጠላቶቻችንን ጨምሮ የዓለም መሣቂያ መሣለቂያ እንደሆን እንቀራለን፡፡ ደግሞም ለውሻ ፍርፋሪ እንደሚጣል ወያኔ ከወሰደብን ብዙ ነገሮች መሀል ስንከተለው እዚህ ግባ የማይባል ጥቂት ነገር ባደረገ ወይም ለማድረግ ባሰበ ቁጥር “ይህ ድል የኛ የትግል ውጤት ነው!” እያልን በከንቱ አንታበይ፡፡ ወያኔ … TPLF is really so smart even to the extent of cheating its own Father in the Netherworld. “በዐመፅ ስላንበረከክናቸው እነእገሌን ከእስር ሊፈቱ ነው!” ዓይነት ጉራ በፍጹም አይጠቅምም፤ እንዲያውም በጣም ጎጂ ነው – ወያኔን ይበልጥ መንቻካና ጨካኝ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ስለተባለም የሚፈቱ እንዳይመስለን፤ ጊዜ መግዣ ነው፡፡ ሲጨነቁ የሚያደርጉትን እኛም እነሱም እናውቃለን፡፡ ምናልባትም ከጌቶቻቸው ምክር እየተሰጣቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ የሚሠራ አይጮህም፡፡ ቁም ነገረኛ አይፎክርም፤ ልባም ‹አይጎርርም›፡፡ ሙያ በልብ ብሎ ከፈጣሪ ዕርዳታ ጋር ሥራውን በኅቡዕ ያከናውናል፤ ያኔም ይሳካለታል፡፡

ብዙ እጅግ ብዙ የሚያናድዱ ነገሮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ቢነሣ ግማሽ ቀን የማይፈጅበት የነፃነት ትግል በመከፋፈሉ ግን ከ30 ዓመታትም ሊዘል ተቃረበ፡፡ በዚህ የክፍፍል መንገድ ከተጓዝን ደግሞ ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት እነሱም እንደሚሉት ከመቶ ዓመት በላይም አራት ኪሎን የሙጥኝ እንዳሉ ዝንታለማቸውን ሲያሰቃዩን ይኖራሉ፤ አሽቃባጭና አጎብዳጅ ደግሞ ሞልቷል፡፡ ስለዚህ የትግልና የእምቢቴኝነት ጥሪዎች ሲተላለፉ አንድን ብሔር ወይም አንድን ሃይማኖት ብቻ ያማከሉ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ የተሰነቀሩብንን አሉታዊ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ቢያንስ የጋራ ሀገር እስኪኖረን ለዘብ እናድርጋቸውና የጋራ ቁስላችንን በጋራ እናክም፡፡ ዝንጀሮዋ “ቀድሞ የመቀመጫየን” እንዳችው ቀድመን ሀገር ይረን፡፡ ትግሉን በመምራት ደረጃ ያላችሁ ዜጎች ደግሞ ለሥልጣንና እሱን ተከትሎ ሊገኝ ከሚችል ዝናና ሀብት ይልቅ የሕዝብን ስቃይ በማስቀደም ለሕዝብ ጥቅም ስትሉ የግል ፍላጎታችሁን አስክኑት፡፡ ሁሉም ይደርሳል፡፡ ወጣቱን ዘረኛና አክራሪ ወይም ጽንፈኛ የሃይማኖት ተከታይ እያደረግን አናፋጀው፡፡ በፈጣሪ ይሁንባችሁ፡፡…

ሆ! ቢበቃኝስ? መልካቸው የሰው የሚመስል ልበድፍን የወያኔ አጋዚዎች የሚገድሏቸው ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፡፡ ትንቢታዊውን በደም ባሕር የታጀበ “የነፃነት ትግል” አስወግዶ በትንሽ መስዋዕትነት ብቻ “የአንድ ማሣ እህልና የአንድ ላም ወተት ላገር ይበቃል” የተባለለትንና “ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ የሚሰደዱባት ሳትሆን ከስደት የሚመለሱባትና ሌሎች ወደርስዋ የሚሰደዱባት ሀገር ትሆናለች” እየተባለ በአባቶቻችን ይነገር የነበረውን ወርቃማ ዘመን በቅርቡ ያሳየን፤ አሜን፡፡