የህወሃት እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ድርድር

Print Friendly, PDF & Email

(በመሳይ መኮንን)

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሀት ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በኬኒያ ሸምጋይነት ድርድር ጀምረዋል። የሶማሌ ክልል ፕሬዛዳንት አብዲ ኢሌና በሶማሊያ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ተወካይ ጄነራል ገብሬ የህወሀትን መንግስት ወክለው በድርድሩ እየተሳተፉ መሆናቸው ተገልጿል። የሚጠበቅ ነው። በዚህን ወቅት፡ የህዝብ ንቅናቄ ሲጠነክር፡ ፖለቲካዊ ትኩሳት ሲጨምር የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ከሚወስዳቸው የተለመዱ እርምጃዎች አንዱ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን ደጅ መጥናት ነው። ድርድር።

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሀት በማዕከላዊ መንግስቱ የበላይነቱን አስጠብቆ በስልጣን ላይ መቆየት የማይችል ከሆነ ለአደጋ ጊዜው ካስቀመጣቸው ካርዶች መሀል የኦጋዴኑ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይህን ካርድ በሁለት ምክንያቶች ሊጠቀም ይፈልጋል። አንደኛው እስከአሁንም በተደጋጋሚ እንዳደረገው የፖለቲካ ውጥረት ሲገጥመው በድርድር ወሬ ማደንዘዝ፡ ለኢትዮጵያውያን እኔ ከሌለሁ ሀገሪቱ እንደሶቪየት ህበረት ትበታተናለች የሚል መልዕክት መስደድ በዚህም ውጥረቱን ማርገብና በስልጣን የመቆየት ዕድሜን ማራዘም ነው። ሌላው የህዝብ ተቃውሞ ጠንክሮ ከገፋና ቤተመንግስቱን የሚነጠቅ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንዲረዳው የኦጋዴንን የመገንጠል ጥያቄ ተቀብሎ በእንግሊዝ መንግስት ከዘመናት በፊት የተቀመመውን ቦንብ ማፈንዳት ነው።

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ይህን ቢያደርግ የሚደንቅ አይሆንም። የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን የሚመሩ ሰዎች ከስህተታቸው አለመማራቸው ግን አስገራሚ ነው። በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት ድርድር ተደርጎ በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሸፍጥና ሴራ ሲከሽፍ እንደነበረ ራሳቸው በአገኙት አጋጣሚ ይገልጻሉ። በየግዜው ይሄን ግንባር ለማፍረስ በህወሀት በኩል ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦ አመራሮቹን የማስከዳት እርምጃ ተወስዷል። ህወሀት በገንዘብ ሃይል ካስከዳቸው የግንባሩ አመራሮች ጋር ዋንጫ አንስቶ ”ኦብነግ በእጄ ገብቷል” የሚሉ ዜናዎችን ነግሮናል። እነዚያ የከዱት ሰዎች ገንዘባቸውን በኪሳቸው አድርገው የህወሀትን ጊዜያዊ የፕሮፖጋንዳ ጥም ካረኩ በኋላ የት እንደሚገቡ አይታወቅም። አሁንም ኦብነግ አለ። አሁንም ድርድር አለ።

የኦብነግ ሃላፊዎች ከዚህ ቀደም ለድርድር ወደናይሮቢ የላኳቸው ሁለት አመራሮቻቸው በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ደህንነቶች ታፍነው መወሰዳቸውን ሲገልጹ እኚህ ሰዎች ዳግም ከህወሀት መንግስት ጋር ለድርድር አንድ ጠረጴዛ ላይ ይቀመጣሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ባለፈው ዓመትም አንድ የኦብነግ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በሶማሊያ መንግስት አማካኝነት ለትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ተላልፈው መሰጠታቸውና በማዕከላዊ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ላስታወሰ በዚህ አጭር ጊዜ ኦብነህግ የህወሀትን የድርድር ጥያቄ ይቀበላል ብሎ ለመገመት ይቸገራል። የኦብነግ አመራሮች ሁሌም ለትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የለበጣና ትኩሳት ማብረጃ ለታለመ ድርድር ፍቃደኛ የሚሆኑበት ምክንያት ግራ ያጋባል። አሁንም ሄደዋል። ኬኒያ ናቸው። ህወሀት ለመጣበት አደጋ መሻገሪያ የሚሆንለት ድርድር አድርጎ ስለሚያምን ቢያደርገው አይገርምም። ኦብነግ ግን ከእንዲህ ዓይነቱ ድርድር ምን ሊያተርፍ ይሆን? ህወሀት በዚህኛው ዙር ድርድር አብዲ ኢሌን የላከውስ ለምንድን ነው?

በ2006 እኤአ ኦብነግ በቻይና የነዳጅ አውጪ ኩባንያ ላይ እርምጃ ወስዶ ከ70 በላይ ሰራተኞችን ከገደለ በኋላ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር እሾህን በእሾህ የሚል ስልትን ነው የመረጠው። ከዚያው ከሶማሊያ ክልል በስራ ማጣትና በሱስ የተተበተቡ ወጣቶችን ሰብስቦ የስራ እድል ሰጣቸው። የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል በሚል አደራጃቸው። ከእንግሊዝ መንግስት በሚገኝ ከፍተኛ ድጋፍ ለዚህ ልዩ ሃይል ዘመናዊ መሳሪያ አስታጠቀው። ተወርዋሪ፡ ተወንጫፊ፡ ልዩ ጦር አድርጎ ካዋቀረው በኋላ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን እንዲደመስስ አሰማራው። በዚህና በዚያ ወገን የተሰለፉ የአንድ እናት ልጆች በኦጋዴን ምድር ፍልሚያ ገጠሙ። እናም ህወሀት በመጠኑ ተሳካለት። የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ጂጂጋ ድረስ እየዘለቀ የሚሰነዝረው ጥቃት እየቀነሰ መጣ። ይህ ልዩ ሃይል ሌላም ተልዕኮ ነበረው። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን ዙፋን ለማስጠበቅ ከሚሰለፉ ሃይሎች ግንባር ቀደም እንዲሆን ተደርጓል። በቅርቡ በኦሮሞ ወገናችን ላይ እንዲዘምት የተደረገውም የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርን ስልጣን ለመከላከል እንደሆነ ከምንም የተሰወረ አይደለም።

እንግዲህ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ከዚህ ፍጹም አረመኔ፡ ጸረ ሰላም ሃይል ከሆነ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሀት ጋር በየጊዜው ድርድር የሚቀመጥበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። የኦጋዴን ነጻ መንግስት በህወሀት ፍቃድ አገኛለሁ ብሎ የሚጠብቅ ከሆነ ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው። ደግሞም ግንባሩ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆኖ ለዲሞክራሲና ነጻነት እንደሚታገል በቅርቡ ገልጿል። በይፋም ባይሆን በተዘዋዋሪ የመገንጠል አጀንዳውን እንደተወው አስታውቋል። ከመገንጠል አጀንዳ ባለፈ ከህወሀት ጋር ድርድር የሚያስቀምጠው ጉዳይ የስልጣን መጋራት ከሆነ በዚህ በኩል መንገዱ ዝግ እንደሆነ ከግንባሩ አመራሮች የተሰወረ አይመስለኝም። አብዲ ኢሌ የተባለ ነውረኛ፡ ከዕውቀት ነጻ የሆነ ሰው እያለ ስልጣን መጋራት የሚታሰብ አይደለም። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በተዳከመበትና ወንበሩ በተነቃነቀበት በዚህን ጊዜ ስልጣን ለመጋራት ድርድር መቀመጥ ያልተጠና፡ ወቅቱን ያላገናዘበ ደካማ የፖለቲካ እርምጃ ነው። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር እንኳን ለሌላው የሚያጋራው ስልጣን ይቅርና ማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ያለውን የበላይነት አስጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል አቅም የሌለው፡ መቃብሩን በቅርብ ርቀት እየተመለከተ፡ ውድቀቱን እያሸተተ ያለ ሃይል መሆኑን የኦብነግ አመራሮች ካልተረዱት የፖለቲካ ግንዛቤአችውን እንድንጠራጠር የሚያስገድደን ነው።

የሆነስ ሆኖ ድርድሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈይደው ነገር የለም። የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር የሚያገኘው አንዳችም ትርፍ የለም። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የተዘፈቀበትን የፍርሃታና የስጋት ዳመና ለመግፈፍ ከታለመ የሸፍጥ ድርድር የሚጠቀም አካል አይኖርም። ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበት ውሳኔ የትኛውንም የሴራ ድርድር የሚሳካ አያደርገውም። ህዝብ ተነስቷል። የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር አመራሮች ከትግራዩ የህወሀት ቡድን ጋር የሚያድርጉት አሰልቺ የድርድር ድራማ ከሁለት አንድ የሚያሳጣቸው መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። ወራጅ ወንዝ እንዲወስዳቸው መፍቀድ የለባቸው። እየሞተ ካለ ስርዓት ጋር ለድርድር መቀመጥ ምንም ትርፍ የለውም። ይልቅስ የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገ ያለውን የሞት ሽረት ተጋድሎ ማገዝ ከኦብነግ የሚጠበቅ የወቅቱ እርምጃ ነው።

*****

Voice of America, VOA Report

ኦብነግና “የኢትዮጵያ” መንግሥት እየተደራደሩ ናቸው

በኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባርና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ለሦስት ቀናት ይቆያል የተባለ ውይይት ትናንት ዕሁድ ተጀምሯል። በኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና በኦብነግ መካከል ንግግሩ የተጀመረው ተለይቶ ባልተገለፀ የኬንያ ከተማ ነው።

ዕሁድ፣ የካቲት 4/2010 ዓ.ም. መጀመሩ የተነገረው ድርድር የንግግሮቹ የመጀመሪያ ዙር እንደሆነ ተገልጿል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ቃል አቀባይ አብዱልቃድር ሃሰን ሂርሞጌ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ሁለቱም ወገኖች አራት አራት ልዑካንን ወደ ኬንያ ልከዋል።

የኦብነግ ልዑካን ቡድን የተመራው በውጭ ጉዳዮች ኃላፊው አብዲራህማን ማኅዲ እንደሆነ ተገልጿል። በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን መሪው ማን እንደሆነ አይታወቅ እንጂ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሐመድ ኦማር ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር እንደነበሩ የውይይቱ አመቻቾች ያወጡት ፎቶግራፍ ያሳያል።

ለንግግር የቀረቡት በርካታ ጉዳዮች መሆናቸውን ለቪኦኤ የገለፁት ቃል አቀባዩ ሂርሞጌ በርህ፣ በካሣ፣ እራስን በራስ ማስተዳደር፣ በነፃነት፣ በውሣኔ ሕዝብ፣ በምጣኔ ኃብትና ለመቶዎች ዓመታት በዘለቀ ወረራ ባሉት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ አመልክተዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡