በአምሓራ ክልል የቆዳ ፋብሪካዎች በአካባቢው ሕብረተሰብ ላይ እያሳደሩት ያለው ተጽዕኖ!

Print Friendly, PDF & Email

በአምሓራ ክልል በባህርዳር ከተማ ዙሪያ ከሚገኙት ቆዳ ፋብሪካዎች የሚወጣው አደገኝ ኬሚካ የአካባቢው ሕብረተሰብ እና የተፈጥሮ ሃብት እየጎዳ ይገኛል። የአካባቢው ነዋሪዎች ከቆዳ ፋብሪካዎች በሚወጠው አደገኛ ዝቃጭና ኬሚካል የደረሰባቸው ጉዳት እንደሚከተለው ነው የገለጹት።

አንዱ —ሃምሳ ፍየል ነው የሞተብኝ!
ሌላው — አራት በሬ ነበረኝ ፣ ሁሉንም ደጃፌ ላይ ገፈፍኩ ፣ደህናው ገበሬ ባንድ በሬ ልጅ ማሳደግ ተሳነኝ!
አንዱ–የዘራነው አይበቅልም፣በሽታችን ተመርምሮ አይገኝ ፣ አትክልት ተክለን አይፀድቅም !
ሌላው –የአልጋ ቁራኛ ከምንሆን ብለን ቤታችንንን ለመሸጥ አስበን የሚገዛን አጣን!

(አዲሳሌም ቀበሌ ባሕር ዳድር ዙሪያ እና ደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ ፯ ነዋሪዎች)
——

በአምሓራ ክልል ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች ይገኛሉ(በባሕርዳር ሁለት፣ በመርሳ፣ በሐይቅ፣ በኮምቦልቻና በደብረ ብርሃን ይገኛሉ)::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከቆዳ ፋብሪካዎች ከ፴፭ ዓይነት በላይ ለሰው ልጅና ለተፈጥሮ አደገኛ የሆኑ በካይ ኬሚካሎች ወደ አካባቢ ይለቀቃሉ::

እነዚህ ፋብሪካዎች ቆዳና ሌጦ ለተለያዩ ምርቶች (ለልብስ ጫማ ቀበቶ የመሳሰሉት) ለማምረት ቆዳና ሌጦውን የሚያለሰልሱት ክሮምየም(Chromium) በተባለ የማልፊያ ንጥረ ነገር ነው::
Cr​+3 እና Cr​+6 የሚባሉ የክሮምየም ዓይነቶችን አሉ (Cr​+6 ቆይቶ ከCr​+3 ይገኛል):: ይሄ Cr​+6 ደግሞ እጅግ ቶክሲክ(ገዳይ) ከሚባሉ ቁሶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው::
ይህ ኬሚካል ካንሠር ፣የዘረመል ለውጥ፣ የአእምሮ ዝግመት፣ የአካል መዛባት፣ አስም፣ የቆዳ መቆጣት፣ የአፍንጫ መድማት፣ ኩላሊት በሽታ እና እስከሞት ሊያደርስ የሚችል በህክምና የማይድን በሽታ ሊያመጣ የሚችል እጅግ አደገኛ ቁስ ነው::

((በዚህም ምክንያት አብዛኛው የዓለማችን ሃገራት ሕግ አውጥተው ፋብሪካዎቹ የተለያየ ደረጃ የማከም ሂደት ማድረግ እንዳለባቸውና ስመሰረቱም ህዝብና አካባቢን የማይበክሉ መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋሉ::))

በዚህ ለማለስለሻና ለማልፊያ በሚጠቀሙበት ክሚካልና ፋብሪካው በሚያወጣው ዝቃጭ ተረፈ ምርትና በካይ ፈሳሽ ምክንያት የአካባቢው (ባሕር ዳርና ደብረ ብርሃን)

ሰዎች ኑሮው ሰቀቀን ሆኖባቸዋል::

የአዲሳሌም ቀበል ነዋሪዎች “ቀበሌው አለ ለማለት አይቻልም፣ ከፍተኛ የሆነ እልቂት አለ! ከብቶቻችን እየመነመኑ አለቁ፣ሰው ግማሹ እግሩ፣ ግማሹ ወገቡ፣ ግማሹ ራሱ ታሟል፣ ጤንነት እርቆናል፣
ባካባቢው ያለው የቅሬቱ ሽታ ነፈሰ ጡር ያስወርዳል! ቤተ ክርስቲያን ማስቀደስ እጅግ ፈታኝ ነው፣ አየሩ ተበክሏል የቤተ ክርስቲያን ማዕዛ ፈልጎ የመጣ ምዕመን የቆዳ ፋብሪካ ዝቃጭ ቆሻሻ ስቦ ታሞ ይሄዳል” ይላሉ::

የደብረ ብርሃን ቀበሌ ፯ ነዋሪዎች በበኩላቸው “ከፍተኛ የበሽታ ወረርሽኝ ያለ ይመስል ልጆቻችን እየታመሙብን ነው”

ፋብሪካው የሚያስወግደው የፍሳሽ ኬሚካል እንዲህ ያስቸገራቸው አርሶ አደሮች ለክልሉ ለሚመለከተው አካል ብሶታቸውን አቅርበው ባለ ሥልጣናቱ ግን ጉዳዩን ቢያውቁትም ስልጣናቸውን መጠቀም እንደተሳናቸው በልሳናቸው በአማራ መገናኛ ብዙኃን መናገራቸው ይታወሳል!

ለሁለቱ ድርጅቶች ማለትም

ለዴቭ ኢምፔክስ ኢንተርፕራይዝ ባሕር ዳር ቆዳ ፋብሪካ በቀን ፲፯/፳፻፭ አም በቁጥር አካ/ዘ/፬፱፫/አተ-፮

ለሀበሻ ቆዳ ፋብሪካ በቀን ፲፯/፳፻፭ ዓም በቁጥር አካ/ዘ/፬፱፬/አተ-፮ በተጻፉ ደብዳቤዎች የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ እገዳ ቢጥልባቸውም ከፌደራል በተላከ ደብዳቤ ተሽሮ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደርገዋል።

የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ አንቀጽ ፫ ንዑስ አንቀጽ ፭ ግን “ጉዳትና ሥጋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጅቶችን መዝጋት ወይም ቦታ ማዛወር ክልሎች ስልጣን አላቸው” ይላል:: ይሄን ሥልጣኑን ኦሕዴድ በደንብ ሲጠቀምበት የኛው ብአዴን ፈራ!

ስለዚህ የሕብረ ተሰቡ እሮሮ ተሰምቶ ፋብሪካዎች በተለይም ሶስቱ ማለትም:-

፩. ሀበሻ ቆዳ ፋብሪካ
2. ዴቭ ኤምፔክስ ኢንተርፕራይዝ ባሕር ዳር ቆዳ ፋብሪካ
፫. ጥቁር ዓባይ ቆዳ ፋብሪካ በደብረ ብርሃን

ከላይ ሁለቱ አስቀድሞ የአምሓራ ክልል ያገዳቸውና ሕገወጥ በመሆናቸው መቆም ወይም ደረጃቸውን አሳድገው የምያስወጡትን ጠጣርና ፈሳሽ በካይ ንጥረ ነገሮችን የሚያጠሉበት የሚያክሙበት የሚያስወግዱበት ዘዴ ሊፈጥሩ ወይም መፍትሄ ልበጅላቸው ይገባል::

ዳቢ ታይምስ

በባህርዳር ከተማ አካባቢ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች ህዝብ እና የተፈጥሮ ሃብት እያደረሱ ያለውን ዘገባ ከዚህ በታች ይመልከቱ