የዐማራው ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደ አንድነት በመምጣት መታግለ አማራጭ የለለው አጣዳፊ ጉዳይ ነው!

Print Friendly, PDF & Email

የዐማራው ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደ አንድነት በመምጣት መታግለ አማራጭ የለለው አጣዳፊ ጉዳይ ነው!

• የዐማራው ድርጅቶች አንድነት አማራጭ የለውም

• በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፍፁም ግራ የተጋባ ሕዝብ ቢኖር አማራው ነው። ራሱን እንደ አማራ ተቀብሎ የማያውቀው አማራ አዲስ ማንነቱ አልዋጥልህ ብሎ እየተናነቀው ይገኛል። በዐማራ ማንነቱ ላይ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ነገር ቤቱን የቀለሰበት በመሆኑ ዛሬ ወደ ኋላ አንድ እርምጃ ሄዶ ነገ ሁለት እርምጃ መራመድ የሚያስችለውን ስልት ከመንደፍ ፈንታ አገሪቱ በአመፅ ማዕበል በምትናወጥበት ወቅት ከመሃል ቆሞ ይወዛወዛል።

• ይህ የፖለቲካ ድህነት ነው። በመሠረቱ ፖለቲካ ውስብስብ የኅብረተሰብ ችግሮችን የምንፈታበት መሣሪያ ነው። የሕዝብ ዓላማዎች መድብል የሆነውን ዲሞክራሲያዊ ፕሮግራም የምንነድፍበት ነው። የትግሉን መነሻና መድረሻ የሆነውን ታክቲክና ስትራቴጂ የምንቀይስበት ነው።ሕዝቡን ለትግል የሚያነሳሱ መፈክሮችን የምንቀርጽበት ነው። ምርቱን ከግርዱ፣ ጠንካራውን ከደካማው የምንለይበት ነው። በጥቅሉ ፖለቲካ ራዕያችን፣ ምኞታችን፣ ፍላጎታችን፣ ኅልማችን ተስፋችን ሰንቀን የምንጓዝበት ረጅም የትግል ጉዞ ነው።

• ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ዐማራው እውነታው ተሰውሮበት እውር ድንብሱን ሲዳክር ማየት የተለመደ ሆኗል። እኔ ዐማራ ነኝ፣ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ በጉንጭ አልፋ ክርክር ጊዜውን ሲያባክን ይታያል።

• ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ወላይታ፣ ሶማሌው፣ ከኢትዮጵያዊነቴ ይልቅ ማንነቴ ይቀድማል ብሎ በብሔር ተደራጅቶ ለራሱ በሚታገልበት ሰዓት፣ዐማራው ከማንነቱና ከኅልውናው በፊት ኢትዮጵያ ማለት ማንን ይዞ ጉዞ አይሆንምን? እስኪ ማን ይሙት ኦሮሞን ያላቀፈ፣ ከትግሬው ያልወገነ፣ ከሶማሌው ጋር ያላበረ፣ በአፋር፣ ወላይታ፣ ከምባታ ወገኖቹ ያልታጀበ ኢትዮጵያዊነት ምን አይነት ኢትዮጵያዊነት ይሉታል? የሚበላውን አለ ነጋዴ! ይባላል፤ ማን ይቅደም፣ ኅልውና፣ ማንነት ወይስ አገር? የቱን ማስቀደሙ ትክክል ነው? ብሎ ጠይቆ፣በሚያስኬደው፣ በሚያዋጣው፣ በሚያስማማው ጉዳይ ላይ መክሮ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

• አንዳንዶች የተውሰነ ጉራጌ፣ በርካታ ሰርጎ ገብ ትግሬ፣ በዋናነት ግራ የተጋባውን ዐማራ እንደከብት እየነዱ ኢትዮጵያዊነቱን እየሞከሩት ስለሆነ ብዙ መጋፋት ባላስፈለገ ነበር። በዐማራ ታጅቦ የሚመጣ አስመሳይ ኢትዮጵያዊነት ብዙም ወንዝ አያሻግርም።

• የብሔራዊ አጀንዳ ዋናው ችግሩ ከላይ በጠቆምነው ዓይነተኛ ምክንያት ብሔር/ብሔረሰቦችን በአንድ ጃንጥላ ሥር ማሰባሰብ ያለመቻሉ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ነው።

• አገር አቀፋዊ ድርጅት ሊፈጠር የሚችለው፣ እነኝህ እንደአሸን የፈሉ የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች ወደ ሕብረትና ውህደት በማምጣት ነው። ከዚያ ውጭ ማንም የግል ሥልጣን ያሰከረው ቡድን ኢትዮጵያዊ ድርጅት ስለፈጠረ ተንጋግቶ የሚጋባ የአብርሃም በግ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።

• ኢትዮጵያዊነትን በአሁኑ ጊዜ፣ እንዳሻን ገበያ ላይ አውጥተን ልናቀናው የምንችል ሸቀጥ አይደለም። ማንኛውም ሸቀጥ ገዥ ይፈልጋል። ገዥ ከሌለ ወደገበያ ጉዞ መጀመር አጉል መንገድ መመታት ነው።

• ዐማራ ኢትዮጵያ ወይም ሞት ብሎ ተነስቷል። ሌላው ግን ቱሪስት ብላ፤ ሞኝህን ፈልግ፤ የለመደች ጦጣ እያለ እያሾፈበት ነው። ነገሩ ብልጥ ለብልጥ ሆኗል።

• በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያዊነት ችግኝ በመላ አገሪቱ እፈላ ነው። ዉኃ የሚያጠጣውና አረሙን ለመንቀል የኢትዮጵያን ልጆች ደቦ ይፈልጋል። በለማ መገርሳ የሚመራው ኦሕዴድ አረሙን በመንቀል ደረጃ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ ነው። ለዚያም ነው ዛፍ ሆኖ ፍሬ ማሳየት የጀመረው።

• እንደገበታ ውሃ የሚዋልለው ዐማራ ከጊዜ ወደጊዜ እየተጠናከረ ከመጣ ብሔርተኝነት ፊት እንዴት መቆም ይችላል?« ሳያሽ የበላ ዝንጀሮ ሲስል ያድራል» እንደሚባለው፣ እርስ በእርሳችን ጉንጭ አልፋ በሆነ ክርክር ውስጥ መዘፈቃችን ለውድቀታችን አይነተኛ ምክንያት እየሆነ ነው።

• ኢትዮጵያዊነትን ለማንገሥ ብቸኛ አማራጩ ማንነትን ማጠናከር ነው። ይህ ግን፣ ብሔርተኝነትን ማጠናከር አይደለም ። ምክንያቱም ብሔርተኝነት በሚከፋፍል ፖለቲካ ስለሚታጀብ ነው። የችግራችን ምንጭ ነው ብለን ሌላውን ሳንኮንና ከሌላው ሳንጣላ በራሳችን መብትና ጥቅም ዙሪያ ስንሰባሰብ ኢትዮጵያዊነት ያብባል።

• ይህ ዓይነቱ ፖለቲካ በጥላቻ ከተበከለ የጎሳ ፖለቲካ ለየት ይላል። የሌላውን ማለትም በጥላቻ ፖለቲካ የተማረረውን ማንኛውንም የሕብረተሰብ ክፍል ሊያሰባስብም ይችላል። የበሰለ ፖለቲካ ጥበብ የተሞላበት ፖለቲካ ፣ አቀራራቢ ፖለቲካ፣ አስታራቂ ፖለቲካ የምንለው ይህን ዓይነቱን ፖለቲካ ነው።

• የኦሮሞ እንቅስቃሴ በአሁኑ ሰዓት የወሰደው ፀረወያኔ አቋም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ የሰቀለ ነው። ከሁሉም በላይ እንቅስቃሴው መላውን የኦሮሞ ሕዝብ በውጭም ሆነ በውስጥ በኦሕዴድ ዙሪያ ተሰልፎ እንዲታገል ማድረጉ ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ምሳሌነቱ ከፍተኛ ነው። ሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ከኦሮሞ ድርጅቶች ተምረው ራሳቸውን ማጠናከር ካልቻሉ፣የራቸው ዕድል በሌሎች እንደሚወሰን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

• ዐማራው አሁን በሚያራምደው ኢትዮጵያዊ አጀንዳ፣ አንድ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ ወይም ሶማሌ መመልመል ቢችል ምላሴን! ያሰኛል። የምንገኝበት የዕድገት ደረጃ በጣም ዝቅተኛና ኋላ ቀር በመሆኑ፣ የራሳችን ዕድል መወሰን እስካልቻልን ድረስ፣ ሌሎች የሚወስኑልን የእኛን ማንነት ያረጋግጣል ተብሎ አይታሰብም።

• ከዚህ አንፃር ወያኔ እስከአሁን ያሳየን ባህሪ፣ የግሉ ብቻ አይደለም። ማንኛችንም የምንጋራው ባህሪ እንደሆነ መታወቅ አለበት። ይህም ባሕሪ የራስን የበላይነት ከመመኘትና በአጠቃላይም ከኋላ ቀርነት ጋር የተያያዘ ነው።

• የኦሮሞ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ፖለቲካ ማራመድ መቻሉ ብዙዎችን ያስደሰተና ያስፈነደቀበት ምክንያት ቢኖር፣ የሚያራምደው ፖለቲካ አዲስ ሆኖ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊነት እንደመፈክር ካልተጠበቀ አካባቢ በመፈንዳቱ ነው። ይህ ኢትዮጵያዊነት ከዚህ ቀደም ባማራው አካባቢ ሳይሞክር አልቀረም። ሆኖም ወያኔ ያን የሚፃረር ፕሮፓጋንዳ በብሔር ብሔረሰቦች አካባቢ በመዝራቱ ያ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

• አሁንም ዐማራው ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ የሚያስችለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ዐማራው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለቱ የፖለቲካ ድህነቱን ከማጋለጥ ውጭ ሊሰጥ የሚችለው ትርጉም የለም። እናም የእሳት ልጅ አመድ እንዲሉ ሁሉ አባቶቻችን፣ ሊያወርሱን የፈለጉት ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ፣ ሥርዐትና አይደፈሬ ማንነት ከጊዜ ብዛት ከራሳችን ላይ ተኖ እንደጠፋ የተገነዘብንበት ሁኔታ ተከስቷል። ምንም ዓይነት ምክር፣ ምንም አይነት ወቀሳ፣ ምንም አይነት ትምህርት ከቶ ከማይቀረው ውድቀት ሊያድነን አይችልም። ጥፋ ያለው ትውልድ ምንም አይነት አዋጅ ቢነገር፣ ነጋሪት ቢጎሰም ከተጠናወተው አባዜ ሊላቀቅ አይችልም።

• ዐማራ ከልቡ የኢትዮጵያ ፍቅር እንዳለው ይታወቃል። የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ለማራመድ ግን ትልቅ ችግር ተፈጥሮበታል። የዐማራ ኢትዮጵያዊነት ከማንም በላይ የሚፈራ ጉዳይ ሆኗል። ለብሔር ብሔረሰቦች ያማራ ኢትዮጵያቂነት አባጨጓሬ ሆኗል።

• በመሆኑም ፖለቲካችን ላይ ጥበብ፣ ዘዴ፣ ሥልት እንጨምርበት። የጨበራ ተስካር አናድርገው። በዐማራነትና በኢትዮጵያዊነት እርስ በርሳችን ለምን እንጣላ? የሚያየን ሁሉ ጉድ ይለናል። ዐማራ ብለው የተደራጁ ወገኖቻችን እኮ ኢትዮጵያን ጠልተው አይደለም። ለሃያ ሰባት ዓመት ሲሸረሸር የመኖረ ኢትዮጵያዊነትን ጠጋግኖ ማቆም ቢሳናቸው ነው። ወገብ የለሽ ኢትዮጵያዊነት የትም እንደማያደርሳቸው አይተውት ነው። ጉዞው በጣም ወጣ ገባና አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ጭምር ነው።

• በሌላ በኩል፣ በዐማራነት ማሰባሰብም ቢሆን ያን ያህል ቀላል አይደለም። አብሮ ማደግ ያናንቃል ሆኖ ነው መሰል፣ የጎሪጥ እያያቸው የሚሄደው ብዙ ነው። ታዲያ! በመካከላችን ያሉትን ዐማራዎች ሞራል መስጠት ቢያቅተን አገር ቤት ውስጥ ሕዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው የሚፋለሙትን ወንድሞቻችን ለምን ፊታችን እናዙርባቸው?

• ዐማራ ማለት ቂመኛ ማለት ካልሆነ በስተቀር፣ እነኚህ ወገኖቻችን ትላንት ከወያኔ ጎን ተሰልፈው ነበር ብለን ድርጅቱን ከግለሰቡ፣ ግለሰቡን ከግለሰቡ ሳንለይ ፣ሁሉንም በጅምላ ማውገዙ ለምን ይበጀን ይሆን? ይህ አካሄዳችን ሕዝባችን ለገጠሙት ዙሪያገብ ችግሮች መፍትሔ አይሆንም። መፍትሔው በዚህ ጉዳይ ላይ በግልጽ ተነጋግሮ መግባባት ሊፈጠር የሚችልበትን መንገድ መሻት ነው። ከዚህ ውጭ ራሳችን ከራሳችን ጋር በመነጋገር ለሌሎች ጆሮ ነስተን ወደ አንድነት ከቶ መምጣት አንችልም።

• ካሰከረን የጥላቻና ከማን አንሸ ፖለቲካ ወጥተን በትክክል ማሰብ እንጀምር። እስኪ የምንናገረውን ነገር መለስ አርገን ፣ራሳችን እናዳምጠው፣ እንገምግመው። ለመሆኑ ትርጉም፣ ስሜት የሚሰጥ ነው። በናንተ ላይ ሰዎች የሚሰነዝሩትን ሃሳብ እስኪ በጽሞና አዳምጡ። በቀናነት የቀረበ ሀሳብ ይሆናል ብላችሁ ተቀበሉት። ያኔ ለውጡን ታዩታላችሁ። አስተሳሰባችሁ ይቀየራል፤ በሌሎች ላይ ያላችሁ የተሳሳተ አመለካከት ይለወጣል። በግል ከማሰብ በጋራ መምከር እንጀምራለን። ከኛ የተሻሉ መሪዎችንም እንዲወጡ ዕድል እንሰጣለን።

• በአሁኑ ሰዓት ብአዴን መላውን ያማራ ሕዝብ በጎኑ አሰልፎ እየታገለ ነው። የትላንቱን ብአዴን እንርሳው። ወያኔን ከኛ በላይ እየታገለው ነው። ከተጠናወተን ሁሉንም በአንድ ዓይነት ከመፈርጀ አባዜ ወጥተን በፈርጅ በፈርጁ በመለየት ከወገኖቻችን ጎን እንሰለፍ። የለማ ድፍረት፣ የገዱ ስጋት የሚያመለክተን ጉዳይ ቢኖር፣ ለማ የመላውን ኦሮሞ (በውጭ/በውስጥ) ድጋፍ በማግኘቱ አካኪ ዘርዝፍ ሲል፣ ገዱ እንደለማ ደረቱን ነፍቶ እንዲናገር፣ የለም አሻፈረኝ እንዲል ፣የዐማራው ወገኖቹ (የውጭ ሆነ የውስጥ) ጠንካራ ድጋፍ አለማግኘቱ ነው። ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ እኛም የበኩላችን አስተዋጽዖ እናድርግ በሚል በስደት ለሚገኘው ሕዝብ ጥሪ ማስተላለፍ እንወዳለን።

• ከዞብል የውይይት መድረክ!

• የዐማራ አንድነት ለኢትዮጵያ !