ከእስር በሚፈቱት ወገኖቻችን ደስ ይለናል፣ የነፃነት ትግሉም ይቀጥላል!

Print Friendly, PDF & Email

(ሄኖክ አበበ)

Andualem Arage and Eskinder Nega

ግርሃም አሊሰን የተባለው ጸሃፊ Destined for War በሚለው መጽሃፉ ላይ ቱሲዳደስ የሚባል የታሪክ ጸሃፊ የጻፈውን ሃሳብ እንደማጠንጠኛ አድርጎ ይጠቀማል። ሃሳቡ እንዲህ ይላል “It was the rise of Athens and the fear that this instilled in Sparta that made war inevitable.” የአቴናውያን መነሳትና ይህ በስፓርታ ውስጥ የዘራው ፍርሃት ጦርነት የማይቀር ጉዳይ አደረገው” ብሎ ጽፏል። እኛም እንላለን “It is the rise of Oromos and Amharas and the fear that this instilled in TPLF that made change inevitable.” የአማራና የኦሮሞ ህዝብ በአንድ ድምጽ መዘመር፥ ለአመታት የዘለቀው የኦሮሞ ወጣቶች ትግል፥ የአማራ ወጣቶች ተጋድሎ ህወሃትን የሚያንበረክክ ለውጥ አይቀሬ መሆኑን አመላካች ነው።

ዛሬ ኢህአዴግ እንዳስታወቀው ጥፋተኛ ተብለው የታሰሩና የተፈረደባቸው እንዲሁም በአቃቢ ህግ እጅ ስር ጉዳያቸው ያሉ የፓለቲካ እስረኞች እንደሚለቀቁ ተናግሯል። የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቃል ብዙ ነገሮችን ሰፋ አድርጎ ያዘለ መሆን መቻል አለበት።
እውነትም ሃገሪቱ የተሻለች እንድትሆን ከታሰበ

1. ክስ የተመሰረተባቸው፥ ክስ ያልተመሰረተባቸው፥ ጥፋተኛ የተባሉ፥ ጥፋተኛ ተብለው የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው፥ ለዘመናት ያሉበት ሁኔታና ቦታ ሳይታወቅ በየማጎሪያ ጣቢያዎች ያሉ የፓለቲካ እስረኞች በሙሉ ሊፈቱ ይገባል።

2. የፓለቲካ እስረኛ የሚባሉት ህወሃትን በመቃወማቸው ብቻ ሽብርተኛ ተብለው፥ የህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በማሰብና በማሴር ተብለው፥ ሃገር ለማፍረስ የመንግስትን ስም በማጥፋት፥ ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው በማድረግ ወዘተ ተብለው ያልሆነ ስም ተለጥፎባቸው የታሰሩ እስረኞችን ማጠቃለል መቻል አለበት።

3. መንግስት official በሆነ መንገድ እስካሁን ለደረሰባቸው በደል ይቅርታ ሊጠይቃቸው ይገባል።

4. በእስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው በደል ካሳ ሊከፈሉ ይገባል። ከወንጀል ድርጊቲ የተገኘ ንብረት በማለት ንብረታቸው የተወረሰባቸው ግለሰቦች ሶስተኛ ወገን በማይጎዳ መልኩ ንብረታቸው ሊመለስላቸው ይገባል።

5. ከስር ከተፈቱ በኋላም ቀድሞ ወደነበሩበት የመንግስትም ይሁን የግል ስራቸው እንዲመለሱ በመንግስት በኩል ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል።

አንዳንድ ሰዎች ወያኔ ይሄን የሚያደርገው ለማዘናጋት ነው ሲሉ ይደመጣል። ሌሎች ደግሞ ወያኔ ይህን በማድረጉ ልንደሰት አይገባም፥ የትግሉ ግብ ይሄ አይደለምና ይላሉ። የአማራም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ግብ የፓለቲካ እስረኞችን ማስፈታት ብቻ አይደለም። ነገር ግን ይሄ አንድ አላማው ነው። ይህ አላማው ተፈጸመ ማለት ማንም እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ማለትም አይደለም። ለታሳሪዎች እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸውም ማሰብ መቻል አለብን። ይህ ትልቅ እፎይታ ነው። ምንም ያህል ወደታሰበው አላማ ያድርስም አያድርስም ለታሳሪዎች እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው ጨለማቸውን የሚያበራ ክስተት ነውና በመልካም ጎኑ ሊታይ የሚገባ ክስተት ነው።

ከዚህ እንካስላንትያና መመጻደቅ ወጥቶ መንግስት ቃሉን በአጭር ግዜ ውስጥ እንዲፈጽምና ሁሉንም የፓለቲካ እስረኛ ያለምንም ልዩነት እንዲፈታ መጠየቅ መልካም ነገር ነው።

ሌላው ይህ ከእስር የመፈታት ጉዳይ ከላይ እንደተጠቀሰው ሁሉንም የፓለቲካ እስረኞች ያማከለ መሆን መቻል አለበት። የፓለቲካ እስረኖች ማለት የመንግስትን ድርጊት፥ ፓሊሲና ህግ እንዲሁም አፈጻጸምና አስተዳደር በመቃወማቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦች ማለት ነው። ስለዚህ፥

1. በሃገር አቀፍ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ፥ በሚዲያዎች እየጻፉ ሳለ አማራ በመሆናቸው ብቻ የታሰሩ አያሌ የፓለቲካ እስረኞች ሊፈቱ ይገባል (ምሳሌ እስክንድር ነጋ፥ አንዷለም አራጌና ሌሎችም )።

2. የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጠያቂ ኮሚቴዎች እስራቸው የፓለቲካ ነውና ሊፈቱ ይገባል (ምሳሌ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ፥ አታላይ ዛፌ እና ሌሎችም)።

3. በ2002 ዓ.ም ሊታሰብ ተደርጎ ነበር ተብሎ በታቀደው መንፈቅለ መንግስት ስም የታሰሩ የአማራ ነጋዴዎች፥ የጦር መኮንንኖች፥ ሙህራን፥ ተማሪዎችና አርሶ አደሮች የታሰሩት በፓለቲካ አመለካከታቸውና በአማራዊ ማንነታቸው የተነሳ ነውና ሊፈቱ ይገባል (ለምሳሌ ኮሌኔል አሳምነው ጽጌ፥ እማዋይሽ አለሙ እና ሌሎችም)።

4. በአማራ ተጋድሎ ወቅት ለእስር የተዳረጉ አያሌ ወጣቶች ምንም ጥፋት አጥፍተው ሳይሆን በፓለቲካ አመለካከታቸው ና በአማራዊ ማነነታቸው ብቻ ነውና የፓለቲካ እስረኞች ስለሆኑ ሊፈቱ ይገባል (ለምሳሌ ንግስት ይርጋና ሌሎችም)።