ኦሮምኛን ማስፋፋት ሌላ፣ አማርኛን ማጥፋት ሌላ ነውና ይህ የፀረ አማርኛ ዘመቻ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል!

Print Friendly, PDF & Email

በኦሮምያ ክልል እየተካሄደ ያለው የአማርኛ ቋንቋን የማጠፋት ዘመቻ

ኦሮምኛን ማስፋፋት ሌላ፣ አማርኛን ማጥፋት ሌላ ነውና ይህ የፀረ አማርኛ ዘመቻ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል!

(ልሣነ ዐማራ- Amhara Press)

ሰሞኑን ኦሮምያ ክልል ውስጥ አማርኛ ቋንቋ ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ መቆም ያለበት ጉዳይ ነው። ይህን ስል ኦሮማራ የሚባለውን ነገር (ምናልባት በእውን ያለ ነገር ከሆነ) ያለመፈለግ ወይም የማፍረስ ጉዳይ መስሎ የሚታያቸው ይኖራሉ። ግን አይደለም።

እኔ የአማራና የኦሮሞን ህዝብ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነትን አጥብቀው ከሚፈልጉት አንዱ ነኝ። በኦሮምያ ክልል ለበርካታ ግዚያት ተደጋግሞ ሲታይ የነበረው የጸረ አማርኛ ቋንቋ ዘመቻ ባለፉት ሳምንታት በአዲሱ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኙ ኦህዴድ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ጉዳዩ ኦሮምኛን ማስፋፋት ቢሆን ባልከፋ: ነገር ግን አማርኛን ከክልሉ የማጥፋት ዘመቻ ነው። ይሄም በሚከተሉት ምክንያቶች ስህተት ነው።

1. ማንኛውም ግለሰብ የመናገር ነፃነት አለው። የመናገር ነፃነት ደግሞ የፈለጉትን መልዕክት በፈለጉት ቋንቋ ማስተላለፍን ይጨምራል። የንግድ ታፔላዎችንና ማስታወቂያዎችን በፈለጉት ቋንቋ የመፃፍ መብትንም ያጠቃልላል። ስለዚህ ይህ የኦሮምያ ክልል መንግስት ርምጃ የፌደራሉንም ሆነ የክልሉ መንግስቶች ህገመንግስቶች እውቅና የሰጡትን የግለሰቦችን የመናገር ነፃነት ይጣረሳል!

2. ይህ የፀረ አማርኛ ዘመቻ በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ላይም እየተተገበረ ነው። በዚህም የተነሳ ዩንቨርሲቲዎች: ባንኮች: የፌደራል መስሪያ ቤት ቅርንጫፎች ወዘተ ከስያሜያቸው ወይም ከማንኛውም አይነት ማስታወቂያና ማሳሰቢያቸው ላይ አማርኛ ቋንቋን እንዲያጠፉና በኦሮምኛ እንዲተኩ እየተገደዱ ነው። በፌደራል መንግስት ህገመንግስት መሰረት የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ አማርኛ ሁኖ እያለ እኒህን የፌደራል ተቋማት አማርኛ ቋንቋ መጠቀም አትችሉም ማለት ህገመንግስቱን መጣስ ነው።

3. ይህ ድርጊት በኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከአስር ሚሊየን በላይ አማራዎችን የቋንቋ መብት መንፈግ ነው። በህገመንግስቱ መሰረት ማንም ግለሰብ ወይም ቡድን በቋንቋው የመግባባትና ቋንቋውን የማሳደግ መብት ተደንግጎለታል። ነገር ግን አዲሱ ኦህዴድ የድሮው ኦህዴድ ተቀፅላ የሆነውን የፀረ አማርኛ ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ የህዝቦችን ና የግለሰቦችን መብት እየጣሰ ነው።

4. ይህ የፀረ አማርኛ ቋንቋ ዘመቻ በአማራና በኦሮሞ ወንድማማች ህዝቦች ትብብር ላይ ቀዝቃዛ ውሃን የሚቸልስ አካሄድ ነው። ዘመቻው ወያኔ የሚፈልገውን የሁለቱ ህዝቦችን ፍትጊያና ጥላቻ የሚያሰፋ አካሄድ ነው።

ኦሮምኛን ማስፋፋት ሌላ: አማርኛን ማጥፋት ሌላ ነውና ይህ የፀረ አማርኛ ዘመቻ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል!

በኦሮምያ ክልል እየተካሄደ ያለው የአማርኛ ቋንቋን የማጠፋት ዘመቻ