አቡነ ማቲያስ በአንድ እራስ ብዙ ምላስ

Print Friendly, PDF & Email

በትግራይ የበላይነት የተወናበደ አመለካከት ካበዱ ከ30 ዓመታት በላይ የሆናቸው የወያኔው ሹመኛ አቡነ ማቲያስ ለወግ ለማዕረግ ያበቃቻቸውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን ከድተው ከወያኔ ጋር በተቀላቀሉበት ጊዜ ይናገሩ የነበረውንና አሁን ደግሞ በወያኔ ተቀብተው የፓትርያርክነት መንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ የሚዘላብዱትን ማገናዘብ ምን ዓይነት የረከሱና የተዋረዱ ሰው ከ50 ሚሊዮን በላይ አማኞች ያሏት ቤተክርስቲያን አናት ላይ መፈናጠጣቸውን ያመለክታል። አቡነ ማቲያስ ከ30 ዓመታት በፊት የወያኔን የኦርቶዶክስ ተወህዶ ቤተክርስቲያንን የመቆጣጠርና የማሽመድመድ ዓላማ ለማሳካት ደርግን አውግዣለሁ በማለት አሜሪካ ውስጥ በስውር የወያኔን ተልዕኮ ተቀብለው እኩይ ተግባራቸውን ጀመሩ። ለዚህም ሽፋን እንዲሆንላቸው ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ያቋቋሙትን ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ተጠግተው ምዕመናንን በማጨናበር ለወያኔ የሚሰጡትን ተልዕኮ በድብቅ ተያያዙት።

የደርግ አገዛዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወህዶ ቤተክርስቲያንን “የአድኅሪያን ምሽግ” በማለት ንብረቶቿን ዘርፎ ምዕመናኖቿ ላይ ከፍተኛ ችግር ይፈጥር እንደነበር አይዘነጋም።ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ተክለ ኃይማኖት ደርግ በቤተክርስቲያኒቷ ላይ ያደርስ የነበረውን በደልና ጫና በጸሎትና በብልሃት ተቋቁመው እንዲሁም የራሳቸው እውነተኛ የእምነት ፅናትና ቆራጥነት እንዲሁም ለአላፊውና ጠፊው ዓለም ያላቸው ንቀትና ንጽህናቸው ታክሎበት ቤተክርስቲያኒቷን ከከፋ በደልና ውድመት ታድገዋታል። በእሳቸው ዘመን ቤተክርስቲያኒቷ ንብረቷ ተዘርፎ ገቢዋ በተመናመነበት ዘመን በባዶ እግራቸው እየሄዱ ወገባቸውን በጠፍር ታጥቀው በትጋት በመስራት ለቤተክርስቲያኒቷ የሰሩት ሥራና ትሩፋታቸው በታሪክ ሲወሳላቸው ይኖራል።

በመጨረሻም የደርግ መንግሥት ጥጋብ ጣሪያ ላይ ወጥቶ ቤተክርስቲያኖችን ወደ ሙዚየምነት እቀይራለሁ በማለት እንዲሁም ቅዳሴ በሚደረግበት ጊዜ የድምጽ ማጉያ መጠቀም መከልከል በመጀመሩ አቡነ ተክለኃይመኖት ይህንን ከማየት ብለው በሱባኤና በጾም እራሳቸውን በማድከም ክብደታቸው እጅግ ቀንሶ ቆዳና አጥንታቸው ብቻ ቀርቶ በሰማዕትነት አልፈዋል። ንቀውት ከነበረው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ከሊቅ እስቀ ደቂቅ ወንደ ሴት ሳይባል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ጭምር በእንባ ተራጭተው እናቶች ደረታቸውን እየደቁ የሚወዷቸውንና የሚያከብራቸውን እውነተኛ የመንጋው ጠባቂ ወደ ዘላላማዊ ማረፊያቸው ሸኝተዋቸዋል።

ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ተለኃይማኖት በደርግ መንግስት በዓይነ ቁራኛ ይታዩና ከፍተኛ ጥላቻ ይንጸባረቅባቸው እንደነበር የሚታወቅ ቢሆንም፣ አቡነ ማቲያስ አሜሪካ ውስጥ ያልጠረጠሩና የመረጃ እጥረት የነበረባቸው ኢትዮጵያዊያንን በሃሰት በማሳመን የደርግ ደጋፊ እያሉ ስማቸውን ሲያጠፉና ሲያብጠለጥሏቸው እንደነበር በጊዜው የነበሩ አዛውቶች ይናገራሉ። አቡነ ማቲያስ የጵጵስና ማዕረግ የሰጧቸውንና ለአየሩሳሌም ገዳማት አስተዳዳሪነት የሾሟቸውን አቡነ ተክለኃይማኖትን ከአንድ ጳጳስ በማይጠበቅ ሁኔታ በሃሰት ስማቸውን ያጎድፉ ነበር።

ወያኔ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና የአድዋ ጦርነት ሽንፈት ከአእምሮቸው ሊጠፋ ባልቻለ አገሮች እርዳታ ኢትዮጵያን ወሮ በያዘበት ጊዜ አቡነ ማቲያስ ጭምብላቸው ገልጠው ለወያኔ ድጋፋቸውን በይፋ በመስጠት አነቀባረው ይዘዋቸው የነበረ ምዕመናንን በመካድ “ሰላም ስለሰፈነ ወደ አገር እገባለሁ” በማለት ለወያኔ ያላቸውን ድጋፍ በይፋ አወጀዋል። ከዚህም በተጨማሪ የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያንን ገንዘብ ከምዕመናን እውቅና ውጭ ከባንክ አጭበርብረው ከማውጣታቸውም በላይ ቤተክርስቲያኑ የግል ንብረቴ ነው በማለት ፍርድ ቤት ቀርበው በሃሰት የመሰከሩ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ሰው ናቸው።

ቀላማጁ አቡነ ማቲያስ ከ5 ዓመታት በፊት ወያኔ ለዋሉት ውለታ ፓትርያክነት ሹመት ሲቸራቸው ታሪካቸውን ለማሳመርና ቤተክርስቲያኒቷ ላይ የሰሩትን አሻጥርና በደል በውሸት ለመፋቅ ከ30 ዓመታት በፊት ሲያዋሩዷቸው የነበሩትን ፓትርያርክ አቡነ ተከለ ኃይማኖትን ሲያመሰግኑና እሳቸውን በትጋት ሲያገለግሏቸውና ሲታዘዟቸው የነበሩ መሆናቸውን ሽምጥጥ አደርገው በክህደት ሲናገሩ አንደበታቸው እንኳ አይደናቀፍም።

አቡነ ማቲያስ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ወያኔ የንጹሃንን ደም እንደውሃ ሲያፈስ አንዳችም ቃል ሲተነፍሱና ሲቃወሙ ተሰምተው አያውቁም። በቅርቡም በቃና ዘገሊላ በዓል ላይ ታቦት አጅበው በነበሩ ምዕመናን ላይ ህጻናት ላይ ጭምር የአጋዚ ነፍሰ በላ ታጣቂዎች ቁጥራቸው ከ50- 80 በሚገመት ምዕመናን ላይ የጥይት ጥናብ ሲያዘንብ አቡነ ማቲያስ ትንፍሽ ሳይሉ ዱካቸውን አጥፍተዋል። እኝህ ሰው እንዲጠብቁት ከፈጣሪ አደራ የተቀበሉትን ህዝብ በአውሬዎች አስበልተው ከአውሬዎቹ ጋር ተቃቅፈው ተቀምጠዋል። በዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው “በኋላ ለመንጋው የማይጨነቁ ጨካኞች ይመጣሉ” የሚለው ቃል በሳቸው ላይ ተፈጽሞባቸዋል። ለማንኛውም በድረገጽ የተለቀቀ ቪዲዮ ተመልከትው የራስዎን ግንዛቤ ይውሰዱ።