መከራ ሊያበራታ እንጂ፣ ሊያዳክም አይገጥምም! – ዐኅኢአድ ልሣን – መቅደላ

Print Friendly, PDF & Email

መከራ ሊያበራታ እንጂ፣ ሊያዳክም አይገጥምም!

ዐማራነትና ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ከደረሱበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የደረሱት የተለያዩ መከራና ችግሮችን ተቋቁመው በማለፍ ነው። ችግሮቹ የተደጋገመ የውጭ የተስፋፊዎችና የቅኝ ገዥዎች ወረራ፣ የውስጥ የሥልጣን ግብግብ የርስ በርስ ጦርነቶች፣ ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉ ጦርነቶችና ግጭቶች እንዲሁም የተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት በሕዝቡ ኑሮ ላይ ያስከተሉት ስደት፣ መፈናቀልና መራቆት፣ በዐማራና በኢትዮጵያዊነት ላይ ከፍተኛ ችግሮች የጋረጡ ነበሩ። ዛሬም እነዚህ ችግሮችና መከራዎች በተለያየ ቅርጽና ይዘት ዐማራነትንና ኢትዮጵያነትን እየተፈታተኑት ለመሆኑ አገራችን የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ ያሳያል።

መከራና ችግር አበረታች እንጂ፣ አዳካሚ ሊሆን ባለመቻሉ ኢትዮጵያዊነትና ዐማራ ውኃና ወተት፣ ሰምና ፈትል ሆነው እያንዳዱ መከራ የራሱን የጥንካሬ ምንጭ በማፍለቅ፣ አንድነታቸውን የበለጠ እያጠናከሩ ከ21ኛው ክፍለዘመን ላይ ደርሰዋል። የግራኝ ወረራ በኢትዮጵያዊነት እና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ የዘመተ ከፍተኛ መከራ ነበር። ያን መከራ ግን ዐማራውና የሌሎች ነገዶች ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ቆመው ባሳዩት ጽናትና በከፈሉት መስዋዕትነት ዐማራነት፣ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትና ኢትዮጵያዊነት ላይለያዩ፣ ላይዳከሙ ጠንክረው እንዲወጡ ማድረጉን ሕያው ታሪካችን ያስረዳል።

ከግራኝ አሕመድ ውድቀት በኋላ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው የማዕከላዊ መንግሥት መዳከምና ሥልጣን በአካባቢ የጦር አበጋዞች እጅ መግባት የአገሪቱን አንድነት ከከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለና፣ በሕዝቡ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ሕይዎት ላይ እጅግ ከፍተኛ መከራ የደቀነ እንደነበር ይታወቃል። ይህ መካራ ግን ኢትዮጵያዊነት አንድነትን ሊያጎለብት እንጂ፣ ሊያዳክም እንዳልገጠመ በሂደት ታይቷል። በዘመነ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ የግዛት ዘመንና ከዚያም በፊት፣ በተከታታይ የተነሱ የቱርክ፣የግብፅና የፖርቹጋል ተስፋፊዎች በቀይባሕር ዳርቻ፣ በቦጎስ እና በሐረር ያደረጉት የመሥፋፋት ዓላማና በሕዝቡ አንድነት ላይ ሊገነቡት የነበረው የልዩነትና የብጥብጥ ግንብ በሕዝቡ የአንድነትና የነፃነት ስሜት መጎልበት የተነሳ መከራውን ተቋቁሞ ኢትዮጵያዊነት እንዲጎለብት የራሱን አሻራ ትቶ አልፏል። ለዚህም በጉራ፤ በጉንደት፣ በከሰላ፣ በሣር ውኃ፤ በጎንደር፣ በመተማ፣ በዜይላ ወዘተ የጦር ሜዳዎች የተከፈለው መስዋዕትነትና ያስከተለው መከራ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አዳብሮ ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ መሆኑ አይዘነጋም። …. (Read more)