አጣብቂኝ ውስጥ የገባው አማራነት!

Print Friendly, PDF & Email

አጣብቂኝ ውስጥ የገባው አማራነት!!

(( ተከታዩ ባለታሪክ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እስከ ተቀጣሪነት የገጠመው ፈተናን እና የወሰነውን ውሳኔ ያስቃኘናል))

በልጅነቴ ብሄሬ ምን/ማን እንደሆነ አላውቅም ነበር፣ እናትና አባቴ እስካሁን ብሄር እንዳላቸው የሚያውቁ አይመስለኝም። እኔም የእኔን ያለብሄር ያሳደጉኝን ልጃቸውን ብሄርተኝነት አይተው እኔን በማስተማራቸው እንዳያፍሩ ስለብሄር ምንም ነገር ነግሬያቸው አላውቅም። ትዝ ይለኛል የሃይስኩል ተማሪ ሆኜ ብሄር/ክልል በሚለው ክፍት ቦታ ላይ 03 የሚል ቁጥር እሞላ ነበር፣ ይህ አሞላል (ብሄር ላይ 03 መሙላት) አርባ ምንጭ ዩንቨርስቲ ገብቼ የ1ኛ አመት ትምህርቴን እስከማጠናቅቅ ድረስ አልተቀየረም ነበር።

ነገሮች መቀየር የጀመሩት ከዩንቨርሲቲ 1ኛ አመት ወደ 2ኛ አመት ከተዛወርኩ በኋላ ነው። ስለእውነት 1ኛ አመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ አማራ በመሆኔ ብዙ ግፍ አይቻለሁ፣ በየቀኑ የብሄር ግጭት ይነሳ ይሆን ብዬ እየተሳቀቅሁ ነበር አመቱን የጨረስኩት፣ ከዚህ በባሰ ግን የጎዳኝ ደፍሬ አማራ ነኝ ለማለት ያደግሁበት ባህል አልፈቅድ ማለቱ ወይም ሌላ ምክንያት እንጃ ብቻ። እናም 1ኛ አመትን እስካጠናቅቅ ድረስ መሃል መንገድ ቆሜ አማራነቴን እየረገምኩ አመቱ እንደምንም አለቀ ወቅቱም 1999 ነበር ወደሚሊንየም ተሸጋግርን።

በኢትዮጵያ የሚሊንየም አመት ነው እንግዲህ እኔም የአማራ ብሄር ተወላጅ መሆኔን ያወጅኩት፣ አምሳያዎቼን መቅረብና መቀላቀል የጀመርኩት። ለካንስ በአማራነታቸው የሚደርሰውን ግፍ ቀድመው አውቀው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ውድ የአማራ እንቁዎች ነበሩ። እነሱን ባገኘሁ ጊዜ ነፍሴ ሀሴት አደረገች። ውስጤ የነበረው የብቸኝነት ስሜት ሁሉ ተኖ ጠፋ።

ስለሆነም ግፍ የገፋን የአማራ ልጆች በአንድ ላይ ሆነን መረዳዳት ጀመርን፣ ተጋገዝን፣ እኔም አማራ በመሆኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ኮራሁ። ሆኖም አሁንም በአፌ አማራ ነኝ ብየ በኩራት አላወራሁም ነበር፣ ምክንያቱም የእኛ አጣብቂኝ ያለው እዚህ ላይ ነው። ሌሎች ብሄራቸውን መናገር እንደጀብድ በሚቆጥሩበት ወቅት ‘የእኛዎቹ’ አጉል ኢትዮጵያዊያን ነን ባዮች ግን ጠባብ፣ ጎጠኛ፣ ቡድንተኛ እያሉ ያሸማቅቁን ነበር። እነሱም ታዲያ በሌሎች ብሄርተኞች ዘንድ ትምክህተኛ፣ የድሮው ስርዓት ናፋቂዎች ምናምን ይባሉ ነበር።

የሆነው ሆነና ግራ ሲገባን አማራ ነኝ ማለት ጠባብነት ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ነው የምትል አንዲት ጽሁፍ ከሆነ ቦታ አገኘንና ለጊዜውም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በሚል ሽፋን አማራነታችንን አጧጧፍነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ዩንቨርሲቲ ውስጥ የሚደርስብንን ግፍና በደል ለመመከት እንጅ ሌላ ድብቅ አጅንዳ ኖሮን ግን አልነበረንም። በእዚህም ውጤታማ ነበርን። የውጤታማነታችን መሰረቱ ደግሞ ከቅንነት የመነጨና የሌላውን ብሄር ላለመጉዳት የሚደረግ በመሆኑ ይመስለኛል። የሆነው ሆኖ ይህን አማራነት ነፍስ የዘራበት ቀንደኛ አመራራችን ከተማሪዎች ህብረት ጋር በተያያዘ በመታሰሩ ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ ገብተን ነበር። በዛ መደናገጥ ውስጥ ሆነን እንኳን ልጁን ለመከላከልና ከችግር ለማዳን ያደረግነው ጥረት ያስደንቀኝ ነበር። ከፍተኛ የሆነ አደጋንም ማስቀረትም ችለን ነበር።

ፍሬ ያፈራው ብሄርተኝነታችን በ2001 ዓ.ም ከአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ ተመርቀን ስንወጣ ውሃ ተቸለሰበት፣ ምክንያቱም ወደቀያችን ተመልሰን ስራ ጀምረን ነበርና ከ2001 ዓ.ም በኋላ ብሄርተኝነቱን እርግፍ አድርገን ትተን በዕለት ጉርስ ፍለጋችን ላይ አተኩረን ነበር። እራሴን ለአብነት ባነሳ የምሰራው በፌደራል ተቋም እንደመሆኑ ቅድሚያ ሰጥቸ የማገለግለው የሌሎች ብሄር ተወላጆችን ነበር፣ ይህንን የማደርገው በሁለት ምክንያቶች ነበር።

1ኛ. እነዚህ ልጆች ለእኛ ለአማራዎቹ እንግዶቻችን ናቸው፣ በባህላችን ደግሞ እንግዳ ክቡር ነው፣

2ኛ. ውስጣቸው ያለውን ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ለመቀየር፣ ይህም ሲባል እንደምገምተው የአማራ ብሄር ለሌሎች ብሄሮች እንደጠላት እንዲታይ የተሰሩ ስራዎች አሉ። ይህም ስር የሰደደ በመሆኑ ሌሎች ብሄሮች በጥላቻ ያዩናል፣ ይህ ግን ምን ያህል ስህተት/ውሸት መሆኑን እንዲረዱ በማሰብ ይህን አደርግ ነበር።

(እንዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት አመክንዮች አሁምንም ቢሆን የማምንባቸውና ወደፊትም የምቀጥልባቸው ናቸው። )

አጣብቂኙ ምን ላይ ነው??

እንግዲህ ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ ስላላይደለች ኢትዮጵያዊነትን ለብቻ ማቀንቀን እውነትም ትምክህት ነው የሚሆነው፣ ስለዚህ መጀመሪያ በማንነታችን ልንኮራ ይገባል፣ መጀመሪያ አማራ ልንሆን ይገባል፣ መጀመሪያ ራሳችንን ማጠንከር አለብን፣ መጀመሪያ በማንነታችን ልንኮራ ይገባል፣ መጀመሪያ አማራ ነን ብለን ልንናገር ይገባል፣ አዎ አማራ ነኝ!! እኔ አማራ ነኝ። መቸም ለሌላው የተፈቀደ ለአማራው እንደማይከለከል ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። አማራ ነኝ!! ስል ብሄር ለመፈለግ ሳይሆን አማራ ስለሆንኩ፣ የአማራ ማንነትና ደም ስላለብኝ ብቻ ነው።

እዚህ ላይ ለአማራው ፈተና የሚሆንበት እንዴት በአንዴ ከኢትዮጵያዊነት ወጥቶ አማራነትን ይቀበላል የሚለው ጉዳይ ነው፣ ነገር ግን አማራነት ኢትዮጵያዊነትን አያጠፋም፣ እንደውም ያጠነክር እንደሆነ እንጅ። ለዚህ በቅርቡ የምናያቸው “የኢትዮጵያዊነት መዝሙሮች” ቀላል ማሳያዎች ናቸው። እስኪ ተመልከቱ እኛ አማራ ነን ባልን ማግስት የተፈጠሩ ክስተቶችን። ተመልከቱ እንጅ አይናችሁን ከፍታችሁ። እናም ወገኖቼ አማራነት ሶስት ጥቅሞች አሉት።

አንድም፥- እራሳችንን ያስከብርልናል፣

ሁለትም፥– ኢትዮጵያን እንደሃገር ያስቀጥላታል፣

ሶስተኛው ደግሞ ምናልባት አንቀጽ 39 ወደ ተግባር ይግባ ቢባል ለማይቀረው ፍች ዝግጁ እንድንሆን ያስችለናል። (ይህ የእኛ ምርጫችን አይደለም ግን ስጋቱን መያዝ ተገቢ ነው)

ሌላው የአማራነት ፈተና የውስጥ ኢትዮጵያውያን የማሸማቀቂያ ስድቦች ናቸው፣ ይህም ጠባብ፣ ጎጠኛ፣ ቡድንተኛ ወዘተ የመሳሰሉት ሲሆኑ እነሱን በተመለከተ ከባድ ፈተና ይጠብቀናል። በሌሎች አጠራር እነዚህ ሰዎች ትምክህተኛ ልንላቸው እንችላለን፣ ምክንያቱም ደግሞ ሌሎች ብሄሮች ቅድሚያ ስለብሄራቸው በሚያቀነቅኑበት በዚህ ጊዜ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ለብቻ ማቀንቀን ከትምክህትም አልፎ እኔ አውቅልሃለሁ ማለት ስለሆነ የሚያዛልቃቸው አይሆንም። ሃገሪቱም ይህን አስተሳሰብ የማትሸከምበት ደረጃ የደረሰች በመሆኑና ለብቻ ለሃገር ተቆርቋሪ ሆኖ መቅረ ሃገርን ያፈርስ እንደሆነ እንጅ ጠቀሜታው ያን ያህል ነው። ይልቁንስ አማራነትን አስከብሮ ከሌላው ብሄርም ጋር በመከባበርና መቻቻል ላይ ተመስርተን ብቻ ነው እንደሃገር ልንዘልቅ የሚገባን ባይ ነኝ።

በመጨረሻ…..

ሃሳቤን የምቋጨው እስካሁን ባሉት ጊዚያት ሌሎች ብሄሮች ስለራሳቸው ብሄር እየዘመሩ አማራው ግን እንደሃገር እያቀነቀነ ሲኖር ትምክህተኛ ሲሉን ኖሩ። ታዲያ አሁን አማራ ነን ስንል ምነው ‘ኮምፓቸው ተንጫጫ’? ይህ ነው እንግዲህ ዋናው የአማራ አጣብቂኝ።

አማራ ስትሆን ኢትዮጵያዊም አማራም መሆን አትችልም። ሁሉም ያልተፈቀዱለት ብቸኛው ብሄር አማራ ነው።

መፍትሄው…

አማራነት ወንጀል አይደለም። በመሆኑም በአማራነታችን ያለምንም ሃፍረትና ስጋት ልንደራጅና ልንቆም ይገባል። ክልሉ ውስጥ በሰላም የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት ተቋቁሞ ሰላማዊ ትግል ሊያደርግ ይገባል።

መደምደሚያ…

አማራነት ወደፊት፣ አማራነት ያሸንፋል!!